ሰዎች ሕይወታቸውን በቀላል መንገድ ለመምራት እና የተለያዩ ዘመን አመጣሽ ሥልጣኔዎችን ለማወቅ ፍላጎት አላቸው። ይህን ፍላጎታቸውን ለማሟላት የተለያዩ መረጃዎች ያመለክታሉ። በርግጥ የአሁኑ ትውልድ ብቻ ሳይሆን ከዚህ ቀደም የነበሩ አሁንም ያሉ እና ወደፊት የሚመጡ ሰዎችም መረጃን መሻታቸው አይቀሬ ነው። ሰዎች መረጃን ከሚያገኙበት መንገዶች መካከል አንዱ ደግሞ ማኅበራዊ ሚዲያ ነው።
ማኅበራዊ ሚዲያ የዜጎች ዋነኛ የመረጃ ምንጭ ከሆነ ሰነባብቷል። ሆኖም ግን የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም በዜጎች ላይ አዎንታዊና አሉታዊ ጎን አለው። ዓለም ወደ አንድ መንደር በቀረበችበት በአሁኑ ጊዜ ሰዎች እንደየ ምክንያታቸው እና ፍላጎታቸው ማኅበራዊ ሚዲያን የመረጃ ምንጭ አድርገው ይወስዳሉ።
ማኅበራዊ ሚዲያ የሰዎችን ፍላጎት ያማከለ በሚመስል መልኩ ተሰናድቶ በፍጥነት ወደ ሕብረተሰቡ መድረስ መቻሉ ተመራጭ አድርጎታል። የሥልጣኔ ዘመን ላይ እንደመሆናችን መጠን ቅድሚያ ሰዎች በቀላሉ ወደ ሚያገኙት ቴክኖሎጂ ፊታቸውን ያዞሩ ይመስላሉ።
ቴዎድሮስ ፍቅሩ ትውልድ እና እድገቱ በአዲስ አበባ ከተማ ነው። በሃያዎቹ መጀመሪያ የዕድሜ ክልል ውስጥ ይገኛል። ከዛሬ ሰባት ዓመት በፊት የማኅበራዊ ሚዲያ መጠቀም መጀመሩን ከግዮን መጽሔት ጋር በነበረው ቆይታ ይናገራል። “የማኅበራዊ ሚዲያ መጠቀም የጀመርኩት የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለሁ ነበር” የሚለው ቴዎድሮስ፣ በጊዜው ማኅበራዊ ሚዲያን የሚጠቀመው መረጃ ከሰዎች ጋር ለመለዋወጥ እና ለመተዋወቅ እንደነበር ያስታውሳል። እንደ ቴዎድሮስ ገለፃ በአሁኑ ወቅት ማኅበራዊ ሚዲያን መረጃ ከሰዎች ጋር ከመለዋወጥ እና ከመተዋወቅ በዘለለ በዋናነት የመረጃ ምንጭ በማድረግ እንደሚጠቀም ያነሳል።
“የሰዎችን አስተሳሰብ ለመመልከት እና የተለያዩ ይዘት ያላቸውን መረጃዎች ለማግኘት እጠቀማለሁ። ነገር ግን እንደ ከዚህ ቀደሙ ማኅበራዊ ሚዲያን ከሰዎች ለመተዋወቅ አልጠቀምም የመዝናኛ ምርጫዬ ነው” በማለትም ያስረዳል። ከሰዎች ጋር በቀላሉ መተዋወቅ፣ ሀሳብ በፍጥነት መለዋወጥ መቻል ብሎም የተለያየ የሥራ ዘርፎች ላይ የሚገኙ ሰዎችን ማግኘት መቻል የማኅበራዊ ሚዲያ አዎንታዊ ገፅታው ነው ሲልም ይናገራል።
ሕብረተሰቡ የሚፈልገውን ማንኛውም ርዕሰ ጉዳይ በድምፅ፣ በሥዕል እና በጽሑፍ ሁሉንም በአንድ ላይ በእጅ ስልክ እና መሰል መገልገያዎች ማግኘት መቻሉ የማኅበራዊ ሚዲያ አስተዎፆ የጎላ አድርጎታል። የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ወጣቱ የሕብረተሰብ ክፍል ትልቁን ድርሻን ይወስዳል። በዚህም ምክንያት መረጃዎች በፍጥነት ከአንዱ ጫፍ ወደ አንዱ ጫፍ ያለ ገደብ የመሰራጨት ዕድሉ ከፍተኛ ሆኗል።
ሰፊ ጊዜ መውሰድ፣ የስለላ ሰለባ ለመሆን ከመመቸቱ እና ከጥላቻ ንግግር እንዲሁም ከሀሰተኛ መረጃዎች አንፃር የማኅበራዊ ሚዲያ አሉታዊ ጎኑ ይከፋ ብለዋል። የጥላቻ ንግግሮች በስፋት በማኅበራዊ ሚዲያዎች በመዘዋወራቸው እና ሕብረተሰቡም መረጃውን በቀላሉ በእጅ ስልኮቻቸው ማግኘት መቻሉ ሀገር ከባድ ኪሳራ ውስጥ ስትገባ ትስተዋላለች። እንዲሁም በሰዎች ላይ የሚሰነዘሩ የጥላቻ ንግግሮች የሚያደርሰው ቀውስ ቀላል የሚባል እንዳልሆነ ተናግሯል። ሰዎችን ለማሸማቀቅ፣ ከማኅበረሰቡ ጋር በነፃነት እንዳይቀላለሉ እና መሰል ጉዳቶችን እንደሚያደርስም ያነሳል።
በተለያዩ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ሰዎች የተለያዩ ምርጫዎች አሏቸው። ማኅበራዊ ሚዲያ የሰዎችን ዕድሜ መሠረት ባደረገ መልኩ ተሰናድቶ ለሕብረተሰቡ ቀርቧል። ይህን ፍላጎት ያለ ጊዜ ገደብ በሚደረግ ልምምድ ስዎች አእምሮ ጤና እና ደህንነት ዙሪያ አንዳንድ ችግሮች ሊስተዋሉ የሚችልበት ዕድል ሰፊ ነው። ከዚህ በተጨማሪም ከማኅበራዊ ሚዲያ በሚያገኙት ተዓማኒነት ያለውም ሆነ በሌለው መረጃ ጭንቀት እና ውጥረት ውስጥ ይገባሉ።
በሀገራችን በታዋቂ ሰዎች ሥም የተለያዩ የትስስር ገፆች ይከፈታሉ። የሐሰት መረጃዎች እና የጥላቻ ንግግር በሕዝብ ሲቀርቡ ሁኔታው ተኣማኒነት እንደሌለው እና ከእነሱ እውቅና ውጭ መሆኑን ለሕብረተሰቡ ለማሳወቅ ታዋቂ ሰዎች በመንግሥት ሚዲያ ቀርበው ለማሳወቅ ሲገደዱ ማየት የተለመደ ነው ይላል። የታዋቂ ሰዎች ሆነ የታላልቅ ሰዎችን ንግግር እና የግል ሕይወት ወደ ማኅበራዊ የትስስር ገፆች በማምጣት የተለየ ምልከታ እንዲሰጠው ሲደረግ ይስተዋላል ብሏል። ይህም የዜጎችን የግል ሕይወት ከመረበሽ እና አደጋ ላይ ከመጣል በተጨማሪም ይህ ዐይነቱ ድርጊት የተከሰተባቸው የማኅበረሰባችን ክፍሎች ከንግግር እና ከተለያዩ ማኅበራዊ ክንዋኔዎች እራሳቸውን እንዲያገሉ ሊያደርግ ይችላል ብሏል።
በማኅበራዊ ሚዲያዎች በሚሰራጩባቸው የተሳሳቱ መረጃዎች እንዳንዶች በዝምታ ሲያልፉ ሌሎች ግን የተፅዕኖ ሰለባ የሚሆኑበት ዕድል ሰፊ ነው። በዚህም ምክንያት እራሳቸውን ለአደጋ አሳልፎ ከመስጠት እስከ መጉዳት ድረስ ይደርሳሉ። “እኔ አጋጣሚዎች ስላሉኝ የማኅበራዊ ሚዲያ መረጃዎችን ብከታተልም በቻልኩት አቅም የሀሰት መረጃዎች እና የጥላቻ ንግግርን ላለማየት እራሴን እቆጥባለው” በማለት ቴዎድሮስ አብራርቷል። በዚህም ምክንያት የማኅበራዊ ሚዲያ አሉታዊ ጎኑ እሱ ላይ ባይደርስም በሌሎች ላይ ግን የሚያሳደረው ተጽዕኖ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁሟል።
ማኅበራዊ ሚዲያ በመጠቀም ሀገርን ለዓለም ከማስተዋወቅ፣ በዲፕሎማሲ መንገድ ከማሳደግ፣ ለሰዎች የትውውቅ እና የተለያዩ የቢዝነስ ሀሳቦችን ከማንሸራሸር አንጻር ትልቅ ሚና ማበርከቱ አይዘነጋም። ሆኖም ግን የሕብረተሰቡን የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ከጊዜ አጠቃቀም እና የመረጃ ምንጮች ካለማወቅ አኳያ በሀገራችን ያለው ሁኔታ ብዙ ይቀረዋል ለማለት ያስደፍራል።
የማኅበራዊ ሚዲያ ከአውንታዊ ጎኑ አሉታዊ ገፅታው እየጎላ ነው የሚሉት ደግሞ ጋዜጠኛ ይበልጣል ግዛው ናቸው። እንደ ጋዜጠኛው አረዳድ ማኅበራዊ ሚዲያ ለመልካም ከጠቀምንበት ሕይወት ቀላል ለማድረግ፣ የተለያዩ መረጃዎችን በቀላሉ ለማግኘት እና እራስን ከዘመኑ ጋር አብሮ ለማስኬድ ጠቀሜታ አለው ብለዋል። በአንፃሩ በሀገራችን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ማኅበራዊ ሚዲያ ለሀሰተኛ የመረጃ ምንጭ እና ለጥላቻ ንግግር እንዲሁም ለእኩይ ተግባራት አመቺ የሆነበት ጊዜ ላይ እንገኛለን ሲሉ ይናገራሉ።
መረጃ ለሰዎች አስፈላጊ መሆኑ ባይዘነጋም በአሁኑ ነባራዊ ሁኔታ የምንጠቀምበት መንገድ ግን ተገቢ አይደለም። አብዛኛው የማኅበረሰባችን ክፍል በሚባል መልኩ እውነተኛ እና ሀሰተኛ መረጃዎችን ከምንጩ የማወቅም ሆነ የማጥራት ልምድ የለውም ብለዋል። ይህን ክፍተት በመጠቀም አንዳንድ ግለሰቦች ማኅበራዊ ሚዲያን ለእኩይ ዓላማ እያዋሉት እንደሚገኙም ገልጸዋል። እንደ ባለሞያው ሀሰተኛ መረጃዎች እና የጥላቻ ንግግሮች ሕዝብ ላይ ጉዳት ሲያመጡ ቢስተዋልም ለውጥ ሊመጣ አልተቻለውም ሲሉ ያስረዳሉ። ማንኛውም ሰው ከእኩይ ዓላማ እና ማኅበራዊ ሚዲያን ለገንዘብ ምንጭነት መጠቀም አግባብነት እንደሌለው በማውሳት ሕብረተሰቡን መረጃዎችን ከምንጩ መመልከት እና ማመን እንዳለባቸው የባለሞያ ምክራቸውን ያስተላልፋሉ።
ለሰዎች ሕይወትን በቀላሉ ለመኖር ማስቻል እና የመረጃ ምንጭ መሆኑ የማኅበራዊ ሚዲያ ትልቁ ጥቅሙ ነው የሚሉት የሥነ ልቦና ባለሞያ እና የሞሼ አማካሪ እና ሥልጠና ድርጅት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ብርሃኑ ራቦ ናቸው። እንደ ባለሞያው ገለፃ በ21ኛው ክፍል ዘመን ላይ ሆነን ቴክኖሎጂን መኮነን ባይቻልም አጠቃቀማችን ግን የሚኮነን ነው ብለዋል። ቴክኖሎጂ መረጃዎች በፍጥነት እንዲሰራጩ እና ኑሮን ቀላል ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል። የሀገራችን እድገት ከማፋጠን፣ የሰዎችን ቅርርብ ከማጎልበት አንፃርም ሚናው ከፍተኛው ነው የሚሉት ባለሙያው፣ በተቃራኒው ቴክኖሎጂውን በመጥፎ ጎኑ ለሚጠቀሙ ሰዎች መረጃ የመሰራጨት እድሉ ሰፊ እንደሆነ ያነሳሉ።
የማኅበራዊ ሚዲያ የተሰራበት ዘዴው እራሱ ሰዎች በቀላሉ ከሱስ እንዳይላቀቁ ያደርጋል የሚሉት ባለሙያው አቶ ብርሃኑ አንድ ሰው ወደ ማኅበራዊ ሚዲያ ለመጠቀም ሲገባ ወደ ቤቱ ሲሄድ በዓላማ እንደሆነው ሁሉ ማኅበራዊ ሚዲያን በምክንያት መጠቀም ይገባል ብለዋል። ማኅበራዊ ሚዲያ ዓለም አቀፍ ቢሮ ነው የሚሉት አቶ ብርሃኑ ያለ ዓላማ ማኅበራዊ ሚዲያ በተገኘው ጊዜ ሁሉ የምንጠቀም ከሆነ ወደ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ እንዲሁም ሱሰኝነት ይወስደናል ብለዋል። የሀሰተኛ መረጃ በፎቶ ሾብ በሌሎች መንገዶች በማሰራጨት የተካኑ እሲከሚመስሉት ወጥመድ ውስጥ ልንወድቅ እንችላለን ሲሉም ያስረዳሉ።
በሀገራችን በአሁኑ ወቅት በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚንሸራሸሩ መረጃዎች ሁሉም ማለት ባይቻልም ጥላቻ አዘል ንግግሮች፣ የግለሰብ ወይም የታዋቂ ሰዎችን የግል ሕይወት በመለጠፍ እንዲሁም ብሔር እና ሃይማኖት መነሻ በማድረግ በሕብረተሰቡ መካከል ልዩነትን፣ ብጥብጥ እና ሁከትን የሚያሰራጩ ሆነው ይገኛሉ።
“ጥላቻ ከልክ ሲያልፍ ወደ ውሸት ይቀየራል” በማለት የሚገልጹት ባለሙያውም አንድ ሰው የሆነን ሀሳብ ጉርብ በሚጠላበት ወቅት ጥላቻው ከመጠን ሲያልፍ ውሸትን እንደሚወልድ ያስረዳሉ። ማኅበረሰቡ መሬት ላይ ያለውን እውነታ ሳያውቅ ወይም ሳይረዳ በጭፍን ጥላቻ ውስጥ እንደሚገባም ይጠቁማሉ። በተለያዩ መድረኮች ላይ የሰዎችን ንግግር በመቁረጥ እና ለይቶ በመውሰድ ለጥላቻ ንግግር እንዲሁም ለሀሰት መረጃዎች ለመጠቀም የሚያውሉ እንዳሉም ያነሳሉ። ሌላው በአርቲስቶች እና በታዋቂ ሰዎች ላይ የሚነዛውን የተሳሳተ መረጃ እና የሞት ዜናዎችን በተመለከተ ይህ ዐይነቱ ድርጊት የተፈፀመባቸው ሰዎች ማብራሪያ ሆነ የመረጃውን ሀሰተኛነት ለሕዝብ ማሳወቅ አስፈላጊነት እንደማይኖረው ያስረዳሉ። እንደ ምክንያት የሚያነሱትም ለሕዝብ አርአያ የሆኑ ሰዎች ክብር እና አቋማቸውን ጠብቀው መቆየት የሚጠቅማቸው ሲሆን የውሸት መረጃውም በጊዜ ሂደት ይከሽፋል ባይ ናቸው።
“ራስን መግዛት” አቶ ብርሃኑ እንደ መፍትሔ የሚያነሱት ሀሳብ ነው። አንድ ሰው የትኛውንም ማኅበራዊ ሚዲያ ሲጠቀም “ራሱን አንድ ዋነኛ ጥያቄ መጠየቅ የሚኖርበት ሲሆን ለምን ዓላማ ወይም ትርፍ እንደሚጠቀም” መኾኑንም ይጠቁማሉ። በተጨማሪም በማኅበራዊ ሚዲያ ጓደኞችን ስናፈርራ ከኛ አመለካከት እና የሥራ ሁኔታ ጋር ተመሳሳይ ቢሆን ይመረጣል። ይህም በለተያዩ ልጥፎች እና መረጃዎች ሥር የሚኖረውን የአስተያየት ወይም የአመለካከት መዘላለፍን በዋነኛነት ከመቅረፉ በተጨማሪም የሥራ ዕድል እና ጥሩ ወዳድን ለማፍራት ሚናው ከፍተኛ ነው ብለዋል። በቀን ውስጥ ምን ያህል ጊዜ የማኅበራዊ ሚዲያን በመጠቀም እንደሚያሳልፉ መጠየቅም ሌላው የመፍትሔ አካል ነው ይላሉ። ሰዎች የማኅበራዊ ሚዲያ ሱሰኛ ከመኾናቸው ብዛት ከሰዎች ጋር ሆነው ብቸኛ እና ውብ የተፈጥሮ ስፍራዎች ላይ ሆነውም ተፈጥሮን ለማድነቅ እንደሚቸገሩ ያብራራሉ። “እኔ እንደ ባለሞያ የምመክረው ሰዎች ከሰባት ሰዓት እስከ ስምንት ሰዓት ያለውን ሰአት ማኅበራዊ ሚዲያን እንዲጠቀሙ ነው” የሚሉት ባለሙያው፣ በአብዛኛው ሰአቱ ከድካም የሚታረፍበት በመሆኑ አመቺ እንደሆነም ይጠቅሳሉ። የስራቸው ፀባይ መረጃን እግር በግር አሳዶ ለሕዝብ ማድረስ እና ሀገርን መጥቀም የሆኑትን ግለሰብ ግን እንደማይመለከት ይገልጻሉ። እንደ ባለሞያው ምክር ጤናማ እና ውጤታማ ቀን ለማሳለፍ ሰዎች ጠዋት እና ከመኝታ በፊት ማኅበራዊ ሚዲያን መጠቀም እንደሌለባቸው ይመክራሉ። የሚኖረውም ጠቀሜታ ከብዙ መረጃዎች ከመጥለቅለቅ እና ቀንን ተረብሾ ከማሳለፍ በተጨማሪም አስፈሪ አእምሮን የሚረብሽ እና የሚጎዳ ሌሊት ከማሳለፍ ይታደገናል በማለት አክለዋል።
