በጋዛ ቢያንስ 14 ፍልስጤማውያንና ሁለት ህፃናትን ጨምሮ በቅርቡ በረሃብና በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ምክንያት ህይወታቸው ማለፉን የጤና ባለስልጣናት ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል ።
ይህ አሳዛኝ ክስተት እስራኤል በጥቅምት 2023 ጦርነት ከጀመረች ወዲህ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት የሞቱት ሰዎች ቁጥርን ወደ 147 እንዲያድግ አድርጓል፤ ከእነዚህ ውስጥም 88ቱ ህፃናት መሆናቸው ነው የተነገረው ።
ይህ አስከፊ ዜና የወጣው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በተከበበችው ጋዛ ግዛት “እውነተኛ ረሃብ” እየታየ መሆኑን ከገለጹ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ነው።
የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ከሁለት ቀን በፊት ባወጣው መግለጫ፣ በጋዛ ውስጥ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ምጣኔ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን አስጠንቅቋል። በተለይም በሐምሌ ወር ብቻ የሞቱ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል ነው ያለው ድርጅቱ ።
ዩኒሴፍ በበኩሉ ባወጣው ሪፖርት፣ በጋዛ ያሉ ህፃናት “በረሃብ እየሞቱ” መሆናቸውን ገልጿል። ከሚያዝያ ወር ጀምሮ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት የሞቱ ህፃናት ቁጥርም ከ52 ወደ 80 ከፍ ብሏል። ይህም ሦስት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የ54 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን አልጄዚራ ዘግቧል።
