አዳነ ጥላሁን ዳኜ(ወልዲያ)
የዘንድሮው 127ኛ የዓድዋ ድል በዓል መታመስ መተራመስ የጀመረው ከክብረ በዓሉ ዕለት ቀድመው በነበሩ ሳምንታት ነበር፡፡ አንቱ ከተባሉት ያገሪቱ ባለስልጣናት ውስጥ አንዳንዶቹ ደግሞ በዚህ ጠለፋ ላይ እጃቸው አለበት፡፡ በዓሉ ሳምንት ሲቀረው ደግሞ እንደፈረንሳይ ሌጋሲዮንና ሽሮሜዳ ባሉ የአዲስ አበባ አካባቢዎች የአፄ ምኒልክንና የእቴጌ ጣይቱ ምስል የተለጠፈበት ቲሸርት የለበሱ ወጣቶች ላይ የፀጥታ ኃይሉ የእሥርና የማሳደድ ተግባር ፈፅሟል፡፡ የአፄ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ ምስል የታተመበት ቲሸርት ይሸጣሉ ብሎ የጠረጠራቸውን የንግድ ሱቆችም አሽጓል፡፡
ይኸ ተግባር ያለከተማዋ ባለሥልጣናት ይሁንታና ትዕዛዝ የተፈፀመ ነው ብሎ የሚያምን ካለ ያ ሰው ቂሉ ማሞ ብቻ መሆን አለበት፡፡ የበዓሉ አከባበር ሙሉ ዝግጅት ኃላፊነት ወደ ሀገር መከላከያ የተዛወረውም ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው የመንግሥት ተቋም ውስጥ ሀገራዊ አመለካከት ያላቸውና በመንደር ፖለቲካ አራማጆች መካከል ስምምነት በመጥፋቱ ስለመሆኑ በሹክሹክታ ሰምተናል፡፡
ክብረ በዓሉ ምኒልክ አደባባይ፣ ዓድዋ ድልድይ አካባቢና መስቀል አደባባይ በሚገኙ ሦስት ቦታዎች እንዲከበር የተደረገውም ሕዝቡ በአንድ ተሰባስቦ በኢትዮጵያዊነት ፍቅር፣ ወዝና ለዛ የድሉ ግንባር ቀደም ባለውለታ በሆኑት በአፄ ምኒልክ ሀውልት ሥር በደመቀ ሁኔታ እንዳያከብር በመከፋፈል የበዓሉን ድምቀት ለማቀዝቀዝና የኢትዮጵያዊነትን ሥነ ልቦና ለመስበር በመንግሥት መዋቅር ከፍተኛው የሥልጣን እርከን የተሰገሰጉ የጎሳ አቀንቃኝ ፖለቲከኞች ብርቱ ፍላጎት ነው ብለን ጣታችንን ወደመንግሥት የምንቀስር ብዙዎች ነን፡፡
በዓሉ እየተከበረ በነበረበት ወቅትም ምኒልክ አደባባይ ላይ የታየው አስገራሚና አሳፋሪ ኃይል የተቀላቀለበት የፀጥታ ኃይል ርምጃ ከላይ ለጠቀስኩት ጥርጣሬ አጠናካሪ ማስረጃ ነው፡፡
በዚያ በዓል ላይ የታደሙት ሕፃናት ያዘሉ እናቶች ናቸው፡፡ ዕድሜ ጠገብ አረጋዊና አረጋዊት ናቸው፡፡ ገና በአፍላ የወጣትነት ዕድሜ ላይ የሚገኙ ብርቅ ያገር ቅመም የሆኑ ወጣቶችም ነበሩበት፡፡ እንግዲህ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች አስለቃሽ ጢስ ብቻ ሳይሆን ሕይወት ቀሳፊ ጥይት የተኮሱት በነዚህ በዓል አድማቂዎችና የሰማዕቱን የቅዱስ ጊዮርጊስን ዓመታዊ በዓል ዙሪያ በቤተክርስቲያኑ ዐውደምሕረት ተገኝተው የንግሥ በዓሉን ሥርዓት እየተከታተሉ በሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ አማኒያን ላይ ነው፡፡
እውነት ለመናገር ከዚህ የበለጠ ግፍና አሳፋሪ ተግባር የለም፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ ይበልጥ ንዴት ውስጥ የሚከተውና እልህ ውስጥ የሚያስገባው ደግሞ ተዓማኒ መረጃ ለሕዝብ መሥጠት የነበረበት የመንግሥት ተቋም በሕዝብ ላይ የተወሰደው ርምጃ ስህተት መኾኑን አምኖና ሕዝቡን በይፋ ይቅርታ ጠይቆ የማረጋጋት ሥራ መሥራት ሲኖርበት ውንጀላውን ድብደባና መንገላታት ወደደረሰበት ሕዝብ ለማዞር መሞከሩ ነው ይህ ድርጊቱም ምን ያህል ሕዝብ መናቁን ወይም ሕዝቡን እንደሞኝ መቁጠሩን ነው የሚያሳየው፡፡
እንደመንግሥት አፈቀላጤ መግለጫ ከሆነ ያ በበዓሉ ላይ ነጭ ልብስ ለብሶና በፈረሱ ላይ ተቀምጦ በሰላም ሲጓዝ የነበረ ግለሰብ ሳያስበው በሰደፍ ተመትቶ መሬት ላይ የተዘረረው ረባሽና ረብሸኞችን እየመራ በነበረበት ቅፅበት ነበር ማለት ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ መንግሥታችን የሚፈልገው በዓይናችን የምናየውን ሳይሆን በጆሯችን የምንሰማውን ብቻ ነው ማለት ነው፡፡
በበኩሌ በዚያ ፈረሰኛ ላይ የተፈፀመው የግፍ ድብደባ ያስታወሰኝ የካቲት 1 ቀን 2015 ዓ.ም በጎጃም መስመር ወደ አዲስ አበባ ሲጓዙ የነበሩ የቤተክርስቲያን አገልጋይ መታወቂያ ተጠይቀው በትህትና በማሳየት ላይ ባሉበት ሰዓት በጥፊ የመታቸው ወጠጤ ወታደር ዕብሪት አዘል ድርጊት ነው፡፡
በግልፅ እንነጋገር ከተባለ ምኒልክ አደባባይ ላይ ከተፈፀመው አሳፋሪ ተግባር መንግሥታችን ምን ዓይነት የፖለቲካ ትርፍ እንደሚያገኝ ሳስበው ግራ ይገባኛል፡፡ በመፈቀር ፈንታ መጠላትን በመከበር ፈንታ መፈራትን እንደሚያተርፍ ግን አስረግጦ መናገር ይቻላል፡፡ በሌላ አገላለፅ ሕዝብ መንግሥትን ከፈራ አምባገነንነት መንግሥት ሕዝብን ከፈራ ዴግሞ ዴሞክራሲ ይነግሣል የተባለው አባባል እውን ይሆናል ማለት ነው፡፡ በመንግሥት ጉያ ተሸጉጠው ይኽ ዕኩይ ድርጊት እንዲፈፀም ያመቻቹ መንደር አፍቃሪ የጎሳ ፖለቲከኞችም ቢሆኑ ሕዝብ በማስደብደብና በማስገደል ጊዜያዊ እርካታ ያገኙ ካልሆነ በስተቀር የሚያስቡትን የጎሳ በላይነት ስኬት እንደማይጎናፀፉ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡
ወደመስቀል አደባባይ በዓል ስናመራም በበዓሉ ላይ እንዲታደሙ ጥሪ የተደረገላቸውና የተገኙት ታዳሚዎች በየቀበሌው በጥንቃቄ ተመርጠው የተጠሩ የብልፅግና አባላት እንጂ በራሱ ፍላጎት ወደአደባባዩ የጎረፈው ሕዝብ ግን ወደውስጥ እንዳይገባ በፀጥታ አካላት ተከልክሎ ወደየመጣበት ተመልሷል የሚለውን የበርካታ ሕዝብ ቅሬታ የምጋራው ሆኖ እዚህ ላነሳው የፈለግሁት ነጥብ ግን በባሕልና ስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ቀጀላ መርዳሳ ንግግር ዙሪያ መብራራት ያለበትን ጉዳይ መሆኑ ይታወቅልኝ፡፡
የአቶ ቀጀላ መርደሳ የመግቢያ ንግግር ዋና መጠንጠኛ ታሪክ ሰሪው ሰፊው ሕዝብ ነው የሚለው ነጥብ ነው፡፡ በተዘዋዋሪ እርሳቸው ምን ለማለትም ሆነ ምን መልዕክት ለማስተላለፍ እንደፈለጉ የሚያውቅ ያውቀዋል፡፡ እንኳን ይችን የዝንብ ጠንጋራ ለይተን እናውቃለን አይደል የሚባለውስ!
ለማንኛውም ታሪክ ሰሪው ሰፊው ሕዝብ ስለመሆኑ እኔም አምናለሁ፡፡ ግን ያለ በሳል አመራር ሰጪ መሪ በኛ ሀገር ብቻ አይደለም በዓለም ዙሪያ ታሪክ የሰራ ሀገር ስለመኖሩ አላስታውስም፡፡ ለዚህ አባባሌ ይረዳ ዘንድ የውሱን ሀገራትን ታሪክ ላንሳ፡-
የዓለምን ሥርዓተ አስተዳደር ታሪክ ቀያሪ ነበር ተብሎ የሚነገርለት የ1917ቱ የሶቪየት ሩሲያ አብዮት ላይ ታሪክ የሠራው ሕዝቡ ይሁን እንጂ ያ አብዮት ያለ ብላድሚር ኢሊች እሊያኖቭ /ሌኒን/፣ ጆሴፍ ስታሊን፣ ትሮትስኪና ሌሎች መሪዎች አመራር ባዶ ነበር፡፡
በረሀብ አለንጋ ሲገረፍ የነበረው የቻይና ሕዝብ አስተማማኝ ታሪክ ሰርቶ ሀገሪቱን አሁን ለደረሰችበት ጠጣር ክንደብርቱነት ያደረሳት ሰፊው የቻይና ሕዝብ ነው፡፡ ግን ይኸ ኃያልነት ያለማኦ ሴቱንግ፣ ቹ፣ ኤንላይ ሊንፓኦ እና ማርሻል ቹ ቴይህ ጭራሽ አይታሰብም፡፡
አሜሪካ አፍንጫ ሥር ያለችውና በቆዳ ስፋቷ ከአሜሪካ ጋር ስትነፃፀር የጉረሮ እንጥል የምታኽለውን የኩባን ሕዝብ ታሪክ ሰሪነት ስናስብ ቀድሞ የሚታሰቡን ፊደል ካስትሮ፣ ራውል ካስትሮ እና ቸ ጉቬራ ናቸው፡፡
ዲያን ቢያን ፉ ላይ የፈረንሳይን ቅኝ አገዛዝ ያንኮታኮተውና ቀጥሎም ከ1961 እስከ 1975ዓ.ም የግዙፏን አሜሪካ ጦር ረግጦና አሳፋሪ ሽንፈት አከናንቦ ከሀገሩ ያስወጣው የቬትናም ሕዝብ ያን የድል ታሪክ በወርቅ ቀለም የፃፈው ከፍቅራቸው ፅናት የተነሳ ቬትናማውያን አጎት የሚል የቁልምጫ ስም ባወጡለት በሆቺሚንና በወታደራዊ ስልት ተደናቂ በነበረው ጀኔራል ጂያፕና ሌሎች መሪዎች ግንባር ቀደምትነት ነው፡፡
ባጭሩ መንግሥት በመንግሥትነት ከተቋቋመበት ጥንታዊ ዘመን አሁን እስከደረስንበት ዘመን ባለው የዓለም ታሪክ ቀያሪነት ዙሪያ መሪዎች የማይናቅ ጉልህ አስተዋፅኦ አድርገዋል፡፡ ጉዳዩን ወደእኛ ሀገር ስናመጣውና ሌላውን ትተን ከ2010 ዓ.ም ወዲህ ያለውን ታሪክ ብናይ በነዚህ አራት ዓመታት በተከወኑ ጥሩም መጥፎም ሀገራዊ ኩነቶች ላይ የዶ/ር ዐቢይን የመሪነት ሚና ማንሳታችን ግድ ነው፡፡
በሜቴክ ባለሥልጣናት ቅጥ ያጣ ዘረፋ ሰበብ ሥራው ሙሉ በሙሉ ሊቋረጥ የነበረውን የሕዳሴ ግድብ ሥራ በማስፈፀሙ ረገድ ታሪክ ከሰራው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን የዶ/ር ዐቢይ ሥም በበጎ ጎኑ መነሳት እንደሚገባ ሁሉ በወለጋ የዘር ማፅዳት ሰበብ በሚጨፈጨፉ አማራዎች ዙሪያ በተፈጠረው ክፍተት ዙሪያም የዶ/ር ዐቢይ ሚና በአሉታ መነሳቱ ግድ ነው፡፡ እንግዲህ ከላይ በዋቢ ማስረጃነት ካቀረብኩት ጭብጥ ስንነሳ ታሪክ ሰሪው ሰፊው ሕዝብ ስለመሆኑ ከአቶ ቀጀላ ጋር እስማማና በዓድዋ ደማቅ ድል ዙሪያ ትልቁን ሚና የተጫወቱትን አፄ ምኒልክንና እቴጌ ጣይቱን ከደማቁ የዓድዋ ድል ታሪክ ጋር ሊያነሷቸው ያልፈለጉት ግን በየዋህነት ወይም ባለማወቅ የተደረገ ተራ ስህተት ነው ብሎ የሚያምን ሞኝ አለመሆናችንና ሚኒስትሩ ለበዓሉ ታዳሚዎች ያለምኒልክና ጣይቱ ታሪክ ተሰራ ብለው ያስተላለፉት የተሟላ ሳይሆን ጎደሎ መልዕክት መሆኑን መግለፅ እፈልጋለሁ፡፡
ለነገሩ ለዓድዋ በዓል ክብረበዓል አከባበር በነበረኝ ጉጉት የተነሳ ፕሮግራሙን ስከታተል በነበረበት ወቅት ያቶ ቀጀላ መርደሳን ንግግር ሰምቸ ቅር ባለኝ ነጥብ ዙሪያ አስተያየት ለመስጠት ፈለግሁ እንጂ አፄ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ ላይ ብቻ ሳይሆን እነራስ ጎበና ዳጨን በመሳሰሉ ቁልፍ የኢትዮጵያ ልጆችና በሀገሪቱ ላይ ጭምር ጥሩ አመለካከት የሌላቸው ውሱን የኦሮሞ ተወላጅ ልሂቃን እንዳሉ እዚህ ላይ መጠቆም እፈልጋለሁ፡፡ አንዳንዶቹማ እነአፄ ምኒልክ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ የሚለው ስም ሲጠራ ሲሰሙ ዛር እንደነሳበት ባለዛር ሲያንዘፈዝፋቸው በትዝብት አይተናል፡፡ የታሪክ ምሁር ነኝ ባዩ ሕዝቅዔል ጋቢሳማ ምኒልክ የሚባል ንጉሥ እንደማያውቁ ሲናገሩ በትዝብት አዳምጠናል፡፡ ሞቲ ቢያ የተባሉ ደራሲ ደግሞ ኢትዮጵያ መታወቅ የጀመረችው ከ2ኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ነው በማለት ሀገሪቱን የአፄ ኃ/ሥላሴ ዘመን ስሪት መሆኗንና የየካቲት 66 አብዮትም የኦሮሞና የደቡብ ሕዝቦች የትግል ውጤት ብቻ እንደሆነ ይነግሩናል ፤ “ኦሮሚያን በፈረቃ፣ አቢሲኒዮክራሲ ወይስ ዴሞክራሲ” በሚለው መጽሐፋቸው ገፅ 86 እና 95 ላይ፡፡
“የውገና ድርሰቶች” የሚል ርዕስ ያለው መፅሐፍ ያስነበበን አቶ ታቦር ዋሚም ሆነ “ኦሮሚያ የተደበቀው የግፍ ታሪክ” በሚል ርዕስ የታሪክ መፅሐፍ ጽፈው ለገበያ ያቀረቡት ወልደዮሐንስ ወርቅነህና ገመቹ መልካ እንዲሁም “የኦሮሚያ የማንነት ታሪክ” የሚል መጽሐፍ ያቀረበልን ድሪባ ደምሴ ቦኩ በየመጽሐፋቸው ላይ የነገሩን ከሞቲ ቢያ ጋር የተመሳሰለ ታሪክ ነው፡፡
ነገርን ነገር እያነሳው ከተነሳሁበት ጭብጥ እየወጣሁ አንባቢን በማሰልቸቴ ይቅርታ እየጠየቅሁ ወደተነሳሁበት ጭብጥ ሰመለስ አቶ ቀጀላ ባሰሙን ንግግር ላይ የአፄ ምኒልክንም የእቴጌ ጣይቱንም የአመራር ሚና ሊነግሩን ይገባ ነበር፡፡ ያን ቢያደርጉ ኖሮ መልዕክታቸው የተሟላ መልዕክት ይሆን ነበር ባለመታደል አላደረጉትምና ጎደሎ መልዕክት ነው ያስተላለፉት፡፡
እዚህ ላይ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ቢኖር ውሱን የኦሮሚያ ልሂቃን እንደሚፈልጉት የአፄ ምኒልክና የእቴጌ ጣይቱን ሥም ከዓድዋ የድል ገድል ላይ እንፋቀው ብንል እንኳ በዓለም ደረጃ ትዝብት ላይ ከምንወድቅ ውጭ የምናገኘው ውጤት የለም፡፡ ምክንያቱም እጅግ በርካታ ደራሲያንና ጋዜጠኞች ታሪኩን ሰንደው ለዓለም አሰራጭተውታልና፡፡ ለአብነት ያህል በዚህ ታሪክ ዙሪያ ከትበው ለትውልድ ያስተላለፉልን ኢትዮጵያውያን ታሪክ ፀሐፊዎችን አለቃ አፅመጊዮርጊስ፣ አለቃተክለየሱስ ዋቅጅራ፣ አቶ ጳውሎስ ኞኞ፣ አቶ ተ/ፃድቅ መኩሪያና ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴን እዚህ ላይ በመረጃነት ብጠቅስ ገለልተኛ ናቸው አይደሉም የሚል አነታራኪ አጀንዳ ላለመክፈት እነርሱን ትቸ ወደውጭ ሀገራት ፀሐፍት በመሄድ ስለኢትዮጵያ ታሪክ ከፃፉት መካከል አንደርዜይ ባርትኒስኪና ዮአና ማንቴል፣ ሬይሞንድ ጆናስ፣ ጆርጅ ኤች በርክሌይ፣ ሳሂድ አዲያንካ አዱጁምቤ፣ ክሩስ ፕሩቲ፣ ሀሮልድ ጂ ማርቆስና ሌሎችም በርካታ ፀሐፍት ካገራችን ፀሐፍት የማይተናነስ ታሪካችንን ከትበው ለዓለም ካሰራጩት መካከል ናቸው፡፡
ከላይ የተጠቀሱት ደራሲያን በዓድዋ ጦርነት ድል መነሻነት አፄ ምኒልክን እቴጌ ጣይቱንና ሌሎች በጦርነቱ የተሳተፉ አመራር ሰጪ መሪዎችን ብቻ ሳይሆን ራሷን ኢትዮጵያን ጭምር በክብር ማማ ላይ ሰቅለዋቸዋል እንጂ አሁን ላይ ጎሳ አምላኪ መንደር ናፋቂ ፖለቲከኞች ምኒልክ የሚባል ንጉሥ አናውቅም እንደሚሉት ከታሪክ መዝገብ አልፋቋቸውም፡፡
እንግሊዛዊው ጅርጅ በርክሌይማ የዓድዋን ተአምረኛ ድል አስመልክቶ ..ዘመናዊውና ሀያ ሺ ሠራዊት የተካተተበት የአውሮፓ ጦር በአፍሪካውያን መሸነፉንና የዓድዋ ጦርነት በአንድ ቀን ሀያ አምስት ሺ ሰው አልቆበት የአፍሪካን ታሪክ ስለመለወጡ ሲዘግብ ላይ ሊበርቲ የተባለ የፈረንሳይ ጋዜጣ ደግሞ የአውሮፓ ሕዝቦች በጨለማው አህጉር ያለውን የኢትዮጵያውያን ኃያልነት አምነው እንድቀበሉ አበክሮ ይገልፃል፡፡
ክርስቲያን ፓትሪየት የተባለው ሕንድ ሀገር የሚታተም ጋዜጣ በበኩሉ ኢትዮጵያ የአውሮፓን ኃያል መንግሥት ከመቋቋም አልፋ ክፉኛ በመምታት ጀግንነቷን ማስመስከሯን ሲገልፅ የአፄ ምኒልክ አማካሪ የነበሩት የስዊዝ ተወላጁ አልፍሬድ ኢልግ ደግሞ “ዳዊት ጎልያድን አሸነፈ” በሚል እጥር ምጥን ያለ አገላለፅ ነው የዓድዋን ገድል የገለፀው፡፡
ከዚህ ውጭ በዓድዋ ድል ሰበብ ሀገራችን ሉዓላዊ ሀገርነቷን አስከብራለች የዲፕሎማሲ ግንኙነቷንም አጠናክራለች፡፡ በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ ጥቁር ሕዝቦችም የነፃነት ተምሳሌትና የፓን አፍሪካኒዝም አጠናካሪ ሞደልም ናት ወዘተ ወዘተ…
በዚህም የተነሳ 11 የአፍሪካ ሀገራት ሰንደቅ ዓላማቸውን አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለም ያለው አድርገው ሲሰቅሉ የኬንያው ጆሞ ኬንያታ፣ የጋናው ክዋሚ ንክሩማህመ የኮትዲቯሩ ሁፌት ቧኜ፣ የማሊያው ካሙዙ ባንዳ በበኩላቸው በየሚሄዱበት ቦታ ሁሉ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ እንደሚያሰቅሉና እነርሱም ለብሰው ተውበውበት ወደሕዝብ ይቀርቡ እንደነበር ቴዎድሮስ በየነ “ኅብር ኢትዮጵያ” ቅፅ 1 መፅሐፉ ላይ ከትቦታል፡፡
በሌላ በኩል የዓድዋ ድል በአውሮፓውያን መንግሥታት በኩል ጥርስ አስነክሶብን የመሳሪያ ማዕቀብ እንዲጣልብን ምክንያት ሆኗል፡፡ በ2ኛው ዙር የኢትዮ ጣሊያን ጦርነት ወቅትም ሞሶሎኒ በዓለም ዙሪያ በተከለከለ መርዝ አባቶቻችንን የፈጃቸው ዳግም አድዋ እንዳይደገም ከፍተኛ ፍርሀት ይዞት ስለመሆኑ የታሪክ ድርሳናት ይናገራሉ፡፡
በኛም በኩል የጣሊያንን አቅም ዝቅ አድርገን በመመልከት እንዳንዘጋጅ ዐይናችንን ጋርዶ ያዘናጋን የ2ኛው ዙር የኢጣሊያ ተዋጊዎች በታንክና በዘመናዊ አይሮፕላን እንደሚዋጉ ጭራሽ ጥርጣሬ እንዳይኖረን አዘናግቶናል፡፡
እንግዲህ የተነሳሁበትን ጭብጥ ሳጠቃልለው ዘንድሮ ለማከበር ጓጉ ተን የነበረው ከላይ ባጭሩ የዘረዘርኩትን ደማቅ ታሪክ ነበር፡፡ አንዳንዴ ይኸ አንፀባራቂ ታሪክ እኛ ሀገር በመፈፀሙ በራሱ ዕድለ ቢስ የሆነ ይመስለኛል፡፡ የዘንድሮው የዓድዋ ድል በዓል በመንግሥት መ/ቤቶች በተሰገሰጉ መንደር ናፋቂ የጎሳ ፖለቲከኞቾ አማካኝነት በፖለቲካ ሰንሰለት ተጠልፎ ስለነበር ደምቀንና አሸብርቀን ባንድ መንፈስ ተስማምተን ልናከብረው ይቅርና በያመቱ መነታረኪያ አጀንዳ እየሆነ ነው የመጣው፡፡ እውነት ለመናገር ይኸ ታሪክ በሌላ ሀገር ተፈፅሞ ቢሆን እንዴት ባለ ፍቅርና ወኔ ደምቀው ያከብሩት እንደነበር ሳስብ ቁጭት ውስጥ እገባለሁ፡፡ የሚያሳዝነው አኩሪና በዓለም ደረጃ በወርቅ ቀለም የተፃፈ ያባቶቻችን ገድል የተመዘገበበትን ታሪክ በደስታ በፌሽታ ለማክበር ሄደን በመንግሥት መዋቅር በተሰገሰጉ መንደር ናፋቄ የጎሳ አፍቃሪ ፖለቲከኞች ሴራ የተነሳ ከበርካታ አላስፈላጊ ጉዳት ይጠብቁናል ብለን በምናስበባው ከራሳችን አብራክ በወጡ የራሳችን ወገን የፀጥታ አካላት ተደብድበንና ተንገላትተን አንገታችንንን በሐዘን ደፍተን ወደቤት መመለሳችን ነው፡፡ ከዚህ የበለጠ ፍቱን መድኃኒት የማይገኝለት የውስጥ ሕመም በፍፁም የለም፡፡
ዛሬ ላይ በጎሳ አምላኪ ፖለቲከኞችና በመንግሥት ዳተኝነት ሰላም ቢርቀንም ሰላም መመኘት አይከፋምና እስከ ሳምንት ቸር እንሰንብት፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይጠብቃት ይታደጋትም!
