የአርሰናል የማጥቃት እንቅስቃሴ ዋና አድራጊ ፈጣሪው ተጫዋች ከልጅነት እስከ እውቀት ከአርሰናል ውጪ ሌላ ክለብ የማያውቀው ቡካዮ ሳካ ለ5 አመት በእጮኝነት አብራው ከቆየችው ቶላሚ ቤንሰን ጋር የነበራቸውን የፍቅር ግንኙነት አንድ ደረጃ ከፍ ለማድረግ በመወሰናቸው ቀለበት ማሰራቸው ወይም Engaged መሆናቸውን በይፋ አብስረዋል።
የአርሰናሉ ኮከብ ቡካዮ ሳካ የረጅም ጊዜ ፍቅረኛውን ቶላሚ ቤንሰንን ለትዳር ማጨቱን በራሱ ማህበራዊ ትስስር ገፆ ላይ ይፋ በማድረግ ለሁሉም አጋርቷል።
ሁለቱ ፍቅረኛሞች በትዳር ለመጣመር የወሰኑት፣ ሳካ በሜዳ ላይ ለክለቡ አርሰናል ድንቅ አቋም እያሳየ ባለበት በዚህ ወቅት ነው።
ሳካ እና ቶላሚ ቤንሰን፣ ሁለቱም 24 ዓመት ሲሆናቸው፣ ግንኙነታቸውን የጀመሩት ከ2020 ዓ.ም ጀምሮ ነው። ጥንዶቹ ሁሌም ቢሆን የግል ሕይወታቸውን ከሕዝብ ዓይን ርቀው ለማቆየት ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል። ይሁን እንጂ ቶላሚ በ2022ቱ የኳታር የዓለም ዋንጫ እና በቅርቡ በተካሄደው የዩሮ 2024 ውድድር ላይ በስታዲየም ተገኝታ ሳካን ስትደግፍ መታየቷ፣ ግንኙነታቸውን ይፋ አድርጎታል።
ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት፣ የሰሜን ለንደኑ ኮከብ ሳካ ፍቅረኛውን ያጫት በለንደን ከተማ በሚገኝ አንድ የቅንጦት ሆቴል ውስጥ ባዘጋጀው ልዩ እና የፍቅር ምሽት ላይ ነው። ሳካ ለቶላሚ ባቀረበው “እጅግ በጣም ትልቅ” ተብሎ በተገለጸው የአልማዝ ቀለበት እንዳስደመማት እና “ፍፁም እንደተደነቀች” ምንጮች ለጋዜጠኞች ገልጸዋል።
ቶላሚ ቤንሰን ከእግር ኳስ ዓለም ውጪ በለንደን የሲኒየር ፕላኒንግ ኤክስኪዩቲቭ ሆና የምትሠራ ሲሆን፣ በበርሚንግሃም ሲቲ ዩኒቨርሲቲ የሕዝብ ግንኙነት እና ሚዲያ ተምራ ተመርቃለች። ከዚህም በተጨማሪ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ባላት የፋሽን ስሜት እና በሚዲያ በሚታይበት ቁመና ምክንያት በደጋፊዎች ዘንድ ተወዳጅነትን አትርፋለች።
የቡካዮ ሳካን የማህበራዊ ትስስር ገፆች የምትቆጣጠረው እሷ ናት።
የሳካ የጋብቻ ጥያቄ በአርሰናል ደጋፊዎች ዘንድ በስፋት አድናቆትንና ደስታን የፈጠረ ሲሆን፣ ተጫዋቹ በግል ሕይወቱም ሆነ በእግርኳስ ሕይወቱም ስኬታማ መሆኑን የሚያሳይ ክስተት ሆኗል።
(መናኸሪያ ሬዲዮ)
