ቤተ ክርስቲያን በምን ዐይነት የአመራር ሁኔታ ውስጥ ትገኛለች?

Date:

አመራር ሲባል የአንድን አካል እሴት፣ እምነት፣ በጎ አስተሳሰብና ጠባይ በተመሪዎች ውስጥ በማሳደር አርአያ በሚሆን አግባብ በጎ ተጽእኖ ማሳረፍ ማለት ነው። ወደ ቤተ ክርስቲያን በቀረበ መልኩ ሲተረጎም ደግሞ መልካም አርአያነት ባለው ሕይወትና በዕውቀት ምእመናን መመገብና ለሰማያዊ ሕይወት ማብቃት ማለት ነው። የሚያሠራና ተደራሽ መዋቅር መዘርጋት፣ አቅም ያለው የሰው ኃይል ማፍራት፣ አገልጋይና አገልግሎትን ማገናኘት፣ የተማከለ የፋይናንስ ሥርዓት መዘርጋት፣ አሳታፊነት እና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ተባብሮ መሥራት የመልካም አመራር መገለጫዎች ናቸው። እነዚህን መገለጫዎች ለሚመሩት ተቋም በሚሆን እና ዘመኑን በዋጀ አግባብ ተግባራዊ የሚያደርጉ ደግሞ መሪዎች ይባላሉ። በዚህ አግባብ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ያለችበትን የአመራር ሁኔታ ስንመለከት ብዙ ፈተናዎች ያሉበት ሆኖ እናገኘዋለን። ዋናዋናዎቹም፡-

  1. በሕይወትና በዕውቀት የሚመሩ አባቶች ቁጥር መቀነስ

አመራርነት በዓለሙም ውስጥ አርአያነት ያለው ሕይወትን እንደሚሻ ይታመናል። አታርፍዱ፣ ሥራ አትበድሉ፣ የተሰጣችሁን ሥራ በጊዜው አጠናቅቃችሁ አቅርቡ ብሎ ሌሎችን ለማዘዝ ሆኖ/አድርጎ መገኘት ያስፈልጋል። በቤተ ክርስቲያን ሲሆን ደግሞ በእጅጉ ይገባል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለሮሜ ክርስቲያኖች በጻፈው መልእክቱ “በሕግ የዕውቀትና እውነት መልክ ስላለህ፣ የዕውሮች መሪ፣ በጨለማም ላሉ ብርሃን፣ የሰነፎችም አስተማሪ፣ የሕፃናትም መምህር እንደሆንህ በራስህ ብትታመን፣ እንግዲህ አንተ ሌላውን የምታስተምር ራስህን አታስተምርምን? አትስረቅ ብለህ ምትሰብክ ትሰርቃለህን? አታመንዝር የምትል ታመነዝራለህን? ጣዖትን የምትጸየፍ ቤተ መቅደስን ትዘርፋለህን? በሕግ የምትመካ ሕግን በመተላለፍ እግዚአብሔርን ታሳፍራለህን?” (ሮሜ 2፡19-23) እንዳለ ሌላውን በአግባብ ለመምራት ራስን መምራት መቅደም አለበት። ቅዱስ ጳውሎስ በወቅቱ የነበሩ አይሁዳውያንን ለመገሠጽ ብቻ ሳይሆን ዛሬ በእኛ ዘንድ እየሆነ ያለውን በትንቢት መልክ የተናገረ በሚመስል መልኩ በቤተ ክህነት ከፍተኛው መዋቅር ውስጥ ሳይቀር አትስረቁ የሚሉ ግን የሚሰርቁ፣ አታመንዝሩ እያሉ የሚያመነዝሩ፣ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ የሚመዘብሩ “መሪዎች” እየታዩ ነው። አባቶች በመንፈሳዊ ሕይወትም ሆነ በነገረ ሃይማኖት ዕውቀት እንደ ስማቸው አንቱ የሚባሉ ሊሆን ይገባል። እንዳለመታደል ሆኖ ግን ሃይማኖትና ምግባር ከዕውቀትና ጥበብ ጋር የተስማማላቸው አባቶችን በአመራርነቱ ቦታ ላይ ማግኘት እየቸገረ መጥቷል። የሚፈሩ፣ የሚከበሩና የሚታፈሩ የዐደባባይ አባቶች ቁጥር ጥቂት ነው። በቅዱስ ሲኖዶስና በጠቅላይ ቤተ ክህነት ደረጃ የሕይወትና የዕውቀት ጥያቄ የሚነሣባቸው አካላት ካሉ አጠቃላይ እንደ ቤተ ክህነት መዋቅር የአመራር ችግር ውስጥ ነን ማለት ነው።

  1. ዓለማዊነትና ጎጠኝነት ያጠላባቸው አመራረሮች

ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሥጋዊ አስተሳሰብ፣ ጎጠኝነት፣ ገንዘብንና ሥልጣንን መውደድ፣ ለወገኔ ይበጃል ብሎ ማድላት ተንሠራፍቷል። የአሕዛብ መምህር የተባለው ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ “በአንድ አሳብ ተስማሙ፣ አንድ ፍቅር፣ አንድም ልብ አንድም አሳብ ይሁንላችሁ፤ ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ አንድ ስንኳን አታድርጉ። ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቁጠር፤ እያንዳንዱ ለራሱ የሚጠቅመውን አይመልከት ለባልንጀራውም ደግሞ እንጂ” (ፊል. 2፡2-4) ብሎ እንደተናገረው የቤተ ክርስቲያን መዋቅር ሊመራ የሚገባው በዚህ ሥርዓት ነው። ነገር ግን በዓለሙ ደረጃ በሕግ የሚከለከሉ ጉዳዮች ስንኳ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሲፈጸሙ ይታያሉ። በተለይም መንጋውን በርትዕ ይጠብቃሉ የሚባሉት ጳጳሳት ለወገኔ በሚል አንደኛውን አካል በማቅረብ ሌላውን በማራቅ ሊሠሩ አይገባም፤ ሥልጣነ ክህነት የሚያስቀማ ድርጊት ነውና። ማንነትን/ዘውግን መሠረት ያደረጉ ሢመቶች፣ ጎጥን ያማከሉ ቅጥሮች እንዲሁም በገንዘብና በአማላጅ የሚፈጸሙ ምደባዎች አገልጋይና አገልግሎት እንዳይገናኝ አድርገዋል። በቤተ ክህነት የሚፈጸመው አንዳንዱ ድርጊት በዓለማዊ መሥሪያ ቤቶች ስንኳ ሊፈጸም ይችላል ተብሎ የሚታሰብ ሆኖ አይታሰብም። ክርስትና ብልጫው ምንድን ነው ብሎ ለመጠየቅ በሚያስደፍር መልኩ የቤተ ክህነቱ መዋቅሮች ከዓለማዊ መሥሪያ ቤቶች ተለይተው የሚታወቁበት በጎ መዓዛ የላቸውም።

  1. የጳጳሳት ገደብ አልባ አስተዳዳራዊ ሥልጣን

በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉት ሦስቱምአካላት ማለትም ሠራዔ ሕግ፣ ፈጻሜ ሕግ እና ፈታሔ ሕግ በጳጰሳት የተያዙ ናቸው። በሕገ ቤተ ክርስቲያንም ሆነ በሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደር ደንብ ጳጰሳት ያላቸው ሥልጣን ገደብ አልባ ነው። የሲኖዶስ አባል ሆነው ሕግ ያወጣሉ፤ ጠቅላይ ቤተ ክህነትን በዋና ሥራ አስኪያጅነት፣ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያንን እና መምሪያዎችን በበላይ ጠባቂነትበማስተዳደርየአስፈጻሚነቱን ቦታ ይዘዋል። በሕግ ተርጓሚነትም የመጨረሻ ውሳኔ/ፍርድ ሰጪ አካል ቅዱስ ሲኖዶስ ነው። ሊቃነ ጳጳሳት ሁሉንም ሥልጣን ጠቅልለው መያዛቸው ብቻ ሳይሆን በአግባቡ መጠቀም አለመቻላቸውም ሌላው ክፍተት ነው። ካህኑ ዮቶር ለሙሴ የነገረው የአስተዳደር ተዋረድ በመዋቅር እንጂ በተግባር እየጠፋ ከመጣ ቆይቷል። ጳጰሳት ውክልና ሰጥተው የሚተውት ሥልጣን የለም፤ ከገንዘብ እንቅስቃሴ እስከ አጥቢያ አገልጋይ ቅጥር ድረስ ውሳኔ ይሰጣሉ። በዚህ ምክንያት ምእመናን ቤተ ክርስቲያን የጳጳሳት ብቻ እንደሆነች እንዲያስቡ አድርጓል። የሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች፣ የመምሪያ ኃላፊዎች፣ የአጥቢያ አስተዳዳሪዎችና አገልጋዮች፣ የገዳማት አበምኔቶችም ሳይቀር በጳጳሳት ፈቃድ እና/ወይም ውሳኔ ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላው እንዲዛወሩ ይደረጋሉ።

  1. የምእመናን ሱታፌ የሌለበት አሠራር

ቤተ ክርስቲያን የምእመናን ናት። በገቢር ግን እያንዳንዱ መዋቅር በመዋቅሩ ላይ ያሉ አካላት ቤት ሆኗል። የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ መተዳደሪያ ደንብ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጀምሮ እስከ አጥቢያ ድረስ መዋቅሩ በካህናት፣ በሰንበት ትምህርት ቤት እና በምእመናን ተወካዮች መደራጀት እንዳለበት ቢገልጽም የድንጋጌው አተገባበር በአጥቢያ ደረጃ ብቻ ተወስኖ ቀርቷል። ይህም ሕግ ከማውጣት ያለፈ ተግባራዊ የማድረግ ክፍተት መኖሩን ከማሳየቱም በላይ ምእመናንን ለቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ባይተዋር እንዲሆኑ አደርጓል። ምእመናንን በሙያቸው ከቅዱስ ሲኖዶስ ጀምሮ እስከ አጥቢያ ሰበካ ጉባኤ ድረስ በአማካሪነት እና በባለድርሻነት ሱታፌ ሊኖራቸው የሚገባ ቢሆንም ይህ ሲደረግ አይስተዋልም። ምእመናን ቅዳሴ አስቀድሰው ከመመለስ ያለፈ ሚና እንዳላቸው ግንዛቤ አልተፈጠረም ወይም ከጉዳዩ መራቅን እንደ መፍትሔ ለመቁጠር የሚያስገድዳቸው ገፊ ሁኔታ በቤተ ክርስቲያን መዋቅር ውስጥ አለ። ስለሆነም ቤተ ክርስቲያን የጳጰሳት ብቻ ሳትሆን የሁሉም አማኞች እንደመሆኗ መጠን ሁሉም ድርሻውን ይወጣ ዘንድ ሥራውን ለሠሪው መስጠት ያስፈልጋል።

  1. በመዋቅር እንጂ በገቢር ተደራሽ ያለመሆን

ቤተ ክርስቲያን አገልግሎቱ የሚፈስበት ከቅዱስ ሲኖዶስ እስከ አጥቢያ ሰበካ ጉባኤ ድረስ መዋቅር አላት። ግን በዚህ መዋቅር ውስጥ የሚፈጸሙ አገልግሎቶች ምእመናንን የሚያሳትፉ አይደሉም። በመዋቅሩ ውስጥ ምእመናን የነበራቸው ሱታፌ በሕግ ደረጃም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ እንዲመጣ ተደርጓል። በሕግ ተቀምጦ የማይተገበር፣ በጠቅላላ ጉባኤያት የምእመናን ተሳትፎ አለመኖሩ እና ውክልናው አግባብነት የሌለው መሆኑ በቤተ ክህነቱ መዋቅርና በምእመናን መካከል ሰፊ ክፍተት እንዲኖር አድርጓል። ከፓትርያርኩ ጀምሮ እስከ መደበኛው ምእመን ድረስ የንስሐ አባት የትስስር ሰንሰለት አላት። ግን ይህን ሰንሰለት የምእመናንን የአገልግሎት ሱታፌና ቀኖናዊ ሕይወት መጠበቂያ መንገድ አድርጎ የሚጠቀም/የሚቆጣጠር መዋቅር የለም።

  1. መርሕ አልባ የሰው ሀብት አስተዳደር

ከጵጵስና ሢመት ጀምሮ እስከ አጥቢያ ሰበካ ጉባኤ ቅጥር ድረስ የመመልመያ መስፈርት ኖሮት የሚፈጸም ሳይሆን ዘፈቀዳዊ ነው። የሰው ሀብት አስተዳደር ሥርዓቱ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የምግባር ሳይሆን የእምነት ጥያቄ የሚነሣባቸው ሰዎች እንዲገቡ የሚፈቅድ ነው። ቅዱሳን ሐዋርያት የእግዚአብሔርን ቃል ትተን መዓድን እናገለግል ዘንድ የሚገባ አይደለም ብለው ሕዝቡን የሚያገለግሏቸው ሰባት ዲያቆናት በመረጡበት ወቅት “ወንድሞች ሆይ፣ በመልካም የተመሰከረላቸውን፣ መንፈስ ቅዱስና ጥበብ የሞላባቸውን መርጣችሁ አምጡ” (ሐዋ. 6፡3) ነበር ያሉት። ከዚህ ባነሰ መስፈርት ቤተ ክርስቲያንን ለማስተዳደር ወደ ከፍተኛው መዓርግ የሚመጡ ተሿሚዎች ሊኖሩ አይገባም። ቤተ ክርስቲያን ምእመናንን የሚያገለግሉ ጳጳሳትን የምትመርጥበት የጸና ሥርዓት ያላት ናት። በጰጵስና ደረጃ ያለውን የምርጫ ሥርዓት ማስተካከል ከታች ያሉትን ጉድለቶች ለማስተካከል መንገዱን ቀና ያደርገዋል።   

  1. ያልተማከለና ለምዝበራ የተጋለጠ የፋይናንስ አስተዳደር ሥርዓት

ቅዱስ ሲኖዶስ ወይም ጠቅላይ ቤተ ክህነት የቤተ ክርስቲያንን ገቢ በተማከለ ሁኔታ የሚያስተዳድርበት፣ ገቢ ሰብስቦና በጀት መድቦ የሚመራበት ሥርዓት የለውም። አህጉረ ስብከት ከሁሉም አጥቢያዎች 20 በመቶ ሰብሰብስበው ከሰበሰቡት ገቢ ላይ 20 በመቶውን ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ይልካሉ። በከተማ ያሉ አጥቢያዎች ገቢ ከፍተኛ ቢሆንም ለሀገረ ስብከት ከ20 በመቶ በላይ ፈሰስ አያደርጉም። ምንም ገቢ የሌላቸው የገጠር አብያተ ክርስቲያናትም በተመሳሳይ ገቢያቸው ዝቅተኛ መሆኑ ግምት ውስጥ ሳይገባ ካላቸው ገቢ 20 በመቶ ፈሰስ እንዲያደርጉ ይጠበቅባቸዋል። ገንዘቡ የሚሰበሰብበት አግባብ ለምዝበራ በእጅጉ የተጋለጠ ነው። ከፍተኛ ገቢ ያላቸው አጥቢያዎች ገቢ የሌላቸውን፣ በንዋያተ ቅድሳትና በአገልጋይ እጥረት የተዘጉትን፣ በተለያዩ ችግሮች የተፈቱ ገዳማትንና የጉባኤ ቤቶችን ማገዝ የሚቻልበት ሥርዓት የለም፤ ለመዘርጋትም አሳቡ የለም።  

በአጠቃላይ ቤተ ክርስቲያን ቀድሞ የነበራት ተሰሚነትና በጎ ተጽእኖ ቀንሷል። በትምህርት፣ በአስተሳሰብ፣ በሥልጣኔ መሪ የነበረች ቤተ ክርስቲያን ዘመኑን ዋጅቶ ባለመራመድ የነበራትን የመሪነት ቦታ በማጣት ሒደት ላይ ትገኛለች። ሠራዔ ሕግ የሕዝብ ተወካይ ምክር ቤት፣ የሥርዓተ ትምህርት አዘጋጅ ትምህርት ሚኒስቴር፣ የመድኃኒት ምንጭ ጤና ሚኒስቴር፣ አገር ጠባቂ የመከላከያ ሚኒስቴር፣ የተተኪ አመራር ማፍሪያ የልሕቀት ማእከል፣ የአገር አንድነት ማሠሪያ ገመድ፣ ለአፍሪካውያን ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለም ጥቁር ሰው መሆኑ ቅቡል ሆኖ በሰውነቱ እንዲከበር ያደረገውን ድል የአሸናፊነትን ልቡና በመሥራት የነጻነት ቀንዲል የሆነች ቤተ ክርስቲያን ዛሬ በብዙ መስፈርቶች ወደ ኋላ እንድትቀር የቤተ ክህነቱ ዘመኑን ያልዋጀ አካሔድ አሳሪ ሆኖባታል። ስለሆነም ቤተ ክርስቲያን ካለችበት ሊሻሻል የሚገባው የአመራር ሁኔታ ልትወጣና ዘመኑን ወደዋጀ የአመራር ሥርዓት መሸጋገር ይኖርባታል።  

ቤተ ክርስቲያን ምን ዓይነት አመራር ያስፈልጋታል?

   ቤተ ክርስቲያን ትውልዱን ለእግዚአብሔር መንግሥት የማዘጋጀት ሰማያዊ ተልእኮዋን በአግባቡ ለመወጣት እና የነገውን ትውልድ ሰብእና በመቅረፅ ረገድ የሰብአዊ ምሕንድስና ሥራዋን ለመፈጸም ዘመኑን የዋጀ አመራርና አሠራር ያስፈልጋታል። ይህም መሻት በብዙ ኦርቶዶክሳውያን ልብ ውስጥ አለ፡፡ ይህ ዕውን ይኾን ዘንድ ዛሬም ኾነ ነገ ቤተ ክርስቲያን ስንዱ እመቤት የሚያሰኛትን የነገረ ሃይማኖት ጥንቃቄ በአስተዳደርና በአመራርም መድገም ስትችል ነው። ቤተ ክርስቲያን በምድር ያለች የእግዚአብሔር መንግሥት ናትና መሠረታዊ መገለጫዎቿ ተጠብቀው ብቻ በምትሰጣቸው የአመራርነት ሚናዋ ተገልጠው ሊታዩ ይገባል። ይህን ዕውን ማድረግም በየዘመኑ የሚነሡ ኖላውያን እና ምእመናን የሁልጊዜ ሓላፊነት ነው፡፡

   በተለይም ቤተ ክርስቲያን ከውጭና ከውስጥ ተገዳዳሪዎች ጋር በተፋጠጠችበት እና እንደ ኢዮብ በፈተና በተከበበችበት በዚህ ዘመን የአሳዳጆቿን በትር መቋቋም የምትችለው በምትሰጠው ውጤታማ አመራር ነው። ፈተናውን ከባድ የሚያደርገው ከውጪው ተጽእኖ በላይ በውስጥ ያለው መንፈሳዊነት መዳከም እና ብልሹ የአስተዳደር ሥርዐት መስፈን ነው፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን በጥንቱ መንፈሳዊ ልዕልናዋ ጸንታ እንድትቆም ማስቻል እና በዘመኑ የአስተዳደር ጥበብ የተዋጀ አሠራር የሰፈነባት መንፈሳዊ ተቋም ማድረግ በሁለቱ ተገዳዳሪዎቿ የተሴረባትን ሴራዎች ማምከኛ መንትያ መንገዶች ናቸው፡፡  

   በማይታበል ሐቅ ቤተ ክርስቲያን ስንዱ እመቤት ናት፡፡ ለእኛ የደረሰችው ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ኾና የተገኘችው ግን ሥራ በፈቱ ጭንቅላቶች፣ ለህልውናዋና ልዕልናዋ ግድ የማይሰጥ ሰብእና ባላቸው አልፎ ሒያጅ የግዴለሽነት ስሜት ባሸነፋቸው መሪዎች እየተመራች አይደለም፡፡ ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ጉዳይ ነው ብለው፣ ነፍሳቸውን ስለበጎቻቸው በሰጡ መሪዎች ነው። ቀዳምያቱንና መጻዕያቱን በመረዳት፣ ያሉበትን ዘመን በመዋጀት፣ ደሀ ተበደለ ፍረድ ተጓደለ የሚል ቋሚ የፍትሕ ርትዕ ቅርስ ባላቸው አባቶች ነው። የቅርቦቹን እንኳ ብናስታውስ ልጆቻቸውን ብቻ ሳይሆን ምድራቸውንም በቅኝ እንዳይገዙ በመገዘት የአገራቸውን አሸናፊት በሩቅ ተሳልመው ያለፉት ሰማዕተ ጽድቅ አቡነ ጴጥሮስ አንዱ ናቸው። ሌላው ኮሚኒስታዊው መንግሥት ደርግ ቤተ ክርስቲያን የነበራትን ማኅበረሰባዊ መሠረት በማናጋት ከድህነት አረንቋ ለመጣል በሠራበት ወቅት ሩቅ አልመው ሁሉንም አሳታፊ የሆነ መዋቅር በመዘርጋት ቤተ ክርስቲያንን የታደጉት አቡነ ቴዎፍሎስን መጥቀስ ይቻላል። የቤተ ክርስቲያን ስንዱነት እንዲሁ ተሠርቶ አልቆ እንደ መና ከሰማይ የወረደ ጸጋ ሳይሆን ዋጋ የከፈሉ፣ የተሰጣቸውን መንፈሳዊ ጸጋና የማስተዋል ጥበብ ለሐዋርያዊ ተልእኳቸው ሥምረት የተጠቀሙበት አባቶች ስለነበሯት ነው፡፡ እናም ይህ ሐቅ ቤተ ክርስቲያንን ስንዱ እመቤት አሰኝቷታል፡፡ ይህ የአበውና እማት ብርታት ኢትዮጵያ ከነሐዋርያዊ እምነቷ ለዚህ ዘመን እንድትደርስ አስችሏታል፡፡ 

   አሁን ጥያቄው “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዚህ ዘመን ከመንፈሳዊ መሠረቷ ሳትናወጽ የማኅበረሰብን እሴት ከመቅረፅ ጀምሮ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የነበራትን በጎ ተጽእኖ ማስቀጠል ወደምትችልበት ቁመና መመለስ የሚቻለው በምን ዐይነት አመራር ነው?›› የሚል ነው፡፡ በቤተ ክህነቱ ውስጥ ነግሠው በሚታዩ መንፈሳዊ ድክመቶችና ከክርስትና መርሕ ጋር በሚጋጭ የዘውገኝነት በሽታ እንዲሁም ዘርፈ ብዙ በኾኑ አስተዳደራዊ ዝቅጠቶች ምክንያት ቤተ ክርስቲያን በመስቀለኛ መንገድ ላይ አቁመዋታል። በመሆኑም በዚህ ዘመን የተነሡ ጥያቄዎችን፣ ያጋጠሙ ፈተናዎችን እና የተጋረጡ ተግዳሮቶችን በመቋቋም ወደ ትክክለኛው መንገድ ለመቀጠል የሚያስችል አመራር ያስፈልጋል። የሚሰጡ ግብረ መልሶች ተገቢነት ብቻ ሳይኾን መልሶቹ የሚሰጡበት ፍጥነትም የቤተ ክርስቲያንን ልዕልና በማስጠበቅ ረገድ ወሳኝነት አለው፡፡

   መንፈሳዊ ጉድለቶችን በማስተካከል፣ አስተዳደራዊ ሥርዓትን በማዘመን፣ አሳታፊና ተደራሽ የሆነ አሠራር በመዘርጋት፣ ሕግና ሥርዓትን የተከተለ የሰው ሀብትና የፋይናንስ አስተዳደር ዕውን በማድረግ ያስፈልጋል። በተለይም ወደላይኛው መዓረግ የሚመጡ አባቶች የሚመረጡበት ጥብቅ መስፈርት በማስቀመጥ ግልጽና ተጠያቂነት ያለበት የአሿሿም ሥርዓት፣ የምእመናንን ሱታፌ ያማከለ ጥቆማ እና እግዚአብሔርን ያስቀደመ ምርጫ በማድረግ ይደልዎ የሚባሉ አባቶችን ብቻ መሾም ይገባል። ወደ ነገ ለመሻገር እንደ ጥንቱ አባቶቻችን ዘመናችንን የሚቀድስ አመራር ማግኘት ለነገ የማይባል የቤት ሥራ ነው፡፡ ይህን ሓላፊነት የሚሸከም አመራር ምን ዓይነት አመራር መሆን ይገባዋል?

  1. ዘመኑን የዋጀ የአገልግሎት ሥርዓት (የነበረና ያለ እሴትን በዘመናዊ የቴክኖሎጂና የሥርዓት ውጤቶች መደገፍ)
  2. ከፕትርክና ጀምሮ እስከ ምንኩስና ድረስ ቀኖናዊ ሥርዓቱን የጠበቀ መስፈርት
  3. አርአያነት ያለው መንፈሳዊ ሕይወትን፣ ሙያንና ሥነ ምግባርን መሠረት ያደረገ የሰው ሀብት ምደባ አስተዳደር ሥርዓት
  4. የተማከለ የገንዘብ አስተዳደር ሥርዓት
  5. ምእመናንን፣ ባለድርሻ አካላትን እና ሁሉንም መዋቅሮች የሚያሳትፍ አሠራር
  6. በኦርቶዶክሳውያን ባለሙያዎች ሙያዊ ምክር የሚመሩ የቤተ ክርስቲያን መዋቅሮች (ከቅዱስ ሲኖዶስ ጀምሮ በየደረጃው ያሉ)
  7. በታወቀና በተጻፈ ሕግ የሚመራ ቤተ ክህነት
  8. የሚያሠራ፣ ፍትሐዊና ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ሕግ 
  9. የልሕቀት ማእከል የሆኑ ገዳማትና አብነት ትምህርት ቤቶች ዕውን የሚያደርግ አሠራር
  10. የቤተ ክርስቲያን ተቀዳሚ ተግባር ለሆነው ሐዋርያዊ ተልእኮ እና ለምእመናን ቀኖናዊ ሕይወት ቅድሚያ የሚሰጥ አመራር ሊኖር ይገባል። ይህ ደግሞ ሊሳካ የሚችለው ለዚህ አመራርነት የሚመጥኑ አባቶች በቦታው ሲቀመጡ ነው።

አክሊል የሆነችው ሢመት መርጣ የምታርፍባቸው አባቶች

ከፍ ሲል ቤተ ክርስቲያን ያለችበትን የአመራር ሁኔታና የሚያስፈልጋትን አመራር ተመልክተናል። አሁን ደግሞ የሚፈለገውን አመራር ለመስጠት የሚችለው ምን መስፈርቶችን የሚያሟላ አባት ነው የሚለውን እንመለከታለን። የኤጲስ ቆጶስነት ሢመት ለሚገባው አባት አክሊል ስትሆን ለማይገባው ደግሞ እሾህ እንደምትሆንበት ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ሲከሠት የኖረ እውነት ነው። መንፈሳዊት ሢመት አክሊል የምትሆነው ኖላዊነታቸውን አምነው የተጣለባቸውን አደራ ለመወጣት ለሚተጉ አባቶች ሲሆን እሾህ የምትሆነው ደግሞ ሳይገባቸው ሰማያዊውን ምሥጢር ጊዜያዊ ጥቅም ለማግኘት ለሚሞክሩ ሲሞናውያን ነው። ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ኤጲስ ቆጶሳትን የምትሾመው ምእመናንን ከአውሬ እንዲጠብቁ ለኖላዊነት ነው። ኖላዊ ደግሞ በበር የሚገባ ጠባቂ፣ ነፍሱን ስለበጎቹ አሳልፎ የሚሰጥ ዋስ፣ “ደጃፍ የመለሰውን፣ ማጀት የጎረሰውን” ለልጆቹ እንደሚያወርስ አባት ነው። መንፈሳዊ አባት ተብሎ የሽፍታ ተግባር የሚፈጽም፣ ኖላዊነቱን ዘንግቶ ምንደኛ የሚሆን፣ ሰማያዊውን ሢመት በጊዜያዊ ጥምቅ የሚለውጥ፣ አምላካዊውን አደራ ዘንግቶ ፈቃደ መንግሥትን ለመፈጸም የሚደክም ከሆነ ሢመት አክሊል መሆኗ ቀርቶ እሾህ ትሆናበታለች።

የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ትምህርት የሚናገረው ጵጵስና መንፈሳዊ አባትነት በመሆኑ ለሢመት የሚመረጡት በጥንቃቄ መሆኑን፣ በጥንቃቄ መመረጥ የሚኖርባቸውም ኃላፊነቱ ሰማያዊ፣ ሹመቱ አምላካዊ በመሆኑ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን ለመንፈሳዊው ሹመት የሚታጩ አባቶች አምላክን የሚያስደስቱ፣ ሰዎችን ወደ አምላካቸው ለማቅረብ የማይታክቱ፣ ምድራውያንን ከሰማያውያን የሚያገናኙ መሆን እንዳለባቸው ነው (ሐመር መጽሔት 30 ዓመት ቍጥር 5፣ ግንቦት 2015 ዓ.ም)። የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ተሿሚዎች በምእመናን ሥጋዊና መንፈሳዊ ሕይወት ላይ ሥልጣን የሚሰጥ፣ የተሰጡትን ኃላፊነት በአግባቡ አለመወጣትም ተጠያቂነቱ ምድራዊ ሳይሆን ሰማያዊ በመሆኑ ነው። ስለሆነም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አባቶችን በጥንቃቄ መምረጥ የሚገባት ከእውነት ላለመውጣትና ከአምላክ ፈቃድ ላለመራቅ ነው። ቤተ ክርስቲያን “ጊዜ የወደደውን ዘመን የወለደውን” የምትከተል ከሆነ ተልእኮዋ የአምላክን ፈቃድ መፈጸም፣ አገልግሎቷም የአምላክን ቃል ለሰው ልጆች ሁሉ ማድረስ መሆኑ ይቀራል።

በየጊዜው በተካሔዱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምርዓተ ጉባኤ ውሳኔ የተሰጠባቸው አንገብጋቢ ችግሮች ተፈጻሚ አለመሆናቸው፣ ምእመናን በአባቶቻቸው ተስፋ እንዲቆርጡ መንፈሳዊ ሕይወታቸውን እንዲጠራጠሩ አንዳንዶችም ከቤተ ክርስቲያን ወጥተው ሲባዝኑ በክፉ አውሬ እንዲበሉ ምክንያት ሆኗል። እንዲህ ያለውን ችግር ማስወገድ ከሚቻልባቸው ተግባራት አንዱ ለኤጲስቆ ጶስነት የሚመረጡ መነኰሳት የተጣለባቸውን መንፈሳዊ ኃላፊነት ለመወጣት ብቁ መሆናቸውን በማረጋገጥ ነው። ይህን ለማድረግ በዋናነት ሁለት ተግባራትን ማከናወን ይገባል።

በአንድ በኩል አምላካችን ለዚህ ለተቀደሰ ኃላፊነት ብቁ የሚሆኑትን አባቶች እንዲገልጥልን በጸሎት መጠየቅ ሲሆን ሁለተኛው ምርጫውን ከምንም ዓይነት ምድራዊ መስፈርት በማራቅ በቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ብቻ እንዲከናወን ማድረግ ነው። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየታየ ያለው ደምና አጥንት ቆጥሮ፣ ገንዘብ ከፍሎና ተቀብሎ፣ ሥጋዊ አሳብና ፍላጎት ባጠላበት አግባብ ደጋፊ ለማብዛት እንጂ እግዚአብሔርን ለማስደስት እና ምእመናንም ትጉህ እረኛ እንዲያገኙ ከመሻት ያልሆነ ምርጫ ሊታረም የሚገባው ነው። እንዲህ ዐይነት ከአባት የማይጠበቁ፣ ከእግዚአብሔር ፈቃድ የራቁ ሥጋዊ ፍትወቶችን መዝጋት የሚቻለው ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን መነሻ በማድረግ የምርጫ መስፈርት በማዘጋጀት ነው።

የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ ደንብ እንደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዘርን ቀዳሚ መስፈርቱ ያላደረገ እንደ አይሁድ ከእኛ በላይ ለፈጣሪ በሚል ከንቱ ትምክህት ከዚህ አካባቢ ብቻ ይመረጥ የማያሰኝ ከየትኛውም ቋንቋ ተናጋሪ ቢሆን መንፈሳዊነቱ፣ መንፈሳዊ ዕውቀቱ እና የአስተዳደር ብቃቱ ብቻ እየታየ የሚሾምበት መሆን ይገባዋል። በወንጌል አንተ አይሁዳዊ አንተ ግሪካዊ የሚል ክፍፍል ስለሌለ መንጋውን ለመጠበቅ ብቃት ያላቸውን ከማንኛውም ቋንቋ ተናጋሪ መፈለግ ይገባል። ይህ ሲባል ግን ቋንቋውን የሚችል ብቻ ሳይሆን የእኔ ዘውግ መሆኑ ተረጋግጦ ይሾምልኝ ከሚል ምድራዊ መስፈርትም መራቅ ያስፈልጋል።

በአገልግሎታቸው እና በመንፈሳዊ ሕይወታቸው እግዚአብሔር የሚደሰትባቸው አባቶች ከየትኛውም ቋንቋ ተናጋሪ ወገኖቻችን መካከል ሲመረጡ መስፈርቱ የጎሣ ወይም የአካባቢ ተዋጽዖ ሳይሆን የመንፈሳዊነትና የመምራት ብቃት ብቻ መሆን ይገባዋል። ዘመዴ፣ የጎጤ ልጅ፣ ወገኔ መመረጥ ይኖርበታል የሚል መስፈርት ማውጣት በአሮጌ አቅማዳ አዲስ የወይን ጠጅ ለመያዝ እንደመሞከር ነው። አምላካችን እግዚአብሔር ሐዋርያትን የመረጠው የቋንቋ መስፈርት አውጥቶ ወይም የአካባቢ ተወካይ ያስፈልጋል ብሎ ሳይሆን ለመንፈሳዊው ሢመት ብቃት ያላቸው መሆናቸውን አውቆ ነው። አሁንም ሆነ ወደ ፊት ተግባራዊ ሊደረግ የሚገባው የብቃት እንጂ የውክልና መስፈርት አይደለም። ማወቅ የሚገባው ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ ሹመትን ሽተው “ሹመት በተርታ ሥጋ በገበታ” ያሉትም፣ ከእኛ ውጪ ማን ሊሾም ብለው ተመክተው “ወንጌል ካለ ኦሪት፣ ጥምቀት ካለ ግዝረት” ያሉትም መጥፋታቸውን ነው።

የጵጵስና አክሊል የምታርፍባቸው አባቶች ሲመረጡ መንፈሳዊ ሕይወት ያላቸው መሆናቸው ቀዳሚው የምርጫ መስፈርት ሲሆን የአስተዳደር ብቃት ደግሞ ሁለተኛው መስፈርት መሆን ይገባዋል። ለመንፈሳዊው ሹመት ብቁ የሆኑትን ማግኘት የሚቻለውም በብልጣብልጥነት ወይም እኔ ያልኩት ካልሆነ በሚል ግትርነትም አይደለም። ገንዘብ ሰጥተው ለመሾም የሚሞክሩትንም፣ ገንዘብ ተቀብለው ለማሾም የሚጣጣሩትንም. የእኔ ወገን ብቻ ይሾምልኝ የሚሉትም ድርጊታቸው ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ያፈነገጠ መሆኑን ማወቅ አለባቸው። ከዚህ በተጨማሪም የዚህ ደም ያላቸው ካልተሾሙ ሞተን እንገኛለን ባዮችም ለቤተ ክርስቲያን አይጠቅሙም። ሢመቱ የሚገባው ትሕትናን ከግብረ ገብነት ለሠመረላቸው አባቶች ብቻ መሆኑን የኒቅያ ጉባኤ የመላጥዮስን ጉዳይ በተመለከተበት ጊዜ ደንግጓል (NPNF, second serious, vol. 3, 2012, P,46)። 

በዘመናችን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ኤጲስ ቆጶሳትን ለመሾም መከተል የሚኖርባት መስፈርት ለሢመት የሚታጩ አባቶች ምግባር ከሃይማኖት የሠመረላቸው መሆናቸው ብቻ ሳይሆን የአስተዳደር ብቃታቸው በጎሰኝነትና ሰውን በአካባቢና በቋንቋ ከመከፋፈል የጸዱ መሆናቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችል መመሪያ ማውጣት ነው። ምግባር ከሃይማኖት ያልሠመረላቸው ቢሾሙ ምእመናን ማግኘት የሚገባቸው መንፈሳዊ አገልግሎት ይቋረጣል፤ ትክክለኛ ኖላዊ አጥተውም ይባዝናሉ። የኢጲስ ቆጶሳት ሢመት እነ እገሌን እንዳይከፋቸው ተብሎ ሰዎችን ወይም መንግሥትን ለማስደስት መካሔድ የለበትም። ቋንቋና ዘርን ብቻ መሠረት በማድረግ ውክልናዊ ሢመት የሚሰጠው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንጂ ለቅዱስ ሲኖዶስ አለመሆኑን ጠንቅቆ መረዳት ይገባል።      

ዘመናችን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ፈተና ላይ የወደቀችበት፣ ምእመናንም ከውጫዊ ፈተናው በተጨማሪ በአባቶቻቸው ድርጊት እየተማረሩ ቤተ ክርስቲያንን ሔደው ለመሳለም ከመሳቀቅ ደረጃ የደረሱት አንዳንድ አባቶች የተሰጣቸውን መንፈሳዊ ኃላፊነት በሚገባ ባለመወጣታቸው ነው። ምእመናንን ከሚያሳቅቁ ተግባራት አንዱ በመንፈሳዊ ሕይወትም በአስተዳደር ችሎታም አርአያ መሆን የሚችሉ አባቶች ቁጥር እየሳሳ መምጣት ነው።

የምግባርና የአስተዳደር ጥያቄ የሚነሣባቸው አባቶች ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ውለታ የሚውሉት እነርሱ መንፈሳዊ ሕይወት ከአስተዳደር ብቃት የሠመረላቸው ባይሆኑ እንኳ የጃፓኑ ንጉሥ ሚጂ ተስፋፊ የመሬት ከበርቴዎችን ድርጊት ለማራቅ የሚያስችለውን ተግባር በመፈጸም አገሩን ከኋላ ቀርነት እንደታደገው ያለ ሥራ በመሥራት ነው። በዘመናችን ቤተ ክርስቲያንን ለመምራት ኃላፊነት የተጣለባቸውም እነርሱ መልካም መሥራት ቢያቅታቸው መሥራት የማይችሉት እየገቡ ለቤተ ክርስቲያን ተጨማሪ ፈተና እንዳይሆኑባት አሻጋሪ ሆነው በመስፈርቱ መሠረት መርጠው መተካት መቻል አለባቸው።

በአጠቃላይ ቤተ ክርስቲያን ለምትሻው አመራር ወደፊት የሚመጡ ተሿሚዎች የሚቀበሉት ሹመት አምላካዊ አደራ መሆኑን የተረዱ፣ የተበላሸውን የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ለመለወጥ የሚተጉ፣ አምላካቸውን አጋዥ አድርገውና ምእመናንን ይዘው በረሃውን ገነት ለማድረግ የሚፋጠኑ፣ እንደ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ ክህነት መክሊት መሆኑን ተረድተው ለማትረፍ የሚተጉ፣ ሰው ተክተው፣ ተተኪ አፍርተው ለማለፍ የሚሞክሩ፣ ከከተማው ይልቅ ሀገረ ስብከታቸው የሚናፍቃቸው፤ ከዋዛ ፈዛዛ ይልቅ መንፈሳዊ ሕይወት የሚያስቀናቸው፣ የተጨነቀ ክርስቲያንም ይሁን አረማዊ ቀርቦ ሲጠይቃቸው እንደ ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ የችግሩን ምክንያት ተረድተው መፍትሔ በመስጠት የቤተ ክርስቲያንን ብርሃንነት ለዓለም የሚገልጡ (ስንክሳር ዘመስከረም)። ክርስቲያኖች አርአያነታቸውን ተከትለው በእምነት እንዲጸኑ ምክንያት የሚሆኑ፣ አሕዛብም ትሩፋታቸውን አይተው ወደ ቤተ ክርስቲያን ለመቅረብ እንደ እኊ ቅዱስ ምክንያት የሚሆኑ መሆን ይገባቸዋል። (ትርጓሜ ወንጌል)።

በካህናት፣ በሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች፣ በምእመናን ሱታፌ የሚመረጡ ኤጲስ ቆጶሳት በዘመናችን የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ከሆኑ አባቶች መካከል በመንፈሳዊ ሕይወትም፣ በዘመናዊ በዕውቀትም አርአያ የሚሆኑት ቍጥር ጥቂት በመሆናቸው ይህን የሚቀይሩ፣ ጎልቶ የሚታየውን ዓለማዊነትና ጎጠኝነት የሚያስተካክሉ፣ ገደብ የሌለው የሆነውን የጳጳሳት ሥልጣን በማስተካከል በቀኖና ቤተ ክርስቲያን የሚመሩ፣ አመራራቸውም ሆነ አገልግሎታቸው ምእመናንን አሳታፊ እንዲሆን የበኩላቸውን የሚወጡ፣ በሕግና ሥርዓት የማይመራውን የሰው ሀብት አስተዳደር የሚለውጡ፣ ለምዝበራ የተጋለጠውን ያልተማከለ የንብረትና ገንዘብ አስተዳደር ኦርቶዶክሳውያን ባለሙያዎችን በማማከር የሚያስተካክሉ መሆን ይገባቸዋል። እንዲህ ያሉትን አባቶች አሁን የሚታማው በሁለትና በሦስት ጎራ ተከፍሎ ቃላት በመወራወር ማግኘት አይቻልም። አሁን ያሉ አባቶች በእግዚአብሔርም በታሪክም ተጠያቂ እንዳይሆኑ ቀኖና ቤተ ክርስቲያን የሚያዝዘውን ብቻ በመፈጸም፣ ጸንቶ በቆየው ቀኖና ከአድሎና ከወገንተኝነት ወጥተው ውግንናቸው ለእግዚአብሔርና ለምእመናን ሊሆን ይገባል።  

በአገልግሎት ሒደት የሚታየውን የማስፈጸም አቅም ማነስ ለማስወገድ ዘመኑ የሚጠይቀውን አባት በተገቢው ቦታ ማስቀመጥ ከተቻለ አሁን ያለው ሁኔታ እየተቀየረ የማይሔድበት ምክንያት የለም። አባቶች መመሪያ ሰጭና ያዘዙት መፈጸሙን መቈጣጠርና መከታተል እንጂ ሲፈልጉ የአስፈጻሚነት ሚናውንም መጫወት፣ ሳይፈልጉ ደግሞ ከነጭራሹ መተው የሚታረመው ለመንበሩ የሚመጥኑት እየተተኩ የማይሠሩትና የማያሠሩት ከእነርሱ ሲማሩ፣ መልካም ከሚሠሩት ካልተማሩ ደግሞ ቦታቸውን ለቀው በጸሎት ተወስነው እንዲኖሩ መደረግ ይኖርበታል። መንፈሳዊው አገልግሎት የሚሠምረው ራሳቸውን ለአገልግሎት አሳልፈው በመስጠት እንጂ አንዱ በጎጥ ሌላው በገንዘብ ደጋፊ ለማብዛት በሚያደርገው ዓለማዊ አሠራር አይደለምና።

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ አደረሳችሁ፤ አደረሰን

ሰማያት ተከፈቱ ፣ ምስጢርም ተገለጠ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘመዷ ቅድስት...

አባቴ ለእኔ አባት ብቻ አልነበረም፤ ለእናቴ ታማኝ ባል፣ ለሁላችንም ደግሞ የደስታ ምንጭ ነበር

"አባዬ… ዛሬ ላለሁበት ማንነት መሰረት የሆንከኝ አንተ ነህ!" ​የአርቲስት...

የአንበሶቹ ትንሳኤ፦ የዳካር እንባ እና የቴራንጋ ድል

​በዳካር ሰማይ ስር ዛሬ ጨረቃ አልወጣችም፤ ይልቁንም በሚሊዮን የሚቆጠሩ...

የጥምቀት በዓል በመላ ሀገሪቱ በድምቀት እየተከበረ ነው

የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እና በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት...