የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዋሽንግተን ኢራንን ወደ ስምምነት ለማምጣት ከአዲስ ወታደራዊ ጥቃቶች ይልቅ በኢኮኖሚ ጫና ላይ ማተኮሯን ተናግረዋል።
ትራምፕ ከአክሲዮስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ ከወራት ግጭት በኋላ ጥንቃቄ የተሞላበት አካሄድ እየተከተሉ መሆኑን ገልጸው፣ ዋሽንግተን ከቴህራን ጋር በከፊል ብቻ ድርድር እያደረገች መሆኑን ጠቁመዋል።
ኢራን ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ስላለባት እና ለራሷ ወታደሮች ክፍያ መክፈል በመቸገሯ በፋይናንስ ረገድ በጣም መጥፎ ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ የገለጹት ትራምፕ፤ከሚያዝያ ወር ጀምሮ የተጣለው የአሜሪካ የባህር ኃይል እገዳ ጫናውን እንዳባባሰው ተናግረዋል።
አክለውም በአሁኑ ወቅት የአንድ በርሜል ነዳጅ ዋጋ ከ75 ዶላር በላይ መረጋጋቱ ለአሜሪካውያን ተጠቃሚዎች ያለውን የኢኮኖሚ ጫና እንደቀነሰው ገልጸዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፤የሆርሙዝ የባህር ሰርጥን ለትራንስፖርት ድጋሚ ለመክፈት በኦማን አሸማጋይነት የሚደረጉት ንግግሮች የመጨረሻ ደረጃ ላይ መድረሳቸውን የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ሆኖም ቴህራን አሜሪካ የባህር ኃይል እገዳውን እስካላነሳች እና የጦርነት ካሳ እስካልከፈለች ድረስ የውሃ መስመሩን ሙሉ በሙሉ እንደማትከፍት አፅንዖት ሰጥታለች።
በሰኔ ወር ላይ ተደርሶ የነበረው የተኩስ አቁም ስምምነት በመፍረሱ ውጊያው እንደገና የቀጠለ ሲሆን፤ ኢራን በአሜሪካ ጦር ሰፈሮች ላይ አልፎ አልፎ የምታደርገውን ጥቃት ቀጥላለች።
በሌላ በኩል፤በጋዛ እና በሊባኖስ ያሉትን ጨምሮ በተለያዩ ግንባሮች የሚደረጉ ውጊያዎችን ለማቆም አሜሪካ የምታደርገው ጥረት በዋሽንግተን እና በእስራኤል መካከል አለመግባባት መፍጠሩን የቅርብ ጊዜ ዘገባዎች ይጠቁማሉ።
