ቀጸላ ክፍሌ
ሀገራችን ኢትዮጵያ ችጋር ምሷ ጦርነት ትራሷ ከኾነባት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ይህ መንገዷ ደግሞ ቁልቁለቷን በእጅጉ አፍጥኖታል፡፡ ኢትዮጵያም እንደሀገር በቅርብ ጊዜ ባካሄደችው ጦርነት በርካታ ቢሊዮን ብሮችን አባክና ብዙዎችን ሰውታ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ውድመትን አስተናግዳለች፡፡ በዚህ ከመጣው ኢኮኖሚያው ችግር አንዱ የኑሮ ውድነት፣ የአቅርቦትና የፍላጎት አለመጣጣም በዋናነት የሚነሳ ሲኾን ማኅበራዊ ቀውሱ ደግሞ ዘርፈ ብዙ ኾኖ ይስተዋላል፡፡ የኾኖ ኾኖ ይህች በጦርነት የደቀቀች ሀገር አሁን ላይ ከ20 ሚሊዮን በላይ ዜጎቿ በችጋር የሚቆሉባት ምድርም ኾናለች፡፡
ሰሞኑን የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት (ኦቻ) እቅድ እንደሚያመላክተው በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2023 የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ 3.99 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሚያስፈልግ ገልጿል። እንደ ኦቻ ገለጻ የሰብዓዊ ድጋፍ ከሚያስፈልጋቸው 20 ሚሊዮን ዜጎች 4.6 ሚሊዮኑ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ሲኾኑ፤ 13 ሚሊዮኑ በግሞ አምስት ተከታታይ የዝናብ ወቅቶች በማለፉ በድርቅ የተጎዱ ናቸው። በጦርነትና በሰላም እጦት ተፈናቅለው ለዚህ ችግር ከተጋለጡት መካከል በአማራ ክልል የወለጋ ተፈናቃዮችና በህወሓት ጦር ከጻግብጅ ዋግ ኸምራ ዞን ተፈናቅለው በመጠለያ ካምፕ የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ከአብርገሌና ከፃግብጂ ወረዳ የተፈናቀሉ ከ70 ሺህ በላይ ሰዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ወገኖች ምንም ዓይነት መንግሥታዊ ግልጋሎት ማግኘት ባለመቻላቸውም በፃግብጂ ወረዳ በወሊድ ምክንያት 15 እናቶች፤ 5 እናቶች ደግሞ ሳይገላገሉ በመሞታቸው 15ቱ ሕፃናት ወደ ሰቆጣ ሄደው መጠለያ ጣብያ ላይ ተጠልለው እንደሚኙ የሕግና ፍትሕ አሥተዳደር ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ገብያነሽ ፈንታ ለዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ምክር ምክር ቤት ሰሞኑን ባቀረቡት ሪፖርት ገልጸዋል።
ተፈናቃዮቹ በምግብ እጦት ምክንያት በተለያዩ በሽታዎች እየተጠቁ እንደኾነም በተለያየ ጊዜ ተገልጿል። በተለይ ነፍሰጡር እናቶች እንዲሁም እናቶች በምግብ እጦት ለበሽታ እየተጋለጡ ሲኾን ለሁለት ዓመታት በዋግኽምራ ዞን ሲቆዩ ከተለያዩ የመንግሥት እና መንግሥታዊ ካልኾኑ ድርጅቶች እርዳታ እያገኙ የነበረ ሲኾን አሁን ላይ ግን ከመንግሥትም ኾነ ከረጂ ድርጅቶች እርዳታ ማግኘት አለመቻላቸው ተገልጿል። ነፍሰጡር እናቶች፣ የሚያጠቡ እናቶች እና ሕፃናት በሳምባ ምች እና በተቅማጥ በሽታ እየተያዙ ይገኛሉ። በቅርቡም የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ጤና መምሪያ ለተፈናቃዮች የሚቀርብ የምግብ ድጋፍ፣ የንጽሕና መጠበቂያ፣ የውሃ አቅርቦት፣ መድሃኒት በመቋረጡ ዜጎች ችግር ላይ ናቸው ብሏል።
በተመሳሳይ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ይልቃል ከፋለም ለክልሉ ምክር ቤት እንዳስታወቁት የሰላም ሰምምነቱ ሲፈጸም እነዚህ አካባቢዎች በህወሓት ሥር የነበሩ በመኾናቸው አሁን ላይ ተፈናቃዩ የኅብረተሰብ ክፍል ከፍ ላለ ችግርና ሰቆቃ የተጋለጠ መኾኑን አብራርተዋል፡፡ የዞኑ ጤና መምሪያም መንግሥት በዋግኽምራ ተጠልለው ለሚገኙ ዜጎች ትኩረት እንዲሰጥ፣ አጋር ድርጅቶችም ከዚህ በፊት ሲያደርጉ የነበረውን የመድሃኒት፣ የንጽና መጠበቂያ እና ሌሎች ድጋፎች እንዲቀጥሉና ትኩረት እንዲሰጡ ጠይቋል። በተጨማሪ የሰላም ስምምነት ከተፈጠረ አካባቢው ነፃ መኾን አለበት ነዋሪዎችም ወደ ቀደመው ቄያቸው ተመልሰው እንዲቋቋሙ እና እንዲደገፉ የማድረግ ሥራ መንግሥት ሊሠራ ይገባ በማለት ጥሪውን አቅርቧል። በተመሳሳይ በጎንደር፣ በባሕር ዳርና በደብረብርሃን የሚገኙ የትግራይና የወለጋ ተፈናቃዮችም የዚህ ችግር እጣ ተጋሪዎች ናቸው፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በድርቁ ምክንያት አርብቶ አደር እና ከፊል አርብቶ አደር በኾኑ አከባቢዎች በተለይም ምሥራቃዊ እንዲሁም ደቡባዊው የሀገሪቱ ክፍል የምግብ ዋስትና እጦት፣ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት፣ የውሃ አቅርቦት እና የጤና አገልግሎት መዳከም ለበሽታና ወረርሽኝ ተጋላጭነትን ከፍ አድርጓል። በዚህም ከፊል ደቡብ ክልል፣ ከፊል ሶማሌ ክልል እና እንዲሁም ቦረና ድርቅ ባመጣው ችግር ምክንያት ኅብረተሰቡ ለከፍተኛ ቀውስ ተዳርጓል፡፡ እንደሚታወቀው ሰሞኑን የቦረናው ድርቅ ከፍተኛ ቅስቀሳ የተሠራበት በመኾኑ በጥቂቱም ቢኾን ችግሩ እየተቃለለ የመጣ ይመስላል፡፡ በአንጻሩ ሰሞኑን ብቻ በደቡብ ኦሞ ዞን እና በሶማሌ ክልል ዳዋ ዞን አስተዳደር ባጋጠመ ድርቅ በርካታ እንስሳት የሞቱ ሲኾን የሰዎች ሕይወትም አደጋ ላይ ወድቋል። የዞኑ አስተዳደርም ያለው ሁኔታ ከአቅም በላይ መኾኑን አስታውቋል። የዳዋ ዞን ከኦሮሚያ የቦረና ዞን ጋር የሚዋሰን መኾኑ እየታወቀ ለቦረና ዞን ያን ያህል እርብርብ ሲደረግ ይህ ዞን መዘንጋቱ መንግሥትንም ኾነ ማንኛውንም ባለድርሻ አካል ሚያስተች ነው፡፡ የኾኖ ኾኖ የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ መሐመድ ሀቢቻ ሰሞኑን ለሪፖርተር ጋዜጣ እንዳስታወቁ ወደ 700 ሺሕ የሚጠጋ አርብቶ አደር ለ3 ተከታታይ ዓመታት የደረሰው ድርቅ ከብቱን በሙሉ ጨርሶበታል።
ምክትል አስተዳዳሪው “በክልሉ አደጋ ሥጋት ቢሮና በተለያዩ የዕርዳታ ድርጅቶች ርብርብ ዘንድሮ ለድርቁ ተጎጂዎች ዕርዳታ እየቀረበ ነው፤ ይሁን እንጂ ዕርዳታው በቂ አይደለም። ችግሩም ከአቅም በላይ ነው። በኦሮሚያ ክልል ለሚገኘው ለአጎራባቻችን ቦረና ዞን በአገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ እንዳለው ሁሉ፣ ለእኛም የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ይድረሱልን።” ሲሉም ተማጽነዋል፡፡ በተመሳሳይ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል በደቡብ ኦሞ ዞን 6 ወረዳዎች ማለትም በማሌ፣ በናፀማይ፣ ሐመር፣ ኛንጋቶም፣ ዳሰነችና ሳላማጎ ወረዳዎች በተከሰተ ድርቅ ከ300 ሺህ በላይ ሰው ለረሀብ መጋለጡን የደቡብ ኦሞ ዞን የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት አስታውቋል። የ300 ሺህ ሰው መራብ ቀላል አይደለም። ቦረና ላይ እርብርብ እንደተደረገው ሁሉ እዚህም መድረስ ያስፈልጋል፡፡
ከረሀቡም በተጨማሪ ውጥንቅጡ በጠፋው ፖለቲካ ሳቢያ ሀገሪቱ በርካታ ማኅበራዊ ቀውሶችን በማስተናገድ ላይ ትገኛለች፡፡ ከእነዚህም ማኅበራዊ ቀውሶች አንዱ ስደት ነው፡፡ ውስጣዊ ስደት መፈናቀል ብለን እንዳየነው ሁሉ ውጫዊ ፍልሰትን ደግሞ ስደት ብለን ልጠራው ግድ ይለናል፡፡ እንደሚታወቀው ኢትዮጵያውያን በስደት በኩል ያለፉትን ለስልሳ የተጠጉ ዓመታት መገለጫችን ኾኖ ቆይቷል፡፡ አሁን ላይ ግን ከምንግዜውም በባሰ መልኩ የውርደታችን ማሳያ እየኾነ መጥቷል፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት ኢትዮጵውያን ስደተኞች የሚደርስባቸው ሰብዓዊ ጥሰት ቁጥር ስፍር የለውም፡፡ ይህን ከግምት በማስገባትም በተለይ ከሳዑዲ የኢትዮጵያ መንግሥት ያለፈው ዓመት ጀምሮ ዜጎቹን ወደ ሀገር ቤት ሲያግዝ መሰንበቱ አይዘነጋም፡፡ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በሳውዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ በርካታ ዜጎችን መልሷል፡፡ በሳውዲ አረቢያ ከ750 ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያን እንደሚኖሩ የሚገመት ሲኾን፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በሳውዲ አረቢያ ለእስር እና ለከፋ ስቃይ እንደተዳረጉ ይገመታል። የኢትዮጵያ መንግሥት በሪያድ እና በሌሎች የሳኡዲ እስር ቤቶች ውስጥ የሚሰቃዩ ኢትዮጵያውያን እናቶች፣ ሕጻናትና አረጋውያንን በማስቀደም፤ በሳምንት እስከ ዘጠኝ በረራዎችን በማድረግ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ እያደረገ መኾኑም አይዘነጋም፡፡
ነገር ግን መንግሥት አሁንም ጉዳዩን የውሃ ቅዳ ውሃ መልስ ነገር አድርጎታል፡፡ ሰሞኑን እንደወጣው መረጃ ከኾነ በኢትዮጵያ በተያዘው ዓመት 500 ሺሕ ሴቶችን ወደ አረብ አገራት በተለይም ወደ ሳውዲ አረቢያ ለሥራ ለመላክ በመንግሥት እቅድ ተይዟል፡፡ ይህን ተከትሎም በአማራ ክልል ኹሉም ዞኖች ሰሞኑን ወደ አረብ አገር ሄደው መሥራት ለሚፈልጉ ወጣት ሴቶች ሥልጠና ሊሰጥ መኾኑ ተነግሯል፡፡ ይህ ደግሞ የመንግሥትን እነቅስቃሴ “አያዎ” ያደረገው ይመስላል፡፡ በጥቅሉ መንግሥት ሀገሪቱን ከዚህ አዙሪት ለማውጣት ከመሥራት ይልቅ ይበልጥ ወደ አዘቅቱ እየገፋት ይመስላል፡፡ ይህን ደግሞ በብዙ መልኩ ያለፉትን አምስት ዓመታት ሲተገብረው ኖሯል፡፡ ሌላው ቀርቶ ከተነሳው ርዕስ ጋር የሚዛመደውን እንኳ ብናይ ሀገሬው ዳቦ ተርቦ እርሱ ወደ ውጪ ስንዴ የሚልክና ለክምችት ክፍል የሚያቁር የክፋት ቁንጮ ተዋናይ ኾኖ ይስተዋላል፡፡ ይህም ኾኖ ግን መንግሥት አሁንም ድርቅን ጨምሮ በተፈጥሯዊ እና በሰው ሰራሽ ችግሮች ለተጎዱ 21 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎች ድጋፍ እየቀረበ መኾኑን በኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በኩል አስታውቋል። እንደእውነታው ግን የኮሚሽኑ ሪፖርት መሬት ላይ የሌለና ስላቅ ብቻ የኾነ ነው፡፡
