ተክለሚካኤል አበበ፤ ቶሮንቶ
አሁን ላለው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ-መንግሥት ጥብቅና አልቆምም፡፡ ግን ደግሞ “ለኢትዮጵያ ችግር ሁሉ ምንጩ ሕገመንግሥቱ ነው፤ ሕገ-መንግሥት ከተለወጠ፤ የኢትዮጵያ ችግር ይቀረፋል” ከሚሉት ወገንም አይደለሁም፡፡ በሰነድ ብቻ የመጣና በሰነድ ብቻ የሚሄድ ችግር የለም፡፡ አንደኛ ሕገ-መንግሥቱ በተወሰነ መልኩ፤ ምድር ላይ ያለ ፖለቲካዊና ብሔራዊ ግብግብ ነጸብራቅ ነው፡፡ ሁለተኛ፤ በተደጋጋሚ በምሳሌ እንደገለጽኩት፤ ቅዱሳን መጻሕፍትን ለእምነት ተከታዮቻቸው እንደ ሕገ-መንግሥት አድርገን ብንወስዳቸው፤ እነዚህ ቅዱሳን መጻሕፍት ከመጠፋፋት፤ ከጦርነት፤ ከተከለከሉ ሀጢያቶች አላዳኑንም፡፡ እንደውም በእምነት/በሃይማኖት ሥም የሚፈጸሙ ግፎች አሁንም ድረስ ሞልተዋል፡፡ ስለዚህ የኢፌድሪን ሕገ-መንግሥት የኢትዮጵያ ችግሮች ሁሉ ምንጭ፤ የዚህ ሕገመንግሥት መለወጥም የችግራችን ሁሉ መፍትሄ አድርገን መመልከት ስህተት ነው፡፡ ችግሩ ከሕገ-መንግሥት ባሻገር ነው፡፡ ስለዚህም ችግሩን ለማግኘት፤ የኢትዮጵያን ሕገመንግሥት ደግሞ ደጋግሞ ማንበብ፤ መፈተሽ፤ መመርመር፤ መወያየት ያስፈልጋል፡፡
በኔ ንባብና እምነት፤ ከሕገመንግሥቱ ውስጥ ቢሻሻሉ፤ ወይም ቢብራሩ፤ ወይም ቢቀነሱ፤ ወይም ቢጨመሩ የሚባሉ አንቀጾች ይኖራሉ፡፡ ለምሳሌ፤ የመሬት የግል ባለቤትነት በሕገ-መንግሥት ቢረጋገጥ ደስ ይለኛል፡፡ የግለሰቦችና የቡድን መብቶችም ጎን ለጎን የሚቆሙ እንጂ፤ አንዱ ሌላውን የሚጨፈልቅ እንዳልሆኑ የሚደነግግ ግልጽ አንቀጽ ቢኖር ደስ ይለኛል፡፡ አንቀጽ 39፤ መኖሩ ይረብሽ ይሆናል እንጂ፤ ተፈጻሚነቱ አጠራጣሪ ነው፡፡ ወይም ይፈጸም ከተባለ፤ ለክልሎችም አደገኛ ነው፡፡ ምክንያቱም፤ አንቀጽ 39 ይፈጸም ከተባለ፤ አማራ የሚባል፤ ኦሮሚያ የሚባል፤ ቤኒሻንጉል የሚባሉ ክልሎች ሁሉ፤ በአንቀጽ 39 ሊናዱ ይችላሉና፡፡ አንቀጽ 39 በሁለቱም በኩል የተሳለ ሰይፍ ነው፡፡ ጠንቁ ለኢትዮጵያ ብቻ አድርገው የሚመለቱ ተሳስተዋል፡፡ ከተተገበረ፤ ሁሉንም ይቆርጣል፡፡ ክልሎችንም፡፡
በአንቀጽ 39ና አንቀጽ 47(2) መሠረት፤ በማናቸውም ክልሎች ውስጥ የተካተቱት ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በማናቸውም ጊዜ የራሳቸውን ክልል የመመሥረት ሥልጣን አላቸው፡፡ አንቀጽ 39 ማብቂያ የለውም፡፡ ስለዚህ አንቀጽ 39 አያስቃዠኝም፡፡ አንቀጽ 39 የእልህ አንቀጽ ነው የምለው፡፡ እንደኑክሌር ፈንጂ፡፡ ማንም አይጠቀምበትም፡፡ በሙሉ አይፈጸምም፡፡ ምክንያቱም ርስበርስ መጥፊያም ነውና፡፡ ለዚህም ነው፤ ሕወሓትን ጨምሮ፤ ኦነግም ሌሎችም የብሔር ድርጅቶች፤ በቅርብ ግዜ ታሪካቸው፤ ስለመገንጠል መብት አያወሩም፡፡ ሕወሓት፤ በቅርብ ግዜ እንደዚያ እየተደበደበ ሁሉ፤ ስለመገንጠል ትንፍሽ አላለም፡፡ ሌሎች በቅርብ ግዜ የተወለዱ ወይም ከዋናዎቹ ድርጅቶች የተገነጠሉ የብሔር ድርጅቶች እንጂ፡፡
የኢትዮጵያ ችግር ሕገመንግሥቱ ሳይኾን፤ ሕገመንግሥቱ አለመተግበሩ፤ ወይም የሕገመንግሥታዊነት ባህል አለመኖር ወይም አለመዳበር ነው፡፡ በርግጥ ይኼ ችግር በተወሰነ መልኩ ከሕገመንግሥቱ ይዘት ቢመነጭም፤ ባብዛኛው ግን የሚመነጨው፤ የመንግሥት አካላት፤ ፖለቲከኞና፤ ሕዝቡም በተወሰነ መልኩ የሕገመንግሥታዊነት መንፈስ ስላልገባው፤ ከትምህርት እጦት ነው፡፡ በከፊል ከሕገመንግሥቱ ነው ስል፤ ለምሳሌ፤ ፍርድቤቶች ሕገመንግሥቱን የመተርጎም ሥልጣን ስላልተሰጣቸው፤ ሕገመንግሥታዊ መብቶችን ከማስፈጸም አንጻር ሽባ ናቸው፡፡ ሰዎች ሕገ-መንግሥታዊ መብታቸው ሲጣስ፤ ወደፍርድቤት አቅንተው መፍትሄ መፈለግ አይችሉም፡፡ ከዚህ አንጻር፤ ሕገመንግሥቱ ጎዶሎ ነው፡፡ የፍርድቤቶችን አቅመ-ቢስነት በሕገመንግሥቱ ብቻ ማላከክ አይቻለም፡፡ የፍርድቤቶች ሽባነት ምንጭ ግን፤ ሕገመንግሥታዊ ብቻ ሳይኾን፤ ሌሎች ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ምክንያችም ስላሉት እሱን በሌላ ጽሑፍ እንመለስበታለን፡፡
ሉዓላዊ ማነው፤ ኢትዮጵያ ወይስ ክልሎች?
አንዳንድ የሕገ-መንግሥቱ አንቀጾችም አሻሚ ወይም ግራ አጋቢ ናቸው፡፡ ለምሳሌ፤ አንቀጽ 2 የኢትዮጵያ የግዛት ወሰን፤ የፌደራሉን አባሎች ወሰን የሚያጠቃልል ሆኖ፤ በዓለም አቀፍ ስምምነቶች መሠረት የተወሰነው ነው፤ ይላል፡፡ አንዳንድ ሰዎች ይኼንን አንቀጽ ይዘው፤ ክልሎች/ብሔሮች ሉዓላዊ ናቸው፡፡ በሕገመንግሥቱ፤ የክልሎች እንጂ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የለም ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ አንቀጹ ግፋ ቢል ግልጽነት፤ ወይም ትርጉም ያስፈልገዋል፡፡ ይሁን እንጂ፤ ለክልሎች ወይም ለብሔሮች ሉዓላዊነትን አይሰጥም፡፡ አንደኛ ነገር፤ የኢትዮጵያ ፌደራል አባላት፤ ክልሎች ናቸው ወይስ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ግልጽ አይደለም፡፡ ሁለተኛ፤ በዓለም አቀፍ ስምምነቶች መሠረት የተወሰነው ሲል፤ ኢትዮጵያ ከ1983 ዓ.ም. በፊት የተመሰረተችና ድንበሯም ከዚያ በፊት የጸና እንደመኾኑ መጠን፤ በዓለምአቀፍ ሕግ መድረክ ወይም ዓይን ሉዓላዊ ተደርጋ የምትታወቀው ኢትዮጵያ እንጂ፤ ክልሎች አይደሉም፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት ሉዓላዊ ክልሎችን ፈጠረ የሚለው ክርክር አያስኬድም፡፡
ሕገ መንግሥቱ፤ ሉዓላዊነትን ለብሔር፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሰጥቷል፤ ዜጋው ቦታ የለውም ወይም ዜጎችን አያውቅም የሚለው ክስም በተደጋጋሚ ይሰማል፡፡ ከአንቀጽ 2 እና 39 ሌላ፤ የኢትዮጵያ ሕገመንግሥት አንቀጽ 8ን ነው እንደማስረጃ የሚጠቅሱት፡፡ አንቀጽ 8 የሚገኘው የሕገመንግሥቱ መሠረታዊ መርሆዎች በሚገኙበት ምዕራፍ 2 ውስጥ ነው፡፡ በዚህ ምዕራፍ ውስጥ፤ ብዙ ሌሎች ሕገ-መንግሥታዊ መሠረታዊ መርሆዎች ተጠቅሰዋል፡፡ ለምሳሌ፤ አንቀጽ 9፤ ማናቸውም ሕጎች፤ አሠራሮች፤ ልማዶች ከሕገመንግሥቱ ጋር መቃረን አንደሌለበቸው፤ አንቀጽ 10 ደግሞ የዜጎችና ሕዝቦች ሰብዓዊ መብቶች መከበር እንዳለባቸው ይደነግጋል፡፡ ስለዚህ አንቀጽ 8ን ከሌሎች አንቀጾች ለይተን መመልከት የለብንም፡፡ ወይንም፤ ሕገመንግሥቱ እንደ አንድ ወጥ ሰነድ ይተረጎማል እንጂ፤ የተወሰኑ አንቀጾችን መዘን ለኛ እንዲመቸን ብቻ አድርገን ጠምዝዘን መተርጎም የለብንም፡፡ ሕገ-መንግሥቱ እንደአንድ ወጥ ሰነድ ሲተረጎም፤ ሉዓላዊነት፤ በቀጥታ እንደ ዜጋም ይሁን በተዘዋዋሪ እንደ አንድ ብሔር/በብሔረሰብ/ሕዝብ አባል፤ የኢትዮጵያዊያን የጋራ ሥልጣን ነው፡፡ እንጂ ብሔሮች በተናጠል የሚይዙት ሥልጣን አይደለም፡፡
ብሔርና ዜጋ፤ የቱ ይበልጣል
የሕገመንግሥቱ አንቀጾች ሁሉ እኩል ናቸው፤ አንዱ ካንዱ አይበልጥም፡፡ በግድ ጠምዝዘን አንቀጽ 8 ከ አንቀጽ 9 ወይም 10 ይበልጣል ካላልን በስተቀር፤ ሕገመንግሥቱ፤ የዜጎችን መብት ከብሔሮች ወይም ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መብት አስበልጦ አላስቀመጠም፡፡ ሁለቱም መብቶች ጎን ለጎን የተቀመጡ ናቸው፡፡ በዚህ ረገድ፤ በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል በመምረጥ መመረጥ መብት ዙሪያ ለቀረበ ሕገመንግሥታዊ ጥያቄ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በመጋቢት 1995 የሰጠው ውሳኔ ዓይን ገላጭ ነው፡፡ “በዜጎችም ኾነ በብሔር ብሔረሰብና ሕዝቦች መካከል ልዩነትና አድልዎ ማድረግ እንደማይቻል፤ እንዲሁም የግለሰቦችና፤ የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መሠረታዊ መብቶችና ነጻነቶች፤ የተሳሰሩ፤ የማይነጣጠሉና እኩል እንደኾኑ፤ አንዱ ከሌላ የማይበልጥ፤ የማያንስ እንደኾነ እንዲሁም አንዱ ለሌላው ሲባል መብቱና ነጻነቱ እንደማይሸራረፍና ገደብ እንደማይጣልበት ነው፡፡” የሕገ-መንግሥታዊ ውሳኔዎቸ መጽሔትን፤ ቅጽ 1፤ ገጽ 25/26 ይመልከቱ፡፡ (በርግጥ ምክር ቤቱ ቋንቋንና ምርጫን በተመለከተ የወሰነው ውሳኔ አልተመቸኝም፡፡)
እነዚህ መብቶች ሳይጋጩ እነዴት አጣጥመን እንደምንተረጉማቸው ዘዴዎችና ብልሀቶች፤ የሕገ-መንግሥት አተረጓጎም ስልቶች ስላልፈጠርንና ስላላዳበርን፤ ወይም ሕገመንግሥቱ በነጻነት፤ በትርጉም፤ በምርምርና በማሻሻል እንዲዳብር እድል ስላልተሰጠው ነው፤ ሕገመንግሥቱ የችግሮች ሁሉ ምንጭ የመሰለው እንጂ፤ ሕገ-መንግሥቱ እንዳለ ሥራ ላይ ቢውል፤ ችግሮቻችንን ሊፈታ፤ ባይፈታ እንኳን፤ በሰላም እንድንፈታ ዕድልና መንገድ ይሰጠናል፡፡
እንዳለመታደል ሆኖ ግን፤ ሕገ-መንግሥቱን ታግለው ያመጡትና ሥራ ላይ እያዋሉት ያሉት ኃይሎችም፤ ለሕገ-መንግሥቱ ታማኞች አይደሉም፡፡ ወይንም በሕገመንግሥቱ ውስጥ የሰነቀሯቸው መብቶች ምድራዊ ትርጉም አልገባቸውም፡፡ ስለዚህ፤ በየዕለቱ፤ ላለፉት 26 ዓመታት፤ በሕገመንግሥቱ የተቀመጡት መብቶች ሲጣሱና ሲቀለበሱ እንመለከታለን (ሕገ-መንግሥቱ ከጸደቀ፤ 26 ዓመቱ ነውና፤ ከዚያ በፊት 4ቱን ዓመት የተዳደርነው በሽግግር መንግሥት ሰነድ ነው)፡፡
በኢትዮጵያ ሕገመንግሥት ውስጥ፤ የዜጎችን መብት የሚጠብቁት አንቀጾች፤ በቁጥር የብሔሮችን መብት ከሚጠብቁት አንቀጾች ይበልጣሉ፡፡ ከአንቀጽ 14 እስከ 38 የሚደነግጉት፤ ስለግለሰብ ወይም ዜጋ ወይም ኢትዮጵያዊያን መብት ነው፡፡ ሕገመንግሥታዊነት ሰርጾብን ቢሆን ኖር፤ አንቀጽ 38፤ ማንኛውም ኢትዮጵዊ በዘር፤ በቋንቋ፤ በብሔር፤ በብሔረሰብ … ልዩነት ሳይደረግበት፤ በአገሪቱ የፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ የመሳተፍ፤ የመምረጥ የመመረጥ መብት እንዳለው ይደነግጋል፡፡ እንደሕገመንግሥቱ ቢሆን ኖሮ፤ እኔን፤ ቋንቋዬም ይሁን ብሔሬ፤ ጨፌ ኦሮሚያ ገብቼ ከመፈንጨት አያግደኝም ነበር፡፡ ሀብት የማፍራት፤ የመኖር፤ በነጻነት የመንቀሳቀስ መብትማ፤ ምንም ጥያቄ ሁሉ የለውም፡፡ ስለዚህ በየግዜው በየሰበብ አስባቡ የምንሰማቸው የዜጎች መፈናቀልና መገደል፤ ከፍተኛ የሰብዓዊና ሕገመንግሥታዊ መብት ጥሰት ናቸው፡፡
አንቀጽ 25 ይኼንኑ የእኩልነት መብት ይደነግጋል፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ፤ ማንኛውም ሰው፤ ከሕግ በታች እኩል ነው፡፡ በብሔሩ፤ በዘሩ፤ በቋንቋው፤ በሃይማኖቱ፤ በጾታው … መድልዎ አይደረግበትም፡፡ በኦሮሚያ ውስጥ፤ ሽመልስ አብዲሳ፤ ከተክለሚካኤል አበበ የበለጠ መብት የለውም፡፡ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ፤ አንዳንዴ ደግሞ ማንኛውም ሰው፤ ኢትዮጵያዊ መኾን ሁሉ አይጠበቅበትም፤ በሕገመንግሥቱ የተደነገጉ መብቶች አሉት፡፡ አንቀጽ 39 ከአንቀጽ 25 አይበልጠም፡፡ ለምሳሌ፤ ሁለቱም የሚሻሻሉበትን አንቀጽ ብንመለከት፤ ተመሳሳይ ናቸው፡፡ በምዕራፍ 3 የተጠቀሱትን መብቶች ሕገመንግሥታዊ ማሻሻያ ሀሳብ፤ የሁሉም ክልሎች ምክርቤቶች፤ የፌዴሬሽን ምክርቤትና የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት፤ በ2/3ኛ ድምጽ፤ ማጽደቅ አለባቸው፡፡ የሕገመንግሥቱን፤ አንቀጽ 104 እና 105ን ይመለከቷል፡፡ በኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት የግለሰብና የብሔር መብቶች እኩል ናቸው፡፡ አንዱ ከንዱ አይበልጥም፡፡ ችግሩ ሕገ-መንግሥቱ አይደለም፡፡
ሕገመንገሥታዊነት አልሰረጸም፤ ሕገ-መንግሥታዊነት ይለምልም!
ኢትዮጵያ ውስጥ ችግሩ ሕገመንግሥቱ ሳይኾን፤ ሕገመንግሥታዊነት አልዳበረም፡፡ የመንግሥት ባለሥልጣናት፤ ሕገመንግሥቱን አልተረዱትም ወይም ሆን ብለው አጣመው ተርጉመውታል፤ ወይም ኢሕአዴግ በፈለገው መንገድ ብቻ እየተተረጎመ ስለመጣና፤ ሕገመንግሥቱ ማለት ኢሕአዴግ/ብልጽግና የሚለው ስለኾነ፤ ሕገመንግሥቱ በነጻነት እንዲዳብርና እንዲያድግ እድል ስላልተሰጠው እንጂ፤ ሕገመንግሥቱ ያለምንም ማሻሻያ፤ የኢትዮጵያዊያንን መብት የሚጠብቅበት ኃይልና ሥልጣን አለው፡፡ ሕገመንግሥታዊነት ምን ያህል እንዳልዳበረ ደግሞ ጥሩ ምሳሌ፤ የራሱ የሕገመንግሥት አጣሪ ጉባኤው የምርጫን መራዘም የተመለከከተው የቅርብ ግዜ ውሳኔ ነው፡፡
የሕገ-መንግሥታዊ አጣሪ ጉባዔው ውስጥ፤ የጠቅላይ ፍርድቤት ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንትን ጨምሮ፤ ሌሎች 6 ታዋቂ ሕግ ባለሙያዎች ቢኖሩም፤ የወሰኑት ውሳኔ፤ ኢሕአዴግ ከቀናት፤ ሳምንታት ስብሰባ፤ ግምገማ በኋላ ከሚያወጣቸው መግለጫዎች ያልተለየ ውሳኔ ነው፡፡ እንኳንስ የኢሕአዴግ/ብልጽግና ባለሥልጣናት ጋር፤ የተማሩ የተመራመሩ የሕግ ባለሙያዎችን፤ የተሰጣቸውን ሕገመንግሥታዊ ሥልጣን፤ በቅጡና የሕዝብን መብት በሚያስጠብቅ መልኩ አልተረዱትም፡፡ ውሳኔያቸው ምንም ይሁን ምንም፤ ቢያንስ የግራ ቀኙን ሀሳብ ማስፈር ሲገባው፤ የመንግሥትን ፍላጎት ብቻ ባማከለ መልኩ፤ እንደውም መንግሥት ከጠየቀው በላይ መብት በሚሰጥ መልኩ ምርጫው ላልተወሰነ ግዜ እንዲራዘምና፤ እስከዚያውም ገዢው ፓርቲ ሥልጣን ላይ እንዲቆይ ወስነዋል፡፡
ስለዚህ፤ የችግራችን ሁሉ ምንጭ ሕገመንግሥቱ ነው፤ ሕገመንግሥቱ ይሰረዝ፤ ይሻር፤ ይቀደድ፤ የሚሉ ኃይሎች፤ አንድም ሕገመንግሥቱን በቅጡ አልተረዱትም፤ በሌላም በኩል፤ አውቀውም ይሁን ሳያውቁት፤ አገሪቱ ላይ ሌላ ችግር የሚጋብዙ ናቸው፡፡ ምክንቱም፤ ይኼ ሕገመንግሥት የሚቀደደው፤ በኛ መቃብር ላይ ነው የሚሉ ኃይሎች በሌላ አንጻር ተሰልፈዋልና፤ ሁላችንም ካከረርን፤ ትርፉ መጫረስ ነው፡፡ እነ ሥዩም መስፍን፤ በተወሰነ መልኩም ቢሆን ሕገ-መንግሥታችንን እናስጠብቃለን ብለው ነው በስተርጅና ጫካ ገብተው፤ ፍጻሜያቸው በሚያሳዝን መልኩ የኾነው፡፡ ለ27 ዓመታት አሸነፉን፡፡ ለ2 ተኩል ዓመታት ታገሉ፡፡ ተሸነፉ፡፡ ለጊዜው፡፡ መጪውን አናውቀውምና፡፡ ማን ይኼን ቀን ይመጣል ብሎ አስቦ ነበር፡፡ ፓርቲያቸው እንጂ፤ ሀሳባቸው ግን ተሸንፏል ማለት አንችልም፡፡ ሕገ-መንግሥቱ ተቀዶ እንዲጣል የምንፈልገውን ያህል፤ ሕገ-መንግሥቱ ከተነካም ለመሞት የተዘጋጁ እንዳሉ እያን ነው፡፡፡ በሁሉም ወገን ማክረር እንቀንስ፡፡ ችግራችን ሕገመንግሥቱ አይደለም፡፡ ከኾነም፤ በከፊል ነው፡፡ (የነሥዩም መስፍንም ይኹን የሕወሓት ተቃዋሚ ነኝ፤ ያን ሀሳባቸውን ከሰዎቹ ነጥሎ ከመመልከት አያግደኝም)፡፡
መቀየር ያለበት ምንድን ነው?
ኢትዮጵያ ውስጥ መቀየር ያለበት፤ ሕገመንግሥቱ ሳይኾን፤ የሕገመንግሥቱ መንፈስና የጊዜው ፓርቲዎች አስተምህሮት፤ የካድሬዎቻቸው የተሳሳተ መንፈስ፤ ወይንም ድንቁርና ነው፡፡ በኢትዮጵያ፤ እስካሁን ባብዛኛው እየተፈጸመ ያለው፤ የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት ሳይኾን፤ ቀደም ሲል ኢሕአዴግ፤ አሁን ደግሞ የተረከበው ብልጽግና የፖለቲካ ርዕዮትና መረዳት ነው፡፡ ሕገ-መንግሥቱ ኢትዮጵያ ውስጥ የብሔር ጭቆና ነበር፤ ብሔር ብሔረሰበቦች ባህላችንን እንድናሳድግ፤ በማንነታችን እንዳንኮራ፤ ራሳችንን በራሳችን ማስተዳደር እንዳንችል ማዕቀብ ተጥሎብን ኖረናል ባሉና፤ እንደቡድን ካልቆምን፤ አውሬ ይበላናል ባሉ ቡድኖች አሸናፊነት የተሰናዳ ሰነድ ነው፡፡ የሕገ-መንግሥቱ መንፈስ በዚህ ተቃኘና፤ እንደብሔር ሥልጣን የያዙ ኃይሎች፤ የቡድን መብታቸውን ለማስከበር የት ድረስ መሄድ እንዳለባቸው ድንበር ጠፋባቸው፡፡ ስለዚህ፤ እነዚህ የቡድን ኃይሎች፤ በማወቅም፤ ባለማወቅም፤ የግለሰቦች መብት ላይ ተረማመዱበት፡፡ ያ ስህተት ነው፡፡ ማስታረቅ ያለብንም እነዚህን ሁለቱን ሀሳቦች ነው፡፡ የቡድንና የግለሰብ መብቶች፤ በሕገመንግሥቱ እንደተረጋገጠው፤ እንዴት ጎን ለጎን መሄድ ይችላል የሚለው ጥያቄ መመለስ አለበት፡፡ የኢትዮጵያ ትልቁ ሕገ-መንግሥታዊ ፈተና እሱ ነው፡፡፡
ሕገመንግሥቱን በሙሉ ማስፈጸም ከጀመርን፤ መብታችንን ማስከበር፤ የማንፈልጋቸውንም አንቀጾች በትዕግስትና በሂደት፤ በድርድር፤ ማስለወጥ እንችላለን፡፡ የኢትዮጵያን ሕገ-መንግሥት መተግበር ማለት ደግሞ፤ የትም ክልል የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን መብት ሳይሸራረፍ መፈጸም/መከበር ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ፤ የኢትዮጵያ ሕገመንግሥት ክልሎችን ፈጠረ፤ እንጂ ክልሎችን፤ ለዚህ ወይም ለነዚያ ብሔሮች በባለቤትነት አልሰጠም፡፡ ቢያንስ ሕገመንግሥቱ ውስጥ በግልጽ የተቀመጠ እንደዚያ ዓይነት አንቀጽ የለም፡፡ የፌደራል ሕገ-መንግሥቱ ይኼንን ሥልጣን ፤ በቀጥታም ይኹን በተዘዋዋሪ፤ ለክልሎች አልሰጠም፡፡ ሥልጣን ፤ እንደሀብት ስለሚጣፍጥ፤ አንዳንድ ቡድኖች፤ ክልሎች፤ በኢሕአዴግ ፖለቲካዊ ትርጓሜ በመታገዝና፤ ሃይ ባይ ስላጡ፤ ያንን ሥልጣን ነጥቀው ለራሳቸው ወሰዱ እንጂ፤ የፌደራል ሕገመንግሥቱ እንዲህ ያለውን ሥልጣን ለክልሎችም ይሁን ለብሔሮች/ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አልሰጠም፡፡ የብሔር ብሔረሰቦችን መብቶች የሚደነግጉት፤ አንቀጾች፤ አንቀጽ 2፣ 8፤ 39፤ 47፤ ለየትኛውም ብሔር፤ የትኛውንም ክልል በብቸኛ ባለቤትነት አይሰጡም፡፡ ይኼ አንድን ክልል ለአንድ ወይም ካንድ ለበለጠ ብሔሮች ብቻ በባለቤትነት መስጠት፤ ሕገመንግሥታዊ አይደለም፡፡ ይኼ ትልቁ መታረም ያለበት ሕገ-መንግሥታዊ ሸፍጥ ነው፡፡ ይኼንን በብዙ መልኩ መመልከት ይቻላል፡፡
የክሎች ብቸኛ ባለቤት ብሔር/ብሔረሰብ የለም!
አንደኛ፤ እነዚህ ከልሎችን ለዚህ ወይም ለነዚያ ብሔሮች በባለቤትነት የሚሰጡ ክልላዊ ሕገ-መንግሥታት ከፌደራል ሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 9 ጋር ስለሚጣረሱ፤ ሕገመንግሥታዊ አይደሉም፡፡ ሁለተኛ፤ ሕገመንግሥቱ ላይ፤ አንቀጽ 40(3) ማናቸውም የገጠርም ኾነ የከተማ መሬትና የተፈጥሮ ሀብት ባለቤትነት መብት የመንግሥትና የሕዝብ ነው ይላል፡፡ ሲቀጥልም፤ መሬት የማይሸጥ የማይለወጥ የኢትዮጵያ ብሔር፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ሀብት ነው፡፡ በሠለጠነው ዓለም ቢሆን ብዙ የሚያከራክርና ለትርጉም የተጋለጠ አንቀጽ ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን፤ መሬት የሕዝብና የመንግሥት ነው፡፡ ክልልን “ክልል” የሚያሰኘው ደግሞ በከፊል ፖለቲካዊ ሀሳብ/ርዕዮተዓለም በከፊል ደግሞ መሬት ነው፡፡ በከፊል፤ ሸዋ፤ ሲዳሞ፤ ሐረርጌ፤ ባሌ፤ አርሲ፤ ኢሉአባቦራ፤ ከፋ፤ የተባሉት መሬቶች ናቸው፤ ባንድ ኦሮሚያ በተባለ ሀሳብ ተሸክፈው ክልል የተፈጠረው፡፡ መሬትና ሀሳብ ገጠሙ፡፡
የሕገመንግሥቱ አንቀጽ 46(2)፤ ክልሎች የሚዋቀሩት፤ በሕዝብ አሰፋፈር፤ ቋንቋ፤ ማንነት እና ፈቃድ ላይ በመመሥረት ነው ይላል፡፡ የኢትዮጵያ ክልሎች የተዋቀሩት እነዚህን መሠረት አደርጎ ነው ወይ የሚለው ክርክር እንደተጠበቀ ሆኖ፤ አሁን ባለው ሕገመንግሥት፤ የኢትዮጵያ ክልሎች የተመሠረቱበት መሬት፤ የክልሎቹ ሳይኾን የኢትዮጵያ ሕዝቦችና መንግሥት ነወ፡፡ ስለዚህ ክልሎች የተቋቋሙት በሕዝብ የጋራ ሀብት፤ መሬት ላይ ነው፡፡ አንዱ ክልል ብድግ ብሎ ይኼ ምድር የእከሌ ብሔር ነው፤ ወይም የነእከሌ ብሔር ነው ማለት አይችልም፡፡ ይኼንን የሚሉ ክልላዊ ሕግጋት ሀገሪቱን የመሠረታትን ሕገመንግሥት ስለሚጥሱ፤ ተፈጻሚ መኾን የለባቸውም ወይም በሕገመንግሥት ተርጓሚው አካል ፊት ቀርበው መፈተሽ አለባቸው፡፡ ቀድሞስ ነገር፤ የነዚያ አካባቢ ሕዝብ መቼ ቀን ድምጽ ሰጥቶና ፈቃዱን ገልጾ ነው እነዚህ ክልሎች የተፈጠሩት፡፡ ክልሎች፤ በውስጣቸው በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ላይ የተጫኑ ፖለቲካዊ ሀሳቦች ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ሕገመንግሥቱን የሚተረጉመው አካል፤ ፍርድቤቶች ወይም ሕገመንግሥታዊ ፍ/ቤት ሳይኾን፤ ፖለቲካዊ ተቋም፤ ማለትም የፌዴሬሽን ምክርቤት ስለኾነ፤ የዜጎችን መብት ለመጠበቅና ለማስጠበቅ፤ ሕገ-መንግሥቱን የብሔሮችን መብት ወይም የክልሎችን ሥልጣን በሚሸራርፍ መልኩ የመተርጎም ዕድሉ ጠባብ ነው የሚል ክርክር ይነሳል፡፡ በሠለጠነውም ዓለም ቢሆን፤ ለምሳሌ ካናዳ፤ አብላጫ ወንበር ያለው ፓርቲ ሕገመንግሥታዊ ማሻሻያዎችን በቀላሉ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ዴሞክራሲያዊ ፉክክርና ባህል ባለበት ዓለም ግን፤ ፖለቲከኞች የነገ ምርጫቸውን ስለሚያስቡ፤ ሕዝብ የማይቀበለው አተረጓጎም ከወሰኑ ወይም ሕግ ካወጡ፤ የሚቀጥለው ምርጫ ላይ ተዓማኒነትና ድምጽ ያጣሉ፡፡ ስለዚህ፤ በዴሞክራሲያዊ ዐውድ፤ ፖለቲከኞች የነገ ድምጻቸውን አደጋ ላይ ጥለው፤ ዘንድሮ ተገቢ ያልኾነ አተረጓጎም ያሰፍናሉ ተብሎ አይታመንም፡፡ ዞሮ ዞሮ ሕዝብ በዴሞክራሲዊ መንገድ የሚደግፈው አተረጓጎም ከኾነም ግን፤ በሂደት ሕዝቡን በማስተማር መለወጥ እንጂ፤ እኛ የማንፈልገው አተረጓጎም ስላሸነፈ፤ የግድ ስህተት ነው ማለት አይደለም፡፡
ሦስተኛ የፌደራል መንግሥቱን ሥልጣን የሚደነግገው አንቀጽ 51(5)፤ የመሬት፤ የተፈጥሮ ሀብትና ቅርሶች አጠባበቅና አጠቃቀም በተመለከተ፤ ሕግ ያወጣል ይላል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት ሥልጣን የሚደነግገው አንቀጽ 55(2) (ሀ) የመሬት የተፈጥሮ ሀብት እንዲሁም ድንበር ተሸጋሪ ወንዞችንና በሁለትና ከዚያ በላይ ክልሎች ውስጥ ያሉ ሀይቆችን አጠቃቀም በተመለከተ፤ ምክርቤቱ ሕግ ያወጣል ይላል፡፡ ክልሎች እንኳንስ ክልሉን በባለቤትን ለተወሰነ ብሔር መሥጠት ይቅርና፤ በመሬቶቹ ላይ ሕግ ማወጣትም አይችሉም ፤ ማስተዳደር እንጂ፡፡ ይኼ ሕግ የማውጣት ሥልጣን የሌለው ክልል፤ ይኼ ክልል የዚህ ወይም የነዚያ ብሔሮች ነው ሊል አይችልም፡፡ ያ ስህተት ነው፡፡ ምክንያቱም ባለቤትነት ከሕግ ይመነጫልና፡፡
ስለዚህ፤ ኢሕአዴግ/ብልጽግና በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ሲያስፈጽመውና ሲተረጉመው በመጣው አካሄድ ምክንያት ዝም ቢባሉም፤ አንዳንድ ብሔሮች፤ አንዳንድ ክልሎችን በብቸኝነት የኛ ነው የሚሉበት አካሄድ ሕገ-መንግሥታዊ አይደለም፡፡ ችግሩ ሕገ-መንግሥቱ ሳይኾን፤ ክልሎችና ባለሥልጣናት እንዲሁም ፖለቲከኞች ሕገመንግሥቱን የተረዱበት ቅኝት አንድም በየዋህነት፤ አንዳንዴም በድንቁርና፤ አለያም በራስወዳድነት መኾኑ ነው፡፡ በተጨማሪም፤ የፌደራል መንግሥቱ የሰብዓዊ መብቶችን ለማስፈጸም ወኔና ፍላጎት ስላነሰውና፤ በክልሎች ጉዳይ ጣልቃ ገባህ እንዳይባል ስለሰጋ የተፈጠሩ ችግሮች ናቸው፡፡ በርግጥ ሕገመንግሥቱ፤ በግልጽ ፍርድቤቶች ሕገመንግሥታዊ ጉዳዮችን መተርጎም ባይችሉም፤ መተግበር፤ ወይም የማስፈጸም ሥልጣን ቢሰጣቸው፤ መልካም ይሆናል፡፡ ከዚህ አንጻር ችግሩ በከፊል መዋቅራዊ ነው፡፡ ሕገ-መንግሥታዊ ማሻሻያ ያስፈልገው ይሆናል፡፡ ሙሉ በሙሉ ግን መዋቅራዊ አይደለም፡፡
ፌደራል መንግሥት ሆይ ወዴት ነህ?
በሕገመንግሥቱ ለክልሎች በግልጽ የተሰጡትን ሥልጣኖች ሳይጋፋ፤ የፌደራል መንግሥቱ፤ የኢትዮጵያዊያን ሕገመንግሥታዊ መብቶችን ሳይሸራረፉ፤ በሁሉም ክልሎች በእኩልነት እንዲፈጸሙ ከተጋና፤ ሕገመንግሥታዊ መብቶች ከማስፈጸም አንጻር የሚያፈነግጡ ክልሎችን፤ በማስተማር ወይም በማስገደድ ሕገ-መንግሥትን እንዲያስፈጽሙ መድረግ ከቻለ፤ ሕገመንግሥቱ ያቆየናል፡፡ በርግጥ፤ የፌደራል መንግሥቱ በክልሎች ጉዳይ ጣልቃ የሚገባበት ሕገ-መንግሥታዊ አግባብ ልቅ አይደለም፡፡ ጥብቅ ነው፡፡ አንቀጽ 51(14) የፌደራል መንግሥቱ በክልል ጣልቃ የሚገባው በክልል ሲጋበዝ ወይም ሲጠየቅ ነው ይላል፡፡ በአንቀጽ 55(16) መሠረት ሰብዓዊ መብት ሲጣስ፤ በሁለቱ የፌደራል ምክርቤቶች ፈቃድ ጣልቃ ሊገባ የሚችልበት አግባብ አለ፡፡ ከክልሉ አቅም በላይ ነው የሚለውን መወሰን ግን ቀላል አይደለም፡፡ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ሲታወጅም የፌደራል መንግሥቱ ጣልቃ ሊገባ የሚችልበት አግባብ አለ፡፡ አሁን የአገሪቱ በሙሉ ገዢ ፓርቲ አንድ በኾነበት ግዜ ይኼንን ሕገመንግሥታዊ እርምት ማድረግ ካልተቻለ፤ በዴሞክራሲያዊ ውድድር የተለያዩ ፓርቲዎች ሲገዙ፤ የፌደራል መንግሥቱ በክልሎች ሥልጣን ጣልቃ ለመግባት ምን ያህል ፈታኝ ሊሆንበት እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡ ከዚህ አንጻር ሕገመንግሥቱ መዋቅራዊ ችግል አለበት ማለት እንችላለን፡፡ ከዚህ አንጻር፤ ሕገመንግሥቱን ለማሻሻልና ክልሎች የዜጎችን መብት በሚጥሱበት ግዜ የፌደራል መንግሥቱ ጣልቃ ስለሚገባበት አግባብ፤ እንዲሁም ሕገመንግሥታዊ የአቤቱታና የይግባኝ መንገዶችን በማሻሻያ መልኩ ማስገባት፤ ወይም ፍርድቤቶችን በተወሰነ መልኩ ሕገመንግሥታዊ ጉዳዮችን/ክርክሮችን እንዲዳኙ ሥልጣን መሥጠት ያስፈልጋል፡፡ ይሁን እንጂ፤ ኃላፊነት የሚሰማው ኃይል፤ ሕገ-መንግሥቱን ለመሠረዝ ለመደለዝ መቸኮል የለበትም፡፡ ሕገመንግሥታዊነት ባህል ነው፡፡ ባህል ደግሞ፤ ትዕግስት ጊዜና ሰላም ይጠይቃል፡፡
ማጠቃለያ ሕገ-መንግሥት የሚዳብረው በስክነት እና በሂደት ነው፡፡ የኢሕአዴግ/ብልጽግናን ፖለቲካ ስለጠላን ብቻ፤ ሕገመንግሥቱን በጥቅሉ አቅልለንና አሽቀንጥረን መጣል ተገቢ አይደለም፡፡ ራሱን ሕገመንግሥቱን ተጠቅመን ሕገመንግሥታዊነት እንዲሰፍን ብንታገል፤ በኢትዮጵያ ሕገመንግሥት ውስጥ ሁሉም ባይሆኑም፤ አብዛኞቹ አንቀጾች ጠቃሚ ናቸው፡፡ ምናልባትም የሚያነታርኩ የሕገመንግሥቱ አንቀጾች በጣት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ምንም እንኳን ቁልፍልፍና ከባድ ቢሆኑም፤ የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት ሊሻሻል የሚችልበት አግባብና አንቀጾች አሉ፡፡ ዴሞክራሲ የድርድርና የሰላማዊ ፉክክር ዐውድ/ሂደት እንደመኾኑ መጠን፤ በድርድርና በፉክክር በምክክር ሕገ-መንግሥቱን በሰላማዊ መንገድ ታግሎ ማሻሻል እንጂ፤ ተቀዶ ካልተጣለ ሰላም አይመጣም የሚለው ሀሳብ ዴሞክራሲያዊም ሥልጡንም አይደለም፡፡ ሁልግዜ አሮጌውን ንደን፤ ደምስሰን፤ አፍርሰን፤ አዲስ መገንባት ብቻ ሳይኾን፤ ባለው ላይ መገንባት፤ ያለውን እያሻሻሉ መጓዝም መልመድ አለብን፡፡ ያ ደግሞ፤ ትዕግስትና መቻቻልን ይጠይቃል፡፡ ስለዚህ፤ በሕገመንግሥቱ ላይ የሚደረገው ውይይትና ንግግር በዚህ መልኩ፤ በትዕግስትና መቻቻል እንዲቃኝ እንመክራለን፡፡ በሚቀጥለው ደግሞ ስለአንቀጽ 39 የኔን አረዳድ እጽፋለሁ፡፡
