መግቢያ
“ሽብር” እና “ሽብርተኝነት” ዳግም ወደ መንቻካው ፖለቲካችን መዝገበ ቃል ተመልሰዋል፡፡ ንባበ ቃላቱ ባለፉት ቅርብ ዓመታት በኢትዮጵያ የፖለቲካና የነጻ ጋዜጠኝነት ዐውድ ላይ የነበራቸውን ሚና ለሚያስታውስ “እንኳን ደህና መጣችሁ” ለማለት አይደፍርም፡፡ ይኽ ግን በዛሬዋ ኢትዮጵያችን ኹናቴ የንባበ ቃሉን ትርጓሜ የሚያሟላ ግልጽ አደጋ የለም ለማለት አይደለም፡፡ እንዲያውም ፖለቲካዊ ፍላጎትን እጅግ መረን በለቀቀና ፍጹም ጭካኔ በተሞላበት መንገድ ተፈጻሚ ለማድረግ ዓይን የማይታሽበት ሀገር መኾኑ ሲታሰብ የላቀ መጠሪያ ፍለጋም ሊያስኬድ ይችላል፡፡ ነገር ግን ዛሬም በኢትዮጵያ የሽብር እና ሽብርተኝነት ጉዳይ እንደሌላው ዓለም ውጫዊ ሥጋት የወለደው ከመኾን ይልቅ ውስጣዊ የፖለቲካ ውጥረት የፈጠረው መኾኑ፣ ዘላቂ ትርጉሙ ላይ አብዝተን እንድንፈራ ምክንያት ሊኾነን ይችላል፡፡
ከምንም በላይ ደግሞ በኢትዮጵያ ነፍጥ “አነሳን” ከሚሉ ኃይሎች በመለስ ባሉ የፖለቲካ ወገኖች ዘንድ እየተካረረ ለመጣው ማኅበረ ፖለቲካዊ ቅራኔ አንዳች መፍትሔ መሥጠት ዳገት እየኾነ መምጣቱን ስናስብ፣ መንግሥት “የንጹሐንን ጭፍጨፋ ለመግታት ያግዘኛል” ያለው የሽብር እና የሽብርተኝነት ፍረጃ ውሎ አድሮ ሌላ መልክ እንዳይዝ እጅጉን ያሰጋል፡፡ እዚህ ጋር ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በጫጉላው ዘመናቸው ሰኔ 11 ቀን 2010 ዓ.ም በታደሙበት ፓርላማ “ሽብር ምንድን ነው ፣ አሸባሪስ ማን ነው?” የሚል ጥያቄ አንስተው የሰጡትን መልስ እንድናስታውሰው ግድ ይላል፡፡ “ሽብር ሲባል ሥልጣን ለመያዝ ብቻ ሳይኾን ሥልጣን ላይ ለመቆየትም አላግባብ ኃይል መጠቀምን ይጨምራል” ነበር ያሉት፡፡ ሁለተኛው ነጥባቸውን አያድርግብን ብለን ወደሚቀጥለው ነጥብ እንሻገር፤
ጥቂት ስለ ሉላዊው ሽብር
ሽብርተኝነት የሉላዊው ዓለም የጋራ አጀንዳ ከኾነበት ጊዜ አንስቶ አያሌ ጥናቶችና ምርምሮች ተደርገውበታል፡፡ መነሻው፣ መድረሻው፣ ሥረ ምክንያቱ፣ ፍላጎቱና ግቡ ተተንትኗል፡፡ ከዚህ ቀደም በዚሁ በግዮን መጽሔት ቁጥር 131 ዕትም “መግደል (Assassinations) ፖለቲካ ነውን?” በሚል ርዕስ በተሰናዳ መጣጥፍ “Combating Terrorism Center” የተባለ ተቋም በዓለማችን ባለፉት 70 ዓመታት በ920 አቀነባባሪዎች 758 የሚኾኑ ፖለቲካዊ የግድያ ጥቃቶች ተፈጽመው ከአንድ ሺህ ግለሰቦች በላይ ስለመሞታቸው ማስነበቡ ተገልጾ ነበር፡፡ ዘገባው እነኚህ ፖለቲካዊ ግድያዎች (በመንግሥትም በተቀዋሚ ቡድኖችም በኩል የሚፈጸሙት) እየተበራከቱ መምጣት በሂደት (በተለይ ከፈረንጆቹ 1970ዎቹ በኋላ) የሽብር ድርጅቶች እንዲቀፈቀፉ አንድ ምክንያት መኾኑንም ያትታል፡፡
ከእነዚህና ሌሎችም ተጨባጭ ሁኔታዎች በመነሳት ዓለማችን ዛሬ ላይ በጥቅል የተቀበለቻቸው የሽብርተኝነት ብየናዎች በዋናነት በአራት የትርጉም ዋልታዎች ላይ ያርፋሉ ማለት ይቻላል፡፡ እነርሱም
ሀ) በግብታዊነትና በተራዘመ ሁኔታ ሰዎችን ማሰቃየት ፤
ለ) በሰዎች ላይ በተናጠልም ሆነ በጅምላ ጉዳት ማድረስ ፤
ሐ) ሰዎች የማይፈልጉትን ነገር እንዲቀበሉ ማስገደድ እና
መ) ከሀገራቸው፣ ከቤታቸው፣ ከቀያቸው ማፈናቀል፣ መግደል፣ ማሰር፣ ማሰቃየት፣ በብልሃትና በዘዴ እልቂትን በማቀነባበር ፍርሃትና መደናገጥን መፍጠር የሚሉት ናቸው፡፡
አሁናዊ የሽብር ሥጋቶች
አሁን ባለው የሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ከፍ ሲል የተዘረዘሩት ቀሊል የሽብርተኝነት ብየናዎች ተሟልተው ሲተገበሩ ይታያል፡፡ በተለይ ድኅረ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም በኋላ የጅምላ ግድያዎችና መፈናቀሎች በቦታና በመጠን ሰፍተው የዜጎችንም የሃገረ መንግሥቱንም ሕልውና ፈተና ላይ ጥለዋል፡፡ መንግሥትም ችግሮቹን እልባት የመሥጠት አቅሙ ደካማ መኾን ችግሩን አስመልክቶ ዜጎችና የተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖች አዲስ መላ እንዲመትሩ በር እስከመክፈት አድርሷቸዋል፡፡
ከእነኚህ ሀቆች በመነሳት በኢትዮጵያችን አሁናዊ ኹናቴ የሽብር ሥጋት አለን? የሚለው ጥያቄ በቀላሉ ምላሽ የሚገኝለት ነው፡፡ በርግጥም ዛሬ በምድረ ኢትዮጵያ በንጹሐን ዜጎች ላይ የሚፈጸመው የማሰቃየት ፤ በጅምላና በተናጠል ጉዳት የማድረስ ፤ የማይፈልጉትን ነገር እንዲቀበሉ የማስገደድ ፤ እንዲሁም ከሀገራቸው፣ ከቤታቸው፣ ከቀያቸው ማፈናቀል ፤ መግደል፣ ማሰር፣ ማሰቃየት፣ በብልሃትና በዘዴ እልቂትን በማቀነባበር ፍርሃትና መደናገጥን የመፍጠር ተግባራት በተደጋጋሚ ተፈጽመዋል ፤ እየተፈጸሙም ነው፡፡
ከዚህ በመነሳት መንግሥት የ”ሽበርተኝነት ሥጋት አለብኝ” ማለቱ ከእውነት አያጎድለውም፡፡ የሽብር ድርጊቶችን የሚፈጽሙ ግለሰቦችና ቡድኖች ላይ እርምጃ ለመውሰድ ከቀጠናዊም ይኹን ዓለም አቀፋዊ አጋሮች ጋር በትብብር ለመሥራት ቢነሳም አንዳች ነቅዕ አይኖርበትም፡፡ ዳሩ ግን መንግሥትም ኾነ ለመንግሥት ቅርብ የኾኑ ውስጣዊና ውጫዊ አካላት መጠየቅ የሚገባቸው ጥያቄ አንድና አንድ ነው፡፡ ይኸውም “መንግሥት በትክክል አሸባሪዎቹን ያውቃቸዋል ወይ?” የሚለው ነው፡፡ ይኽ ጥያቄ ቀላል ወይም እንቶ ፈንቶ መኾን የማይችልበት በርካታ ምክንያት አለ፡፡ ዝቅ ብለን በዝርዝር እንመልከተው ፤
“ሸኔ” እና “ወያኔ”
ከሳምንት በፊት የሚኒስትሮች ም/ቤት “የሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ሕወሓት)” እና “ሸኔ” በሽብርተኝነት መሰየም” በሚል ርዕስ ባወጣው መግለጫ፣ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በሰላማዊ ዜጎች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች ሲፈጸሙ የቆዩ መሆኑን በማሰታወስና በዚህ ምክንያትም የበርካታ ዜጎች ሕይወት መጥፋቱን፣ አካል መጉደሉን እንዲሁም ንብረት መውደሙንና ፤ ከቀዬ መፈናቀላቸውን በመጥቀስ፣ ሕብረተሰቡ ቀጣይነት ባለው ሥጋት እና ፍርሐት ውስጥ እንዲኖር በማድረግ በመንግሥት ላይ እምነት እንዲያጣ፣ ዜጎች እርስ በእርስ እንዳይተማመኑ ተደርጓል ብሏል፡፡
ከዚህ በመነሳትም እነኚህ ተግባራት የሃገረ መንግሥቱን ሕልውና አደጋ ላይ ለመጣል ታቅደው ሲፈጸሙ የነበሩ መሆናቸውን ከተለያዩ ማስረጃዎች ለመረዳት መቻሉን በመግለጽ፣ “ተግባራቱ የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በወጣው ዐዋጁ 1176/2012 አንቀጽ 3 ሥር ስለሽብር የወንጀል ድርጊት የተሰጠውን ትርጓሜ ሙሉ በሙሉ የሚያሟሉ ተግባራት እንደሆኑ መገንዘብ ተችሏል” ብሏል፡፡
ይኽ የሚኒስትሮች ም/ቤት ውሳኔ በመርህ ደረጃ በኢትዮጵያ ያለፉትን ሦስት ዓመታት ሲፈጸሙ የነበሩ ተግባራትን “ሽብር” ማለቱ ትክክል ነው፡፡ ህወሓት እና ሸኔ በሽብርተኝነት እንዲሰየሙ መወሰኑም ለበርካታ ጊዜያት ሲጠየቅ የነበረ ጥያቄ ከመኾኑ አኳያ ተቃውሞ ላያስነሳ ይችላል፡፡ መሠረታዊው ጥያቄ ግን ባሻቸው ሰዓትና ጊዜ፣ መንግሥት ያስተዳድረዋል በሚባለው ከተማና መንደር በወታደራዊ ሰልፍ የሚንጎማለሉ፣ ሻማ አብርተው የምሥረታ በዓላቸውን በፌሽታ የሚያከብሩ፣ ሩሲያ ሰራሽ መሣሪያ ታጥቀው እንደልባቸው የሚፏልሉ፣ የመከላከያ ታርጋ ነቅለው በድል አድራጊነት የሚፎክሩ፣ አንድ መንደር ሕዝብ “ስብሰባ” ብለው ጠርተው በጅምላ የሚፈጁ፣ መኪና አስቁመው ቋንቋ መርጠው የሚበቃቸውን ያህል የሚገድሉ፣ ወዘተ… ቡድኖችን መንግሥት በትክክል ያውቃቸዋልን የሚለው ነው፡፡
ይኽ ጥያቄ አስፈላጊ ኾኖ እዚህ ጋር የሚነሳው እንበለ ምክንያት አይደለም፡፡ መንግሥት ከፍ ሲል የተዘረዘሩትን ድርጊቶች የሚፈጽመውን ቡድን “ኦነግ ሸኔ ነው” ብሎ በየአካባቢዎቹ ለወራት የሚዘልቅ ስልክና ኢንተርኔት አልባ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆችን በማወጅ፤ በሺህ የሚቆጠሩትን በተለያየ ጊዜ “ገደልሁ፣ ደመሰስሁ” ብሎ በመግለጽ፤ ሲያሻው ደግሞ ዳግም “በዐሥራ አምስት ቀን ዘመቻ እደመስሳለሁ” ብሎ በመፎከር እና የተለያዩ አፍአዊም ገቢራዊም እርምጃዎችን በመውሰድ ችግሩን እንኳንስ መቅረፍ ጋብ ማድረግ ባልቻለበት ሁኔታ በሽብርተኝነት መሰየሙ በተለየ ሁኔታ የሚያመጣው ለውጥም ኾነ የሚያሳድረው ተስፋ ምንድነው የሚል ጥያቄን ያጭራል፡፡ ጥያቄው ጥያቄ ኾኖ እንዲቀጥል አሁንም ተጨማሪ ምክንያት አለ፡፡
ይኸውም ድርጅቱን አስመልክቶ ም/ቤቱ ያሳለፈው የሥያሜ ውሳኔ ነው፡፡ “ሸኔ” የሚል መጠሪያ ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ ይኼ መቼም በሽብርተኝነት ዙሪያ የዓለምንም ይኹን የሀገራችንን ያለፈ ተሞክሮ ለሚያጤን ግራ እንደሚያጋባ አያስጠረጥርም፡፡ እንደሚታወቀው በዓለም ላይ ሀገራት ሽብርተኛ ድርጅቶችን ለመዋጋት ሉላዊ ድንጋጌዎችን ሲያጸድቁም ኾነ ሲፈርጁ ቡድኑ ራሱን የሚጠራበትን መጠሪያ ጥቅም ላይ ያውላሉ፡፡ “አልቃዒዳ”፣ “አልሸባብ”፣ “ቦኮ ሃራም” እና ሌሎችም በዚህ ረገድ ጥሩ ምሳሌ ናቸው፡፡ በሀገራችንም እንዲሁ ህወሓት መሩ የኢሕአዴግ አገዛዝ ለፖለቲካ ሥልጣን የሚታገሉትን ግንቦት 7፣ ኦነግ እና ኦብነግን “አሸባሪ” ብሎ ሲሰይማቸው የገዛ መጠሪያቸውን ዋቢ አድርጎ እንደነበር ከቶም አይዘነጋም፡፡
አሁን ላይ ይኽ አካሄድ እንቆቅልሽ ኾኖ መጥቷል፡፡ መንግሥት በምዕራብ ወለጋ የተለያዩ አካባቢዎች ሳይቀር በቡድኑ ላይ ከፍቷቸው የነበሩ የጦር ዘመቻዎች “ኦነግ ሸኔን መደምሰስ” ይሰኙ የነበሩ ቢኾኑም በሰሞነኛው ፍረጃ ግን “ሸኔ” ብቻዋን እንድትቀር ተደርጋለች፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን ይኽ አይደለም፡፡ “ኦነግ ሸኔ”ም ተባለ “ሸኔ” ራሱን በዚህ ሥም የሚጠራ ታጣቂ ኃይል አለመኖሩ ነው፡፡ የዚህ ሸማቂ ኃይል መሪ እንደኾነ የሚነገረው ኩምሳ ዲሪባ ወይም “ጃል መሮ” በተለያዩ ሚዲያዎች በመቅረብ የሚመራውን ኃይል “የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት” (WBO) ብሎ ሲጠራው ተሰምቷል፡፡ “ኦነግ ሸኔ የሚባል ድርጅት አናውቅም” ሲልም በተደጋጋሚ ገልጾዋል፡፡ መንግሥት በርግጥም በንጹሐን ላይ እየደረሰ ላለው ማንነትን መሠረት ያደረገ አረመኔያዊ ጥቃት ይኽ ቡድን ተጠያቂ መኾኑን ካመነበት ሊጠራው ወይም ሊፈርጀው የሚገባው ቡድኑ ራሱን በሚጠራበት ሥም መኾን ነበረበት፡፡ ይኽ ግን በሚያሳዝን ሁኔታ አልኾነም፡፡
ያልተመለሰው ጥያቄ ግን ይኽ አይደለም፡፡ በተደጋጋሚ በራሱ በመንግሥት ውስጥ ባለ ሌላ መንግሥት (State within state) አጋዥነት ቡድኑ ሲፈጽማቸው የነበሩትን ጭፍጨፋዎች ማስቆም ያልቻለው መንግሥት በ”ሽብር” አዋጁ “ሽብርተኛ” ስላስባለ ብቻ ችግሩን ማስቆም ይችላል ወይ የሚለው ነው፡፡ ይኽ ጥያቄ በመግቢያችን በመጠኑ ለመጥቀስ እንደሞከርነው፣ “ነፍጥ አነሳን” ከሚሉ ኃይሎች በመለስ ባሉ የፖለቲካ ወገኖች ዘንድ እየተካረረ ለመጣው ማኅበረ ፖለቲካዊ ቅራኔ አንዳች መፍትሔ መሥጠት ዳገት እየኾነ መምጣቱ፣ መንግሥት “የንጹሐንን ጭፍጨፋ ለመግታት ያግዘኛል” ያለው የሽብር እና የሽብርተኝነት ፍረጃ ውሎ አድሮ ሌላ መልክ እንዳይዝ እጅጉን ያሰናል፡፡
አዲሱ ሽብርን የመቆጣጠር አዋጅ
ከምርጫ 97 በኋላ በኢትዮጵያ በአዲስ መልክ የሰፈነው የእመቃ ፖለቲካ በአቶ መለስ ዜናዊ ዋነኛ አርቃቂነት “የጸረ ሽብርተኝነት አዋጅ” የሚል ሕግ አዋልዶ ፖለቲከኛውንና ጋዜጠኛውን ማሳደጃ ኾኖ ቆይቷል፡፡ የአዋጁ ቀንደኛ ባለቤት የነበረው ህወሓት ታዲያ ዕጣው ደርሶት ዛሬ ከአሳዳጅነት ወደተሳዳጅነት ወርዶ በአሸባሪነት ለመፈረጅ በቅቷል፡፡ “ቦ ጊዜ ለኩሉ” ብለን እንቀጥል፡፡
ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ወደሥልጣን ኮርቻው ከመጡ በኋላ ከፍ ሲል በመንደርደሪያችን እንደጠቀስነው በቀዳሚነት ያነሱት ጥያቄ ባለፉት ዓመታት “አሸባሪ ማነው?” የሚል ነበር፡፡ በምላሻቸውም መንግሥት አሸባሪ እንደነበረ ጠቅሰው “ሽብር ማለት ሥልጣን ለመያዝ ብቻ ሳይኾን ሥልጣን ላይ ለመቆየትም አላግባብ ኃይል መጠቀምን ይጨምራል” ብለዋል፡፡ ይኽንን ተከትሎም ሕግ የጠሉትን መምቻ ኾኖ እንዲያገለግል ለአስፈጻሚው አካል መረን የሌለው ሥልጣን የሰጠውን አዋጅ ለማሻሻል ወደሥራ ተገብቷል፡፡ በመኾኑም ከግንቦት 2010 ዓ.ም ወዲህ ሰፊ ጊዜ ወስዶ የተሻሻለው አዲሱ ሽብርን የተመለከተ ሕግ በብዙ መልኩ ከቀድሞ እንዲለይ መደረጉን መመስከር ይቻላል፡፡ የአዋጁ መንፈስና ድንጋጌዎች፤ ከዓለም አቀፍ ሕጎች ጋር እንዲጣጣሙ፤ ሰላማዊ ሰልፍ እና የሥራ ማቆም አድማ በሽብር የማያስከስሱ ተግባራት እንዲኾኑ መደረጉና ሌሎችም ነጥቦች ማሳያ ናቸው። ሥያሜውም ‹‹የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር›› በሚል ተቀይሯል፡፡
ከዚህ በፊት አስፈጻሚው አካል እና ምክር ቤት ብቻቸውን ከተስማሙ አንድን ድርጅት አሸባሪ ብለው ይፈርጁ የነበረበትን ድንጋጌም በማሻሻያው እንዲነሳ ተድርጓል። በተመሳሳይ የፍትሕ አካላት ማንኛውንም በሽብር የጠረጠሩትን ግለሰብ ስልክ መጥለፍ እና ልዩ ክትትል ማድረግ የሚፈቅደውን አንቀጽ በማንሳት አስገዳጅ ከሆነም በፍርድ ቤት ትእዛዝ ብቻ እንዲከናወን የሚል ማሻሻያ ሊሰፍር ችሏል።
አዲሱ የሽብር ድርጊት ከሽብር ወንጀል ጋር እንዳይምታታም በትርጉም ክፍል የሽብር ድርጊትን እንዲይዝ ተደርጎም እንዳዲስ ተዘጋጅቷል፡፡ ይኽ ድንጋጌም የአዋጁ መሠረት ተደርጎ የተቀመጠ ሲሆን፣ በሽብር ድርጊት የተሳተፈ ሰው ሊቀጣ የሚችልበትን የቅጣት ወሰን በሦስት እርከኖች ተከፍሎ ተቀምጧል፡፡ የመጀመርያው ከ10 እስከ 15 ዓመት እንደሚያስቀጣ ሲደነግግ፣ ሁለተኛው እርከን ከ15 እስከ 25 ዓመት እንዲሆን ተደርጓል፡፡ የመጨረሻውና ሦስተኛው የቅጣት እርከን ደግሞ ከ15 ዓመት እስከ ዕድሜ ልክ ወይም ሞት የሚያስቀጣ ሆኖ ተመልክቷል፡፡ ይህ የቅጣት ደረጃ በነባር አዋጅ በጥቅሉ ከ15 ዓመት እስከ ዕድሜ ልክ ወይም ሞት የሚያስቀጣ ሆኖ የተደነገገ እንደነበር አይዘነጋም፡፡
“ሽብር” እና “አሸባሪ ድርጅት” በአዲሱ አዋጅ
በአዲሱ የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በወጣው አዋጅ ቁጥር 1176/2012 መሠረት የሽብር ድርጊት የሚባለው ማንኛውም ሰው የፖለቲካ፣ የሃይማኖት ወይም የርዕዮተ ዓለም ዓላማን ለማራመድ በማሰብ ሕዝብን ወይም የተወሰነ የሕብረተሰብን ክፍል ለማሸበር ወይም መንግሥትን፣ የውጭ አገር መንግሥትን ወይም ዓለም አቀፍ ድርጅትን ለማስገደድ፡-
ሀ) በሰው አካል ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ፤
ለ) የሰውን ሕይወት ለአደጋ ያጋለጠ፤
ሐ) ሰውን ያገተ ወይም የጠለፈ፤
መ) በንብረት፣ በተፈጥሮ ሐብት ወይም አካባቢ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ፤ ወይም
ሠ) የሕዝብ ወይም ማህበራዊ አገልግሎት እንዳይሰጥ በከፍተኛ ሁኔታ ያስተጓጎለ እንደኾነ ነው፡፡
ይኽም ከዐሥር ዓመት እስከ ዐሥራ ስምንት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እሥራት እንደሚያስቀጣ ተደንግጓል፡፡ ድርጅትን በአሸባሪነት በመሠየም ረገድም አዋጁ ሥልጣኑን ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ሙሉ በሙሉ የሰጠ ሲኾን እንደቀድሞ አሠራር የሚኒስትሮች ም/ቤት ከወሰነበት ጊዜ አንስቶ ተፈጻሚ የሚኾንበትን በርም ተዘግቷል፡፡
ማጠቃለያ
የሽብር እና ሽብርተኝነት ተዋስዖ ዳግም ወደፖለቲካችን መድረክ መምጣቱ ሁለት ውጤት አለው፡፡ ቀዳሚው በግልጽ እያየናቸው የመጣናቸውን የሽብር ተግባራት በተለየ የሕግ ማዕቀፍ ለማስቆምና ዕልባት ለመሥጠት ከማስቻል አንጻር የሚገመገም ሲኾን፣ ኹለተኛው ደግሞ በቀጣይ የዴሞክራሲ ልምምድና የፖለቲካ ምሕዳሩ ላይ ነባሩን አዙሪት እንዳይደግም የሚያሰጋ መኾኑ ነው፡፡ እንደ አፍሪካ ባሉ ሕግን የጠሉትን መምቻ ለማድረግ መሽቀዳደም ባለበት አኅጉር፣ እንደ ኢትዮጵያ ባለ እሥርን “ሚዛናዊ” ለማድረግ በደለኛን ከንጹሕ ጋር አጃምሎ በሚያስር ሥርዓት፣ ግልጽ የወጡ የሽብር ድርጊቶችን ለመቆጣጠር የወጡ አዋጆች ሲቪል ፖለቲከኞችን ለማጥቃት እንዳይውሉ ያሰጋል፡፡
ይኽም ኾኖ የኢፌዲሪ ፓርላማ የሚኒስትሮች ም/ቤት ያቀረበለትን የውሳኔ ሐሳብ መርምሮ በማጽደቅ “ህወሓት” እና “ሸኔ” አሸባሪ ድርጅቶች ሊባሉ ችለዋል፡፡ ከፍ ብለን እንደጠቀስነው የሥም ጉዳይ ግራ አጋቢነት ባያጣውም በገቢር የድርጅቶቹ በ”ሽብርተኝነት” መፈረጅ ጠቃሚነት እንዳለው ግን አያጠራጥርም፡፡
በተለይ የሚኒስትሮች ም/ቤት ባወጣው መግለጫ የጠቀሰው “በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ሲፈጸሙ የቆዩት እነዚህ ጥቃቶች የተለያዩ ፈጻሚ አካላት ነበሯቸው። ከጥቃቶቹ ጀርባ ግን በዕቅድ፤ በገንዘብ፣ በሐሳብ እና በሰው ኃይል ሥልጠና በመደገፍ፤ የሚዲያ ሽፋን እና እገዛ በመስጠት ረገድ የመሪነት ሚናውን ሲጫወቱ የነበሩ ቡድኖች አሉ።” የሚለው ኃይለ ቃል በመሃል አዲስ አበባ ተቀምጠው በዜጎች ሞት ለሚቆምሩና የተሳሳተ የሀሰት ዘገባና ፕሮፓጋንዳ ለሚያሰራጩ ግለሰቦችና ቡድኖች አደብ ማስገዣ ይኾናል፡፡ ሞት ትንሣኤ እንዲኾንለት መመኘትን ምርጫው አድርጎ ለመኖር ለተገደደው ወገን አዋጁ የሚያመጣለትን ውጤት ተስፋ ለማድረግ እንጂ ለመገመት እንደሚቸገር ግን ግልጽ ነው፡፡
ሠላም ለኢትዮጵያ!
