ትራምፕ ሐሙስ ዕለት በትሩዝ ሶሻል የማህበራዊ ገፅቸው ላይ እንዳስታወቁት ጥቃቱ የተፈጸመው “በእኔ አዛዥነት ነው” ብለዋል።
በናይጄሪያ ከአይኤስአይኤስ ጋር ግንኙነት ያላቸው ታጣቂዎች “በዋናነት ንጹሃን ክርስቲያኖችን በጭካኔ እየገደሉ ነው” ሲሉም ትራምፕ ከሰዋል።
ነገር ግን ትራምፕ ይህን የአየር ድብደባ አሜሪካ እንዴት እንደፈጸመች የገለጹት ነገር የለም።
የናይጄሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሀገሪቱ ሽብርተኝነትን እና አክራሪነትን ለመዋጋት አሜሪካን ጨምሮ ከአለም አቀፍ አጋሮች ጋር እየተተባበረች መሆኑን አስቀድሞ መናገሩ ይታወሳል።
ሚኒስቴሩ በሰሜን ምዕራብ ናይጄሪያ በሚገኙ የአሸባሪ ቡድኖች ላይ ያነጣጠረ የተሳካ የአየር ድብደባ እንዲካሄድ ማስቻሉን ገልጿል።
እንደ ቦኮ ሀራም እና የምዕራብ አፍሪካ እስላማዊ መንግሥት (ISWAP) ያሉ ታጣቂ ቡድኖች፣ በተለያዩ እምነት ተከታዮች ላይ የጅምላ ግድያ፣ ጠለፋ እና ጥቃቶችን ሲፈጽሙ ቆይተዋል።
የክርስቲያን መብት ተሟጋች ድርጅቶች እና አንዳንድ የአሜሪካ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባላት በናይጄሪያ በክርስቲያኖች ላይ የሚፈጸም “የዘር ማጥፋት” ነው ሲሉ ይገልጹታል።
