አስቴር አወቀ – የማይበርድ ፍም ያላት ኮኮብ

Date:


(በእውቀቱ ስዩም)

በኪነጥበብ ሁለት አይነት ችሎታ አለ፤ የመጀመርያው አብነት የሚባል ነው፤ ‘አብነት’ የሚለውን ቃል የተዋስሁት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሊቃውንት አንድምታ ተርጉዋሚዎች ሲሆን ‘ዋና ምንጭ’ ወይም ኦሪጅናል ማለት ይሆናል፤ አስቴር አወቀ እንዲህ አይነት ከያኒ ናት፤ አንዳንዴ አልፎሂያጅ ዘፈን ሰምተን -እገሊትኮ አስቴርን ትመስላለች -እንላለን፤ አስቴርን የሚያስመስሉ ሰዎች ችሎታ እንዳላቸው ባይካድም ችሎታቸው አምሳል ነው፤ በዚህ ምድር ብዙ አምሳሎች ሲኖሩ አብነት ግን አንድ ለናቱ ነው፤

አስቴር የሚለው ስም የልደት ይሁን የግብር ስም በቅጡ ባላውቅም በልኩዋ የተሰራ ይመስለኛል ፤ አስቴር ማለት ትርጉሙ ኮኮብ ማለት ነው፤ ከኮኮቦች ሁሉ የምትበልጥ ኮኮብ -ደመና የማይሰውራት፤
የጠረፍ ላይ ብርቅ መብራት –

ያስቴር ድምጥ ዝም ብሎ ድምጥ አይደለም፤ ዜማዋ የትዝታችን ማስተርተርያ ነው፤ የሆነ ዘፈኑዋን ስትሰሚ አንድ የሚያስደስት የሚያስተክዝ የግል ታሪክሽ ቁራጭ ድቅን ይልብሻል፤ እኔ ዜማዋን ስሰማ በለጋነቴ ያለፉ ክረምቶች በፊቴ እንደ ፉርጎ ተከታትለው ያልፋሉ ፤ ከማጀት እየተመዘዘ የሚመጣ የጎመን መአዛ ይሸተኛል፤ በምኝታ ቤታችን መስኮት በኩል ተመዝዞ የሚወጣው ሙጃ ይታየኛል፤

ያስቴር በሁለት በኩል እድለኛ ናት፤ ባንድ በኩል መሰል የሌለው ተሰጥኦ ይዛ ተወለደች፤ በሌላ በኩል፣ በጣም ሀያል የሙዚቃ ባለሙያዎችን እና ደራሲዎችን መጎዳኘት ቻለች፤ ( እነ ደረጀ መኮንን ፣ እነ ጥላየ ገብሬ፣ አነ አበጋዝ፣ ከድርሰት እነ አበበ መለሰ ይልማ ገብረአብ ፣ ያየህራድ አላምረውን እና ሌሎችን ማለቴ ነው)

አስቱ፣ ከሰሞኑ የተመረጡ ዘፈኖችዋን እንደገና ሰርታ ለዲጂታሉ ትውልድ አቅርባለች፤ እኛ ከካሴት ክር እስከ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ድረስ የተዘረጋ ትውልድ አባሎች ይህንን እድሳት እንዴት ተቀበልነው? ከለውጥ ሰውረኝ ማለት ይቻላል? አክሱምና ላሊበላም ከጠጋኝ እጅ አላመለጡም፤ በበኩሌ የሙዚቃ ክህነት ያላቸው እንደ ሰርዐፍሬ ስብሀት አይነት ሰዎች የተሰማቸውን ቢያጋሩን ደስ ይለኛል፤ ገጣሚና ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ጸጋየ ሙዚቃ የሚመዝን የሰላ ጆሮ እንዳለው አውቃለሁ፤ የሱን ምዘና ብሰማ እወዳለሁ፤

ያስቴር የድምፅ አቅም ከምገምተው በላይ ሆኖ ነው ያገኘሁት፤ በርግጥ አስቴር በአፍላ ዘመን አዘፋፈኑዋ ላይ ልባችንን የሚያቀልጠው ልስልስ ቃና ከስሞ ,የሆነ ዘመን ላይ በፈረጠመ ቃና የተተካ ይመስላል፤ አንዳንዴ ከዘፈኑ የድርሰት ሀሳብና መንፈስ የሚርቅ ይመስላል፤ አንዲያም ሆኖ ምቾት አይነሳም፤

ከታደሰው ውስጥ ‘ባይኔ ሙሉሙሉን’ ከሁሉ አብልጨ መርጫለሁ፤

አስቴር ለህይወታችን ቅመም ሆና በጤና እንድትኖር ምኞቴ ነው፤

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

አዲስ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ኢራን የበለጠ ምላሽ በመስጠት የተራዘመ ጦርነት እንደምታካሂድ አስታወቀች

ከፍተኛ የኢራን ወታደራዊ ባለሥልጣናት አሜሪካ ሌላ ዙር ጥቃት በአገራቸው...

ምክክሩ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ደርሷል

ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በሥራ ቡድን ደረጃ እየተካሄደ የሚገኘውን...

የጎንደር ቃል-ኪዳን ቤተሰብ 28 የውጭ ዜጋ ተማሪዎችን ከኢትዮጵያውያን ቤተሰቦች ጋር ማስተሳሰሩን ገለጸ

ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በጎንደር ቃል-ኪዳን ቤተሰብ መርሃ-ግብር አማካኝነት በዘንድሮው ዓመት...

የሕግ ተማሪዎቹ አፍሪካን ወክለው ለዓለም አቀፍ የምስለ-ችሎት ፍጻሜ አለፉ

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ ተማሪዎች በአህጉራዊው የዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት...