ከሰሞኑ መቀመጫውን በኖርዌይ ያደረገውና በሰላም ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን አድርጎ ጥናቶችን የሚሠራው ተቋም፤ በሰሜን ኢትዮጵያ የተደረገው ጦርነት ከፈረንጆቹ 1984 ወዲህ እንደዓለም ከተደረጉ ግጭቶች መካከል የከፋ ነው ሲል አስነብቧል፡፡ ጥናቱ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ብቻ በፖለቲካ ምክንያት በዓለም በተቀሰቀሱ ግጭቶች የ204 ሺሕ ሰዎች ሞት መመዝገቡን የገለጸ ሲሾን፣ ከዚህ ውስጥ በዩክሬን እና ኢትዮጵያ የተመዘገበው ሞት 89 በመቶ ድርሻ እንዳለው ጠቅሷል። በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል የነበረው ግጭት የዓለምን ትኩረት የሳበ እና ከፍተኛ የመገናኛ ብዙኃን ሽፋን ያገኘ ይሁን እንጂ፤ በኢትዮጵያ በፌዴራል መንግሥት እና በሕወሓት ኃይሎች መካከል የተደረገው ጦርነት እጅግ የከፋ እና የብዙ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈ ነው ሲል ጥናቱ አመላክቷል፡፡
በሩሲያ እና ዩክሬን እየተደረገ ባለው ጦርነት 81 ሺሕ 500 ሰዎች መሞታቸው ሲጠቀስ፤ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ግን ከ100 እስከ ሺሕ 200 ሰዎች መሞታቸውን ጠቁሟል። ጥናቱ አክሎም በፌዴራል መንግሥት እንዲሁም ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ በሚጠራውና በመንግሥት ኦነግ ሸኔ ተብሎ በአሸባሪነት በተፈረጀው ታጣቂ ቡድን መካከል በተለያዩ የአገሪቱ ቦታዎች እየተደረገ ያለው ውጊያ፤ በፈረንጆች 2022 በዓለም ከተደረጉ ሰባት አስከፊ ውጊያዎች አንዱ ነው ሲልም ጥናቱ ጠቁሟል፡፡ መንግሥት በቅርቡ ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት፤ ለኹለት ዓመታት በዘለቀው የሰሜኑ ጦርነት እንዲሁም በቤኒሻንጉል ጉምዝና ኦሮሚያ ክልሎች በሚከሰቱ ግጭቶች ከ22 ቢሊዮን ዶላር በላይ ውድመት መድረሱም አይዘነጋም።
የኾኖ ኾኖ ዋናው ጉዳይ ግን ይህ አይደለም፡፡ አሁንስ ከዚህ እልቂት እና የጥናት አባሪ ማሳለጫነት ኢትዮጵያውያን ፖለቲከኞች ምን ይማራሉ የሚለው ነው፡፡ በዚህ ጥናት እንደተገለጸው ምንም እንኳን ህወሓት ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች ሞተውብኛል ቢልም ሟቾቹ ከመቶ እስከ ሁለት መቶሺህ እንደሚደርሱ ተጠቁሟል፡፡ ይህ በኾነበት ሁኔታ ህወሓት ግን በሟቾች ቁጥር ፖለቲካዊ ቁማርን ለመሸቀጥ በመሻቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ትግራዮች እንዳለቁበት ደሰኮረ፡፡ የክልሉን ማንነት ካነገቡ አካላት ውጪ ያሉ ማናቸውንም የፖለቲካ ሰዎች ወይም ማኅበራዊ አንቂዎች በጂኖሳይድነት ለማስመዝገብ ሴራዊ ግብዝነትን በመጠቀም ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለማሳወቅ ሞከረ፡፡ ነገር ግን ወያኔ ምንም እንኳን በተለይም የአማራና የመንግሥት ኃይላትን በጂኖሳይደርነት ቢከስም ተቀባይነቱ የዘገየ ይመሰስላል፡፡ ከዚያ ከፍ ሲልም በእርሱ በኩል ያሉት እነጭና እነማይካድራና በርካታ መሰል ቦታዎች ላይ የፈጸመው የዘር ማጽዳት ወንጀል ይበልጥ ሳያስጠይቁት አልቀረም፡፡ ለዚያም ይመስላል ሰሞነኛው የጌታቸው ረዳ አሜሪካ ጉዞ ከመጨናገፍ ለጥቂት የተረፈው፡፡ አለፍ ሲልም ለእነስብሐት ነጋ፣ ጌታቸው ረዳ፣ ጻደቃን ገ/ተንሳይ እና መሰሎቻው የተፈቀደው የሀገር ውጪ ጉዞ ለእነደብረጺዮንና መሰሎቻቸው የተዘጋው ለዚህ ይመስላል፡፡
ህወሓት አሁንም ልቦናው ጦርነትን አልተጸየፈም፡፡ የእርሱ ላልኾነው ነገር ግን ጥያቄ አለኝ ለሚልበት የወልቃይትና ራያ ግዛት ድፍን የትግራይ ሕዝብን በጦርነት አረር ማግዶ ለመጨረስ የወሰነ ይመስላል፡፡ ይህን የሚያጠናክረው ደግሞ ሰሞነኛው የክልሉ ጊዚያዊ ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ የአሜሪካ ንግግር ነው፡፡ አቶ ጌታቸው ረዳ በዚያ ንግግሩ እንዳመላከተው ህወሓት የሚደማለትና የሚቆስልልት ትግራይን ሀገር የማድረግ ዓላማ ዛሬም አልቆመም፡፡ ለዚህ ደግሞ ወልቃይትና ራያን ከአማራ መንጠቅ ግዴታ ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ እነዚህ ግዛቶችን በተመለከተ እንደጌታቸው ረዳ ንግግር በመርህ ደረጃ የፌደራል መንግሥት የቦታው ባለቤት የኾነውን ነዋሪ ሕዝብ የአርባ ዓመታት ትግልና ጥያቄ ቸል በማለት ለህወሓት አሳልፎ ሰጥቷል፡፡ ይህ የኾነው ግን በመርህ ደረጃ በመኾኑ እስካሁን ግጭት የለም፡፡ ነገር ግን ወደተግባር ከተገባ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ለማንም ግልጽ ነው፡፡
ለዚያም ነው ለተግባራዊነቱ ሁለቱ የተከዜ ተጎራባች ክልልሎች ሰሞኑን ከፍ ያለ ወታደራዊ ሥልጠናና ምልመላ ላይ የከረሙት፡፡ በትግራይ በኩል አቶ ጌታቸው ረዳ በንግግራቸው እንዳረጋገጡት በብዙ አሥር ሺዎች የሚቆጠር ሠራዊት ተዘጋጅቶ በተጠንቀቅ ቆሟል፡፡ አዲስ ምልመላም እየተካሄደ እንደሚገኝ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ በተጨማሪም ማይካድራ ላይ ጭፍጨፋ ፈጽመው ሱዳን የገቡ የህወሓት ታጣቂዎች ዳግም የሚመለሱበት ሁኔታ ላይ የክልሉ ፖለቲከኞች ሰሞኑን በተለየ መልኩ በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡ በአማራ ክልል በኩል ያለው ሁኔታም ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ክልሉ አሁን ላይ በሁሉም ዞኖቹ ብረት ያነገቡ ኃይሎች ከመንግሥት ጋር ውጊያ ላይ ይገኛሉ፡፡ ስለዚህ በህወሓት በኩል አንድ ነገር ቢሞከር ጉዳዩ ምን ያህል እንደሚከብድ ግልጽ ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የማንነት ጥያቄ ያለባቸው የራያና ወልቃይት ግዛት ሕዝብ እራሱን አደራጅቷል፡፡ ለምሳሌ ሰሞኑን በወልቃይት “የተከዜ የሰላም ዘብ ጦር” የሚሰኝ ተዋጊ ኃይል ተመሥርቶ በርካታ ቁጥር ያለው ሚሊሻና ፋኖ ተመርቋል፡፡ ይህ ምን እንደሚያሳይ ግልጽ ነው፡፡
በሌላ በኩል የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ እና የሰላምና የፀጥታ መምርያ ኃላፊ የኾኑት ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በፓርላማ “ሁለቱ ክልሎች የሚዋሰኑባቸውን አካባቢዎች በሕዝብ ውሳኔና በሕጋዊ መንገድ መፍታት አለባቸው” በሚል ስለሰጡት አስተያየት ተጠይቀው ሲመልሱ “በወልቃይት ጉዳይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔ እናደርጋለን ሲሉ በግልጽ አልሰማንም፡፡ ነገር ግን በሕጋዊ መንገድ ቢፈታ ይሻላል የሚለውን ምክር አዘል ነገር ለፓርላማው ሲናገሩ ሰምተናል፡፡ ግን በዚህኛው ቀጣና በዚህኛው ዞን ብለው ሲያነሱ እኔም በግል አልሰማሁም፣ እኛም የምናውቀው ነገርም የለም። ነገር ግን የወልቃይት ጉዳይ በየትኛው መንገድ ነው ሊፈታ የሚገባው የሚለውን ቀደም ሲል በተደጋጋሚ ተናግረናል፡፡ ራያም፣ ጠለምትም፣ ወልቃይትም ስላሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለየትኛው እንደተናገሩ ግልጽ አልሆነልኝም። በግምት መልስ ለመስጠት ያስቸግራል። ብዙ ሰው መላምት ሊኖረው ይችላል፡፡ የአገር መከላከያ ሠራዊት የወልቃይት አካባቢን እየተከላከለና እየጠበቀ እንዳለ ነው የምናውቀው።” በማለት ጉዳዩን አብራርተው አስቀምጠዋል፡፡ በተደጋጋሚ ተናገርነው ያሉት መፍትሔ ደግሞ በብዙዎች ዘንድ እንደሚታወቀው ከሕገመንግሥቱ ማዕቀፍ ውጪ በጉልበት እንደሄደ ሁሉ በጉልበት ተመልሷልና የፌድሬሽን ምክር ቤት እውቅና ይስጠው የሚል ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለትግራይ ፖለቲከኞች ከኮሶ በላይ የሚጎመዝዝ ሀቅ ነው፡፡ በጥቅሉ በእነዚህ ሁለት ክልሎች መካከል ያለውን ቅራኔ ለመቋጨት መፍትሔው በቀላሉ የሚገኝ አልኾነም፡፡ የፕሪቶሪያው ስምምነትም ቢኾን ከተስፋው ይልቅ ስጋቱ አይሏል፡፡ የመጀመሪያው የስጋት ምንጭ ደግሞ ተግባራዊ አለመደረጉ ነው፡፡ ለምሳሌ በስምምነቱ መሠረት ህወሓት ለታይታ ካደረገው የጦር መሣሪያ ርክክብ ውጭ እስካሁንም ትጥቅ አልፈታም፡፡ አልፎም ተረካከቡ የተባሉት መሣሪያዎች ከፎቶና ቪዲዮ ቀረጻው በኋላ መከላከያ ወደ መሐል ሀገር ያምጣቸው ወይም እዛው ይተዋቸው የሚታውቅ ነገር የለም፡፡ የኾኖ ኾኖ አሁንም ዳግም ይህ አስከፊ ጦርነት እንዳይከሰት ማስቆሚያው ወደየት ነው የሚለው ከባድ ኾኖ ይገኛል፡፡ ህወሓት በታሪክ እንደሚታወቀው የናየጀሪያ ቢያፍራ ግዛት አማጺያን ልቡ በእብሪትና በተንኮል የተመላ ነው፡፡ በ1960 (እ.አ.አ) በሰሜናዊ ናይጄሪያ ግዛት ቢያፍራ የሚገኙት የሃውሳ ጎሳዎች በራሳቸው ግዛት የሚኖሩትን የኢግቦ ጎሳዎች ወሰን ጥሰው እና በእብሪት ተነሳስተው መጨፍጨፍ ጀመሩ፡፡ ከሞት የተረፉት እና በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ኢግቦዎች በምሥራቁ የሀገሪቱ ጫፍ እንዲሰደዱ አደረጓቸው፡፡ ህወሓትም በእነዚህ ራያና ወልቃይት ዞኖች ውስጥ በአማራ ላይ ኢግቦዎች በናይጀሪያ ከደረሰባቸው ግፍ በላይ ለዓመታት ሲያደርስ ቆይቷል፡፡ አሁን ላይ ግን የአካባቢው ማኅበረሰብ ይህን አልፈቀደም፡፡
