
ሹፌሩን በገመድ አንቀው ጉዳት በማድረስ የቤት መኪናውን ዘርፈው ሊሰወሩ የነበሩ ሁለት ተጠርጣሪዎችን መያዙን ፖሊስ ገለፀ።
በኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ የቢራሮ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ሙሃመድ ይማም እንደገለፁት መነሻቸውን ከአፋር ክልል አዋሽ አርባ ያደረጉት ግለሰቦቹ አንድን ሹፌር መቀሌ ድርስ በኮንትራት ክፍያ ይዟቸው እንዲሂድ በመነጋገር ጉዞ በመጀመር ደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ ወረዳ ልዩ ስሙ ወርሴ ቀበሌ ሲደርሱ አሽከርካሪውን በገመድ በማነቅ መኪናውን ይዘው ሊሰወሩ ሲሞክሩ ከፌድራል ፖሊስ ጋር በመቀናጀት በቁጥጥር ስር ሊውሉ ችለዋል ብለዋል።
ኢንስፔክተር ሙሃመድ አክለውም ተጠርጣሪዎቹ በ50 ሺህ ብር ክፍያ ተነጋግርው ጉዞ በመጀመር ሹፌሩን በገመድ አንቆ በመግደል ከባድ ወንጀል ለመፈፀም ሙከራ ያደረጉ ቢሆንም አሽከርካሪው አፈትልኮ በማምለጥ ህይወቱን በማትረፉ አሁን ላይ በሙሉ ጤንነት ላይ ይገኛል ነው ያሉት።
አሁን ላይ የምርመራ ቡድን ተዋቅሮ በተጠርጣሪዎች ላይ አስፈላጊው ምርመራ እየተካሄ እንደሆነ ኢንስፔክተር ሙሃመድ ተናግረዋል ሲል የአማራ ፖሊስ ነው የዘገበው።