አቡነ ሰላማን የማያውቁ ”የአቡነ ሰላማ መንበር” አቀንቃኞች

Date:

ቀሲስ ዶ/ር መንግሥቱ ጎበዜ

“የአቡነ ሰላማን መንበር” መስርተናል የሚሉ በሃይማኖት ካባ የተሸፈኑ የጎሳ ፖለቲከኞች የሚሠሩት ሥራ አቡነ ሰላማን በፍጹም የሚወክል አይደለም። ሲጀመር አቡነ ሰላማ በቀደመው ስማቸው ቅዱስ ፍሬምናጦስ በትውልድ ሶሪያዊ (በአንዳንዶች ዘንድ ግሪካዊ) እንጅ ትግራዊ አይደሉም። በነገራችን ላይ “ትግራይ” የሚለው ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ በታሪክ በጽሑፍ ተጠቅሶ የሚገኘው (በአሁኑ የኤርትራ አካባቢ) በ10ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የአክሱም መንግሥት ካከተመ ከሦስት መቶ ዓመት በኋላ ነው። በዘመነ አክሱም የነበረውን ሁኔታ ከሚያስረዱን ወሳኝ የሆኑ የታሪክና የአርኪኦሎጂ ማስረጃዎች መካከል የአዶሊስ የሐውልት ላይ ጽሑፍ (Adulis Inscription)፣ የ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የንጉሥ ኢዛና የድንጋይ ላይ ጽሑፍ (Ezana Inscription)፣ እንዲሁም የ6ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኮስሞስ ጽሑፍ (Christian Topography of Cosmas Indicopleustes) ላይም የሌሎች ብሔረሰቦች እንጅ ትግራይ የሚባል ነገር አልተጠቀሰም። አንዳንድ የታሪክ ሊቃውንት እንደሚገልጹት ”አክሱም” የሚለው ሥርወ ቃል ራሱ ‘አኽ’ ከሚለው የአገውኛ ቃል (ትርጉሙ ውሃ ማለት ነው) እና ‘ሥዩም’ ከሚለው የግዕዝ ቃል (የተሾመ፣ ሹም እንደ ማለት ነው) በአንድ ላይ ተጠቃሎ ሲነበብም ‘የውሃ ሹም’ የሚለውን ትርጉም የሚሰጥ እንጅ ከትግርኛ ቋንቋ ጋር የሚገናኝ አይደለም። እስከ ዛሬ ድረስ በአክሱም ‘ማይ ሹም’ (የውሃ ሹም) ተብሎ የሚታወቅ ቦታ መኖሩ የስያሜውን እውነትነት ያጠናክረዋል። ለረጅም ዘመን የዋግ (ሰቆጣ) መሪዎች ‘ዋግ ሹም’ በሚል የማዕረግ ስም ይጠሩ እንደነበርም ይታወቃል። ከላስታ ነገሥታት መካከልም ሁለቱ ‘ግርማ ሥዩም’ (የንጉሥ ይምርሃነ ክርስቶስ አባት) እና ‘ዣን ሥዩም’ (የንጉሥ ላሊበላ አባት) ተብለው ይጠሩ እንደነበር ልብ ይሏል። ይህ ከሆነ አቡነ ሰላማንም ሆነ የአክሱም ዘመን ሥልጣኔ ቅርሶች የትግራይ ማኅበረሰብ ብቻ እንደሆኑ አድርጎ መግለጹ አግባብነት አይኖረውም።

በ330 ዓ.ም ተሹመው የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ጳጳስ የሆኑት ቅዱስ ፍሬምናጦስ ብርሃነ ወንጌልን በመላው ኢትዮጵያ እንዲዳረስ ታላቅ ሐዋርያዊ ተጋድሎ የፈጸሙ አባት በመሆናቸው በኢትዮጵያውያን ዘንድ አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን (የሰላም አባት፣ ብርሃን ገላጭ) ተብለው ይጠራሉ። የአሁኖቹ ”የአባ ሰላማ መንበር” አቀንቃኞች ደግሞ በተቃራኒው ለቤተ ክርስቲያን የሰላምና የይቅርታ ጥሪ ጀርባቸውን የሰጡና በቅዱስ ፓትርያርኩ ለተመራው የሰላም ልዑክ በር ዘግተው የጠፉ የጨለማ አበጋዞች ናቸው። አባ ሰላማ በአክሱም ባለ 13 መቅደስ በጽዮን ማርያም ስም የምትጠራ በሀገራችን የመጀመሪያ የሆነች ትልቅ ቤተ ክርስቲያን አሠርተዋል፤ ከአክሱም ውጭ በሌሎች የሀገራችን አካባቢዎችም በርካታ አብያተ ክርስቲያናትን አሳንጸዋል። የ”አቡነ ሰላማ መንበር” መሥራች ነን ባዮች ደግሞ እንኳን ቤተ ክርስቲያን ለመሥራት የተሠራውን ቤተ ክርስቲያን ዘግተው ቅዱስ ፓትርያርኩና የመሩት ልዑክ በአፍአ ጸሎታቸውን አድርሰው እንዲመለሱ አስገድደዋቸዋል።

አባ ሰላማ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሲኖዶስ ሕግ የኤጲስ ቆጶስ መንበር እንዲኖራትና በ350 ዓ.ም ክርስትና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሃይማኖት እንዲሆን ያስቻሉ ታላቅ መንፈሳዊ መሪ እንጅ እንደዛሬዎቹ ጠባብ ብሔርተኞች  የጎሳ ሲኖዶስና መንበር ለማቋቋም በሚያልሙ ስብስቦች ልክ የሚመዘኑ አይደሉም። አባ ሰላማ በመላ ሀገራችን ትምህርተ ክርስትና እንዲስፋፋ፤  ሥርዓተ ቤተክርስቲያን መሠረት እንዲይዝና እንዲጠናከር ያደረጉ እንዲሁም ቅዱሳት መጻሕፍትን ከልዩ ልዩ ቋንቋዎች ወደ ግዕዝ ቋንቋ የተረጎሙ (የመለሱ)  ታላቅ የሀገርና የቤተ ክርስቲያን ባለውለታ ናቸው። የአሁኑ የ”አባ ሰላማ መንበር” አቀንቃኞች ደግሞ በትግራይ ምድር ኦርቶዶክሳዊ ክርስትና እንዲዳከምና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን እንዲፈርስ በአንጻሩ ደግሞ የተሃድሶ ኑፋቄ እንዲስፋፋና የጎሳ ፖለቲካ ርእዮተ ዓለም እንዲሰለጥን እያደረጉ ያሉ የሀገርና የቤተ ክርስቲያን ዕዳዎች ናቸው።

አባ ሰላማ ለግዕዝ ፊደላችን አናባቢ በመፍጠርና ከግራ ወደ ቀኝ የመጻፍና የማንበብ ዘዴን በመጀመር ለግዕዝ ሥነ ጽሑፍ መሠረት የጣሉ ድንቅ አባት ናቸው። የዛሬዎቹ ስብስቦች ደግሞ ሁሉን ነገር ወደ ግራ ለመውሰድ የሚታትሩና  የሀገሪቱን ብሔራዊ ቋንቋ (official language) መጠቀም እንኳን ነውር አድርገውት በአደባባይ ማገዳቸውን እንደ ጀግንነት የሚቆጥሩ አስገራሚ ፍጥረቶች ናቸው።

አባ ሰላማ በመላው ኢትዮጵያ የወንጌል ትምህርት ለማዳረስና ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያንን ለመፈጸም የሚራዷቸውን ቀሳውስትንና ዲያቆናትን ሹመዋል። የእርሳቸውን ስም መጠቀሚያ ያደረጉት የአሁኖቹ ግለሰቦች ደግሞ የከበረውን የጵጵስና ሥልጣን አውርደው የጎሳ ሹመት ለመስጠት ማሰባቸው ብቻ ሳይሆን እንደ ምድራዊ የሥራ መስክ ያለ ኀፍረት መነኮሳት ለኤጲስ ቆጶስነት እንዲወዳደሩ ማስታወቂያ እስከ ማውጣት የደረሱ አንገት አስደፊዎች ናቸው።

አባ ሰላማ ነገሥታቱን አብርሃና አጽብሃን በትምህርተ ክርስትና ኮትኩቶ በማሳደግ መንፈሳዊ ፍሬ እንዲያፈሩና ምስጉን የሀገር መሪዎች እንዲሆኑ ታላቅ ሥራ ሠርተዋል። የቅዱሱ አባታችንን ስም መጠቀሚያ ያደረጉት የአሁኖቹ ስብስቦች ግን የጎሳ ፖለቲከኞች አሽከሮችና መሳሪያዎች ሁነው ሀገርና ቤተ ክርስቲያንን ለማፍረስ እንቅልፍ አጥተዋል።

ሲጠቃለል፦

በታሪክ ”የአቡነ ሰላማ መንበር” የሚባል ኑሮ አያውቅም። አቡነ ሰላማ ከሳቴ ብርሃንም  የኢትዮጵያውያን ሁሉና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ አባት እንጅ በጎሳ ስም የተደራጀና በአንድ አካባቢ የታጠረ ቤተ ክህነት ወኪል አልነበሩም። በተሃድሶ መናፍቃንና በጎሳ የፖለቲካ መሪዎች ከጀርባ እንደሚዘወር የሚነገረውና ራሱን ”መንበረ ሰላማ” እያለ የሚጠራው ስብስብ ሥራው በፍጹም አቡነ ሰላማ ከሳቴ ብርሃንን የሚወክል ቀርቶ  ስማቸውን ለመጥራት የሚገባው አይደለም። እዚህ ላይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “አባታችን አብርሃም ነው” እያሉ ያስቸግሩ ለነበሩ ተመጻዳቂዎች ”የአብርሃም ልጆች ብትሆኑ የአብርሃምን ሥራ ባደረጋችሁ ነበር” (ዮሐንስ 8፥ 39) ያለውን ለእነዚህ በታላቁና በቅዱሱ አባት በአቡነ ሰላማ ስም ለሚነግዱ ለዘመናችን ጸሓፍት ፈሪሳውያን  መጥቀሱ አግባብነት ይኖረዋል።

በነገራችን ላይ ታሪክ እንጥቀስ ካልን በአክሱምና አካባቢው ያሉ ጥንታዊ ቅርሶች የአንድ ብሔረሰብ ማንነቶች፣  የሥራና የባሕል ውጤቶች  እንዳልሆኑ እንረዳለን።  ለዚህ ደግሞ ከአባ ሰላማ ጋር በተያያዘ አስቀድመን ከጠቀስናቸው ሀገራዊ ሀብቶች በተጨማሪ ሌሎች በርካታ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል። ከምሥራቁ የሮማ አስተዳደር ወይንም ከቢዛንታይን ግዛት በሃይማኖታቸው ምክንያት ወደ ሀገራችን ተሰደው የመጡት ዘጠኙ ቅዱሳን ቅዱሳት መጽሐፍትን ከውጭ ቋንቋዎች ወደ ግዕዝ የመለሱ (የተረጎሙ) እና በአክሱምና አካባቢው በርካታ ገዳማትን የመሠረቱ ናቸው። ለምሳሌ በዓለማችን በጥንታዊነቱ የሚታወቀው የ6ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የአባ ገሪማ ወንጌል ከዘጠኙ ቅዱሳን አንዱ በሆኑት በአባ ገሪማ ገዳም የሚገኝ ሲሆን ለሀገራችን የመጀመሪያው ገዳም የሆነው ደብረ ዳሞ ከዘጠኙ ቅዱሳን አንዱ በሆኑት አቡነ አረጋዊ (በውጭ ስማቸው ሚካኤል) የተመሠረተ ነው።

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

አባቴ ለእኔ አባት ብቻ አልነበረም፤ ለእናቴ ታማኝ ባል፣ ለሁላችንም ደግሞ የደስታ ምንጭ ነበር

"አባዬ… ዛሬ ላለሁበት ማንነት መሰረት የሆንከኝ አንተ ነህ!" ​የአርቲስት...

የአንበሶቹ ትንሳኤ፦ የዳካር እንባ እና የቴራንጋ ድል

​በዳካር ሰማይ ስር ዛሬ ጨረቃ አልወጣችም፤ ይልቁንም በሚሊዮን የሚቆጠሩ...

የጥምቀት በዓል በመላ ሀገሪቱ በድምቀት እየተከበረ ነው

የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እና በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት...

“ሎዛ ዘፀአት”እና “የሎዛ ድርሳናት”ተከታታይ ረጅም ልቦለድ መጻሕፍት ተመረቁ

በጋዜጠኛና ደራሲ መርዕድ እስጢፋኖስ የተጻፉት ሎዛ ዘፀአት(2014 ዓ.ም) እና...