“አትሌት ኃይሌ ለፕሮግራሙ ከፍ ያለ አስተዋፅኦ አደርጓል ” ‹‹አስቴር አወቀ 15 ዘፈኖችን በአንዴ ትጫወታለች››

Date:

ወንድወሰን ከበደ (ጋዜጠኛና መድረክ መሪ)

አሁን ላይ ኑሮውንና ተቀማጭነቱን በሃገረ አሜሪካ ያደረገው ጋዜጠኛ እና የመድረክ መሪ ወንድወሰን ከበደ፣ ከወራቶች በፊት በርካታ ከያኒያንና የጥበብ ወዳጆቹ በተገኙበት ይህንን ሳቢ በሆነ ይዘትና ቅርጽ ያዘጋጀውን መጽሐፍ አስመርቆ ለንባብ አብቅቷል፡፡

ስለመጽሐፉ፣ ስለወርቃማው የመድረክ ሕይወቱና ትውስታዎቹ ከግዮን መጽሔት ጋዜጠኛ ፍቃዱ ማኅተመወርቅ ጋር የሚከተለውን ቆይታ አድርጓል፡፡ መልካም ንባብ! የመጨረሻ ክፍል።


ግዮን፡- ከአትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ ጋር የበጎ አድራጎት ሥራ ትሠሩ ነበር ፤ ለምን ያህል ጊዜ ሠራችሁ? የነበረው ሂደትስ ምን ይመስላል? አንተ ከሄድክ በኋላስ ቆመ?


ወንደሰን፡- የጸጋዬ እሸቱ የሙዚቃ ማኅበር የሚል በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የሆነ ማኅበር አቋቁሜ ፈቃድ በወቅቱ አጠራር ከ‹‹ክልል 14›› (የዛሬው አዲስ አበባ መስተዳድር) የወሰድኩ የመጀመሪያው ሰው እኔ ነኝ፡፡


ከዚያ በኋላ የጸጋዬ እሸቱ የወዳጆች ማኅበርን አንድ ዓመት ለማክበር አስቤ ትልልቅ አርቲስቶችን ጋብዤ ለየት ያለ ፕሮግራም የማዘጋጀት እቅድ ነበረኝ፡፡ ነገር ግን ይህን ከማደርግ አጋዥ አልባ ወገኖቻችን በየመንገዱ የወደቁትን ልርዳ በሚል አዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም ሄጄ አስፈቀድኩ፡፡ የፈቀዱልኝ የወቅቱ የመረብ ኳስ ተጫዋችና ኃላፊ አሁን በቦስተን አሜሪካ የሚኖሩት ጋሽ አቤ ናቸው፡፡


ከዚያ በኋላ በፕሮግራሙ የክብር እንግድነት አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ እንዲገኝ ጠየቅኩት፡፡ ኃይሌም ባዶ እጄን አልመጣም በሚል ለፕሮግራሙ ከፍ ያለ አስተዋፅኦ አደረገ፡፡ ከዚያም በኋላ በየጊዜው ያንን እያሳደግነው ሄድን፡፡ የመጀመሪያው የፋሲካ ጊዜ ነበር፣ ቀጥሎ ደግሞ ለገና በዓል አደረግነው፡፡ ሦስተኛው ፕሮግራም ደግሞ በዘመን መለወጫ ላይ አደረግነው፡፡


ያን ግዜ የክርስቲያን በጎ አድራጎት ድርጅት ፕሬዝዳንት ዶ/ር ከበደ አስራት፣ ወይዘሮ ባዝግ ወ/መድህን ትልቅ ድጋፍ አደረጉልን፡፡ በወቅቱ ዐሥር ሺህ ለሚጠጉ ለጎዳና ተዳዳሪዎች ምሳ አበላን፡፡ ከመካከላቸው መርጠንም 150 ለሚሆኑ መተዳደሪያ ይሆናቸው ዘንድ የሊስትሮ ዕቃ ገዛን፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ለሚማሩት ሙሉ የአንድ ዓመት የትምህርት ቤት ደብተር፣ እርሳስና እስኪብርቶ ለገስናቸው ፤ ሁሉም የቪድዮና የፎቶ መረጃ ያለው ነው፡፡ በጸጋዬ እሸቱ ስም ነው የበጎ አድራጎት ሥራው መነሻ የሆነው፡፡ ይህ ልዩ ዝግጅት እኔ ከሀገር ከወጣሁ በኋላ አልቀጠለም፡፡


ግዮን፡- በአንድ ወቅት የጥቁር አንበሳ የሕክምና ባለሙያዎችን የተመለከተ መድረክ አዘጋጅተህ ነበር፡፡ በመድረኩ ጥላሁን ገሠሠ የተገኘው እንዴት ነው?


ወንደሰን፡- መድረኩ የተዘጋጀው ‹‹ሐኪም ሁለት ሺህ›› በሚል ነው፡፡ የጥቁር አንበሳ 50 ተመራቂ ዶክተሮች ናቸው ባለፕሮግራሞቹ፡፡ እንደሚታወቀው ጥቁር አንበሳና ሬድዮ ፋና ጎን ለጎን ያሉ ተቋማት ናቸው፡፡ እኔ እዚያ የስፖርት ጋዜጠኛ በነበርኩበት ሰዓት ከጥቁር አንበሳ ዶክተሮች ጋር እንተዋወቃለን፡፡

በወቅቱ ጥቁር አንበሳ በር ላይ አንድ ጁስ ቤት ነበረች፡፡ እዚያች ጁስ ቤት ለመጠቀም ስንሄድ ሁልግዜ ከዶክተሮች ጋር እንገናኛለን፡፡ በቴሌቭዥን ማስታወቂያ ሲተላለፍ ስለሚያዩ የፕሮግራሙ ኮሚቴዎች ያሰቡት ዝግጅት እንዳለ መጥተው ነገሩኝ፡፡ እኔም ስያሜውን ‹‹ሐኪም ሁለት ሺህ›› እንበለው ብዬ ተነጋግረን ዝግጅቱን ለማካሄድ ተስማማን፡፡ በዚህም መሠረት በዝግጅቱ ተሸላሚ አካላትን መረጥን፡፡


የመጀመሪያው አቶ ታከለ ተፈሪ የሚባሉ የመጀመሪያው የግል የቴክኒክ ትምህርት ቤት መሥራች ናቸው፡፡ ሌላኛው ፕ/ር ጀማል አብዱልቃድር ይባላሉ ፤ የልብ ስፔሻሊስት ናቸው፡፡ ሦስተኛው ሰው የወቅቱ የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት የነበሩት ዶ/ር ፍስሐ እሸቱ ናቸው፡፡

እንዲሁም ጀግናው አትሌት ኃይሌ ገ/ሥላሴና ሼህ መሐመድ አልሃሙዲንም ተሸላሚ ነበሩ፡፡ በዚህ የሽልማት ፕሮግራም ላይ ኤክስፕረስ ባንዶች እንዲገኙም አደረግን፡፡ ድምፃውያን ስንመርጥም ጋሽ መሐሙድና ጋሽ ጥላሁንን መረጥን፤ ነገር ግን ጋሽ መሐሙድ በወቅቱ ከሀገር ውጭ በመሆኑ ጋሽ ጥላሁን ገሠሠ በመድረኩ ተገኘ፡፡

የሙዚቃው ንጉስ ጥላሁን ገሠሠ ዋናው ሆኖ በሱ ሥር በርካታ ድምፃውያን በመድረኩ ተገኝተውም ነበር፡፡ ዝግጅቱ እጅግ ትልቅ ዝግጅት ነበር፡፡ የመድረክ መሪው እኔ ነበርኩ፡፡ በርካታ ድርጅቶችም ፕሮግራሙን ስፖንሰር አድርገው ነበር፡፡ በዚህም ተመራቂ ተማሪዎች በዝግጅቱ ትልቅ ገንዘብ አግኝተዋል፡፡


ግዮን፡- ፕሮግራሙን ያዘጋጁት ዶክተሮች ናቸው?


ወንደሰን፡- ፕሮግራሙን ያዘጋጀነው በጋራ ነው፡፡ ለማዘጋጀት አብዛኛውን ጊዜ የገንዘብ አቅም ይኖርና እውቀት ግን ላይኖር ይችላል፡፡ እነሱ ደግሞ በወቅቱ ገንዘቡም የመድረክ እውቀቱም አልነበራቸውም፡፡ በመሆኑም በጋራ ልናዘጋጀው ችለናል፡፡


ግዮን፡- ተሸላሚዎቹ ሁሉም በዝግጅቱ ላይ ተገኙ?


ወንደሰን፡- ከሼህ ሙሐመድ አልሃሙዲን በስተቀር አራቱም ተሸላሚዎች በመገኘታቸው ሸልመናቸዋል፡፡ ሼህ ሙሐመድ አልሃሙዲን ከሀገር ውጭ ስለነበሩ ሰላም ነርስ ኮሌጅ የእሳቸው ስለነበር ፕሬዝዳንቱን ዶ/ር አድማሱን በመላክ የተበረከተላቸውን ሽልማት ተረክበዋል፡፡


ግዮን፡- አንድ ወቅት ለሁለት ቀን የሚቆይ የአስቴር አወቀ ፕሮግራም ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ ስለዚህ ፕሮግራም ምን ትውስታ አለህ?


ወንደሰን፡- ለመጀመሪያ ጊዜ አስቴር አወቀ የመጣችው 1989 ዓ.ም ነው፡፡ ዝግጅቱም ጃን ሜዳ፣ መግቢያውም 10 ብር የነበረበት ዝግጅት ነው፡፡ ቀጥሎ የነበረው ዝግጅት ደግሞ መግቢያው 200 ብር ሆኖ ኢግዚብሽን ማዕከል ነው፡፡

በወቅቱ የሰሜን አሜሪካ ኮሚኒቲ እንዲመሠረት ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረገውና ዛሬ በሕይወት የሌለው አቶ ወንድወሰን፣ አርቲስት አበበ ባልቻ እና ሪፖርተር ጋዜጣ የዝግጅቱ ዋና አካላት ነበሩ፡፡ በወቅቱ በአስቴር ላይ አንዳንድ ያልተገቡ ነገሮች በመነሳታቸው አስቴር በሚዲያ እንዳትተዋወቅ ተደረገች፡፡ በዚህ የተነሳ ትልቅ ስፒከሮች ተዘጋጅተው ከአዲስ አበባ እስከ ናዝሬት፣ ሻሸመኔና ደብረ ዘይት ድረስ በእኔ በኩል ተቀርጸው ቅስቀሳውን አደረግን፡፡ በመድረኩም ላይ ተሳተፍኩ፡፡


አስቴርን ከኤርፖርት ስንቀበላት ትንሽዬ መኪና የድሮ ዲ ታክሲ ፈልገን ነበር የተቀበልናት፡፡ ከዚያም ከአየር መንገድ ወደ ቦሌ ሳይ ኬክ ቤት ጀርባ ወደ ጋዜጠኛ አማረ አረጋዊ ቤት ሄድን፡፡ አስቴር ስትገባ ሴቶች ልጆች የሚጫወቱትንና በቾክ የሚዘጋጀውን ‹‹ካሬ›› የሚባለውን የልጆች ጨዋታ ተጫውታ ወደ ቤት ገባች፡፡

ከዚህ ውጭ ከአስቴር አወቀ ጋር በዚህ በሰሜን አሜሪካ ትልልቅ መድረኮች ላይ አብረን ሠርተናል፡፡ በአትላንታ፣ በሎሰ አንጀለስ፣ በዋሽንግተን ብዙ ሥራዎች ሠርተናል፡፡ አስቴር እጅግ በጣም የማከብራትና የምወዳት ባለሙያ ናት፡፡


ግዮን፡- አስቴር የጃንሜዳው ዝግጅት ላይ በአንድ ጊዜ ወደ ሰባት ስምንት ዘፈን ትጫወት ነበር፡፡ ይህ አቅም አላስደነቀህም?


ወንድወሰን፡- አስቴር አሁን 15 ዘፈኖችን በአንዴ ትጫወታለች፡፡ በነገራችን ላይ በዚህ ሁኔታ እኔ ሁለት ሰዎች አውቃለሁ፡፡ አስቴርና ጋሽ መሐሙድ፡፡ ያላቸው አቅም ወደር የለውም፡፡ 8 እና 9 ዘፎችን ተጫውተው አርፈው ሲመለሱና ሲዘፍኑ ሳይ እገረማለሁ፡፡ አስቴር ይህን አቅም ያዳበረችው በየጊዜው ስፖርት ስለምትሠራ ይመስለኛል ፤ ከሌሎች አላስፈላጊ ነገሮችን እራሷን ማቀቧ የጠቀማት ይመሥለኛል፡፡


ግዮን፡- ከእጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) ጋር ትውውቃችሁ እንዴት ነበር? ከሀገር ከወጣች በኋላስ ትገናኙ ነበር?


ወንድወሰን፡- ከጂጂ ጋር ትውውቃችን ኢግዚብሽን ማዕከል ነው፡፡ በ1988 ዓ.ም ጀምሮ ነው የምንተዋወቀው ፤ ወደ ኢግዚቢሽን ማዕከል ስትመጣ በእነ ቻቺ ታደሰ ባንድ አማካኝነት ነበር፡፡ በወቅቱ ጂጂ የአስቴርን ሙዚቃዎች ትጫወት ነበር፡፡

ጂጂ ጥሩ ድምጽና ሥነ ምግባር ያላት ልጅ ነበረች፡፡ ከዚያ በኋላ ብዙም ሳትቆይ ወደ ኬንያ ሄደች፡፡ በመቀጠልም አሜሪካን ሀገር መጣች፡፡ እኔ አሜሪካ ከሔድኩ ጀምሮ በርካታ ትላልቅ መድረኮች ስመራ አላገኘኋትም፡፡ ከዚያ በኋላ እሷ በገጠማት ነገር ምክንያት ከመድረክ ራቀች፡፡


ይህ ከሆነ በኋላ የተለያየ ጊዜ እየደወልኩ አገኛት ነበር ፤ በአካልም ኒውዮርክ በመሄድ ተገናኝተናል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲሀ ግን ተገናኝተን አናውቅም፡፡ ፈጣሪ ወደ ቀደመ ጤናዋ ይመልሳት ዘንድ እመኛለሁ፡፡ አንድ ቀን ወደሚወዳት ሕዝብና መድረክ ትመለሳለች የሚል ተስፋ አለኝ፡፡ ሁሉም ሰው በየእምነቱ ጸሎት ቢያደርግላት ደስ ይለኛል፡፡


ግዮን፡- ከጀማሪነት ዘመኗ ጀምሮ አጠቃላይ ያዘፋፈን ሂደቷን እንዴት ታየው ነበር?


ወንድወሰን፡- በጣም ጎበዝ ነበረች ፤ በወቅቱ የአስቴርን ሙዚቃ ትጫወት ነበር፡፡ የብዙዬንም ትጫወት ነበር፡፡ የመድረክ አያያዟም ልዩ ነበር፡፡ ከሰውም ጋር ተግባቢ ነበረች፡፡


ግዮን፡- ሰነድ አያያዝህ እጅግ ጥንቃቄ የተሞላበት ይመስላል? ይኽን ልምድ የት ነው የቀሰምከው?


ወንድወሰን፡- ከልጅነት ጀምሮ ዶክመንቶች ላይ ጎበዝ ነበርኩ፡፡ በልጅነት የተማርኩባቸው ደብተሮችና የምስክር ወረቀቶች ዛሬም ድረስ አሉ፡፡ ለምሳሌ ሃይስኩል እያለሁ መጽሔት ላይ የማወጣቸው ጽሑፎችን እስበስብ ነበር፡፡


ኤግዚብሽን ማዕከል እያለሁም የምሠራቸውን እያንዳንዳቸውን ነገሮች ብሮሸሮችን ጨምሮ እሰንድ ነበር፡፡ ምናልባትም አንድ ወቅት ሊፈለግ ይችላል የሚል እሳቤም ነበረኝ፡፡ ከእነ አባባሉ ‹‹በቃል ያለ ይጠፋል ፤ በጽሑፍ ያለ ይወረሳል›› ይባል የለ፡፡

በወቅቱ ተሳታፊ የነበሩ ሰዎች አንድም መረጃ የላቸውም ፤ እውነት ለመናገር እያንዳንዱ ሰው እለታዊ ሂደቱን ቢሰንደው የወደፊት ታሪኩ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ የኔ ትልቅ ታሪኬ ነው፡፡ በሰማንያና ዘጠናዎቹ የነበሩ የሙዚቃ ሰዎች እነማናቸው ቢባል ብዙዎች ላያውቁ ይችላሉ፡፡ አንዳንዶች እነ ቴዲ አፍሮ እነ ሸዋንዳኝ ኃይሌ ዛሬ የመጡ ይመስላቸዋል፡፡ ነገር ግን መነሻቸው በ80ዎቹ መጨረሻ ኢግዚአብሽን ማዕከል ነው፡፡


የዛን ጊዜ የኤግዚቢሽን መግቢያው 10 ብር ነው፡፡ አንዴ መግቢያው 12 ብር ሆኖ ሕዝብ ጮሆብናል፡፡ ዛሬ ግን ስንት ብር እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በጥቅሉ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የዘመኑ ሙያተኞች ሰነድ መኖሩ ጥቅሙ በርካታ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው ኤምባሲ ሲገባ ሙሉ መረጃው አብሮ ይገባል፡፡

ማጠናከሪያ መረጃ ካስፈለገው ከዚህ መጽሐፍ መውሰድ ይቻላል፡፡ በዚህ መጽሐፍ በሕይወት የሌሉ ሰዎችም ጭምር ታሪክ ተሰንዷል፡፡ ይህ ለወዳጆቻቸው ትልቅ ማስታወሻና ታሪክ ነው፡፡ ይህ ሥራ ከ25 ዓመት በኋላ የወጣ ትልቅ ታሪክ ነው፡፡ ያን ዘመን ተመርኩዞ ምርምር ለሚያካሂድም ያግዘዋል፡፡


ግዮን፡- ለዘመናችን ወጣቶች ወንድወሰን ማነው የሚለውን ብትነግራቸው?


ወንድወሰን፡- የመድረክ መሪ፣ የፌስቲቫል አዘጋጅና ጋዜጠኛ ካልኩ ይበቃል፡፡ አጠቃላይ ነገሬን በተመለከተ ከውልደት እስከ አሁን ያለውን ሂደት የሚያሳይ የግለ ታሪክ መፅሐፍ በቅርቡ አሳትማለሁ፡፡ ስለዚህ አስቀድሜ ግለታሪኬን ላለማባከን ጥቂት ነገር ማለት እችላለሁ፡፡

ወደ አሜሪካ የመጣሁት በፈረንጆቹ 2004 ጀምሮ ነው፡፡ በ2008 በሰሜን አሜሪካ ትዳር መስርቻለሁ፡፡ የባለቤቴ ስም ኢትዮጵያ ኃይሉ ነው፡፡ አንድ ወንድና አንድ ሴት ልጆችን አፍርቻለሁ፡፡ ሴቷ ልጄ ዘንድሮ 12ኛ ክፍል ታጠናቅቃለች፡፡ ወንዱ ልጄ ደግሞ 10ኛ ክፍል ነው፡፡ ሀገሬን እወዳለሁ፡፡ ስለሁሉም ነገር እግዚአብሔር ይመስገን፡፡


ግዮን፡- በጋዜጠኛነት የት የት ነበር የሠራኸው?


ወንድወሰን፡- ቀደም ሲል በትምህርት ቤት እያለሁ በሚኒ ሚድያ ውስጥ ንፋስ ስልክ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ብዙ ከጽሑፍ ጋር የተገናኙ ነገሮችን አደርግ ነበር፡፡ ከዚያም ትምህርት ቤት ብዙ ልጆች ትልልቅ ደረጃ ደርሰዋል፡፡ ለቢቢሲ የመጀመሪያው የአማርኛ ኮርስፖንዳንት ሆኖ ይሠራ የነበረው ወሰንየለህ ኪሮስ፣ እነ ስመኝ ግዛው፣ ሙልዬ ፋንታሁን፣ አለማየሁ ዲባባ፣ የመሳሰሉት ጋዜጠኞችን ያፈራ ትምህርት ቤት ነው፡፡


ሬድዮ ላይ እኔ መሥራት የምፈልገው መዝናኛ ነበር፡፡ ነገር ግን የሠራሁት ስፖርት ላይ ነው፡፡ ስፖርት በኢትዮጵያ ሬድዮ ‹‹ዜና ፋይል›› ሲባል እኛ ጋር በሬዲዮ ፋና ደግሞ ‹‹ዜና ትንታኔ›› ይባላል፡፡ በሳምንት ሁለት ቀን ዜና ትንታኔ እገባ ነበር፡፡ አልፎ አልፎ ደግሞ መዝናኛ ላይ እስራ ነበር፡፡


ወደ አሜሪካ ከመጣሁ በኋላ ደግሞ ‹‹ልዩ ሬድዮ›› የሚባል አቋቁሜ ለ5 ዓመታት የስፖርት ዝግጅት ስሠራ ነበር፡፡ አሁን በቅርቡ ደግሞ በልዩ ሁኔታ አንድ ሥራ እየሠራን እንገኛለን፡፡ በመዝናኛው ዘርፍ በሚዲያ እየመጣን ነው፡፡ ጊዜው ሲደርስ ይፋ ይሆናል፡፡


ግዮን፡- መጽሐፉ 58 ርዕሰ ጉዳዮች አሉት ፤ የገፅ ብዛቱም 238 ነው፡፡ ቅርፁ ከመፅሐፍ ይለያል፡፡ ሰዎች ይህን መፅሐፍ ቢፈልጉ በምን መልኩ ሊያገናኙት ይችላሉ?


ወንድወሰን፡- ኢትዮጵያ ውስጥ በሁሉም መፅሐፍት ማከፋፈያዎች ይገኛል፡፡ እዚህ ሀገርም በርካቶች እየጠየቁኝ ነው፡፡ ገበያ ላይ የሚውለው ከምርቃቱ በኋላ ነው፡፡ በዚህም አማዞንን ጨምሮ በሁሉም የገበያ ማዕከላት ይገኛል፡፡ በመፅሐፉ ውስጥ ያሉት 58 ታሪኮች የየራሳቸው ገለጻ አላቸው፡፡


ግዮን፡- ኤግዚብሽን ማዕከል በነበርክበት ጊዜ ሳይሸለም በመቅረቱ የተቆጨህበት ወይም ተሸልሞ ከመጠን በላይ የተደሰትክበት ሰው አለ?


ወንድወሰን፡- ዝግጅቱ ቀጣይነት ቢኖው ኖሮ በርካቶች ቢሸለሙ ደስ ይለኝ ነበር፡፡ በተለይ ግን አሁን ላይ ሳስባቸው ለዛሬዎቹ የስፖርት ጋዜጠኞች ለሁሉም መሠረት የሆኑት ትልልቆቹ እነ ኢብራሂም ሃጂ አሊን መሸለሜ ደስ ይለኛል፡፡ ኢብራሂም ሀጂ አሊ የሬድዮ ፋና ጋዜጠኛ ነው፤ ሙዚቀኛም ነበር፡፡ እነ ደምሴ ዳምጤ፣ እነ ጎርፍነህ ይመር፣ እነ ከበደ በየነ ከወጣቶች ደግሞ እነ ሁሴንን በመሸለሜ ደስተኛ ነኝ፡፡ እነ አስራት ኃይሌን፣ እነ ሥዩም አንተነህን እውቅና በመስጠቴ እደሰታለሁ፡፡


ግዮን፡- ተሸለሚዎችህ ለምን የስፖርት ሰዎች ብቻ ሆኑ?


ወንድወሰን፡- እውነት ነው ይበልጥ ለስፖርት ስሜታዊ ነኝ መሰለኝ፡፡ ጋዜጠኞች በሙያቸው ላይ ተጠምደው ያሉ በመሆናቸው እነሱን ለማስታወስ በሚል ነው የምንሸልመው ፤ እኔ ግን በስፖርቱ ዘርፍም ምርጫዬ አትሌቲክሱ ነው፡፡ በቅርቡ አሜሪካን ሃገር ዘጠነኛው የአርአያ ሰው ሽልማት ተካሂዷል፡፡ አትሌት አሰፋ መዝገቡ ደግሞ አንደኛው ሸላሚ ነበር፡፡ እኔም መድረክ መሪ ነበርኩ፡፡


ግዮን፡- ቀረ የምትለውና ያልተነሳ ሐሳብ ካለህ? በመጨረሻም የምታስተላልፈው መልዕክትም ካለ?


ወንድወሰን፡- በርካቶቹን ነጥቦች አንስተናቸዋል፡፡ በኤግዚአቢሽን ማዕከል ስለ እኔ ሲነሳ አበበ ተካ አብሮ ይነሳል ፤ የሽልማት ሥነ ሥርዓት አብረን ነበረን፡፡ ሙሉ ጤናው ተመልሶለት በመድረክ ባየው ምኞቴ ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ያላነሳኋቸው ሰዎች ካሉ ይቅርታ እጠይቃለሁ ፤ በወቅቱ የነበሩትን ባለሙያች ግን ከልብ አመሰግናለሁ፡፡

ያለ እነሱ እርዳታ ይህ መጽሐፍ ለዚህ አይበቃም ነበር፡፡ ጸጋዬ እሸቱን እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ፡፡ በምርቃቱ ዕለት አክሱማዊት ባንድን ይዞ መጥቶ በነጻ ነው ያንን ሁሉ ያደረገው፡፡ ለዝግጅቱ መድመቅ የእሱ ሚና ከፍተኛ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ያክብርልኝ፡፡


ግዮን፡- ስለነበረን ቆይታ በአንባቢያን ስም ከልብ እናመሰግናለን፡፡

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

አርሰናል ከቦርንማውዝ በጉጉት የሚጠበቅ ጨዋታ

በ32ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መርሐ ግብር ዛሬ ቀን...

በአሜሪካ እና ኢራን ድርድር ላይ የሚነሱ አራት ቁልፍ ጥያቄ

በፓኪስታን የሚደረገው የአሜሪካ እና የኢራን ድርድር እየተጠበበፓኪስታን ነገር ግን...

መንገዳችን ረጅም፣ ጉዟችን ፈታኝ መሆኑን እናውቃለን

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል...

የተመድ ዋና ጸሐፊ ኢራን እና አሜሪካ “በቅን ልቦና” ወደ ድርድሩ እንዲገቡ ጠየቁ

የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ አሜሪካ እና ኢራን...