አቶ ገዱ በም/ቤቱ ያቆሙት ሕያው ሀውልት!

Date:

አለባቸው ደሳለኝ አበሻ (ለንደን)

‹…ከእግዚአብሔር መንግሥት በቀር የፍጡር መንግሥት ሁሉ አንዱ ከአንዱ የማይበልጥ ሥራ የለውም፡፡ ነገር ግን በምድር ላይ ኃይለኛ የሆነው መንግሥት ምንም በደል የሌለበትን የሌላውን መንግሥት ሕዝብ ለማጥፋት የሚገባው መስሎት በተነሳበት ጊዜ ተጠቂው ወገን ለመንግሥታት ማኅበር የተበደለውን የሚያቀርብበት ሰዓት ነው፡፡ እግዚአብሔር ታሪክ ለምትሰጡት ፍርድ ለመንግሥት ማኅበርም ምስክር ሆነው ይመለከታሉ…›› 

ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ

የፋሺስት ኢጣሊያን ወረራ አስመልክቶ በጄኔቭ የመንግሥታቱ ማኅበር (ሊግ ኦፍ ኔሽንስ) ሸንጎ ላይ ካደረጉት ንግግር የተወሰደ ኃይለ ቃል ነው፡፡ 

ዛሬ ይህንን ንግግር ያስታወሰኝ የአቶ ገዱ አንዳርጋቸው የምክር ቤት ውሎ ነው፡፡ እርግጥ ነው የሰው ልጅ ቢኖርም ባይኖርም በምድር ላይ አንድ ጊዜም ቢሆን ታሪክ ሰርቶ የራሱን እውነት ቋጥሮ ነፃ ሕሊና ይዞ ለዘላለም በታሪክ ፊት ሳይሸማቀቅ ይኖራል፡፡ ብቻ የትም ይሁን መቼ ታሪክ ከመቃብር በላይ ነውና አፈር ሳይለብስ እንደ ፀሐይ በጥዋት እንደ ጨረቃ በለሊት ደምቆ ይታያል፡፡ ታሪክ ይዋል ይደር እንጅ ድፍርሱ ንጋት ሲጠራ ለዛሬው ሕይወታችን ለነገው ፈራሽ ሥጋችን ምሥክርነቱን ሰጥቶ እውነት ቦታዋን ትይዛለች፡፡ ለዛሬው ብዕሬን ያስጨበጠኝ ቁጭት ይኸው ጉዳይ ነው፡፡

እንደምን ከረማችሁልኝ ወዳጆቼ፤

ትናንት በለውጡ ዋዜማ የቲም ለማን ቡድንን ተባብረው ‹‹የኦሮሞ ደም የአማራ ደም ነው›› በማለት ለውጡን ካቀጣጠሉት አንዱና ዋናው የጀርባ አጥንት ናቸው፡፡ በሁለት ጎራ የተከፈለውን የወያኔ ኢሕአዴግ የፖለቲካ ድርጅት አንገዳግደው ከጣሉት የለውጥ አርበኞች ውስጥ የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት የነበሩትና ‹‹የአማራው ጄኔራል›› በመባል በቅፅል ሥም ሲጠሩ የኖሩት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ናቸው፡፡

አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰኞ ነሐሴ 8 ቀን 2015 ዓ.ም ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ምክር ቤት ውስጥ ተገኝተው ለትውልድ የሚተላለፍ  ታሪክ ምክር ቤቱ ውስጥ ጽፈው ወጥተዋል፡፡ አብረው ታግለው በጀርባቸው ተሸክመው ቤተ መንግሥት ያስገቡትን የለውጥ ኃይል በብርቱ ወቅሰውታል፡፡  የሀገሪቱን ሀብትና ንብረት በጦርነት በማውደም  ኢትዮጵያን የምታህል ታላቅ ሀገር በጦርነት እሳት እንድትለበለብ ብሎም የኢትዮጵያ ሕዝብ  ከአንድነቱ ይልቅ መለያየትን እንዳይመርጥ በአማራ ክልል የተነሳው የጦርነት ሰደድ እሳት በአስቸኳይ መቆም አለበት ሲሉ ምክር ቤቱን አሳስበዋል፡፡

አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ንግግራቸውን በማያያዝ የሐገር መከላከያን የሚያህል ትልቅ ተቋም ከአማራ ሕዝብ ጋር ማጋጨት ‹‹ታሪካዊ ስህተት ነው›› በማለት  አቋማቸውን በግልፅ አሳውቀዋል፡፡ ‹‹መንግሥት በራሱ ክፋት እና አቅመ ቢስነት ያጣውን ቅቡልነት በመሳሪያ ኃይል ለማስመለስ መሞከር የጥፋት መንገድ ነው›› በማለት ጠንካራ ትችት አቅርበዋል፡፡ ‹‹የአማራ ሕዝብ ሲያቀርበው የቆየውን ጥያቄ የጥቂት ቡድኖች አድርጎ የመመልከት፣ ክብረ ነክ የሆኑ ፍረጃዎችን በማኅበረሰብ ላይ በማሳረፍ፣ የበለጠ ሕዝቡ እንዲቆጣ በማድረግ የበለጠ ጥፋቱን እንደሚያባብሰም›› ሥጋታቸውን ጨምረው አስረድተዋል፡፡ ‹‹መፍትሔው›› አሉ ገዱ፣ ‹‹ፖለቲካዊ መሆኑን አውቀን የትግራይ ጦርነትን የተፈታበትን መንገድ መከተል ተገቢ ነው›› ሲሉ በምሳሌነት ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም ክልሉን የሚመጥን አስተዳደር እንዲቋቋምና  ያለምንም  ጦርነት በሰላም ድርድር መጨረስ እንደሚቻል ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡ መከላከያ ኃይሉ ከአማራ ክልል በመውጣት ገበሬው ወደ ግብርናው  ወጣቱም ወደ ትምህርት ገበታው እንዲመለስ ማደረግ የመንግሥትን ቁርጠኛነት የሚጠይቅ ውሳኔ እንደኾነም እቅጩን ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን ጦርነቱን አቅልለን  ‹‹ትንሽ ታጣቂዎች›› በሚል የተሳሳተ ግምት የምናጣጥለው ሳይሆን ገበሬውና ወጣቱን ያሳተፈ ትልቅ ጦርነት  በአማራ ክልል እየተደረገ መሆኑን ሁላችንም የምክር ቤት አባላት ልናውቅ ይገባናል በማለት አስገንዝበዋል፡፡

አቶ ገዱ መፍትሔ ያሏቸው ሐሳቦችን እየዘረዘሩ 12 ደቂቃ በፈጀው ንግግራቸው ላይ አንዳንድ ግለሰቦች ያልተገባና ሥነ ሥርአት የጣሰ ትችት በማቅረብ ሊያደናቅፏቸው ቢሞክሩም በትዕግስትና በትህትና የአማራውን ሕዝብ ብሶት በመዘርዘር ለምክር ቤቱና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ለማስረዳት ያደረጉትን ትዕግስት አለማድነቅ ንፉግነት ነው፡፡

በአንድ ውቅት ቀድማዊ ኃይለሥላሴ ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት   ወደ ጄኔቭ በመሔድ በዓለም መንግሥታት ፊት ቆመው ጦርነቱን እንዲያስቆሙላቸው ተማጽነው ነበረ፡፡ ነገር ግን  የተሰበሰቡት መንግሥታት  ብዙም ትኩረት ሳይሰጧቸው ቀርተው ሐስብቸውን እንዳይጨርሱ ከየአቅጣጫው የደረሰባቸውን ተቃውሞ አስታወሼ በመግቢያዬ ላይ ያስቀመጥኳት ታሪካዊ ጥቅስ  ያለምክንያት አይደለም፡፡ ለኔ እንደገባኝ የአቶ ገዱ አንዳርጋቸው ተማፅኖ በዚች ጥቅስ ልክ የተገለፀ ነው፡፡ ‹‹እግዚአብሔርና ታሪክ ለምትሰጡት  ፍርድ ምስክር ሆነው ይመለከታሉ›› የሚል ሕያው ቃል በአማራው ድምፅ ታትሞበታል፡፡

አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በሚሊዮን ለሚቆጠሩት የአማራ ሕዝብ ድምፅ ሆነው ያሳዩት ፅናት፣  በማንነታቸው ለተገፋትና ለተገደሉት ምስኪኖች በምክር ቤቱ ውስጥ ያቆሙላቸው ሀውልት ያስቀመጡላቸው እቅፍ አበባ ነበር፡፡ በግሌ ግን በዚያች ቅፅበት  በምክር ቤቱ  ውስጥ ይህንን ያህል የአማራ ጥላቻ እንደነበረ  አለመረዳቴ ግርምት ፈጥሮብኝ  ከራሴ ጋር እየተሟገትኩ ግማሽ ለሊት እንቅልፍ አልነተኛሁም፡፡

በነገራችን ላይ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በአማራ ክልል ደላንታ ዳውንት  የምርጫ ክልል ተወዳድረው ያሸነፉ የሕዝብ ተወካይ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ  አዋጁ ፀደቀም አልፀደቀም ብቻውን መፍትሔ ሊሆን እንደማይችል በክልሉ ያለውን እውነታ አይቶ መፍረድ ስለሚቻል ትዝብቱን ለሕዝቡ  ትችዋለሁ፡፡ እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ግን  ተመራጭ የሚሆነው  እንደሰለጠኑት ሕዝቦች  ችግሮቻችንን ጠረጴዛ ላይ አሰቀምጠን በግልፅ  መነጋገርና መግባባት ስንችል  እንደ ሐገር አብረን መቆም እንችላለን፡፡ ይህን ማድረግ ሳንችል ቀርተን  ከመሸና ፀሐይ ከጠቀለች በኋላ ብንሯሯጥ አብሮ መቀጠል ሳይሆን አብሮ ከፀሐይ ጋር መጥለቅ የማይቀርልን ምርጫ ነው፡፡ እስከ አሁን ባለመነጋገራችን ባለ መከባበራችን፣ አምናና ታቻምና የሰራናቸውን ስህተቶች ዛሬም ባልሰለጠነ የጥላቻ ፖለቲካ ዴሞክራሲውን አንሻፈነዋል፡፡

ስለሀገር ደህንነት የምናስብና የምንጨነቅ ከሆነ  በችግሮች  አፈታት የሰለጠኑ ምሁራኖቻችንና ሊቃውንት አባቶቻችንን የሐገር ሽማግሌዎቻችንን ሰብስብ አርገን ፀሐይ ሳትጠልቅብን መምከሩ  አንዱ የመፍትሔው አካል ይሆን ነበር፡፡ ነገር ግን በኛ ያለ መተሳሰብ በኛ ያለ መደማመጥ  ምክንያት  በአንድ ዓመት ውስጥ ከ1 ሚሊዮን በላይ ዜጎቻችንን በትግራይ ጦርነት  ለሞት ገብረናል፡፡ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሕዝቦችን አፈናቅለን ጎዳና ላይ ጥለናቸዋል፡፡ በኛ አለመተሳሰብና አለመስማማት ሆስፒታሎቻችንን በጦርነት አውድመን ብዙ ፈውስ ያጡ በሽታዎችን መከላከል አቅቶን  ወገኖችችንን ዓይናችን እያየ ቀብረናቸዋል፡፡ ከውጪ የሚነሱብን ጠላቶች  በጀግንነት በተጋድሎ እንደ አባቶቻችን ማሸንፍ እየቻልን እርስ በእርስ ለመተላለቅ መሳሪያ ስንወለውል ምርት ማምረት አቅቶን የተቀቀለ ስንዴና ለባጀት መደጎሚያ ገንዘብ ስንለምን ዓለም ጥሎን ሽው ብሏል፡፡

ችግሮቻችን ሁሉ በአዋጅና በዝምቻ የምናቆማችው እየመሰለን እኛ ግራ ተጋብተን ሕዝቡንም ግራ አጋብተን  ሐገር ልናፈርስ  ጫፉ ላይ ቆመናል፡፡ በተለይ የሕዝቡን መብት የሚገድቡ የረዥም ጊዜ አዋጆችን ማፅደቅ ችግሮቹን ከማወሳሰብ በዘለለ የሚሰጡን ጥቅሞች  አለመኖሩን አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ለምክር ቤቱ በግልፅ  አስረድተዋል፡፡

አቶ ገዱ አንዳርጋቸው  በአማራ ክልል  ለተከሰተው ወቅታዊ ችግሮች  መሠረታዊው ምክንያቱ የገዢው የብልጽግና መንግሥት የፖለቲካዊ አመራር ውድቀት እንደሆነ ነግረውናል፡፡ በትክክለኛ መረጃ  የተመሠረተ፣ ግልፅና ጤናማ የፖለቲካ ባህልን ማዳበር. ባለመቻላችን  እየመጣብን ያለው አደጋ መፍትሔው ጦርነት ብቻ ከሆነ ለሕዝቡም ለሐገሪቱም እስከ ወዲያኛው የሚበጅ ባለመሆኑ ፈፅሞ የጨለማ መንገድ መምረጥ የለብንም፡፡

እንደ አለመታደል ሆኖ ላለፉት ሀምሳ ዓመታት ጦርነት እያወጅን  እርስ በእርስ መገዳደላችን አልበቃን ብሎ አሁንም ጦርነቱ ቀጥሏል፡፡ እውነት እውነት እላችኋለሁ፣  እኛ ኢትዮጵያውያን ትልቅ የታሪክና  የሐገር እርግማን አለብን፡፡ ጧት ማታ በየጎዳናው ላይ የምንሰማው የሕፃናቶች ዋይታ ጥቁር ለብሰው ገመድ ታጥቀው እንደ ጎርፍ የሚፈስ የእናቶች እንባ ከመጤፍ አልቆጠርነውም፡፡  የበቁ አባቶቻችንን ምክርና ተግሳፃ አልሰማም ብለን በየገዳማቱ መቋሚያ ዘቅዝቀው በማልቀስ  ረግመውናል፡፡

ለመሆኑ ፍላጎታችን ምንድ ነው?  የአባቶቻችንን ሐውልት አፍርሰን የልብወለድ ተረት ተረት የሐሰት ትርክት ቡትቶ እየጎተትን እርስ በእርስ  መተላለቃችን ይቀጥላል፡፡ ወይንስ እንደ ሰለጠነ ሕዝብ ቁጭ ብለን ችግሮቻችንን ፈተን የሰላም ዘንባባ ቆርጠን መዘመር እንሻለን? ለመሆኑ ምርጫችን የትኛው መሆን አለበት? መቼ ነው … እንደሰው የምንፀፀተው? ለዚህ መልስ የሚሰጠኝ ወገን እፈልጋለሁ፡፡

በእውነት እንደ ሀገር ተረግመናል! እርግማን መጥፎ ነው፡፡ እርግማን የሩቅ አሉታዊነት፣ ከባድ ችግርን የሚያስከትል ጉዳት ነው፡፡ እንደኔ ግምት አሁንም አልዘገየንም፡፡ ቤታቸውን በዶዘር አፍርሰን በግፍ ሜዳ ላይ የጣልናቸው ወገኖቻችን እጆቻቸውን ወደ ሰማይ ዘርግተው እንደ ራሔል እንባቸውን እየረጩብን ነው፡፡ በእኛ ኃጢአት ልጆቻችን እየተቀጡብን ነው፡፡  በትውልድና በሀገር የሚያስከትለውን መዘዝ ደግሞ በዓይናችን እየተመለክትን ነው፡፡  ምን እናድርግ? መፍትሔው ምንድ ነው? እንደኔ ምርጫ ሌላ ማድረግ ቢያቅተን  እንደየእምነታችን ወደ ፈጣሪያችን በይቅርታ መመለስ ያስፈልገናል፡፡

አቶ ገዱ አንድርጋቸውን በምክር ቤቱ ያቀረቡት የሰላም ተማፅኖ ሰሚ ጠፍቶ በ12 ድምፀ ተአቅቦ በ16 ተቃውሞ በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል የሚል ዜና በቴሌቪዥን ሰምተናል። በእርግጥ ለክልሉ እውነተኛ ሰላም የሚያመጣ ከሆነ መልካም ነው፡፡ ግን አይመስለኝም የ60 ሚሊዮን የአማራ ሕዝብ ጥያቄ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚፈታ መስሎን ከሆነ በትክክል አማራውን አናውቅውም ማለት ነው፡፡

የአማራ ሕዝብ የሕልውና ጥያቄ  ትናንት የተነሳ ሳይሆን ለረዥም አመታት ሲንከባል የቆየ ትልልቅ አጀንዳዎችን የተሸከመ የፍትሕ ጥያቄ ነው፡፡ ፍትሕ ደግሞ እንደ እሴት ለእያንዳንዱ ሕብረተስብ የሚገባውን ወይም የእርሱ የሆነውን በመስጠት ለመኖር የወሰነ የእያንዳንዱ ግለሰብ የሞራል መርህ ነው፡፡ ፍትሕ የማኅበራዊ፣ ሥነ ምግባራዊ እና ዴሞክራሲያዊ እሴቶች አካል በመሆኑ የአቶ ገዱ አንዳርጋቸው  ሐሳብ ትክክል የሚሆነው በዚህ መሰረት ነው፡፡

እናም ገዱ አንዳርጋቸው ቃል በቃል ባይናገሩትም የአማራውን ሕዝብ ብሶት በማያድፍ ቀለም በምክር ቤቱ ዉስጥ  በቅርስነት እንዲቀመጥ ፅፈውታል፡፡ አማራው በማንነቱ መፈናቀሉን፣  የሚደርስበትን ግድያ ድብደባና ለዘመናት ያፈራውን ሐብት መዘረፉን ዘርዝረው ሁላችንንም አስለቅሰውናል፡፡  እናም ሆድ ይፍጀው፡፡ ሌላው ቢቀር  ኢሳትን የሚያህል ትልቅ የሚዲያ ተቋም በማንነት ላይ እየተፈፀመ ያለውን ግፍ ለኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት ሪፖርት በማድረጉ፣ ለአማራ ሕዝብ ወግናችዃል ተብለው ተቋሙ እንደ ተቋም እንዳይቀጥል የተሰጣቸውን ማስጠንቀቂያና ክስ ልከውልኝ  አንብቤአለሁ፡፡ በዚህ ምክንያት ጋዜጠኞቹ ለደህንነታቸው ስጋት ሲሉ ሥራቸውን እየለቀቁ መሔዳቸውን ስሰማ ልቤ በሀዘን ተሰብሯል፡፡

ኢሳትን እንደ ተቋም ለአብነት ጠቀስኩ እንጂ ከአማራ ሕዝብ ጋር በተነሳ እስጥ አገባ ለሕሊናቸው ያደሩ በርካታ ጋዜጠኞች ታፍነው እስር ቤት መወርወራቸውን ዘንግቼው አይደለም፡፡  መፍትሔው ግን እሥራት ሳይሆን  ፍትሕ ያጡትን ጋዜጠኞችና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች በአስችኳይ በይቅርታ ተፈተው የሰላሙ የመፍትሔው አካል እንዲሆኑ ማበረታት ተገቢ ነው ብየ አምናለሁ፡፡

የብልጽግና ፓርቲ  ያልተሰሩ  ብዙ ጉድለቶች እንዳሉበት በማመን በራሱ ላይ ግለሒስ በማድረግ  እስከ አሁን ድረስ ለተፈጠሩ ጥፋቶች  ኃላፊነቱን በመውሰድ ሕዝቡን ይቅርታ ጠይቆ  በተሐድሶ እርሱን መለወጥ ይኖርበታል፡፡ በማንነታቸው እየታፈሱ በሚታሰሩ ወጣቶች ላይ የተከፈተውን ዘመቻ አቁሞ ከወላጆችና ከእምነት አባቶች ጋር በመመካከር ውይይት ማድረግ የተሻለ ይመስለኛል፡፡ በዚህ ዐይነት ሁኔታ  ቶሎ ቶሎ ብለን ለችግሮቻችን  መፍትሔ ካልሰጠናቸው ጦርነቱ ያልጠበቅነውን ብሶት ወልደ መቋጫ የለለው የዘመናት ችግራችን  ሆኖ እንዳይቀጥል እሰጋለሁ፡፡ ይህንን መራራ ሐቅ የማንቀበል ከሆነ ግን  ጦር  አዝምቶ አገር አረጋጋለሁ ማለት ተመራጭ መፍትሔ ነው ብዬ  አላምንበትም፡፡ 

ወደድናቸውም  ጠላናቸውም አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንዲሁም የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሆነው የሰሩና ብዙ ተሞክሮ ያላቸው ሐገር ወዳድ አንጋፋ ፖለቲከኛ መሆናቸውን መዘንጋት የለብንም፡፡ ከዚህ ባለፈም ለኢትዮጵያን ነፃነት  በአያት በቅድመ አያቶቻችን ደምና አጥንት የተገነባችውን ሐገር  በጥቂት የጎሳ መንደርተኛ ፖለቲከኞች፣ ተሸራርፋ የተገጣጠመች አድርገው የሚሳቡ አጥፍቶ ለማጥፋት የተነሱ ዘረኞች በተነሱባት ወቅት ከመከላከያ ሰራዊቱ ጎን ወታደር ሆነው የቆሙ ናቸው፡፡

ገዱ አንዳርጋቸው በዘመናቸው ሐገራቸው የጠየቀችውን መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ የነበሩ በተግባር የተፍተኑ ስለመሆናችው የኢትዮጵያ ሕዝብ ምስክር ነው፡፡ ስለዚህ ገዱ የዘመናች አሥራት ብሔራዊ ጀግናችን ናቸውና ተመስግነው  ቢሸለሙ ተገቢ ነው፡፡ በእርግጥ ያለንበት ክፉ ዘመን እንደ ገዱ አንዳርጋቸውን ለመሳሰሉ ኢትዮጵያዊያኖች ከባድ ጊዜ ቢሆንም  በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደጋፊዎቻቸው  ከጎናቸው መቆማቸው አስደስቶኛል፡፡

በመጨረሻም ሐገርን ለማፍረስ ሲኦል ድረስ እንወርዳለን የሚሉትን ፖለቲከኞች፣ የክልል ፕሬዝዳንት፣ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችን በሚንስትርንት ማዕረግ በሥልጣን ያስቀመጠች ሐገር፣ ገዱ አንዳርጋቸውና ዮሐንስ ቧያለውን የመሳስሉ የለውጥ አርበኞች ከሥራ አግዶ ማንገላታት በሕዝብም በፈጣሪም ያስጠይቃል፡፡ ስለዚህ በአስቸኳይ ወደ ምድብ ሥራቸው ተመልሰው  ለሰላም ግንባታው የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ማድረግ ራሱን የቻለ የሰላም ድርድሩ አንዱ አካል መሆን አለበት፡፡

በመጨረሻ  ደጋግሜ የማሳስበው ጉዳይ ቢኖር ይህ ጦርነት የሁለት ወንድማማቾች ውጊያ በመሆኑ  አሸናፊም ተሸናፊም የለውም፡፡ ስለዚህ ሕዝብ ሳይጎዳና ሐገራዊ ውድመት ሳያስከትል በፊት  መንግሥት ኃይል ከመጠቀም ተቆጥቦ  ሀገራዊ ምክክር በማድረግ ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲፈታ ደጋግመን ማሳሰባችን ይቀጥላል፡፡ 

ልብ ያለው ልብ ይበል!! አበቃሁ!

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የክሪፕቶ ሥራ ፈጣሪው የ15 ዓመት እስር ተፈረደበት

የቀድሞው የክሪፕቶከረንሲ ሥራ ፈጣሪ ተሰውሯል ከተባለ 40 ቢሊየን ዶላር...

5ኛው የኢሰመኮ ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል ተካሄደ

በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አዘጋጅነት በየዓመቱ በፈረንጆቹ ታኅሣሥ...

የንግድ ሚኒስቴር 13 ምርቶችን በመነሻ ሀገር የጥራት ማረጋገጫ (PVoC) እንዲያገኙ ወሰነ

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ባወጣው አዲስ መመሪያ መሠረት፣ በሀገር...

ገዳ ባንክ ከ444 ሚሊየን ብር በላይ ትርፍ ማስመዝገቡን ገለፀ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፤ ባንኮች የተከፈለ ካፒታላቸውን በ2018 ዓ.ም...