አንደበት

Date:

“ዶምባ ሞናና” ሀሳቡ የመጣልኝ ገበያ ላይ አንዲት  ቆንጆ  ልጅ  ጎመን  እየሸጠች አይቼ ነው፡፡  ምንም አይነት ሜካፕ የላትም፣ በጣም ነው የምታምረው፤ ሦስት ጊዜ ተመላለስኩ፤ ወዲያው “ልቅና ሞናና” ብየ ዜማውን ሠራሁት፤  ወደ ጫካ ገብቼ ነበር በሞባይል ዜማውን የቀረጽኩት፡፡ “ሞኔው ሞኔው” ደግሞ ለምቀኛ ለወረኛ የተሠራ ነው፡፡ “ካስካሲምባ” ደስ ብሎህ ተጫወት ማለት ነው፤ እልሌና ማለት እልበል፤ የሀገራችን ልጆች ወደ ሀጋረችሁ ኑ ሥራን ሳንንቅ እሥራ አንድነትን ፍቅርን የሚሰብክ ሙዚቃ ነው፡፡ በርካታ ኮሌክሽን ሥራዎች ለሕዝብ አቅርቤያለሁ፡፡ ወላይትኛ እና አገወኛን አቀናጅተን አስኔ ዙምባራ ጋር የሰራነው አንዱ ተጠቃሽ ነው፡፡ ካሳሁን ታዬ፣ ሰለሞን ደምሌ እና የዋግ ህምራ የባህል ቡድን ጋር ሆነን ሱልጣን ኑሪ (ሶፊ) ያቀናበረው አልበምም አለ፤ ከዚህ ውስጥ ሁለት ዘፈኖች አሉኝ፡፡  ከአዊ ብሔሰረብ የባሕል ቡድን ጋር  ኮሌክሽን በብዛት ሠርቻለሁ፡፡”

ድምጻዊ አስማማው በለው

አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ መስከረም 26/2017 ዓ.ም                       

“የግብርና ትራንስፎርሜሽን በአጭሩ ዕውን ሆነ የሚባለው አርሶና አምርቶ ከመመገብ፣ አርሶና አምርቶ ወደ መሸጥ መሸጋገርን ትልም ስለያዘ ነው፡፡ በቁጥር ስናስቀምጠው አሁን እስከ 25 በመቶ ከሆነ ወደ ገበያ የሚወስደው ትራንስፎርሜሽን አይባልም፡፡ ትራንስፎርሜሽን የሚባለው አርስ አደሩ ከሚያመርተው 75 በመቶና ከዚያ በላይ ምርት የሚሰጥ ከሆነ ነው፡፡ አንድ አራተኛውን ለራሱ አድርጎ ሦስት አራተኛውን ለገበያ ማቅረብ ከቻለ አንድ አርሶ አደር የሸማቹንና ወደ ውጭ ገበያ የሚላከውን ፍላጎት ማርካት የሚችል አቅም ላይ ደርሰናል ማለት ነው፡፡ በንግድ ስታየው ከተቋቋመበት ጀምሮ በ20 ዓመታት ውስጥ ምርታማነትን በእጥፍ ማሳደግ ነው፡፡

ማንደፎሮ ንጉሤ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስፈጻሚ

ሪፖርተር ጋዜጣ፣ መስከረም 26/2017 ዓ.ም

“አሜሪካ የብሔር ችግር የሌለባት ሀገር ነች፡፡ ሁሉም ብሔረሰብ ጥያቄው የተመለሰበት ሀገርም ነች፡፡ ለዚያም ነው መልከዓ ምድራዊ ፌደራሊዝም አወቃቀርን የምትከተለው፡፡ የሲውዘርላንድና የቤልጂየም ጉዳይም በተለየ መንገድ የሚታይ ነው፡፡ ለምሳሌ በሲውዘርላን አራት ቋንቋዎች በሕገመንግሥታቸው ተቀባይነት አግኝተው ብሔራዊ ቋንቋ ናቸው፡፡ በተመሳሳይ በቤልጂየምም አራት ቋንቋዎች ያሉ ሲኾን ሦስቱ ቋንቋዎች ብሔራዊ ቋንቋዎች እንዲኾኑ ሕገመንግሥታቸው ይደነግጋል፡፡ ተቀባይነትም አግኝተው በሥራ ላይ ውለዋል፡፡”

ዶ/ር አየነው ብርሃኑ፣ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር

አርትስ ቲቪ፣ መስከረም 17/2017 ዓ.ም

“አክሱም ላይ ደረሰ የተባለው ጭፍጨፋ በተባለው መጠን አይደለም፡፡ እርግጥ ነው ጉዳት ደርሷል፡፡ ጉዳቱ የደረሰው ደግሞ በራሱ በህወሓት ጥፋት ነው፡፡ ጉዳቱ ለሚዲያ ፍጆታ የዋለውን ዓይነትም አይደለም፡፡ በወቅቱ የሻዕቢያ ሠራዊት በከተማዋ በሰላም እያለፈ ባለበት ሂደት ላይ ህወሓት ተኩስ ከፈተ፡፡ የሻዕቢያ ሠራዊትም የተከፈተበትን ተኩስ ለመመከት በሁሉም አቅጣጫ መተኮስ ቀጠለ፤ በዚህ ሂደትም የተጠቀሰው ጉዳት ሊደርስ ችሏል፡፡ ተኩሱ የተከፈተው በድንገት በመኾኑ የሻዕቢያ ሠራዊት የታጠቀ ያልታጠቀ ሳይል መለየት ባለመቻሉ በከተማው ፊትለፊት የታየው ሰው ሁሉ ላይ ጥቃት ሰነዘረ፡፡”

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

ሉዓላዊ ሚዲያ፣ መስከረም 25/2017 ዓ.ም

“የትግራይ ህዝብ ከቁጥር በላይ ተአምር እንዲሰራ ያደረጋቸው አንድነታቸው ነው። በህዝባዊ ኮንፈረንሱ ላይ የሚሳተፉት ሰዎች ከድጋፍ በላይ ጥያቄዎች ስላሏቸው ትልቅ ኃላፊነት ይሰጠናል። በህወሓትና በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር መካከል ምንም ዓይነት ጠብ የለም፡፡ በፓርቲያችን አመራር መካከል ያለው አለመግባባት ከኛ ጋር ይኖራል እንጂ ወደ ህዝብ አይወርድም። በፀጥታ ኃይሎች ላይ የሚደርሰው ስም ማጥፋትም እውነት አይደለም።”

አቶ ጌታቸው ረዳ፣ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት

ትግራይ ቲቪ፣ መስከረም 19/2017 ዓ.ም

“በሕይወቴ ያጋጠመኝ ትልቁ ስኬት ትዳሬ ነው፡፡ በትዳር ሕይወት ውስጥ 21 ዓመታትን አሳልፌያለሁ፡፡ በትዳር ውስጥ የሚጋጥሙ አስቸጋሪ ነገሮች ይኖራሉ፡፡ ነገር ግን መሠረቱ የተቃና ከኾነ ትዳሩ የሰመረ ይኾናል፡፡ በትዳር ውስጥ የመጀመሪያው ነገር እርስ በእራስ መኗኗር ነው፡፡ እኔም ለእሷ እሷም ለእኔ መተሳሰብና ሁሉም ነገር ከእኛ በታች ነው ብሎ ማሰብ በትዳር ውስጥ ትልቁ ነገር ነው፡፡ ሰው አስቦና አቅዶ በትዳር ውስጥ ጥፋት አይሠራም፡፡ ድክመቶች ይኖራሉ፡፡ እነርሱን መተላለፍ ደግሞ ግድ ነው፡፡ የትዳር አስፈላጊነቱ አንዱ ችግሮችን በጋራ መጋፈጥ መቻል ነው፡፡ ትዳር ፍቅርና መተማመን ላይ የተመሠረተ ሲኾን ከእግዚአብሔር ጋር አብሮ የሚሄድ በመኾኑ ማንኛውንም ችግር የማለፍ ኃይል አለው፡፡”

አርቲስት አለማየሁ ታደሰ

ኢቢኤስ ቲቪ፣ መስከረም 19/2017 ዓ.ም

“እኛ እንግዲህ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር፣ ከአመሰራረቱ ጀምሮ ችግር አለበት ብለን ነው የምናምነው። መጀመሪያ ሲቋቋም ከመርሁና ከአመሰራረቱ ጀምሮ፣ ችግር ያለበት ሆኖ ነው የሚታየኝ። ይኸውም ምንድን ነው? በማዕከላዊ መንግሥትና በህወሓት ስምምነት የተፈጠረ አስተዳደር ነው። ነገር  ግን በፕሪቶሪያው ስምምነት፣ ሁሉን-አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር ይቋቋማል ነበር የተባለው፡፡ በመጨረሻ የተመሰረተው ግን የህወሓት አስተዳደር ነው። ፓርቲዎችንና ሌሎች የማሕበረሰብ ክፍሎችን አላሳተፈም። አካታች አልነበረም። ስለዚህ ችግር አለበት። ሌላ ደግሞ፣ በአስተዳደሩ ውስጥ ሥራ አስፈጻሚ እንጂ፣ ሥራ አስፈጻሚውን የሚቆጣጠር ሌላ አካል የለም። እንደ ምክር ቤትም ሆኖ፣ ይህን የሚቆጣጠር የለም። ስለዚህ ሥራ አስፈጻሚው ብቻውን ነው እያስተዳደረ ያለው፤ እርሱን የሚቆጣጠር ምክር ቤትም ሆነ ሌላ አካል የለም። እና፣ ከጅምሩ ችግር ያለበት ሆኖ ይታየኛል።”

አቶ ገብሩ አሥራት፣ የትግራይ ክልል የቀድሞ አስተዳዳሪ

አዲስ አድማስ ጋዜጣ፣ መስከረም 11/2017 ዓ.ም

“ኢሬቻ በአንድ ቃል ወይም በአንድ ዓረፍተ ነገር ይሔ ነው ብሎ ለመግለፅ ያስቸግራል። ትርጉሙ ብዙ ነው። በዋናነት ኢሬቻ ማለት ሳር ነው። ሳር (Coqorsa) የሚባል አለ። ሳሩ በጣም ጠንካራ እና በየትኛውም አካባቢ በማንኛውም አየር ጠባይ የሚበቅል ነው። በክረምትም ሆነ በበጋ አይጠወልግም፤ ወይም አይሞትም። ደጋም ሆነ ቆላ ላይ ይገኛል። ከክረምት እስከ ክረምት ይታያል። ኢሬቻ ለማክበር የሚኬደው ጫፉ ያልተቆረጠ ይህንን ሳር በመያዝ ነው። ይህ የሙሉነት ምልክት ነው። ከጨለማ ወደ ብርሃን መውጣትን፤ ምስጋና እና ጥጋብን ያመለክታል። የሰላም እና የእርቅም ምልክት ነው።ኢሬቻ በአንድ ቃል ወይም በአንድ ዓረፍተ ነገር ይሔ ነው ብሎ ለመግለፅ ያስቸግራል። ትርጉሙ ብዙ ነው። በዋናነት ኢሬቻ ማለት ሳር ነው። ሳር (Coqorsa) የሚባል አለ። ሳሩ በጣም ጠንካራ እና በየትኛውም አካባቢ በማንኛውም አየር ጠባይ የሚበቅል ነው።”

አቶ ሌኒን ቁጦ፣ የባሕል እና የፎክሎር መምህር እና ተመራማሪ

አዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ መስከረም 26/2017 ዓ.ም

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫ በሚያካሂድባቸው ቦታዎች ሁሉ እሳተፋለሁ

በዘንድሮው ሀገራዊ ምርጫ እንደሚሳተፍ ያስታወቀው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትህ...

በሲዳማ ክልል ከ62% በመቶ በላይ የሚታረሰው መሬት በአሲዳማነት የተጎዳ ነዉ

በኢትዮጵያ ግብርና ዘርፍ የሚታየው የምርታማነት ማነቆ በዋናነት የመሬት አሲዳማነት...

የኢትዮጵያ እዳ እና ሃብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን የሥራ ኃላፊዎች ስብሰባ ሳይገኙ ቀሩ

የመንግስት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ እዳ እና...

የኢትዮጵያ እና ሕንድ የቆየ ዲፕሎማሲዊ ግንኙነት

የኢትዮጵያ እና ሕንድ የቆየ ዲፕሎማሲዊ ግንኙነት የአፍሪካ-ሕንድ...