በአፍሪካ ስድስት ሃገራት በጤና እና ትምህርት ዘርፉ በጀት በመቀነሱ ሰራተኞች የከፋ ችግር ውስጥ መውደቃቸውን አዲስ ጥናት አመላከተ።
ጥናቱን አክሽን ኤድ የተሰኘ ግብረሰናይ ድርጅት የሰራው ሲሆን በኢትዮጵያ ፣ ጋና ፣ ኬንያ ፣ ላይቤሪያ ፣ ማላዊ እና ናይጄሪያ 600 የጤና ባለሙያዎች፣ መምህራንና የማህበረሰብ ክፍሎችን ያሳተፈ ነው ተብሏል።
በጥናቱ ከተሳተፉት መሃል 97 በመቶ የሚሆኑት የጤና ባለሙያዎች የሚያገኙት ደሞዝ መሰረታዊ የሚባለውን ወጪያቸውን ለመሸፈን እንደማያስችላቸው ተናግረዋል።
በተጨማሪ 87 በመቶ የሚሆኑት መምህራን የማስተማሪያ ቁሳቁሶች እንዳልተሟሉላቸው ሲገልፁ፥ 73 በመቶ ያህሉ የትምህርት ማስተማሪያ ቁሳቁሶችን ከኪሳቸው አውጥተው እንደሚገዙ ተናግረዋል።
የመምህራኑ ደሞዝ ባለፉት 5 አመታት ከ10 – 50 በመቶ በሚሆን መጠን የቀነሰ ሲሆን 97 በመቶ የሚሆኑት የጤና ባለሙያዎች በደሞዛቸው የቤት ኪራይ መክፈል፣ የምግብ እና ሌሎች ወጪዎችን መሸፈን እንዳልቻሉ አንስተዋል።
ለዚህ ሁሉ ቀውስ አክሽን ኤድ መንግስታት በትምህርት እና ጤና ላይ የሚያወጡት ወጪ መቀነሱ ነው ሲል ያስቀመጠ ሲሆን ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋምም (IMF) መንግስታት የመከረበት መንገድ መኮነን አለበት ሲል ገልጿል።
አይ ኤም ኤፍ መንግስታት እንደ ትምህርት እና ጤና ባሉ ልማቶች ላይ የሚያወጡትን ወጪ በመቀነስ ዕዳቸውን እንዲከፍሉ ይመክራል ያለው አጥኚው ተቋም፥ በማሳያነት በናይጄሪያ በ2024 ከሃገራዊ ገቢዋ 4 በመቶ ያህሉን ለጤና ስታውል 20 በመቶ ያህሉን ዕዳ ለመክፈል አውላለች ነው ያለው።
በጥናቱ በ6ቱ ሀገራት የሚገኙ የጤና ተቋማት ተገልጋዮች በሃኪሞች እጥረት እና በዋጋ መጨመር ደስተኛ አይደሉም ሲል ያስቀመጠ ሲሆን መንግስታት ውጤት አልባ ከሆነ የIMF የበጀት መቀነስና ዕዳ መክፈል ፖሊሲ ወጥተው ትኩረታቸውን ዜጎቻቸው ላይ ማድረግ አለባቸው ብሏል።
በሽተኞች ወደ ጤና ተቋማት ለመሄድ ረጅም መንገዶችን እንደሚጓዙ፤ የወባ መድኃኒትም በ10 እጥፍ ዋጋው መጨመሩ በጥናቱ የተካተተ ነው።
ለአብነትም በኢትዮጵያ ሙያከላ ቀበሌ የምትኖር ሴትን በመጥበስ ከ5 አመት በፊት የወባ መድሃኒት በ50 ብር ትገዛ እንደነበር እና አሁን ግን ከግል ተቋማት በ500 ብር እንደሚገዛ መናገሯን ያነሳል።
በጥናቱ 87 በመቶ መምህራን መሰረታዊ የሚባሉ የክፍል ውስጥ ቁሳቁሶች እንደማይሟሉላቸው እንዲሁም 84 በመቶ መምህራን ከገቢያቸው ከ10 – 50 በመቶ እንደቀነሰ ተናግረዋል።
በተለምዶ አንድ ሃገር የበጀቷን አንድ አምስተኛ ለትምህርት ማዋል አለባት ቢባልም በጥናቱ ከተካተቱት ስድስት ሃገራት ውስጥ አራቱ የትምህርት በጀታቸው ከዚህ መጠን በታች ነው።
አክሽን ኤድ መንግስታት እና IMF እየሄዱ ያሉበትን መንገድ በመቀየር ለነዚህ ዘርፎች ትኩረት በመስጠት የሰራተኞቹን ኑሮ እንዲያሻሽሉ እና ዜጎችም ጥራት ያለው ትምህርት እና የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ እንዲያደርጉ ምክረ ሃሳብ አቅርቧል።
@tikvahethmagazine
