የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ ግዙፉ የጥገና ማዕከል ከመሆን ባለፈ፣ ለዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ኢንዱስትሪ ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ግብዓቶችን ወደ ማምረት መሸጋገሩን አበሰረ።
አየር መንገዱ በአዲስ አበባ ባካሄደው ዓለም አቀፍ የጥገና እና እድሳት (MRO) ኮንፈረንስ ላይ እንደገለጸው፣ ለአውሮፕላን በረራ መቆጣጠሪያ የሚያገለግሉ ‘RF ኬብሎችን’ እና ሌሎች መለዋወጫዎችን በማምረት ለታዋቂው የቦይንግ ኩባንያ ማቅረብ ጀምሯል።
ይህ ስኬት አየር መንገዱ ከአገልግሎት ሰጪነት ወደ ኢንዱስትሪ መሪነት የተሸጋገረበት ታሪካዊ ምዕራፍ ሲሆን፣ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ የአየር መንገድ ግብዓት አምራቾች መዝገብ ውስጥ አስፍሯታል።
ከ40 በላይ የአፍሪካ ሀገራትና ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በተሳተፉበት በዚህ የሶስት ቀናት መድረክ ላይ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው እንደተናገሩት፣ አየር መንገዱ በአሁኑ ወቅት ሁሉንም የአውሮፕላን አይነቶች በራሱ አቅም መጠገን የሚችል በአህጉሪቱ ብቸኛው ተቋም ነው።
አየር መንገዱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተውን የጥገና ግብዓቶች እጥረት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም፣ ለአፍሪካና ለመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት በሚሰጠው የጥገና አገልግሎት በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ገቢ እያስገኘ ይገኛል።
ይህም ተቋሙ ከአህጉራዊ ተወዳዳሪነት አልፎ ከዓለም አቀፍ ግዙፍ ድርጅቶች ጋር የሚፎካከርበት ደረጃ ላይ መድረሱን ያሳያል።
