ናይጄሪያን ከ150 በላይ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች ጋር አገናኝቷል
በአፍሪካ ግንባር ቀደሙ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከጥቅምት 18 ጀምሮ ከአቡጃ ወደ አዲስ አበባ ተጨማሪ ሦስት ሳምንታዊ የምሽት በረራዎችን በማስጀመር አጠቃላይ ቁጥሩን 34 ማድረሱን አስታወቀ፡፡
በናይጄሪያ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሥራ አስኪያጅ ፍሬህይወት መኮንን፤ “ናይጄሪያን ከ150 በላይ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች ጋር አገናኝተናል። ለዚህም ኤርባስ ኤ350-1000 እና ቦይንግ 787 ድሪምላይነርን ጨምሮ በዓለም ላይ ካሉት እጅግ ዘመናዊና አዳዲስ አውሮፕላኖች መካከል ቀዳሚዎቹን ተጠቅመናል” ሲሉ ተናግረዋል።
አየር መንገዱ አሁን ላይ ወደ ሌጎስ ሁለት ዕለታዊና 14 ሳምንታዊ በረራ እንዲሁም ወደ አቡጃ 10 ሳምንታዊ በረራ ያደርጋል፡፡ በተጨማሪም ወደ እኑጉ ሶስት ሳምንታዊ በረራ፣ ወደ ካኖ ደግሞ ሰባት ሳምንታዊ በረራ እንደሚያደርግ ለማወቅ ተችሏል፡፡
