አድሮ ቃሪያ የሆነብን የትግራይ ክልል ፖለቲካ

Date:

አዳነ ጥላሁን ዳኜ (ወልድያ)

በፌደራል መንግሥቱና በትግራይ አማፂ ቡድን መካከል ፕሪቶሪያ ላይ የተደረገው የሰላም ስምምነት ስለመፈፀሙ በሰማንበት ወቅት ድርጊቱን በማመን ፈንታ የተጠራጠርን ብዙዎች ነን፡፡ በበኩሌ በግዮን መፅሔት ላይ የሰላም ስምምነቱ ጊዜ መግዥያ እንዳይሆን በሚል የሚሰማኝን ጥርጣሬ ውሱን ማጣቀሻዎችን በዋቢ መረጃነት አጣቅሼ ማቅረቤን አልዘነጋውም፡፡ አሁን ላይ እያየነው ባለው ሁኔታም የሰላም ስምምነቱ ዘላቂነት ከሥጋት የፀዳ አይደለም፡፡ 

የትግራይን ፖለቲካ ከሚከታተሉ ታዛቢዎች መካከል አንዳንዶቹ እንደሚሉት በትግራይ መሬት ሰላም እንዲሰፍን ከተፈለገ የአቶ ስብሐት ነጋ ቤተሰብ ስብስብ የሚዘውረው ሕወሓት አንድም ሙሉ በሙሉ መፍረስ፣ ያለበለዚያም በአፄ ዮሐንስ ቤተመንግሥት በቁልፍ የአመራሩ ቦታ ላይ የተቀመጠው ባለዙፋኑ የቤተሰብ ስብስብ ወደተለያየ ቦታ መበታተን አለበት ይላሉ፡፡

ሕወሓት በአቶ ስብሀት ነጋ ቤተሰብ ስብስብ ዘዋሪነት የሚንቀሳቀስ ድርጅት ስለመሆኑ እነዚህ ታዛቢዎች በዋቢነት የሚያቀርቡት  ማጣቀሻም  አንድ ወቅት በድረገፅ የተለቀቀን መረጃ ነው፡፡  በዚያ መረጃ ላይ የተለቀቀው የቤተስብ ዝርዝር ሲታይ  በወሳኙ የሕወሓት ቁልፍ ሥልጣን ላይ የተቀመጡት አይነኬ የትግራይ ባለሥልጣናት ውስጥ፡-

  • ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካዔል የአቦይ ስብሃት የእህት ልጅ፤
  • ወ/ሮ ቅዱሳን ነጋ የአቶ ስብሃት እህት፤
  • አቶ ፀጋየ በርሄ የአቶ ስብሃት ነጋ እህት ባል፤
  • ዶ/ር አብርሃም ተከስተ የአቶ ስብሃት ነጋ ልጅ ባል፤
  • አቶ ዓለምሰገድ ገ/ዋህድ የአቶ ስብሃት ነጋ እህት ልጅ ባል፤
  • ፕሮፌሰር ክንዳያ የአቶ ስብሃት ነጋ የወንድም ልጅ ባል፤
  • ወ/ሮ ፈትለወረቅ ገ/እግዚአብሔር (ሞንጀሪኖ) የአቶ ስብሃት ነጋ ወንድም ልጅ፤
  • አቶ ዳዊት ገ/እግዚአብሔር የአቶ ስብሃት ነጋ  ወንድም ልጅ (የሞንጀሪኖ ወንድም)፤
  • አቶ ዐባይ ፀሐየ የአቶ ስብሃት ነጋ  ወንድም ልጅ ባል (በሕይወት የሌሉ)፤
  • ዶ/ር አርከበ እቁባይ የአቶ ስብሃት ነጋ ወንድም ልጅ ባል፤
  • ዶ/ር አዲስዓለም ባሊማ የአቶ ስብሃት ነጋ  እህት ልጅ ባል፤
  • አቶ ጌታቸው አሰፋ የአቶ ስብሃት ነጋእህት ልጅ ባል እንደሆኑ ይዘረዝራል፡፡

ድረገፁ ያቀረበው ከላይ የተዘረዘረው ቤተሰባዊ ዝርዝር እውነት ከሆነ እውነትም የትግራይ ሕዝብ በአንድ ግዙፍ ቤተሰብ መረብ መታሰሩንና ይኸ የቤተሰብ ስብስብም ኢትዮጵያን ለ27 ዓመት ትግራይንም ደግሞ አሁን ጭምር በእሳት አለንጋ ሲገርፏት መቆየቱንና አሁንም እየገረፋት ስለመሆኑ እንረዳለን፡፡ በተለይ ከሰላም ስምምነቱም ወዲህ ቢሆን ይኸ ቡድን የሚመራው ፓርቲ አርፎ በመቀመጥ ፈንታ ለሌላ ዙር ጦርነት የሚገፋፋ የጦርነት ታምቡር መደለቁ የሚያስገነዝበን የሰላም ስምምነቱ ዘላቂነት አጠራጣሪ መሆኑን ነው፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቡድኑ ከፌደራል መንግሥት ጋር የጀመረው ነፋስ የማያስገባ እፍ ያለ ፍቅር የማዘናጊያ የብልጠት ዘዴ እንዳይሆን የሚጠራጠሩ ተጠራጣሪዎችም ጉዳዩን በጥርጣሬ የሚመለከቱት ቡድኑ ከዚሁ የጦርነት ከበሮ ድለቃ ባለመውጣቱ ነው፡፡

ቡድኑ አሁንም በወልቃይትና ራያ ዙሪያ የያዘው አቋም የሚያመለክተው ፈጥኖም ሆነ ዘግይቶ የጦርነት አይቀሬነትን (በተለይ ከአማራ ክልል ጋር) እንጂ የሰላምና መረጋጋቱ ተግባር መጠናከሩን አይደለም፡፡

በዚህ ላይ በሕወሓት ፍቅር የተነደፉት የምዕራብ ኃያላን ሀገራት ባለፉት ሁለት ዓመታትም ሆነ አሁን ላይ እያራመዱት ያለው የፖለቲካ አቋም ድርጅቱን ለሌላ ዙር ጦርነት የሚያነሳሳ እንጂ የሰላምን ስኬታማነት የሚያጠናክር ተግባር  አይደለም፡፡

የምዕራብ ኃያላን ሀገራት ባለፉት 2 ዓመታት ከትግራይ ሺፍታ ቡድን ጎን ቆመው ቁም ስቅላችንን ሲያሳዩን መቆየታቸው ሳያንስ አሁንም አርፈው አልተኙልንም፡፡ ለሥራ ጉዳይ ወደኢትዮጵያ በተመላለሱ ቁጥር ትግራይን ለመጎብኘት የሚሯሯጡት በሕወሓት መሣሪያነት በኢትዮጵያ ላይ ተጨማሪ የትርምስ መርዝ ለመርጨት እንጂ መቀሌን ለመጎብኜት ብርቱ ፍላጎት አድሮባቸው አይደለም፡፡

የሟቹ ጠ/ሚ/ር የአቶ መለስ ዜናዊ የቅርብ ወዳጅ እንደነበረ የሚነገርለትና በብራሰልስ ፖለቲካ ቁልፍ ሚና የነበረው የአውሮፓ ህብረት የልማት ትብብር ኮሚሽነር የነበረው ሉዊ ሜሽል  የትግራይ ሺፍታ ቡድን ዋና ደጋፊ እንጂ ስለገለልተኝነቱ ሲነገር አልሰማንም፡፡

የአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት ፕሬዚዳንቱ የሉዊ ሜሽል ልጅ ቻርለስ ሜሼል በበኩሉ በውጭ ሀገራት ከሚገኙት የትግራይ ተወላጆቹ ከነአምባሳደር ብርሀነ ገ/ክርስቶስ፣ አምባሳደር ፍስሀ አስገዶም፣ ዶ/ር ሙሉጌታ ገ/ህይወት በርሄ (ጫልቱ)፣ ዶ/ር መሀሪ ታደሰና ሌሎችም ጋር እጅና ጓንት በመሆን በኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ ዘመቻ ማካሄዱ ፀሐይ የሞቀው ሀቅ ነው፡፡

የዓለም ሰላም ተቋም ከፍተኛ ተመራማሪውና በእንግሊዙ ዜና አገልግሎት (ቢቢሲ) የአፍሪካ ቀንድ ተንታኙ እንግሊዛዊዉ አሌክስ ዱዋልም ሆነ በእንግሊዝ የባህር ማዶ የጋራ ብልፅግና ሚ/ሩ ማርቲን ፕላውት የትግራይን ጦርነት ሲመሩ ከነበሩት የትግራይ ሸማቂ አዋጊዎች የሚለዩት በመልክ ነጭ በመሆናቸው ብቻ ነበር፡፡

የተዛባ ሪፖርት በማቅረቡ ከኢትዮጵያ የተባረረውና በግጭት አፈታት ዙሪያ ተንታኝ የሆነው ዊሊያም ዴቭሰንም ሆነ የኖርዌይ ተወላጁ ቮትል ሮንቮል እንዲሁም የቢቢሲ የአፍሪካ ኤዲተር ዊልሮስና ከዊልያም ደቭሰን ጋር ኢትዮጵያ ኢንሳይት (Ethiopian in sight) የሚል ድረገፅ የከፈተው ፓትሪክ ኒልክስ በጦር ሜዳ ጠመንጃ አንግበው ከመዋጋት ያልተናነሰ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ አካሂደውብናል፡፡

በዓለም ዙሪያ የገዘፈ ስም ያላቸው እንደቢቢሲ፣ ሲኤንኤን፣ ሮይተርስና ዋሺንግተን ፖስት የመሳሰሉ የብዙሀን መገናኛ የዜና አገልግሎትና ጋዜጦች ከትግራይ ሺፍታ ቡድን ጎን ቆመው የብብት ስር ተባይ ሆነው አሳር መከራችንን አሳይተውናል፡፡

የትግራይን አማፂ ሺፍታ ቡድን በአንቀልባ አዝሎ እሺሩሩ በማለቱና ኢትዮጵያን በክፋት ጥቁር መዝገብ ውስጥ በማስመዘገቡ ረገድ የምዕራባውያን ተፅዕኖ ፈጣሪ ባለሥልጣናትና የመብት ተሟጋች ተቋማት ብሎም ግብረሰናይ ድርጅቶች ነበሩበት አሁንም አሉበት፡፡

ከአሜሪካ ልማት ተራድኦ ጌይልስሚዝና ከሂውማን ራይትስ ወች ኬኔት ሮትስ ፣እንዲሁም የአባማ ብሄራዊ አማካሪዋ ሱዛን ራይትስም ሆነች ሳማንታ ፓወር በትግራይ ሺፍታ ቡድን ፍቅር ልባቸው ሲነደፍ በኢትዮጵያ ዙሪያ ደግሞ አዕምሯቸው በመረረ ጥላቻ ታውሮ ነበር አሁን ላይ ላለመታወሩም አስረግጦ መናገር አይቻልም፡፡

ከነዚህ ጉምቱ ባለስልጣናት ጎን ለጎን የምዕራብ ኃያላን ሀገራትም ከትግራይ ሺፍታ ቡድን ጎን ነበር የተሰለፉት፡፡ የአሜሪካ መንግሥት ድርጊትማ ከማሳዘን አልፎ ያስተዛዝባል፡፡ በሀገራችን ውስጣዊ ፖለቲካ በእብሪት ዘው ብላ ገብታ ለትግራይ ክልል ይኸ ይፈፀም ወይም ይኸ ይሻሻል  ወዘተርፈ የሚል ትዕዛዝ እያስተላለፈች ስታምሰን ስታተረማምሰን ላየ የባይደን አስተዳደር ትግራይን በ53ኛ የአሜሪካ ግዛትነት ሊጠቀልላት አሰበ እንዴ? የሚል ጥያቄ ለማንሳት ይገደዳል፡፡

እዚህ ላይ ሊሰመርበት የሚገባው ትልቁ ቁም ነገር የአሜሪካ መንግሥት ሉዐላዊ ሀገርነታችንን ተዳፍሮ በውስጥ ጉዳያችን ገብቶ ሲፈተፍት የፌደራል መንግሥታችን ጉዳዩን በቸልታ ከመመልከት የዘለለ ቆንጠጥ የሚያደርግ ርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል አቅም ማጣቱን ነው፡፡

የትግራይ ክልል ፖለቲካ አሁንም አድሮ ቃሪያ ሆኗል፡፡ የወልቃይትና የራያ ሕዝብ የማንነት መብቴ ሊከበር ይገባል በሚል ህጋዊ ሰላማዊ ትግል እያካሄደ ባለበት በአሁኑ ወቅት የአቦይ ስብሃት ቤተሰብ የሚዘውረው የሕወሓት ቡድን ወልቃይትም ራያም የግድ የኔ አካል ናችሁ ማለቱ ሲገረመን የአሜሪካ መንግሥት በበኩሉ ወልቃይትና ራያን ለትግራይ መልሱ የሚል ገታራ አቋም መያዙ ደግሞ ከአሳዛኝነቱ አልፎ ያስተዛዝባል፡፡

ከዚህ ውጭ የፌደራል መንግሥቱም ቢሆን ለነዚህ ጊዜ ጠብቆ የሚፈነዳ የፖለቲካ ፈንጂ ለተጠመደባቸው አካባቢዎች ወሳኝ የሆነ ፈጣን ውሳኔ አለመስጠቱ ለተጨማሪ 4ኛ ዙር ጦርነት ጠመንጃ ወደመወልወሉ እንዳያስገባን ሥጋት ወጥሮ የያዘን በርካቶች ነን፡፡

በጥቅሉ የትግራይ ክልል ፖለቲካ አሁንም በጠና እንደታመመ ነው፡፡ እንኳን ኗሪው ዜጋ ከባቢው አየር ጭምር በዘረኝነት ክርፋት ተሞልቷል፡፡ በተለይ የዘረኝነት ክርፋቱ ከፖለቲከኞቹ አልፎ  መንፈሳዊ ናቸው ብለን በምናስባቸው የሀይማኖት አባቶች ላይ ተጋብቶና ተዛምቶ መታየቱ   የሚያመለክተን የዚያ ክልል ሁሉ ነገርበዘረኝነት መርዝ ስለተመረዘ ፈዋሽ ፀበል የሚያስፈልገው መሆኑን ነው፡፡

የሰሞኑ የትግራይ ክልል የተዋህዶ ቤተእምነት መሪዎች ድርጊት ፍቅርንና ይቅርባይነትን ከሚያስተምረን የክርስትና አስተምህሮ ማፈንገጡ የሚያመለክተን የተቋሙን በፖለቲከኞቹ ተፅዕኖ ስር መውደቅ ነው፡፡ ለነገሩ ሻምበል በርሄን የመሰለ ወታደራዊ መኮንን አባገብረስላሴ በሚል ስም የምንኩስና ቆብ በመጫን ለ8 ዓመታት በዋልድባ ገዳም ላይ ስለላ እንዲያካሂድ በዋልድባ ገዳም መነኮሳት ውስጥ አስርጎ ያስገባ በአቦይ ስብሃት ቤተሰብ የሚመራው ሕወሓት በለመደው ስልቱ በትግራይ የሀይማኖት ተቋማት ውስጥ ሰላይ አስርጎ አስገብቶ የትግራይን የተዋህዶ ቤተእምነት አባቶች እጅ የመጠምዘዝ ሴራ አይፈፅምም ብሎ ደፍሮ ለመናገር ይከብደኛል፡፡ በተለይ  የትግራይ ተዋህዶ ቤተእምነት መሪዎች ከመንፈሳዊነቱ ይልቅ ዘረኝነትን በሚያቀነቅነው   የፖለቲካ ገመድ ተጠልፈዋል ወደሚል መደምደሚያ የደረስነውም እኒህ አባቶች ከእናት ቤተእምነታቸው ለመነጠል ያቀረቡት ምክንያት አሳማኝነቱ ከጌሾ የቀለለ ሚዛን የሚደፋ ውሀ የማይቋጥር ስበብ በመሆኑ ነው፡፡

ለኔ እስከገባኝ ድረስ በሕወሓት ጀማሪነት ባለፉት 2 ዓመታት በሀገር ደረጃ የነበረው የጦርነት እሳት የለበለበው የትግራይን ህዝብ ብቻ ሳይሆን የአማራና የአፋርን ህዝብ ጭምር ነው፡፡ ያኔ እነጌታቸው ረዳ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲዖል ድረስ እንደሚሄዱ ሲምሉ ሲገዘቱ በነበረበት ወቅት የትግራይ የሀይማኖት አባቶች ቢያንስ የሲዖልን ጉዞ መጓዙን ሳይሆን ለመጓዝ መመኘት በራሱ የፈጣሪን ትዕዛዝ የመተላለፍ ሀጢያት ስለመሆኑ እንኳን ስለመናገራቸው ያደመጥነው ነገር የለም፡፡

ሌላው ቀርቶ ያ ሁሉ የጦርነት ጥፋት የደረሰው የአቦይ ስብሃት ቤተሰብ በሚዘውረው ሕወሓት ዕብሪትና ጦርነት ለኳሽነት መሆኑንና ሀያ ዓመት አብሯቸው ክፉና ደጉን አኗኗር ሲኖር የነበረው የመከላከያ ሠራዊት መጨፍጨፉም ሆነ ሰውን ያህል ክቡር ፍጡር በክብር የመገደል ክብር ተነፍጎት አስፋልት መንገድ ላይ በታንክ በተጨፈለቀበት ወቅት በቅርብ የነበሩት የትግራይ አባቶች ድርጊቱን በማውገዝ ፈንታ ዝምታን ነበር የመረጡት፡፡ እነዚህ አባቶች የፌደራል መንግሥቱ ወታደሮች በትግራይ ህዝብ ላይ ግፍ ፈፅሟል ብለው በቅሬታ የሚንገበገቡትን ያህል የትግራይ ሺፍታ ቡድንም በአማራና አፋር ህዝበች ላይ የፈፀመውን ዘረፋም ሆነ ከሥነሥርዓት የወጣ የብልግና ድርጊት እኩል አውግዘው ቢሆን ኖሮ ከመንፈሳዊ አባት የሚጠበቅ ትክክለኛውን የሀዋርያት ሚዛናዊ ተግባር ፈፅመዋልና እንደት ባከበርናቸው ነበር፡፡ ከዚያ ውጭ እነርሱ ብቻ ተጎጂ፣ እነርሱ ብቻ ተጠቂ ሆነው መቅረባቸው ግን ወደፊት እንኳን አብሮለ መሥራት ባንችል  በጉርብትና እሳት እንዳንጫጫር የሚገድብ የድንበር አጥር ይመስለኛል፡፡

በበኩሌ የትግራይ አባቶች ግፍ ተፈፀመብን እንደሚሉት ሁሉ እኛም በእነርሱ ወገኖች የትግራይ ሺፍቶች መቸም ቢሆን ፀፀቱ የማይደበዝዝ በርካታ ግፍ ተፈፅሞብናል፡፡ ሆኖም በዚህ አጀንዳ ዙሪያ ከዚህ በላይ መወቃቀሱ በቀጣይ ምናልባት ፈጣሪ  ልቦናቸውን ከዘረኝነትና ጥላቻ አፅድቶና ወደቀልባቸው ተመልሰው ወደአንድነት ለመምጣት የምናደርገውን ጉዞ ያደናቅፋልና ከዚህ በላይ ምንም ከማለት እቆጠባለሁ፡፡ ያ ማለት ግን የትግራይ የሀይማኖት አባቶች ኢትዮጵያን የመሰለች ሀገር ጋለሞታ በሚል ቃል ያቃለሉትንና  ያገሪቱን መሪ  የዘለፏትን፣ እንዲሁም  የአማራን ህዝብ ደግሞ ሲናገሩት አፍ የሚኮሰኩስ የስድብ ናዳ ያወረዱበትን አባ ሠረቀብርሀን የተባሉትን ሺፍታ  መነኩሴ በማውገዝ ፈንታ ለሹመት አጭተው ከአውስትራሊያ የመጥራታቸው ድፍረት ሳያንስ ቦሌ አየር ማረፊያ ላይ ታግተዋልና በአስቸኳይ ካልተለቀቁ የትግራይን ህዝብ አስተባብረን ሰላማዊ ሰልፍ እንወጣለን የሚል ማስጠንቀቂያ አዘል መግለጫ መስጠታቸው የሚያመላክተን  ከመንፈሳዊነቱና ለሰማይ ቤት ከማሰብ ይልቅ በዓለማዊነቱ ባህር እየዋኙ የምድር ቤቱ የፖለቲከኛነት በሽታ የጠናባቸው መሆኑን ነው፡፡

አባ ሠረቀብርሀን ዶ/ር ዐቢይ  በመፅሐፍ ቅዱስ መፅሐፈ ነገሥት  ቀዳማዊ ከምዕራፍ 16 ቁጥር 29 እስከ ምዕራፍ 22 ቁጥር 40 የክፋት ታሪኩ የተከተበለት አክዓብ የተባለ ጨካኝ የእስራዔል ንጉሥ ነው ሲሉት ኢትዮጵያን ደግሞ እጅግ አረመኔ ጣዖት አምላኪ የነበረችው የአክዓብ ሚስት ኤልዛቤል ናት ይሉናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ የምትሉ ትግሬዎች ካላችሁ አውግዣለሁ ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

በበኩሌ ዶ/ር ዐቢይን በቅርብ ስለማላውቃቸው አባ ሠረቀብርሀን በፈረጇቸው መጠን  እግዚአብሔርን ክዶ በእስራዔል ህዝብ ላይ ከፍተኛ በደል ያደረሰውን አክዓብን ይመስላሉ አይመስሉም ብየ መከራከር አልችልም፡፡ ኢትዮጵያ ግን መነኩሴው የጠቀሷትና የእስራዔልን ነቢያት ያስጨፈጨፈቺውን ብሎም ናቡቴ የተባለውን ቅን  እስራዔላዊ ርስቱን ለመቀማት በማሰብ በድንጋይ አስወግራ በግፍ ያሰገደለቺውን ኤልዛቤልን በግብርም በመልክም እንደማትመስል አስረግጨ እናገራለሁ፡፡

እውነት ለመናገር የአባ ሠረቀብርሀን ብልግና የተሞላበት ንግግር የጌታ ኢየሱስን መስቀል ከተሸከመ መነኩሴ ቀርቶ ከሰው ተለይቶ በረሀ ከብት እየጠበቀ ከሚኖር ከብት እረኛ የማይጠበቅ ፈሪሀ እግዚአብሔር ከራቀው ጃዊሳ ሺፍታ የሚነገር አፈዘራፍነት የተሞላበት አነጋገር ነው፡፡

እኒህ መነኩሴ በአማራ ህዝብ ላይ ያወረዱትን የስድብ ናዳ እዚህ ልዘርዝር ብል እኔ ከእርሳቸው የባስኩ ወራዳነት ይሰማኛልና በዚህ ጉዳይ ምንም ከማለት እቆጠባለሁ፡፡ እርሳቸው የተናገሩትን ያልተገራ የብልግና ስድብ ላዳመጠ ታዛቢ በአዕምሮው ቀድሞ የሚመጣበት አንድ ወቅት ዊሊያም ሸክስፒየር ‹‹Hail is empty and all devils are here!›› ያለው አባባል ነው፡፡ ጥሬ ትርጉም ‹‹ሲዖል ባዶ ነች ፤ ሰይጣናት በሙሉ በምድር ላይ እየኖሩ ነውና›› የሚል ሲሆን በኔ ግንዛቤ አባ ሠረቀብርሀንና እርሳቸውን መሰል ምድረ ሰይጣን በመሬት ላይ ስለሚርመሰመስ ሲዖል አፉን ከፍቶ እየጠበቀቸው  ነው  የሚል ትርጉም ብሰጠው የኔ ትርጉም የሸክስፒየርን አባባል ያፋልሰዋል የሚል እምነት የለኝም፡፡

እዚህ ላይ እኒሁ የአማራን ህዝብ በጠቅላላ የሰደቡ፣ ኢትዮጵያንና መሪዋን በአረመኔ ጣዖት አምላኪነት የመሰሉና የሰየሙ ከመንፈሳዊነቱ ይልቅ አጉራዘለልነቱ የጠናባቸው፣ ከምንኩስናው ብቻ ሳይሆን ከሰውኛ ክብር የወረዱም የተዋረዱም ባለጌ አፈዘራፍ መነኩሴ ሰሞኑን ወደ አዲስ አበባ ስለመምጣታቸው ስንሰማ በመንግሥት በኩል በሕግ ቁጥጥር ስር ውለው ለሕግ ይቀርባሉ ብለን ስንጠብቅ  ወደመጡበት ሀገር ብቻ እንዲመለሱ መደረጋቸው አግባብነት ያለው ፍትሓዊ እርምጃ አለመሆኑን ጠቁሜ የተነሳሁበትን ፍሬ አጀንዳ ሳጠቃልል በአንድ በኩል መሽቶ በነጋ ቁጥር የትግራይ ክልል ፖለቲካ አድሮ ቃሪያ እየሆነ መሸገራችንና በሌላ በኩል የአሜሪካንን ድርጊት ስንመለከት ደግሞ የባይደን አስተዳደር ትግራይን 53ኛ ግዛቱ ሊያደርጋት ፈለገ እንዴ? የሚል ጥያቄ እየጠየቅን የባስ አታምጣ በሚል ፀሎት በሀገሪቱ ላይ ደልቷቸው የሚኖሩ ውሱን ኗሪዎች አኗኗሪ ሆነን ቀን እስኪያልፍ ቀን እየገፋን እንንከላወሳለን፡፡ እስከሳምንት ቸር እንሰንብት!

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

አባቴ ለእኔ አባት ብቻ አልነበረም፤ ለእናቴ ታማኝ ባል፣ ለሁላችንም ደግሞ የደስታ ምንጭ ነበር

"አባዬ… ዛሬ ላለሁበት ማንነት መሰረት የሆንከኝ አንተ ነህ!" ​የአርቲስት...

የአንበሶቹ ትንሳኤ፦ የዳካር እንባ እና የቴራንጋ ድል

​በዳካር ሰማይ ስር ዛሬ ጨረቃ አልወጣችም፤ ይልቁንም በሚሊዮን የሚቆጠሩ...

የጥምቀት በዓል በመላ ሀገሪቱ በድምቀት እየተከበረ ነው

የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እና በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት...

“ሎዛ ዘፀአት”እና “የሎዛ ድርሳናት”ተከታታይ ረጅም ልቦለድ መጻሕፍት ተመረቁ

በጋዜጠኛና ደራሲ መርዕድ እስጢፋኖስ የተጻፉት ሎዛ ዘፀአት(2014 ዓ.ም) እና...