ኢንጂነር ተረፈ ራስወርቅ ሲታወሱ

Date:

ከእዝራ እጅጉ/ተወዳጅ የሚድያ እና የኮሚኒኬሽን ማእከል    

እንደ በር መግቢያ  

 ጊዜው ግንቦት 2005 ዓ.ም  ነበር፡፡ የዛሬ 10 ዓመት መኾኑ ነው፡፡ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምሥረታ ዙርያ አንድ ሰው ቃለ-ምልልስ ማድረግ እፈልግ ነበርና ወዳጄ የሕግ ምሁሩ ጋሽ ተሾመ ገብረማርያም አንድ ሰው ጠቆሙኝ፡፡ እኒህ ሰው በጊዜው የ77 ዓመት ሰው የነበሩት፣ ኢንጂነር ተረፈ ራስወርቅ ነበሩ፡፡ ስቱዲዮ መጥተው ከ2 ሰዓት በላይ ኢንተርቪው አደረግኳቸው፡፡ እናም ቃለ-መጠይቁን አጠናቅቀን በአሳንሰር እየወረድን ሳለ አንድ ጨዋታ አነሳሁ፡፡

‹‹ኢንጂነር የሕይወት ታሪክዎ ተጽፎ ተሰንዷል ወይ?›› ስል በጥያቄ ወጌን ጀመርኩ፡፡

ኢንጂነርም በሰከነ እርጋታቸው ‹ደግሞ ምን ሰርቼ?› በሚል መንፈስ ከተመለከቱኝ በኋላ

‹‹ትንሽ ማስታወሻማ ጫር ጫር ማድረጌ አልቀረም›› አሉና መለሱልኝ፡፡

እኔም እርሳቸው የሚጻፍ ታሪክ እንዳላቸው ነግሬ ይኽን መጽሐፍ ደግሞ እኔ ልጽፈው እንደምችል አንስቼባቸው ተሰነባበትን፡፡ ከዚያም ጅምር ማስታወሻቸውን ከጥቂት ወራት በኋላ በኢሜይል ላኩልኝ፡፡ ኢንጂነር የእውነትም የሚጻፍ ታሪክ ነበራቸው፡፡ እንዳልኩትም መጽሐፉን ለመጻፍ ተነሳሁ፡፡ በርካታ ቃለ-ምልልስ አደረግኩ፡፡ አንኮበር ሎጅ ለ5 ቀን አርፌ ረቂቁ ተጀመረ፡፡

6 ዓመት ቆይቶ መጽሐፉ በ2011 ዓ.ም ሲመረቅ ለእኔም ለኢንጂነርም ነገሩ ታላቅ እፎይታን አስገኘ፡፡ የሌይ አውት ዲዛይነሩ ዘሪሁን አሰፋም በታላቅ መነሳሳት የኢንጂነርን መጽሐፍ ከሽኖ አቀረበ፡፡ የዛሬ 10 ዓመት ‹‹ሀ›› ተብሎ የተጀመረው የእኔና የኢንጂነር ተረፈ ራስወርቅ ግንኙነት ሕይወታቸው እስካለፈበት እስከ ሚያዝያ 30 ቀን 2014 ዓ.ም ዘለቀ፡፡ አንድ ተብሎ የተጀመረው የእኔና የኢንጂነር ግንኙነት አድጎ ባለቤታቸው ወይዘሮ ብርሃኔ አስፋውም እንደ አንድ የቤተሰባቸው  አባል ቆጠሩኝ፡፡ ልጆቻቸው  አንድነት፣ ኢዛና እና መላዬም የቤተሰቡ ታሪክ ዘጋቢ እንድሆን እድሉን ሰጡኝ፡፡ የዛሬ ሳምንት ቅዳሜ ግንቦት 5 ቀን 2015 ዓ.ም በሳይንስ ሙዚየም የተዘጋጀውን የኢንጂነር ተረፈ ራስወርቅን የ1ኛ ዓመት ማስታወሻ እንዳዘጋጅ ያቀረብኩትን ሐሳብ ተቀብለው ግንቦት 5 ቀን 2015 ዓ.ም ኢንጂነርን አስታወስን፡፡ ከኢንጂነር ተረፈ የሕይወት ታሪክ መጽሐፍ የተወሰኑ ነጥቦችን እያነሳሁ ያልተነገሩ ጉዳዮችንም እንካችሁ እያልኩ ማስታወሻ መከተቤን ልቀጥል፡-

ውልደትና የቤተሰብ ጉዳይ

ኢንጂነር ተረፈ ራስ ወርቅ መጋቢት 2 ቀን 1928 ዓ.ም አንኮበር ውስጥ በምትገኝ አፈርባይኔ በምትባል መንደር ከአባታቸው ከመምህር ራስ ወርቅ ወልደ መስቀል ማንአውቆ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ አስካለ ማርያም ገ/ጊዮርጊስ ንጉሤ ተወለዱ።          

ኢንጂነር ስለ አባታቸው ሲያጫውቱኝ እንዲህ አሉ ‹‹…አባቴ መምህር ራስ ወርቅ ከአባ ወልደ መስቀል ማናውቆና ከእመት አጫወቱኝ መስከረም 14 ቀን 1879 ዓ.ም በጅሩ ቆላ ሺማ ወረዳ ተወልደው በጥቅምት 7 ቀን 1954 ዓ.ም አዲስ አበባ ላይ አረፉ። የማናውቆ አባት አለቃ ወልደ ሥላሴ በሸዋው ንጉሥ ሳህለሥላሴ የተመሠረተውን የአፈርባይኔ ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን የመጀመሪያው አስተዳዳሪ ነበሩ።›› ብለውኝ ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ የኢንጂነርን ትረካ ላስከትል፡፡

የአባቴ የሥራ ዘመን

አባቴ ከእስክንድርያ ከመጡት አፄ ምኒልክን መጀመሪያ አንኮበር ላይ በንጉሥነት፣ ከዚያም እንጦጦ ላይ በንጉሠ ነገሥትነት ከቀቡት ከአቡነ ማቴዎስ የድቁና፣ ከዚያም የቅስና ማዕረግ ተቀብለዋል። ታዋቂ መምህርም ነበሩ፡፡

በዚሁ በማስተማር ሥራቸው ላይ ፋሽሰት ጣሊያን ሀገራችንን እስከ ወረረችበት እስከ 1928 ዓ.ም ድረስ ቆይተዋል። በዚያን ዘመን አባቴ ካስተማሯቸው ሰዎች መካከል ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት የሃብተወልድ ቤተሰቦች፤ እነጀኔራል መንግሥቱ ንዋይን፣ የታሪክ ፀሐፊው ተክለጻዲቅ መኩሪያ ተጠቃሽ ናቸው።

አባቴ፣ ብሩህ አእምሮ ስለነበራቸው መደበኛ ትምህርት እያስተማሩ በጎን ደግሞ የፈረንሳይ ቋንቋን እንዲሁም ዘመናዊ የመጽሐፍ መጠረዝና መደጎስን ሙያ ስለቀሰሙ የኋላ ኋላ የትንሣኤ ዘጉባዔ ማተሚያ ቤትን ለማቋቋም ቻሉ፡፡

ስለእናቴ ወይዘሮ አስካለ ማርያም ገብረ ጊዮርጊስ

የእናቴ የዘር ግንድ በአባት በኩል በፊታውራሪ ገብረ ጊዮርጊስ ከቀም ቀም ቃሮዳ ከጎንደር ሲመዘዝ፣ በእናት በኩል ደግሞ ከጅሩ ሸዋ ጠቅላይ ግዛት ተወላጅ ናቸው። በሐምሌ 16 ቀን 1883 ዓ.ም ተወልደው በሐምሌ 25 ቀን 1969 ዓ.ም በ86 ዓመታቸው አረፉ፡፡

የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት በተፈሪ መኮንን /ቤት (ቲኤምኤስ)

‹‹ሀሁ የቆጠርኩት አንኮበር አባቴ ጉያ ቁጭ ብየ ነበር።›› ሲሉ ኢንጂነር 80 ዓመት ወደኋላ ተጉዘው አጫውተውኛል፡፡ አባታቸው እንደ አስተማሪ በጣም ኃይለኛ ነበሩ፡፡ ልጃቸው ተረፈ ጎበዝ ተማሪ እንዲሆን በኩርኩም ያስጠኑ ነበር፡፡

የጠላት ጦር እንደወጣ በ1933 ዓ.ም የኢንጂነር ቤተሰብ ወደአዲስ አበባ ተመለሰ። ታዳጊው ተረፈም በአንድ የቄስ ትምህርት ቤት መምሬ ሞገስ ዘንድ ገባና ዳዊትን ደገመ። ከዚያም ለአንድ ዓመት ዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ተላከና የአንደኛ ክፍሉን አጠናቅቆ ወደ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ተዛወረ።

‹‹ተፈሪ መኮንን በጣም ወደድኩት። ቤታችንና ትምህርት ቤቱን አጥር ነበር የሚለየው። በዘመኑ በአገሩ ውስጥ ትልቅ ከሚባሉት ትምህርት ቤቶች አንዱ ነበር። ካንድ ሺህ ተማሪዎች በላይ ነበሩት። የንጉሠ ነገሥቱ ቤተ መንግሥት ቅርብ ስለነበር ጃንሆይ በየጊዜው ይጎበኙን ነበር። ይህም ዘወትራዊ ጉብኝት ተማሪዎቹንና መምህራኑን ያስድስታቸውና ያበረታታቸው ነበር።›› ሲሉ ኢንጂነር የተፈሪ መኮንን ትዝታቸውን አውግተውኝ ነበር፡፡ የኮሌጅ ሕይወታቸውን ደግሞ ዳግም በጣፋጭ አንደበታቸው ይተርካሉ፡፡

የአዲስ አበባ የኒቨርሲቲ ኮሌጅ ኑሮና ትምህርት

በመስከረም ወር 1947 ዓ.ም የዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ደጅን እግሮቼ ረገጡት። ሥሜን በሳይንስ ክፍል ሳስመዘግብ ‹‹ልጁ ሁሉ አብደሃል ወይ?›› ብሎ ታዘበኝ። ምክንያቱም ከተፈሪ መኮንን የሚመጡ ልጆች እንደሌሎቹ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ንጹህ ኬሚስትሪና ንጹህ ፊዚክስ በመውሰድ ፈንታ ጠቅላላ ሳይንስ ስለሚማሩ የኮሌጅ ሳይንስ ይከብዳቸዋል ይባል ስለነበረ ነው። እንደሚባለውም ብዙ የቲኤምኤስ ተማሪዎች ወደአርትስ ክፍል ይገቡና አስተማሪነት፤ ሕግ ወዘተ ለመማር ይመርጡ ነበር።

የዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ኑሮ በጣም አርኪ ነበር። የሚሰጠውም የትምህርት ዓይነትና ጥራት በጣም ጥሩ ነበር።

በወቅቱ ኮሌጁ በሳይንስ ዘርፍ ሙሉ የዲግሪ ፕሮግራም ስላልነበረው ከ3 ዓመት ትምህርት በኋላ በመንግሥት ወጪ ወደ ፈረንጅ አገር እንላክ ነበር። በዚህም መሠረት ከሌሎች ጓደኞቼ ጋር ወደ ሬንስለር ፖሊቴክኒክ ኢንስቲትዩት ወደ ትሮይ ኒውዮርክ ስቴት ተላኩ።

የሬንስለር ፖሊቴክኒክ ኢንስቲትዩትት (አርፒአይ) ትምህርትና ኑሮ

በ1950 ዓ.ም ነሐሴ ወር ኢንጂነር አዲስ አበባን ለቅቀው ወደ አሜሪካ ለመሄድ ተነሱ።

በመጀመሪያ ኢንጂነርና ጓደኛቸው ማህዲ በኤሌክትሪክ መሐንዲስነት መማሪያ ዋና ክፍል ተመዘቡ። ትምህርቱም በጣም ከባድ ሆኖ አገኙት፡፡

ኢንጂነር፣ በአንድ ወቅት ስለ አሜሪካ ትምህርታቸው ሲያወሱ እንዲህ ብለው ነበር ‹‹…ተማሪዎቹም በወዳጅነት መፍጠር በኩል ከአስተማሪዎቹ አይሻሉም። ለምሳሌ እኔ ወይም ማህዲ አንድ 300 ሰው በሚይዝ አዳራሽ ውስጥ ቀድመን አንዱ 15 ሰው በሚይዝ ረድፍ ላይ ቁጭ ስንል አዳራሹ ሞልቶ ከፊታችንም ከኋላችንም ያሉት ረድፎች ቢሞሉ እኛ ረድፍ ላይ አንድም ነጭ ተማሪ አይቀመጥም ነበር። ይህ ኹናቴ በጣም ያስጨንቅ ነበር። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ማህዲ ይህን ሁናቴ መቀበል ስላቃተው የኤሌክትሪክ መሐንዲስነት ትምህርት ክፍሉን ለቅቆ ወደጂኦሎጂ ትምህርት ክፍል ተዛወረና የበለጠ ደስተኛ ሆነ። እኔ ግን ያደረጉኝን ያርጉኝ ብዬ ጥርሴን ነክሼ ቀጠልኩ። በቀን መአት ሰዓት ጥናቴ ላይ አሳልፍ ነበር። ከሁሉም የሚከፋው የቤተ- ተሞክሮ ጊዜ ሥራ ነበር። ምክንያቱም የዚህ ዐይነት ጥናት ሁለት በሁለት ሆኖ ተመራርጦ ነበር የሚሰራው። እኔን ግን ማን መርጦኝ? ብቻዬን ስታገል አስተማሪው ሲያየኝ በዚያን ቀን ያልመጣውን ተማሪ በሚመጣ ጊዜ ከእኔ ጋር እንዲሠራ ይመድበዋል። በተባለው ቀን ተማሪው ሲመጣ እኔ ቦታው ላይ ቆሜ ሲያገኘኝ አብሮ ለመሥራት ፈቃደኛ አለመሆኑን ያላንዳች ሀፍረት ገልጾ ጥሎ ይሄድ ነበር። በዚህም ምክንያት ብቻዬን እፍጨረጨር ነበር። ምንም ያንጊዜ ብናደድና ብራገም አሁን ወደኋላ መለስ ብዬ ሳጤነው የመንፈስ ጥንካሬ ያልበገርነት ባይነት ትምህርት ሰጥቶኝ በማለፉ ተመስገን እላለሁ።›› ብለው ትዝታቸውን አውግተው ነበር፡፡

ኢንጂነር በ1952 ዓ.ም የተሰጣቸውን ክፍለ-ትምህርት ጨርሰው ዲግሪ ተቀብለው ወደ ሀገር ቤት ተመለሱ፡፡

በሃያ አምስት ዓመት እድሜ ከባድ ሃላፊነት

ኢንጂኒየር የመጀመሪያ ሥራቸውን ቴሌ እንደጀመሩ ሁሉንም ክፍሎች በሚገባ እንዲጎበኙ ነው የተደረገው። ከባሕር ማዶም እንደመጡ በሙያቸው ከፍተኛ ተሰሚነት ነበራቸው፡፡ የነበሩትን ክፍሎች ከጎበኙ በኋላ የትራንስሚሽንና የረጅም ርቀት ስርጭት ከሚባል ክፍል በኃላፊነት ተመደቡ፡፡ የ25 ዓመት ወጣት ሳሉ ቴሌ ውስጥ ትልቅ የሚባል ኃላፊነት ተሰጣቸው፡፡ የእድሜ ማነስ አንድም ተጽእኖ ሳይፈጥርባቸው ሥራቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይሞክሩ ነበር፡፡ በዛን ጊዜ የነበሩት ስዊድኖች አንድን ሰው የሚመዝኑት በእድሜው ሳይሆን በሥራ ብቃቱና በአመለካከት ብስለቱ ነው፡፡

እርሳቸው፣ ከውጭ መጥተው ቴሌ በሚሰሩበት ጊዜ የፋክስ ግንኙነት አልነበረም፡፡ አብዛኛው መልእክት ይተላለፍ የነበረው በቴሌግራፍ ነበር፡፡ ኢንጂኒየር ሁኔታውን ሲገልጹ ‹‹…በጣም የደነቀኝ የዚያን ጊዜ በኢትዮጵያ ቋንቋ የሚላክ ቴሌግራም ሁሉ በላቲን ፊደል ነበር የሚተየበው፡፡ ለምሳሌ ‘እመጣለሁ’ ለማለት ሲፈለግ emetalehu ተብሎ ነበር የሚጻፈው፡፡ ‹እንዴት የራሳችን ፊደል እያለን በላቲን ፊደል ይጻፋል› ስል ለራሴ ጥያቄ አቀረብኩ፡፡ ለምን በራሳችን ፊደል መጻፍ አልተቻለም? የሚል ጥያቄ ባነሳም አበረታች መልስ አላገኘሁም፡፡ ‘ፈጽሞ አይቻልም፤ ብዙ ሰዎች ሞክረው ትተውታል’  ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ነበር የገጠመኝ፡፡ በኋላም ኦሊቬቲ የተባለ ኩባንያ የአማርኛ ቴሌፕሪንተርን ለመስራት ሞክሮ አልቻለም ሲሉ ሌላ መረጃ አቀበሉኝ፡፡ እኔም ‘በኢትዮጵያ ፊደል ቴሌፕሪንተር’ ሊኖር አይችልም የሚባለውን ተስፋ ቢስ ዜና ልቀበለው አልቻልኩም፡፡›› ይላሉ፡፡

ቴሌፕሪንተርና – ወጣቱ ኢንጅነር ተረፈ ራስወርቅ

አሁን ወጣቱ መሃንዲስ ተረፈ የአማርኛ ቴሌፕሪንተር ለመሥራት ተነሳስቶ ምርምሩን ጀምሯል፡፡ በወቅቱ ፕሪንተሮቹ ለላቲን ፊደል ነው የተፈጠሩት የሚል ግትር መከራከሪያ ተነስቶ ነበር፡፡ እንደሚታወቀው የላቲን ፊደል 26 ነው፡፡ የአማርኛ ደግሞ 270 ነው፡፡ ታዲያ የመከራከሪያ ሐሳቡ ፕሪንተሩ ለ270 ፊደላት ቦታ የለውም የሚል ነበር፡፡

ኢንጂኒየር፣ ይህ ሃሳብ ሲነገረው ጊዜ ሰጥቶ ምርምሩን ቀጠለበት፡፡ እርሱ ያደረግው ዋናው ጥናትም የኢትዮጵያን ፊደሎች እንዴት ቴሌፕሪንተር ውስጥ ማስገባት ይቻላል የሚል ነበር፡፡ ኢንጂኒየር ያኔ ለማስተዋል እንደሞከረው የኢትዮጵያ ፊደሎች ቅርጽና ውበት እጅግ የሚያስደንቅ ነው፡፡ በብዛት 270 ቢሆኑም፣ ቅርጻቸው ግን ከ20 አይበልጥም፡፡ ያኔ እርሱ ለማቅረብ እንደሞከረው የላቲን ፊደሎች 26 ይባሉ እንጂ “ካፒታል ሌተር፤ ስሞል ሌተር” ሲባል ወደ አርባ ይጠጋሉ፡፡ የእኛ ግን ይላሉ የያኔው ወጣት ተመራማሪ “ቅርጹ ሲታይ በጣም ተመሳሳይ ነው፡፡ ለምሳሌ ‘ሀ’   ሲገለበጥ ‘በ’ ይሆናል፡፡ በአናቱ ላይ ዘንግ ሲደረግበት ‘ሰ’ ይሆናል፡፡ ‘ሰ’ ላይ መስመር ሲደረግበት ‘ሸ’ ይሆናል፡፡”  በማለት ጥናታዊ ምርምሩን አጠናክሮ ቀጠለ፡፡

እነዚህን ቅርጾች በማስተካከል ብቻ ቴሌፕሪንተሩን መስራት እንደሚቻል ወጣቱ ተመራማሪ የዛሬ 60 ዓመት አረጋገጠ፡፡ ከዚህ በኋላ የዚያን ዘመን ቴሌፕሪንተር የፊደላት ድርድር (ኪቦርድ) ቅርጽ ማስተካከል ያዘ፡፡ ማሽኑ ላይ የሚቀረጹት ፊደሎች ቁመታቸውና አቀማመጣቸው ወረቀቱ ላይ የቱ ጋር እንደሚቀመጡ በደንብ ካስተካከለ በኋላ ሲጻፍ ፈጽሞ እንደማያስቸግር በሚገባ አረጋገጠ፡፡

ከዚህ በኋላ ኢንጂኒየር የሄዱበትን መንገድ በራሳቸው እንደሚከተለው ያወጉናል፡፡

የኢንጂኒየር ቴሌፕሪንተር

‹‹…የኪቦርዱን ቅርጽ ካስተካከልኩት በኋላ በዚያን ጊዜ የአዕምሯዊ ንብረት ሕግ የፈጠራ ውጤቴን በይፋ አስመዘገብኩ፡፡ በኋላም፣ ሶፍትዌሩን ሲመንስ ለሚባለው የጀርመን ኩባንያ አስረከብኩ፡፡ በ1960 ዓ.ም መኪናው (ቴሌፕሪንተሩ) የአማርኛ ፊደል ይዞ ሀገር ቤት ሲመጣ ልዩ ስሜትና የስራ ተበረታችነት ተሰማኝ፡፡

ወዲያው፣ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ቴሌፕሪንተሩን መረቁ፡፡ በምረቃው ዕለት አንዱ ቴሌፕሪንተር አሥመራ ቤተ-መንግሥት ተደረገ፡፡ አንደኛው አዲስ አበባ ተቀመጠ፡፡ በወቅቱ የኤርትራው ገዢ ራስ አሥራተ ካሣ በአዲሱ መኪና መልዕክት ወደ አዲሰ አበባ ሲልኩ ግርማዊነታቸው መልዕክቱን አይተው የደስታ ስሜታቸውን መደበቅ አልተቻላቸውም ነበር፡፡

ይህ ቴሌፕሪንተር ምንድነው? እንዴት ነው የሚሰራው? ብያኔው ከምን የመጣነው.. የሚል ጥያቄ ግለ-ታሪክ ጸሐፊያቸው አቅርቦ ነበር፡፡ ግለ-ታሪክ ጸሐፊው ጥያቄውን ሲደረድር ኢንጂነር በእርጋታ ሲያዳምጡት የተሰማው የነጻነት ስሜት ነበር፡፡

“ቴሌፕሪንተር በርቀት የሚያትምና የሚያሰራጭ መሳሪያ ነው” ሲሉ ብያኔውን በአጭሩ አስቀመጡለት፡፡ ቴሌፕሪንተር በዋናነት አንድን መልእክት በመተየብ ለማሰራጨትና ለመቀበል የሚያገለግል መሳሪያ ነው፡፡ ኢንጂነር ሶፍትዌሩን የፈጠሩ ሲሆኑ፤ ሲመንስ ኩባንያ ደግሞ የቴሌፕሪንተሩን ቅርፅ ያወጣው ኩባንያ ነው፡፡ ይሁንና ፊደሎቹ እንዴት መቀመጥ እንዳለባቸውና የቁመታቸውን መጠን በዝርዝር አጥንተው ያቀረቡት እሳቸው ናቸው፡፡ ለሥራ ውጤታቸውም በወቅቱ ጠቀም ያለ የገንዘብ ክፍያ ተደርጎላቸዋል፡፡

“የዛሬ 60 ዓመት ኢትዮጵያ የቴሌፕሪንተር ሶፍትዌር የሰራ የሰለጠነ ባለሙያ ነበራት” የሚል ዜና ዛሬ ላይ ቆመን ስንሰማ ውስጣችን የሚጭረው የደስታ ስሜት የላቀ ነው፡፡

ወደጋብቻ ዓለም

ኢንጂነር 59 ዓመት ወደኋላ ተመልሰው ከባለቤታቸው ወይዘሮ ብርሃኔ ጋር የተዋወቁበት አጋጣሚ ሲያስረዱ ‹‹…በዓይን የወደድኳት ልጅ የ4ኛ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ አዳሪ ተማሪ መሆኗን ተረዳሁ። ከዚያም ከሥራ በኋላ ማታ ማታ ብቅ እያልኩ ቡና ሻይ ማለትን ተያያዝኩት። ለሥራም ከከተማ ካልወጣሁ ቅዳሜና እሁዴ ከወይዘሪት ብርሃኔ ጋር ማሳለፍ የዘወትር ዕቅዴ ሆነ። ካንድ ስድስት ወር ትውውቅ በኋላ ነገሩ ወደዘላቂ መንገድ የሚወስድ ስለመሰለኝ መዳፈር ጀመርኩ።

ሞጆ ከተማ ከመግባቴ በፊት ወደጎን ታጠፍኩና አንድ ውብ የሆነች ድብቅ ቦታ ላይ የወንዙ ፏፏቴ በሚያፏጭበት ሥፍራ ወሰድኳትና ኮለል ያለውን ውሃ እየተመለክትን አሸዋው ላይ እግራችንን ዘርግተን ጨዋታችንን ጀመርን። ቀኑ ሞቅ ያለ፤ ሰማዩ ጥልቅ ሰማያዊ አንዳንድ ጠብ ጠብ ያሉ ነጭ ዳመናዎች የሚታዩበት ውብ ቀን ነበር። ያመጣሁበትን ጉዳይ ለመግለጽ ከየት እንደምጀምር ጠፍቶኝ የባጡን የቆጡን መቀበጣጠር ጀመርኩና ዓይን ዓይኗን ማየት ቀጠልኩ። እሷ ደግሞ ትክ ብላ እያየችኝ በጥሞና ታዳምጠኝ ነበር። ደቂቃዎቹ እጅግ ረጅም ሆነው አገኘኋቸው ልቤም ዝም ብሎ መደለቅ ቀጠለ…

የኋላ ኋላ እጇን ግጥም አድርጌ ይዥ ብርሃኔ አስፋው፤ ተረፈ ራስ ወርቅን…. ታገቢኛለሽ ብዬ እጅግ የከበደኝን ጥያቄ አፈረጥኩት…..እርሷ ግን ዝም አለች፤ ደነገጥኩ፡፡ አልሰማችኝ ይሆን? እምቢ ማለቷ ይሆን? እነኛ ሰኮንዶች ረጅም ዘመን መሰሉኝ፡ ከዚያ ከንፈሯ መነቃነቅ ሲጀምር ትክ ብዬ አይ ነበር፡፡

ለመሆኑ ይህን ሐሳብ ከመቼ ጀምሮ ነው ያጤንከው? አለችኝ፡፡ ቶሎ ብዬ መጀመሪያ ካገኘሁሽ ቀን ጀምሮ ነው ስላት፤ እንግዲያውስ እሺ አለችኝ›› በማለት ትውውቃቸውን አስመልክቶ አስታውሰው ነበር፡፡

ኢንጂነር ተረፈ ራስወርቅና እና ወይዘሮ ብርሀኔ አስፋው በነሐሴ 20 ቀን 1954 ዓ.ም ተጋቡ፡፡

ኢንጂኒየር  በጄኔቭ

የዓለም አቀፍ የቴሌኮምኒኬሽን አንድነት በ1865 ዓ.ም የተፈጠረ መቀመጫውን ጄኔቭ ያደረገ ትልቅ ድርጅት ነው፡፡ ይህ ድርጅት ኢንጂኒየር በሄዱበት ዘመን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አንድ ክፍል ነበር፡፡ ያኔ የሕብረቱ ዋና ጸሐፊ የቱኒዚያው ሚስተር መሐመድ ሚሊ ነበሩ፡፡ ሕብረቱ ሰዎችን ሊቀጥር ሲያወዳድር የአፍሪካ ክፍል ክፍት ሲሆንባቸው ለአባል ሀገሮች ሁሉ ክፍት ቦታ መኖሩን አሳወቁ፤ ኢንጂኒየርም ያኔ ነበር ከተወዳዳሪዎቹ አንዱ ለመሆን የበቁት፡፡ የትምህርት ሁኔታውና የሰሩት ሁሉ በሚገባ ታይቶ የሕብረቱ ባልደረባ ሊሆኑ ቻሉ፡፡ ከዛም  በዓለም አቀፍ የቴሌኮምኒኬሽን ህብረት የአፍሪካ ጉዳይ ክፍል ውስጥ ማገልገል ያዙ፡፡ በጄኔቭ አንድ ብለው የጀመሩት የሥራ ዘመን ለ40 ዓመታት ዘልቋል፡፡

እርሳቸው እንደሚያስረዱት የክፍሉ ሥራ አፍሪካ በቴሌኮም ዘርፍ ዕድገት እንድታመጣ ማስቻል ነው፡፡ በሕብረቱ ውስጥ የአፍሪካ ጉዳዮች ኃላፊ ሆነው በሰሩባቸው ዓመታት የአፍሪካን የቴሌኮም ዕድገት ዕውን ለማድረግ የአቅማቸውን ያህል ሞክረዋል፡፡ የመጀመሪያው የሕብረቱ ቀዳሚ ተግባር የቴሌኮምኒኬሽን ማሰልጠኛዎች በየሀገሩ መመስረት ነው፡፡

ሌላው በኢንጂኒየር አመራር ጊዜ የተለወጠው የተለመደው የቅኝ ግዛት የስልክ መስመር መሰበሩ ነው፡፡ አንዳንድ የአፍሪካ አገራት ነፃም ከወጡ ወዲያ፣ የቴሌፎን የመገናኛ መስመራቸው ከድሮ ቅኝ ገዢያቸው ጋር ስለነበረ በዛ ላይ መስመሩን የሚያስተላልፉት በብራስልስ፣ በፓሪስ፣ በለንደንና በሮም በኩል ስለነበር ቅኝ ገዢዎቹ መረጃውንም ይጠቀሙበት ነበር፡፡ ለምሳሌ ፓትሪስ ሉሙምባ የተገደለው የስልክ መስመር ተጠልፎ ነው፡፡ የኢንጂኒየር ትልቁ ስኬት የነበረውን የቅኝ ግዛት መስመር መስበር መቻላቸው ነው፡፡

በዚህ መሥሪያ ቤት በነበራቸው ቆይታ የበርካታ ሀገራትን የቴሌኮም የዕድገት ደረጃ ለመለየት ችለዋል፡፡ እንደ እርሳቸው አባባል በዚያን ዘመን (በ1981 ዓ.ም ግድም ማለታቸው ነው) የቻይና ቴሌኮምኒኬሽን ከኢትዮጵያም ያነሰ እንደነበር ይመሰክራሉ፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ በቴሌው ዘርፍ ብዙ መሠራቱን ያምኑበታል፡፡ ሆኖም ግን የኔትወርክ መቆራረጥ ችግር የብዙ ሰው መነጋገሪያ መሆኑን አግባብነት ይረዳሉ፡፡ በሌላ በኩል የአገልግሎት ለውጥና፤ የተጠቃሚ መበራከት በአንድ ላይ ሲከሰት እንዲህ ዐይነት የኔትወርክ መጨናነቅ ሊኖር እንደሚችል ይገልጻሉ፡፡ ይሁንና ጉዳዩ የሚመለከተው ክፍል ትኩረት ሰጥቶ፤ ተግቶ ጊዜው የሚጠይቀውን አገልግሎት በተቀላጠፈ መልኩ መስጠት ይጠብቅበታል ይላሉ፡

የአንኮበር ቤተ መንግሥት ሎጅን መሥራት

ኢንጂነር የአንኮበር ሎጅን ለመስራት የወሰኑበትን አጋጣሚ በአንድ ወቅት እንዲህ ተርከው ነበር፡-

‹‹…የአንኮበርን ታሪካዊነት በመገንዘብ እፊታችን ደግሞ የወደመውን የታላቁን የንጉሥ ምኒልክን ቤተ መንግሥት ስመለከት ያለፉት መንግሥታት መልሰው ባይሰሩትም እኔ ራሴ እንደገና አሰርቼ ላገሬው ሥራ መፍጠር የቀድሞውንም ታሪክ በመዘከር የጎብኝዎች መስህብ እንዲሆን አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ ወሰንኩ። አንኮበር ከአዲስ አበባ እምብዛም ስለማትርቅ፤ አዲስ አበባ ላይ ደግሞ ብዙ ያገር ውስጥና የውጭ አገር ነዋሪዎች መናኸሪያ በመሆኗ ለእንግዶች የሚስማማ የመስተንግዶ ቤት (ሎጅ) ቢሰራ አዋጭ ይሆናል ብዬ ድምዳሜ ላይ ደረስኩ።

ከዶክተር ኃይለ ገብርኤል ዳኜ ጋር ሽርክና በመግባት አምባ ኤኮቱሪዝም ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር አቋቁመን ከመንግሥት በሊዝ ውል የቀድሞውን ቤተ መንግሥት ይዞታ ተረክበን ፋሽስቶች ኢትዮጵያን በወረሩ ጊዜ ያወደሙትን የዐፄ ምኒልክ የነበረውን አዳራሽ በማስመሰል በባሕላዊ መንገድ እንደገና እንዲሰራ ሆኖ፤ ትልቁ አዳራሽ እንደግብር ቤትና እንደመሰብሰቢያ አዳራሽ ሲያገለግል በዙሪያው የነበሩትን የሹማምንቱን መኖሪያ መሰል ቤቶችን በጥንቱ አሠራር እንደገና ገንብተን የእንግዶች መኝታ ቤቶች እንዲሆኑ አቀድን።

የቀድሞውን ቤተ መንግሥት በ1928 ዓ.ም ጠላት ሲያወድመው የቀረው ነገር ከላይ የሚታየው ከቤቱ ፊት ለፊት ያለው የድንጋይ ግንብ ብቻ ነው።›› በማለት ገልጸው ነበር፡፡

ኢንጂነር  ተረፈን ለማስታወስ 

በተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ዋና የሐሳብ አመንጪነት እና አዘጋጅነት የተሰናዳው የኢንጂነር ተረፈ ራስወርቅ የ1ኛ ዓመት ማስታወሻ ቅዳሜ ግንቦት 5 ቀን 2015 ዓ.ም በሳይንስ ሙዚየም ተካሂዶ ነበር፡፡ የኢንጂነር ተረፈ ልጆች ከተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ጋር በትብብር ባዘጋጁት በዚህ መሰናዶ ላይ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፤ ታዋቂ ምሁራን፣ የሃይማኖት አባቶች፤ የኢንጂነሩ ወዳጆችና ዘመዶች ተገኝተዋል፡፡

ቅዳሜ ግንቦት 5 ቀን 2015 ዓ.ም ከጠዋቱ 5 ሰዓት እስከ 6 ሰዓት ተኩል በተከናወነው የማስታወሻ መሰናዶ የተገኙ የመንግሥት የሥራ መሪዎች የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው፣ የአዲስ አበባ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሂሩት ካሳው ፤ የቀድሞ የትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ፣ ዶክተር ሹመት ግዛው፤ ፕሮፌሰር ተከተል ዮሐንስ እንዲሁም የሸገር ሬድዮ ባለቤትና መሥራች መዓዛ ብሩ ታድመዋል፡፡

በእለቱ ተረፈ ራስወርቅ የቴክኖሎጂ ሽልማት ይፋ የተደረገ ሲሆን በየዓመቱም በሳይንስ ፤ በቴክኖሎጂ እና በኮሚኒኬሽን ልዩ ሚና ላበረከቱ ተመራማሪዎች እስከ 500 ሺህ ብር የገንዘብ ሽልማት የሚሰጥበት ነው፡፡ እንዲሁም በዕለቱ በኢንጂነር ተረፈ ከ55 ዓመት በፊት የተሰራው የአማርኛ ቴሌ ፕሪንተር ለኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት ተለግሷል፡፡

በማስታወሻ መሰናዶው እለት ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ እና በተወዳጅ ሚዲያ እና ኮሚኒኬሽን ፕሮዲዩስ የተደረገ ‹‹THE PIONEER›› የተሰኘ ባለ 14 ደቂቃ በእንግሊዝኛ የተዘጋጀ ዘጋቢ ፊልም ለእይታ ቀርቧል፡፡ የዚህ ዘጋቢ ፊልም ስክሪፕት አንባቢ ካናዳዊ ዜግነት ያለው ባለሙያ ሲሆን የሞሽን ግራፊክሱን የሰራው ደግሞ ሄኖክ ድሪባ ነው፡፡ ይህ ዘጋቢ ፊልም በቅርቡ በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ላይ እንደሚቀርብ ታውቋል፡፡

በዕለቱ የኢንጂነር ተረፈ ራስወርቅ ባለቤት ወይዘሮ ብርሃኔ አስፋው፣ ኢንጂነሮቹ ልጆቻቸው አንድነት፤ ኢዛና እና መላዬ ተረፈ ይህ ዝግጅት ደረጃውን በጠበቀ መልኩ መዘጋጀቱና የአባታቸው ታሪክ ለትውልዱ መቀመጡ ደስ እንዳሰኛቸው ገልጸዋል፡፡ በተለይም ጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ ከሐሳቡ ጀምሮ ፕሮግራሙ እውን እስኪሆን ድረስ ላበረከተው ትልቅ አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን ገልጸዋል፡፡

ከጽሑፉ አቅራቢ

ተወዳጅ ሚዲያ እና ኮሚኒኬሽን ታሪክን ለአዲሱ ትውልድ እየሰነደ ይገኛል፡፡ እስከዛሬ የ45 ሰዎችን ታሪክ በሲዲ የ11 ሰዎችን ታሪክ በመጽሐፍ በማስቀመጥ በርካታ ኢትዮጵያን የሚገልጹ ሰነዶችን ተደራሽ እያደረገ ይገኛል፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን የ180 የሚዲያ ሰዎችን ታሪክ የያዘውን የአማርኛ ኢንሳይክሎፒዲያ በማሳተም ሚና አበርክቷል፡፡ ከተመሰረተ 19 ዓመቱን ያስቆጠረው ተወዳጅ ሚድያ ለ31 ባለሙያዎች ጊዜያዊ የሥራ እድል የፈጠረ ነው፡፡ ኹነቶችን በማዘጋጀት ከዚህ ቀደም የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተወልድ የዘጋቢ ፊልም መርኃ ግብር፤ የየረር ሆምስ የቤቶች ምረቃ ሥነ ሥርዓትን በአጠቃላይ ከ17 በላይ ኹነቶችን ሙያዊ ብቃትን በተላበሰ መልኩ ያዘጋጀው ተወዳጅ ሚዲያና ኮሚኬሽን ዋና ግቡ ታሪክን ሰንዶ ለትውልድ ማስተላለፍ ነው፡፡ የድርጅቱ መሥራች እና ባለቤት ጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ ለ23 ዓመት በሚዲያ ሥራ ያገለገለ ነው፡፡

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

አባቴ ለእኔ አባት ብቻ አልነበረም፤ ለእናቴ ታማኝ ባል፣ ለሁላችንም ደግሞ የደስታ ምንጭ ነበር

"አባዬ… ዛሬ ላለሁበት ማንነት መሰረት የሆንከኝ አንተ ነህ!" ​የአርቲስት...

የአንበሶቹ ትንሳኤ፦ የዳካር እንባ እና የቴራንጋ ድል

​በዳካር ሰማይ ስር ዛሬ ጨረቃ አልወጣችም፤ ይልቁንም በሚሊዮን የሚቆጠሩ...

የጥምቀት በዓል በመላ ሀገሪቱ በድምቀት እየተከበረ ነው

የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እና በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት...

“ሎዛ ዘፀአት”እና “የሎዛ ድርሳናት”ተከታታይ ረጅም ልቦለድ መጻሕፍት ተመረቁ

በጋዜጠኛና ደራሲ መርዕድ እስጢፋኖስ የተጻፉት ሎዛ ዘፀአት(2014 ዓ.ም) እና...