Home ነጻ ሐሳብ እስከመቼ በአገር ውስጥ አጀንዳ እንጫረሳለን?

እስከመቼ በአገር ውስጥ አጀንዳ እንጫረሳለን?

እስከመቼ በአገር ውስጥ አጀንዳ እንጫረሳለን?

መታሰቢያ መልአከሕይወት

በዓለማችን ሁሉም ሊባል በሚችል መልኩ ያሉ ሀገሮች የሀገር ውስጥ አጀንዳዎችን ጦርነት ሊያስነሳ በማይችል መልኩ አጥርተው ያላቸውን ጊዜ እና ገንዘብ ለልማት እና ለብልፅግና እየተጠቀሙበት ነው፡፡ የፖለቲካ አለመግባባት ቢፈጠር እንኳን ዳኛው መራጩ ሕዝብ በመኾኑ ምርጫ ከተካሄደ በኋላ የተፈጠረው የፖለቲካ አለመግባባት ተረስቶ ወደ መደበኛ ሕይወት ይገባል እንጂ ወደ ጦርነት የሚገባበት ሁኔታ አይኖርም፡፡ ለምሳሌ አሜሪካን ብንወስዳት በ1860ዎቹ “American civil war” ተብሎ በተካሄደው እጅግ ደም አፋሳሽ ጦርነት ከ800ሺ በላይ የሚኾኑ ዜጎች ለሞት ቢዳረጉን በወቅቱ ተነስቶ የነበረውን የፖለቲካ አለመግባባት በአሸናፊነት የሰሜን ኃይሎች በበላይነት በመያዛቸው አጀንዳው ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እልባት ሰጥተውታል፡፡ አሜሪካ ከዚያ በኋላ ይህ ነው የሚባል ጦርነት በሀገር ውስጥ አካሂዳ አታውቅም፡፡ በሌሎችም በርካታ ሀገራት በተመሳሳይ መልኩ በሀገር ውስጥ ጦርነት ሊያስነሱ የሚችሉ አጀንዳዎች በአግባቡ መልስ በመስጠታቸው ዋናው ትኩረታቸው ልማትና የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ ከኾነ ሰነባብቷል፡፡

ኢትዮጵያ ከዛሬ 300 ዓመት በፊት የሀገር ውስጥ ጦርነት ነበር፤ የዛሬ 200 ዓመት የሀገር ውስጥ ጦርነት ነበር፤ ከዛሬ 100 ዓመት በፊትም የሀገር ውስጥ ጦርነት ነበር፤ አሁንም እየተካሄደ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ በግልፅ የሚያሳየን በተከታታይ ወደ ሥልጣን የመጡ መሪዎቻችን በሀገር ውስጥ ጦርነት ሊያስነሱ የሚችሉ አጀንዳዎችን እንዳይፈጠሩ የማድረግ ብቃት እንደሌላቸው ነው፡፡ ወደፊትም በተመሳሳይ መልኩ በተለያዩ የርዕዮተ ዓለም አመለካከት በሥልጣን ሽኩቻ ሊነሱ የሚችሉ ጦርነቶችን ሊያስቀር የሚችል ሥርዓት አልተዘረጋም፡፡ በመኾኑም ልጆቻችን ከዚህ አዙሪት ለመውጣታቸው ማንም እርግጠኛ ኾኖ መናገር አይችልም፡፡

በዶ/ር ዐቢይ አራት ዓመት ተኩል የሥልጣን ዘመን በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ወደ ስድስት መቶ ሺህ የሚጠጉ ዜጎች በመላው ሀገሪቱ እና በተለይ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ለሕልፈት ተዳርገዋል፡፡ ኢትዮጵያ በታሪኳ መቼም ጦርነት እና አለመረጋጋት ተለይቷት አያውቅም፡፡ ነገር ግን በየትኛውም ጊዜ በሀገር ውስጥ አጀንዳ ይሕንን ያህል ዜጎች ተሰውተው አያውቁም፡፡ ይህ በግልፅ የሚያሳየን ዶ/ር ዐቢይ ችግሮች ገና ከመነሳታቸው በቂ ጥናት በማድረግ ጦርነት ሳይነሳ እንዲቀር የማድረግ ችሎታ እንደሌላቸው ነው፡፡

የቅርቡን የአፍሪካ ታሪክ ብንመለከት በደቡብ አፍሪካ ሕዝቦችን የከፋፈለ አፓርታይድ የሚባል ሥርዓት ለዜጎች መተላለቅ የውስጥ አጀንዳ ኾኖ አገልግሏል፡፡ በሩዋንዳ ውስጥ ደግሞ ዘርን መሠረት ያደረገ የውስጥ አጀንዳ ተፈጥሮ ከ800 ሺህ በላይ ዜጎች አልቀዋል፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ እነዚህ አጀንዳዎች አጥጋቢ መልስ በማግኘታቸው ሥጋት መኾናቸው ቀርቷል፡፡ እነዚህን ሕዝቦች አጨቀጫቂ የውስጥ አጀንዳዎች ማጥራታቸው ሙሉ አቅማቸውን ወደ ልማት እንዲያዞሩ አስችሏቸዋል፡፡ አሜሪካኖች አፍጋኒስታንን ከ2001 እ.አ.አ ወረራ ካካሄዱና ለሃያ ዓመት ቆይተው ሲወጡ በፊት ደካማ የነበረው ታሊባን እጅግ ጠንካራ አድርገውት ነው የወጡት፡፡ አፍጋኒስታን በአሁኑ ጊዜ ከአሜሪካም ወራሪ በፊት ከነበረችበት ሁኔታ በእጅጉን የተሻለ ሁኔታ ላይ ትገኛለች፡፡ የተለያዩ ሃይማኖታዊ ጽንፍ የረገጡ አስተሳሰቦች ባሉባቸው ሀገሮች ለረጅም ጊዜ አጨቃጫቂ እና ደም አፋሳሽ ግጭቶች በተለያዩ ሀገሮች እየደበዘዘ በመምጣቱ ጽንፍ የረገጡ የሃይማኖት አስተሳሰቦች ለሀገሮች ሰላም መጥፋት እንደ አጀንዳ የማገልገላቸው ሁኔታ በእጅጉን እየቀነሰ ነው፡፡ ለምሳሌ ኢራንን ብንወስድ በዓለማችን እጅግ በከረረ ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ የምትታወቅ ሀገር ነበረች፤ ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ ለሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ልዩ ትኩረት በመሥጠቷ አሁንም ምጡቅ በኾኑ ወታደራዊ ምርቶቿ በመታወቅ ላይ ነች፡፡

እኛ ኢትዮጵያውያን ሃይማኖታዊ አክራሪነት የሕልውናችን ጠንቅ ብዙም ኾኖ አያውቅም፡፡ ሀገራዊ ሰላም እያጣን እርስ በእርሳችን የምንባላው በመንግሥት ሥልጣን ውስጥ ያሉ መሃይሞች በሚፈጥሩት የግጭት አጀንዳ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉም ብሔረሰቦች ሊባል በሚችል መልኩ በአንድ መንደር፣ በአንድ ከተማ፣ በአንድ መሥሪያ ቤት በአጠቃላይ በሁሉም የሀገሪቷ ክፍል በሠላም እና በመፈቃቀር መኖር የቻለ ነው፡፡ ጠላቶቻችን ሁሌም መሪዎቻችን ናቸው፡፡ አሁን ለጦርነት የበቁ ራሺያና ዩክሬን በአንድ ወቅት የአንድ ሀገር ሕዝቦች ነበሩ፡፡ በዚያን ጊዜ ሊያጋጫቸው የሚችል ምንም አጀንዳ አልነበረም፡፡ አሁን እነዚህ ሕዝቦች የሁለት ሀገር ሕዝቦች በመኾናቸው የሩሲያ መሬት ይገባኛል እና የዩክሬን የኔቶ አባል የመኾን ፍላጎት የግጭት አጀንዳ እየፈጠሩ በመተላለቅ ላይ ናቸው፡፡ አንድ ሀገር የነበሩ ሕዝቦች ለሁለት ሲከፈሉ ለጦርነት የሚዳረጉ በርካታ አጀንዳዎች ይፈጠራሉ፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባለሀገር ደግሞ በታሪክ በብሔሮች መካከል ድንበር ባልነበረበት ሁኔታ በተጨማሪም ተቆጥረው የማያልቁ ጦርነት ሊቀሰቅሱ የሚችሉ አጀንዳዎች ያሉ በመኾኑ በኢትዮጵያዊነት ጥላ ሥር አብሮ መኖር እና የብሔር ማንነት አስከብሮ ለመኖር መሥራት አማራጭ የሌለው የሞት ሽረት ጉዳይ ነው፡፡

ህወሓቶች በዚህ ደረጃ በጦርነት የተበለቡት እራሳቸው ባነሱት አጀንዳ እንጂ የትግራይን ሕዝብ ለመውጋት ጦር የጫነ አንድም ኃይል የለም፡፡ ማንኛውም ሕዝብ ወይም ቡድን የያዘውን ይዞ የተሻለ ነገር ለማግኘት በሰላማዊ መንገድ መታገል ይኖርበታል፡፡ በጦርነት አንድን ነገር ለማግኘት መጣር ጊዜው ያለፈበት አካሄድ ነው፡፡ በቅርብ የሚገኙ እንደኬኒያ፣ ኡጋንዳ፣ ታንዛኒያ ያሉ ሀገሮች ለውስጣዊ አንድነታቸው ቁመው ለጋራ ዓላማ ይሠራሉ፡፡ ሀገራቸውን ለማተራመስ አይሠሩም፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን በሀገር ውስጥ ያሉ ፀረ ሰላም ኃይሎች እንደልባቸው በታሪካዊ ጠላቶቻችን ድጋፍ የሚያገኙበት ምክንያት አንዱ ምዕራባውያንን በሀገራችን ኢኮኖሚ ተጠቃሚ ማድረግ አለመቻላችን ነው፡፡ በሀገር ውስጥ አጀንዳ መተራመስ የምናቆመው ምዕራባውያን በመላው ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲኾኑ በማድረግ እነርሱ ንብረታቸው እንዳይወድም ከእኛ ጋር ሰላም እንዲሠሩ ማድረግ ስንችል ነው፡፡ ምዕራባውያን በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ኢንቨስት ካደረጉ ፀረ ሰላም ኃይሎችን አይረዱም፡፡

በሥልጣን ላይ ያሉ ስብስቦች ሥልጣን ማለት እራስን ብቻ ተጠቃሚ ማድረግ ነው ብለው የሚያምኑ በመኾኑ ኅብረተሰቡን የውጪ ኢንቨስተሮች ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው አልምተው  እንዲጠቅሙት አይፈልጉም፡፡ የውጪ ኢንቨስተሮች ወደ ሀገር ውስጥ በበቂ ሁኔታ አለመግባባታቸው በመጀመሪያ ለሀገራችን ሠላም መጥፋት አንደኛው ምክንያት ነው፤ በተጨማሪ ሀገራችን ማደግ በሚገባት ፍጥነት እና ልክ ኢንቨስትመንት እንዳታገኝ ምክንያት ኾነዋል፡፡ በመጨረሻም እኛ ኢትዮጵያውያን በሁሉም ሊባል በሚችል መልኩ የመጨረሻዎቹ ኾነናል፡፡ እዚህ ጎረቤታችን ያለችው ኬኒያ ሁሉንም ነገር ማለት በGDP፣ በነፍስ ወከፍ ገቢ፣ ከባድ መኪናዎች ብዛት፣ ከኢንሽራንስ በሚሰበሰብ ገንዘብ ባጠቃላይ በሁሉም ነገር በአራት ዕጥፍ ትበልጠናለች፡፡ እኛ ግን አሁንም እጅግ ኋላ በቀሩ አጀንዳዎች እርስ በእርሳችን እየተባላን ነው፡፡ ቢያንስ ለልጆቻንን በሀገር ውስጥ አጀንዳ እንዳይጣሉ የተሻለ ሥርዓት እናውርሳቸው፡፡