ፓተስ ዝንጀሮ፤ ዳንሰኛው ወይም ቀዩ ዝንጀሮ ተብሎ ይታወቃል፡፡ ፓተስ ዝንጀሮ በሰዓት እስከ 55 ኪሎ ሜትር ድረስ በመሮጥ በምድራችን ፈጣኑ የጦጣ፣ ዝንጀሮ ዝርያ ነው፡፡ ይህ የዝንጀሮ ዝርያ አብዛኛውን የቀን ሰዓት መሬት ለመሬት ምግብ በመመገብ ያሳልፍና አዳሩን ምቹ ዛፍ ላይ ያደርጋል፡፡ በፍጥነት የመሮጥ ብቃቱ ችሎታው ምግብ በመፈለግ መሬት ለመሬት ሲንቀሳቀስ ከአዳኞቹ ሮጦ ለማምለጥ ይረዳዋል፡፡ ነብር፣ ቀበሮ፣ የቤት ውሻ፣ ጅብ፣ ንስር አሞራ፣ አቦሸማኔ፣ ተኩላን ጨምሮ የሚያድኑት ሲሆን አንዳንድ ጊዜም በእፉኝት አይነት የእባብ ዝርያ ተነድፎ ሊሞት ይችላል፡፡ ሴቷ ለመራባት የምትደርሰው 3 ዓመት ሲሞላት ሲኾን ወንዱ ደግሞ ከ5 ዓመት በኋላ ይደርሳል፡፡ የእድሜ ቆይታቸው በአማካይ እስከ 17 ዓመት ገደማ ይሆናል፡፡ ረዣዥም የኋላ እግሮች ያሉት ፓተስ ዝንጀሮ ወንዱ ከእራስ እስከ መቀመጫው ድረስ እስከ 87.5 እና ሴቷ እስከ 52 ሴንቲ ሜትር ይረዝማሉ፤ ክብደታቸውም ወንዱ እስከ 13 እና ሴቷ እስከ 7 ኪሎ ግራም ይመዝናሉ፡፡ የአፍሪካ ብርቅዬ ዝርያ ሲሆን ከምዕራብ እስከ ምስራቅ ድረስ በምድር ወገብ አካባቢ ይገኛል፡፡
The animal facts
ስለ ሕግ
ስለ ውንብድና ምን ያህል ያውቃሉ?
ውንብድና ማንም ሰው ተገቢ ያልሆነ ብልፅግና ለራሱ ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ የሌላው ሰው ንብረት የሆነውን ተንቀሳቃሽ እቃ ለመውሰድ እንዲያመቸው ወይም በሚወስድበት ጊዜም ሆነ ከወሰደ በኋላ የገጠመውን ተቃውሞ ለመቀልበስ በሌላ ሰው ላይ የሀይል ድርጊት መፈጸም ወይም ከባድ የሆነ የማንገላታት ተግባር ወይም ከባድ ዛቻ መፈፀም ወይም በማናቸውም ሌላ መንገድ ይህን ሰው ለመከላከል እንዳይችል ማድረግ የውንብድና ተግባር እንደሆነ በወንጀል ህጉ አንቀጽ 670 ላይ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ ይህን ወንጀል ፈፅሞ የተገኘ ሰው ከአስራ አምስት አመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት የሚቀጣ ይሆናል፡፡
ወንጀሉን የሚያከብዱ ሁኔታዎች (ከባድ ውንብድና)
በወንጀል ህጉ አንቀጽ 671 ላይ የውንብድና ወንጀልን ከባድ የሚያደርጉ ምክንያቶች የተዘረዘሩ ሲሆን ወንጀል ፈጻሚው ወንጀሉን የፈጸመው
• በሰዎች ላይ ወይም በንብረት ላይ የኃይል ተግባር ለመፈጸም በተቋቋመ የወንበዴ ቡድን አባል በመሆን ሲሆን
• ተበዳዩን እገልሀለሁ ብሎ እርግጠኛ የሞት አደጋ እንደሚደርስበት በመዛት፣ በጦር መሳሪያ ወይም በተለይ አደገኛ በሆነ ሌላ አይነት መሳሪያ በማስፈራራት ወይም ስቃይ በሚያደርስ ሁኔታ በማንገላታት ወይም ከባድ የአካል ጉዳት በማድረስ ሲሆን
• አደገኝነቱን በሚያሳይ በማናቸውም ሌላ ሁኔታ ሲኾን ወንጀል ፈጻሚው ከአምሰት ዓመት እስከ ሃያ አምስት አመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ሊቀጣ ይችላል፡፡ በሌላ በኩል ወንጀል ፈጻሚው ወንጀሉን የፈጸመው ወንጀል ለመፈጸም ከተደራጀ ቡድን ጋር በመሆን ወይም የጦር መሳሪያ ወይም ሌላ አደገኛ መሳሪያ በመያዝ የህዝብ ጸጥታን አደጋ ላይ የሚጥል ወይም የተለየ ጨካኝነት የሚያሣይ ዘዴን በመጠቀም፣ ወይም የተፈጸመው የሀይል ተግባር ዘላቂ የአካል ጉዳትን ወይም ሞትን ያስከተለ ሲሆን ቅጣቱ እድሜ ልክ እስራት ሲሆን የውንብድና ወንጀል አፈጻጸሙ እጅግ ከባደ በሆነ ጊዜ የሞት ቅጣት ሊሆን እንደሚችል የወንጀል ህጉ ደንጎት ይገኛል፡፡ የጦር መሳሪያን በመጠቀም በቡድን በመሆን በልማደኝነት የውንብድና ወንጀልን መፈጸም በሞት እንደሚያስቀጣ የወንጀል ህጉ አንቀጽ 671 በግልጽ ደንግጎት ይገኛል፡፡
ጠቅላላ ዕውቀት
ሞክሼ ፊደላት፡-
ሞክሼ ፊደላት የሚባሉት አንድ አይነት ድምጽ ያላቸው ነገር ግን በቅርጽ እና በስራቸው የተለያዩ ፊደላት የኾኑ ናቸው። አባቶቻችን ሀን ከ ሐ ፣ ጸን ከፀ ፊደሎችን በድምፅ አወጣጥ ይለዩአቸው ነበር። እኝህ ፊደላት በቁጥር ፱ (9)ሲኾኑ ሀ ፣ ሐ ፣ ኀ ፣ ሠ ፣ ሰ ፣ አ ፣ ዐ ፣ ጸ ፣ ፀ ናቸው። ሀ- ሃሌታው “ሀ” ይባላል። ሐ- ሐመሩ “ሐ” ይባላል። ኀ- ብዙኃኑ “ኀ” ይባላል፡፡ አ- አልፋው “አ” ይባላል፡፡ ዐ- ዓይኑ “ዐ” ይባላል። ሠ- ንጉሡ “ሠ” ይባላል። ሰ- እሳቱ “ሰ” ይባላል። ጸ- ጸሎቱ “ጸ” ይባላል። ፀ- ፀሐዩ “ፀ” ይባላል። ነዚህ ሞክሼ ፊደላት አንዱ በአንዱ ቦታ መግባት የለበትም ምክንያቱም የትርጉም ለውጥ ያመጣሉ። ለምሳሌ:- ሠረቀ = ወጣ ፣ ሰረቀ = ሰረቀ፣ አመት = አገልጋይ ፣ ዓመት = ዘመን ፣ ሰዓለ = ስዕል ሳለ ፣ ሰአለ = ለመነ ፣ መሀረ = አስተማረ ፣ መሐረ = ይቅር አለ ፣ ኀለየ = አመሰገነ ፣ ሐለየ = አሰበ ፣ ፈጸመ = ጨረሰ ፣ ፈፀመ = ነጨ ፣ ማኅሌት = ማመስገን ፣ ማሕሌት = ማሰብ፡፡
ድንቃይ
በፓኪስታን በሰርጉ እለት ለባለቤቱ አህያ በስጦታ መልክ የሰጠዉ ባል መነጋገሪያ ሆኗል። በፓኪስታን የሚገኙት ጥንዶች ቫሪሻ ጃቬድ ካን እና አዝላን ሻህ በቅርቡ የጋብቻ ስነ ስርዓታቸዉን ፈጽመዋል። ፓኪስታናዊው ሙሽራ በሠርጋቸው ቀን ለሙሽሪት የሰጠው ያልተለመደ ስጦታ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎችን ቀልብ ስቧል። በሠርጉ ግብዣ ላይ አዝላን ሻህ ባለቤቱን አህያ በመስጠት አስገርሟል፡፡ የስጦታውን ምስል በኢንስታግራም በማጋራት ሻህ ልዩ ስጦታውን ያቀረበበትን ምክንያት አብራርቷል። ” አህዮችን እንደምትወድ ሁልጊዜ አውቃለሁ ስለዚህ የሰጠኋት የሰርግ ስጦታ ይሁንልኝ” ሲል ጽፏል። ሙሽሪት ስጦታውን ካየች በኋላ በጣም መደሰቷን ተናግራለች፡፡
