” ካላቸው ቅሬታ ማቅረብ ይችላሉ። ግን መሬቱ መቼ እንደተወሰደባቸው ዝርዝሩን አላውቅም ” – የሸገር ከተማ ም/ክንቲባ
በኦሮሚያ ክልል በተለይ ሸገር ከተማ የሚገኙ ከ100 በላይ ጠጠር አምራች ድርጅቶች መሬት መቀማቱንና ሥራ ማቆሙን የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ግብዓት አቅራቢዎችና ማዕድን ሀብት ሥራ አሰሪ ባለሃብቶች ማህበር ገለጸ።
አምራቾቹ ለየትኛውም ቦታ በግንባር ቀደምነት ጠጠር የሚያቀርቡ ሆነው ሳለ መሬታቸውን መቀማታቸውን ገልጾ፣ በአጠቃላይ በኦሮሚያ ክልል ” ከ140 በላይ ጠጠር አምራቾች ሙሉ በሙሉ ቆመዋል። ይሄ አንድ አመት ሊሆነው ነው ” ብሏል።
የማህበሩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ኃይለማርያም ገቢሳ ።።።።።።።።።።።።።።።።።በሰጡት ቃል፣ ከመንግስት መመሪያ፣ አዋጅና ደንብ ውጭ ጠጠር ማምረቻዎችን መዘጋታቸውን በመግለጽ፣ ” እነዚህ በሸገር ሲቲ ውስጥ በማን በምን እንደሚዘጉም አናውቀውም ” ብለዋል።
” መሬትም የተቀሙ አሉ። ያለምንም ምክንያት መሬት ቀምቶ ‘ከዛሬ ጀምሮ ውጣ’ ብለው ለሌላ ሰው የመሩበት ሁኔታም አለ ” ሲሉ ተናግረው፣ ” ‘ሸገር ኢንቨስትመንት ግሩፕ’ ብለው አቋቁመው መሬት ቀምተውናል” ነው ያሉት።
ነገር ግን ማህበራቸው፣ መሬቱን ተረክቦ የነበረው፣ ” በኢንቨስትመንት ኮሚሽን መመሪያ ” እንደሆነ ተናግረው፣ ይሁን እንጅ መመሪያውን ” ሰብረው አልፈው መሬቱን ለራሳቸው አድርገውታል ” ሲሉም ተናግረዋል።
” አስር ወር ተዘግተዋል” ያሉት አቶ ኃይለማርያም፣ ወደ ውይይት ተገብቶ እንዲከፈቱ የማድረግ ሁኔታ ቢኖርም፤ ” እንዲከፈቱ ሲደረግ ግን በጉዳዩ አምነንበት ሳይሆን እንደ ስካቫተር፣ ክሬን የመሳሰሉ ንብረቶች እየተፈቱ መዝረፍ ስለተጀመረ ነው ” ብለዋል።
አቶ ኃይለማርያም በሰጡን ቃል፣ ችግሩ አሁንም ” አልተፈታም ገና እንሄድታለን። ተፈታ ማለት አንችልም ” ብለው፣ እንዲያውም ከአሰራር ውጭ 70/30 (ከገቢያቸው 30 በመቶውን) ” ለመንግስት ” ክፈሉ መባላቸውን ተናግረዋል።
ይሁን እንጅ። ” 70/30 ከኛ ውጭ ነው። ምንም ወጭ ሳይኖረው 30 ለመንግስት ተብሏል። ስለዚህ መሬቱን ነው የቀሙን፤ ‘እናንተ መሬት መውሰዳችሁን አናውቅም’ ብለውናል ” ነው ያሉት።
” 70/30 ” የሚለው፣ ” እነርሱ ያመጡት ነው። መመሪያ፣ ህግ የለውም የኢንቨስትመንት፣ መመሪያ ያን አያዝም፤ ሰሚ ካገኘን ወደ ትክክለኛው መስመር የምናመጣበት መመሪያ እንዲከበር በሚቻልበትን ሁኔታ ለመምከር ጥረት እናደርጋለን ” ብለዋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ፣ ይህ ድርጊት ተፈጽሟል ? ከሆነ ለምን ? ሲል በኦሮሚያ ክልል የሸገር ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ጉግሳ ደጀኔን ጠይቋቸው፣ ቅሬታው ” ለእኛ አልቀረበም፤ እንዲህ አይነት ኬዞችን አላውቅም ” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
” ድርጅቱ እኛ ጋ [መሬት] ይኑረው አይኑረው እርግጠኛ አይደለሁም ” ያሉት ም/ከንቲባው፣ ” ካላቸው ቅሬታ ማቅረብ ይችላሉ። መቼ እንደተወሰደባቸው ዝርዝሩን አላውቅም ” ሲሉም ተናግረዋል።
ለተጨማሪ ማብራሪያ ወደ ሸገር ከተማ ከንቲባ ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር) በተደጋጋሚ በእጅ ስልካቸው ቢደውልም ሳያነሱ ቀርተዋል።
TikvahEthiopia
