በኢራን ላይ አዲስ ጥቃት ለመክፈት የሚያስቡ ወገኖች ካሉ ከባድ አፀፋ እንደሚገጥማቸዉ የኢራን ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አባስ አራጋቺ አስጠነቀቁ።
ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሩ ዛሬ ማስጠንቀቂያዉን የሰጡት የዓለም የአቶሚክ ተቆጣጣሪ ድርጅት (IAEA) የበላይ ሐላፊ ራፋኤል ግሮሲ የሰጡትን አስተያየት በመቃወም ነዉ።
ግሮሲ ትናንት ለታተመ ለአንድ የስዊስ ጋዜጣ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ኢራን የኑክሌር መርሐ-ግብሯን እንድታስፈትሽ የሚደረገዉ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ካልተሳካ «ዳግም የኃይል እርምጃ» ይወሰዳል ብዬ እፈራለሁ ብለዋል።
እስራኤል ባለፈዉ ሰኔ አጋማሽ በኢራን ላይ ድንገት የከፈተችዉ ጥቃት ኢራን ሥለ ኑክሌር መርሐ ግብሯ ከዓለም አቀፉ ድርጅትም፣ ከዩናይትድ ስቴትስም ጋር የምታደርገዉን ድርድር አቋርጦታል።
እስራኤልና ኢራን በገጠሙት ጦርነት ዩናይትድ ስቴትስም በቀጥታ ተካፍላ የኢራንን የኑክሌር ተቋማትን ደብድባለች።
ከ12 ቀናት በኋላ ሶስቱ መንግሥታት ጦርነቱን ቢያቆሙም ድርድሩ እንደተቋረጠ ነዉ።
«ገለልተኛ» የሚባለዉ የተባበሩት መንግሥታት የአቶሚክ ተቆጣጣሪ ድርጅት ኃላፊ «ዲፕሎማሲዉ ካልተሳካ የኃይል ርምጃ ይወሰዳል» ሲሉ፣እርምጃዉን ሊወስዱ የተዘጋጁ መንግሥታት ሥለመኖራቸዉም ሆነ ያገኙት መረጃ ሥለመኖሩ በዝርዝር አላስታወቁም።
የኢራን ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አባስ አረጋቺም የግሮሲ መግለጫ «ሥጋት ይሆን ማስፈራሪያ ግልፅ አይደለም» ብለዋል።ይሁንና አራጋቺ አክለዉ «እንዲሕ ዓይነት ማስፈራሪያ የሚሰጡ ወገኖች፣ ያለፈዉን የከሸፈ ልምዳቸዉን መድገም ለሌላ ክሽፈት እንደሚዳርጋቸዉ ሊገነዘቡት ይገባል» ብለዋል።
ኢራንና የዓለም የአቶሚክ ተቆጣጣሪ ድርጅት ባለፈዉ መስከረም አዲስ የትብብር ሥምምነት አድርገዉ ነበር።
ይሁንና እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር በ2015 ከኢራን ላይ ተነስቶ የነበረዉ ዓለም አቀፍ ማዕቀብ ዳግም እንዲጣል ብሪታንያ፣ ፈረንሳይና ጀርመን በፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ካስወሰኑ በኋላ ኢራን ዉሉን ሠርዛለች ሲል የጀርመን ድምጽ DW ዘግቧል።
ጥቅምት 13/2018 ዓ.ም
