በ1942 ዓ.ም ሲዳሞ ክፍለ ሃገር ጀምጀም አዉራጃ ክብረመንግሥት ከተማ ተወለዱ። የሐረር ጦር አካዳሚ የ14 ዙር ምሩቅ የሆኑት እኝህ ከፍተኛ መኮንን በቀድሞው ጦር ውስጥ አንፀባራቂ ገድል ከፈፀሙ የጦር ከፍተኛ መኮንኖች መካከል አንዱ ሲሆኑ በአገልግሎት ዘመናቸው ከፈፀሙት ተጋድሎዋች ውስጥ ጥቂቱን እነሆ።
በመቶ አለቃ ማዕረግ በኢትዮጵያ አየር ወለድ ክፍል ውስጥ በተለያዩ ግዳጆች ላይ ከመሳተፋቸውም በላይ በእብሪት ተነሳስቶ በምስራቅ ኢትዮጵያ በሦስት አቅጣጫዋች በደቡብ በሁለት ግንባሮች ወረራ የከፈተብንን በጀነራል ሰኢድባሬ የሚመራውን የሶማሊያ ወራሪ ጦር ለመመከት ወደ ማሰልጠኛ ከገቡት አዲስ ምልምል ወታደሮች ስልጠና ላይ በመሳተፍ የአንደኛ ፓራ ኮማንዶ በርጌድ ምልምሎችን በማሰልጠንና ለመጨረሻው ፍልሚያ ወደ ምስራቅ ጦር ግንባር በጀግናው ብርጋዴር ጀነራል ተሰፋዬ ኃብተማሪያም ብርጌድ አዛዥነት ሲዘምት የመቶ አለቃ ሰረቀ ብርሃን በብርጌዱ ውስጥ በሻለቃ አዛዥነት የሻለቃውን ጦር እየመራ በኮምቦልቻ ግንባር ሐረርን ለመቆጣጠር ጥቂት ኪሎ ሜትር የቀረውን ወራሪ የሶማሊያ ጦር መክቶ በማቆምና በመልሶ ማጥቃት ዘመቻው የጠላት ጦር ድባቅ እንዲመታ ካስቻሉ መሪ መኮንኖች አንዱ ናቸው፡፡
ግዳጃቸውን በአኩሪ ሁኔታ ፈፅመው ከካራማራ ድል በኋላ “የምሥራቁ ድል በሰሜን ይደገማል” በማለት ብርጌዱ ፊቱን ወደ ሰሜን ሲያዞር ከሽሬ ተነስቶ ወደ ባሬንቱ የማጥቃት ግዳጅ በተሰጠው 502ኛ ግ/ ኃይል ስር የአንደኛ ፓራ ኮማንዶ እስከ አቆርዳት ድረስ ብዙ መቶ ኪሎሜትሮች በክረምት ዝናብና ጎርፍ ጋር እየታገለ ድል በድል የተጓዘው ግ/ኃይል አመርቂ ድል አንዲያስመዘግብ ካስቻሉ የሻለቃ አዛዥች በግንባር ቀደም ተጠቃሽ ከመሆናቸውም ሌላ የአንደኛ ፓራ ኮማንዶ ብርጌድ በተከታታይ በተሰጠው ግዳጅ ከአቆርዳት ከረንን ለመያዝ እንዲሁም ከረን ከተያዘ በኃላ በመሳህሊት በተደረገው ከፍተኛ ውጊያ አንደኛ ፓራ ኮማንዶ ብርጌድ ላስመዘገበው ወጤት ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማድረግ በብርጌዱ ስር የሻለቃ ጦራቸውን በመምራት አፍአቤትን እና ኩብኩብን ይዞ ወደ ናቅፋ በር የሚገሰግሰው 508ኛ ግብርኃይል ከናቅፋ በር እንዲደርስ የተሰጣቸውን ግዳጅ በጋለ የሀገር ፍቅር ስሜት ካስፈፀሙት ወጣት መኮንንኖች አንዱ ናቸው።
በናቅፋ በር ግንባር በመጀመሪያው ረድፍ ላይ በተሰለፈው አንደኛ ፓራ ኮማንዶ ብርጌድ በማጠቃትና መከላከል ውጊያ ውስጥ ተስፋ ከተጣለባቸው ወጣት መኮንኖች ግንባር ቀደም የሆኑት መቶ አለቃ ሠረቀ ብርሃን በናቅፋበር ግዳጅ ውስጥ እንዳሉ የ3ኛ ክፍለጦር 10ኛ ብርጌድ ዘመቻ መኮንንነት ታጭተው በመዛወር በሻምበል ማዕረግ የ10ኛ በርጌድ ዘመቻ መኮንን ከመሆናቸውም በላይ በዚህ ብርጌድ ውስጥ በዘመቻ አስተባባሪነታቸው ባሳዩት ውጤት ብዙም ሳይቆይ በያዙት ማዕረግ የብርጌዱ አዛዥ መሆን ችለዋል።
የ10ኛ ብርጌድ አዛዥ ሻምበል ሠረቀ ብርሃን በክፍለ ጦሩ ዘመቻ ክፍል የበለጠ ኃላፊነት እንዲጣልባቸውና ተፈላጊ እንዲሆኑ በማድረጉ የክፍለ ጦሩ ዘመቻ ረዳት እና ዋና የዘመቻ ኃላፊነትን ቦታ በመያዝ ክፍለ ጦሩ የሚሰጠውን ግዳጅ በአግባቡና እጅግ ጀግንነት በተሞላው አኩሪ አፈፃፀም እንዲከናወን በማስቻላቸው በተፋጠነ የማዕረግ እድገት ሻለቃና ሌ/ ኮሎኔል የደረሱት እኝህ መኮንን የታሪካዊው አንበሳው 3ኛ ክፍለ ጦር አዛዥ ለመሆን ችለዋል። ያለምንም ማጋነን የዚህ ክፍለ ጦር አዛዥ ለመሆን የብዙ ከፍተኛ መኮንኖች ፍላጎት ቢሆንም ይህንን ዕድል ካገኙት ጥቂት ከፍተኛ መኮንኖች አንዱ ለመሆን በቅተዋል። ለዚህ ለመብቃት የሚያስከፍለው መስዋዕትነት እንደተጠበቀ ሆኖ በአመራር ብቃትና ክህሎት ልዩ ሆኖ ሁል ጊዜ መገኘትን የሚጠይቅ በመሆኑ ኮሎኔል ሠረቀ ብርሃን በዚህ ረገድ ስኬታማ ነታቸውን ለተከታታይ 6 አመታት አሳይተዋል።
በኮሎኔል ሠረቀ ብርሃን የሚመራው 3ኛ ክፍለጦር ችግር ባለበት ሁሉ ተወርዋሪና ሁሌም በተከፈተ ውጊያ ውስጥ እልባት ሰጪ እንዲሆን በመደረጉ የክፍለ ጦሩ አባላትና አዛዡ ሰለቸን ደከመን ሳይሉ አልፎ ተርፎ ከሀገር ሀገር ተወርዋሪ እየሆኑ በአኩሪ ሁኔታ ግዳጃቸውን ተወጥተዋል።
በ1982 በሰሜን ሸዋ መራኛ አካባቢ የደረሰው የህወሓት ኃይል በዚህ ጀግና ክፍለጦር እንዲመታ በሚል ለክፍለ ጦሩ የተሰጠው ግዳጅ እጅግ አስቸጋሪ ቢሆንም የክፍለ ጦሩ አባላት በተለመደ ህዝባዊ ወኔአቸውና ቆራጥነታቸው የጠላትን ኃይል ክፉኛ መትተውና ቀላል የማይባል ቁጥር ምርኮኛ ይዘው በተከታታይ ለረዥም ቀናት ባካሄዱት ውጊያ ጥይት እየጨረሱ በመሄዳቸው የወገን ቁስለኛ ከመበራከቱም ሌላ ለማግለልና ህክምና ወደሚያገኙበት ለማጓጓዝ ለበላይ አካል የሚቀርበው ጥያቄ በወጉ ባለመስተናገዱ በአንበሳው ክፍለ ጦር አባላት ላይ የፈጠረው ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ላይ የክፍለ ጦሩ ስመጥር አዛዥ በገደል አፋፍ ላይ በነበረው ጉዞ በመንሸራትና በመውደቅ የጉልበት ሰብራት ማጋጠም ተደምሮበት ሰራዊቱ ወደ ግል እርምጃ እንዲገባ ምክንያት ሆኖ ክፍለጦሩ ከመራኛ ሊገፈተርና አዛዡ ጀግናው ኮሎኔል ሠረቀ ብርሃን በጠላት እጅ ሊወድቁ ችለዋል።
በዚህ ዘመቻ ወቅት ኃላፊነት የነበራቸው የሦስተኛው አብዮታዊ ሰራዊት ዘመቻ ክፍልና አዛዦች ይህንን ሰራዊት ለመታደግ የወሰዱት እርምጃ አለመኖሩና ይልቁንም ያቀረቡት ተልካሻ ምክንያት በታሪክ ውስጥ ጥቁር ነጥብ ጥሎ አልፎአል። ወደ መራኛ ለክፍለ ጦሩ እንዲደርስለት የተላከው ተጨማሪ ኃይል መጓጓዣው አይፋ ኤል 60 ተሽከርካሪዋች በጭቃ በመያዛቸው ሊደርስለት አልቻለም የሚል እንደነበር የዘመቻ ሁኔታ መግለጫ በዘመቻ መኮንኑ መሰጠቱ እጅግ አሰተዛዛቢና ድብቅ ፍላጎትን የሚያጋልጥ ነበር። በጠላት እጅ የወደቀው ጀግናው ኮሎኔል ሰረቀ ብርሃን ከህወሀት ቀጣይ ጉዞ አንፃር በተለይ በኃየሎም ማግባባት ለቀጣይ ዘመቻዋቻቸው የዘመቻ ዕቅድ በማውጣት ረገድ አስተዋፅኦ እንዳደረጉላቸው በስፋት ቢነገርም ኮሎነል ሰረቀ ብርሃን በወያኔ እጅ በእስር ቤት ብዙ ማቀውና ተሰቃይተው ህይወታቸው ሊያልፍ ችሏል። እኒህ ጀግና ቢያልፉም ተጋድሎውና ለእናት ሀገራቸው የሰሩት አኩሪ ስራ በህይወት በሚገኙ የቀድሞ ሰራዊት ልብ ውስጥ ይኖራል። ታሪክ ወደፊት ይዘክረዋል።
ኮሎኔል ሠረቀ ብርሃን ከጦር አካዳሚ ባገኙትና በህንድ ሀገር ከተማሩት የውትድርና ሳይንስ ባለይ ለውትድርና የተፈጠረ ከተግባር ተምሮ ተግባራዊ ድርጊትን ቀላል ለማድረግ ንድፈ ሀሳብ ማውጣት የሚችሉ ሰራዊቱን በተገኘ አጋጣሚ በማስተማርና በተግባር አዳዲስ ስልታዊ ሁኔታዋችን መፍጠር የሚችል የጦር ሊቅ እንደነበሩ ከዚህ በታች የሰፈረው እማኝነት ምስክር ነው። በኢትዮጵያም ይሁን በአለም ወታደራዊ ስልጠና ተመሳሳይ የሆነ የኢላማ ተኩስ ትምህርት አለ፡፡ ወታደር ኢላማ ተኩስ ሲሰለጥን ለጥ ያለ ሜዳ ተፈልጎ ነው ለጥ ያለ ሜዳ እንኳን ባይኖር በግሬደር አባጣ ጎበጣው ተስተካክሎ እዛለይ ነው ጦሩ የሚለማመደው ነገር ግን ውጊያ ወረዳ ላይ እንደዛ ያለ ቦታ አያጋጥመው፡፡
በቀድሞው መንግስት የ3ኛ ክ/ጦር አዛዥ የሆኑት ኮለኔል ሰረቀ ብርሀን ግን በክፍለ ጦሩ ወስጥ የራሳቸውን ጦር አንበሳው 3ኛ ክፍለጦርን ሲያሰለጥኑ ከመከላከያ ሚኒስትር ስልት ወጣ ባለ መልኩ ከተራራ ላይ ወደ ታች ቁልቁል የሚደረግ የኢላማ ተኩስ ከዝቅተኛ ቦታ ሆኖ ወደ ከፍታ ቦታ የሚደረግ የኢላማ ተኩስ በአባጣ ጎባጣ (ሰበርባራ) ቦታ የሚደረግ የኢላማ ተኩስ ያስተምሩ ነበር፡፡ ይቺ ፈጠራ የእርሳቸው ትሁን የሌላ አላውቅም እኔ ግን የአየሁት ከእርሳቸው ነው።ምንጭ፡- Former Ethiopian Armed Force- የቀድሞዉ የኢትዮጵያ ሠራዊት
