“ዘወረደ” የዐቢይ ጾም የመጀመሪያው ሣምንት

Date:


የዐቢይ ጾም የመጀመሪያው ሣምንት “ዘወረደ (ዘመነ አዳም)”  ይባላል፡፡ ዘወረደ ማለት ከላይ የመጣ፣ የወረደ ማለት ነው፡፡ስያሜውም የቅዱስ ያሬድ ነው። ትርጉሙም “ከሰማያት የወረደ” ማለት ነው። ቅድመ ዓለም ከአባቱ ከአብ የተወለደ፣ ድኅረ ዓለም ከድንግል ማርያም የተወለደ ነው። ስም አጠራሩ ያለና የነበረ፣ እግዚአብሔር፣ በፈቃዱ ዓለምን ለማዳን የመምጣቱን ምሥጢር የምንረዳበት ሳምንት ነው። 


አዳምንና ልጆቹን ከሞት ለማዳን ሲል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆኑንና የፈጸመውን የማዳን ሥራ ያመለክታል፡፡ “ከሰማይ ከወረደው በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም” ካለው ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ቃል በመነሣት ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በድጓው “አዳምን  ለማዳን ከሰማይ የወረደውን አምላክ አይሁድ ሰቀሉት፤ የሰማይ ሥልጣን ያለው የሁሉ ጌታ እንደሆነም ምንም አላወቁም” በማለት ገልጾታል፡፡


ዘወረደ፡ ጾመ ሕርቃል


የመጀመሪያው የዐቢይ ጾም መግቢያ እሑድ “ዘወረደ” ይባላል፤በሌላ በኩልም “ጾመ ሕርቃል”  እየተባለም ይጠራል፡፡ ሕርቃል (ኤራቅሊዮስ) በ፮፻፲፬ ዓ.ም የነበረ የቤዛንታይን ንጉሥ ነው፡፡ ለክርስቲያኖች ባደረገው ርዳታ ምክንያት አንድ ሳምንት ጾመውለት ነበር፡፡ ዛሬም ድረስ ጾመ ሕርቃል እየተባለ ይጠራል፡፡ ሙሉ ታሪኩ በፍትሐ ነገሥት ትርጓሜ አንቀጽ ፲፭ ላይ ይገኛል፡፡


በ641 ዓ.ም ኪርዮስ የተባለ የፋርስ ንጉሥ ኢየሩሳሌምን ወርሮ ጥቃት አደረሰ፡፡ በኢየሩሳሌም ንግሥት ዕሌኒ ባሠራችዉ ቤተመቅደስ ዉስጥ ሲገባ ንግሥቷ በክብር አስቀምጣው የነበረዉ የጌታችን የመድኃኒታችን  የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል እንደ ፀሐይ ሲያበራ አገኘው፡፡ ቢነካዉ አቃጠለው ዲያቆናቱን አሸክሞ፣ንዋያተ ቅዱሳት ዘርፎ ወደ ፋርስ ባቢሎን ወሰደው /Enclopedia of Aethiopica/፡፡

በዚያን ጊዜ ከጦርነቱ ያመለጡ፣ በየጉራንጉሩ ገብተዉ የተሸሸጉ ሰዎች  ከ14 ዓመት በኋላ ተሰብስበው ጩኸታቸዉንና የደረሰባቸዉን በደል ለክርስቲያኑ የሮም ንጉሥ ለሕርቃል ነገሩት፡፡ እርሱም ሐዋርያት በሲኖዶሳቸው “ነፍስ የገደለ ሰው እስከ ዕድሜ ልኩ ይጹም” ብለው ሥርዐት ሠርተዋልና እንዴት ላድርገዉ አላቸው፡፡

በኢየሩሳሌም የነበሩ ምእመናን ሐሳቡን ደግፈው “አንተ ጠላታችንን አጥፋልን፤ መስቀሉን አስመልስልን እንጂ የአንድ ሰው ዕድሜ ቢበዛ ሰባ፣ ሰማንያ  ዓመት ነው፡፡ ጾሙን እኛ ተከፋፍለን እንጾማልሃለን” ብለዉ  ጾሙን በሚገባ ጾመዉታል፡፡


ይህንን መሠረት በማድረግ ያላወቁት አንድ ጊዜ ጾመው ትተውታል፡፡ ያወቁት ግን ቀድሞም ሐዋርያት ጾመውታል ብለው ሥርዐት አድርገው በዓመት በዐቢይ ጾም መጀመሪያ ላይ “ጾመ ሕርቃል” እያሉ የሚጾሙት ሆነዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ይህንን ሥርዐት መሠረት በማድረግ ከጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጾም የመጀመሪያውን ሳምንት “ጾመ ሕርቃል” በሚል ሰይማ እንዲጾም አድርጋለች /ስንክሳር መጋቢት ፲ ቀን/፡፡


ጾመ ሕርቃል በዐቢይ ጾም


ጾመ ሕርቃል በጌታ ጾም ላይ እንዲጾም የሆነበት ምክንያት ጾሙ የጌታ ጾም በሚጾምበት ወቅት ላይ ስለተጾመ ቤተክርስቲያናችን አብራ ደንግጋዋለች፡፡ ለሕርቃል የተሰጠዉን በጠላቶቹ ላይ ድል መንሣትን ለእኛም እንዲሰጠን የምንጠይቅበት ስለሆነ የመጀመሪያዉ ሣምንት በሕርቃል ሰይመን ጾሙን እንጾማለን፡፡

በዚህ ሳምንት ቤተ ክርስቲያን ስለ ጾም ጥቅምና እንዴት መጾም እንዳለብን ታስተምረናለች፡፡ቅዱስ ያሬድ በጾመ ድጓው “ለሥጋቸሁ ፈቃድ የተገዛችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃችኋል፤ ከአሁን በኋላ ግን ጹሙ፣ ጸልዩ ለእግዚአብሔር ተገዙ” እያለ የጾም ዐዋጅ ያውጃል።

ጾም ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ነፍስ፣ ፈቃደ ነፍስን ለፈቃደ እግዚአብሔር የምናስገዛበት መንፈሳዊ መሣሪያ ነው፡፡ የእኛ ጠላት የጨለማ ገዢ የሆነዉ ዲያቢሎስ ነዉና እሱን ደግሞ በጾም እንደምናሸንፈዉ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስተምሮናል፡፡ ጾም ሥጋችንን ለነፍሳችን የምናስገዛበት ከፈጣሪ ጋር የምንገናኝበት የጽድቅ መንገድ ለሥጋ ጤንነትም ቢሆን አስፈላጊያችን የሆነ አንዱና ዋነኛዉ የጽድቅ ዕቃ ጦራችን ነዉ፡፡


ጾም ፈቃደ ነፍስን በፈቃደ ሥጋ ለማሠልጠን የአጋንንት ኃይል ለመቋቋም የሚያስችል የክርስቲያኖች ጋሻ በመሆኑ በሃይማኖት ለሚመሩ ምእመናን እጅግ አስፈላጊና ከምንም በላይ የሕይወታቸው መርሕ መሆን እንደሚገባ ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ እንዲህ በማለት ያስተምራል፡፡

“አሁንም ወንድሞቻችን በዚህ በሥጋችን ሳለን ፈቃደ ሥጋችንን ልንሠራ አይገባም፤ ፈቃደ ሥጋቸውን የሚሠሩ ሰዎች በወዲያኛው ዓለም ምውታን ናቸውና፡፡ የሥጋችሁን ፈቃድ በነፍሳችሁ ፈቃድ ድል ከነሣችሁት ለዘለዓለም ሕያዋን ትሆናላችሁ፡፡ የነፍሳቸውን ፈቃድ የሚሠሩ ሰዎች ሁሉ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸውና፡፡” /ሮሜ ፰፥፲፪-፲፬/፡፡


ዘመነ ጾም    

 
በቅዱስ ያሬድ ጾመ ድጓ ዘወረደ እየተባለ የሚታወቀው፣ በጾመ ዐርባው ወቅት በተለይም በመጀመሪያው ሣምንት የሚገኘው ድርሰት በነግህ በሠለስት፣ በቀትርና በሠርክ እንደዚሁም ቅዳሜና እሑድ በሌሊት የሚዘመር ነው፡፡ በውስጡም የያዘው ፍሬ ሐሳብ የጾምን፣ የጸሎትን፣ የምጽዋትንና የፍቅርን ጠቃሚነት አጕልቶ የሚያስተምር ነው፡፡

ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በዘወረደ ጾመ ድጓው  “እግዚአብሔር  ሙሴን ሕዝብህ  የከብትህ  መንጋህ  ቤተሰብህ  ሁሉ በሰንበት  ቀን  ከድካማቸው ይረፉ በማለት አዘዘው”  በማለት ሰንበት ለሰው ልጆች ብቻ ሳይሆን፣ ሕይወት ላለው ነገር ሁሉ ጸጥታና ሰላም የሰፈነባት የዕረፍት ቀን ስለመሆኗ ተናግሯል /ዘፀ.፳፥፲፤ ፳፫፥፲፪/፡፡ በዚህም ወቅቱ “ዘመነ ጾም”  ወይም “ጾመ ሙሴ”  ይባላል፡፡


እንደ ማጠቃለያ


ጾም ከእግዚአብሔር ለሰው ልጆች የተሰጠ በረከት ነው፡፡ ነቢዩ ኢዩኤል “ጾምን  ያዙ፤ አጽኑ፡፡ ምሕላንም  ዐውጁ፡፡ ሸማግሌዎቹን  ከፈጣሪያችን  ቤት  ሰብስባችሁ  በአንድነት  ሆናችሁ ወደ  እግዚአብሔር  ጩኹ”  እንዲል /ኢዩ.፩፥፲፩፤፪፥፲፪፤፲፪፥፲፭-፲፮/፡፡  ጾም አበው ቅዱሳን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በጊዜ ቀምረው፣ በበታ ወስነው፣ በሁኔታ ገድበው… ባስቀመጡልን ወቅት ከእህልና ከውኃ በመከልከልና ሰውነትን በማድከም ብቻ ሳይሆን ለስሕተት ከሚዳርጉ ነገሮችና ቦታዎች ተቆጥቦ በጸሎት መትጋትም እጅጉን አስፈላጊ ነው፡፡

ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊትም ይህንን እውነታ በተመለከተ እንዲህ ይላል፡፡ “እኔ ግን እዘንልን፤ ለምንልን ባሉኝ ጊዜ ማቅ ለብሼ አዘንኩላቸው፤ ሰውነቴን በጾም አደከምኩዋት፤ ልመናዬም እኔም ወደመጥቀም ተመለሰችልኝ፡፡” /መዝ. ፴፬/፴፭፥፲፫/፡፡ ሠለስቱ ምዕትም “ሐዋርያት  የጾሙትንና  እንዲጾም  የወሰኑትን  መጾም  ይገባል”  ብለው አጽዋማትን እንድንጾም ወስነዋል፡፡  
                እግዚአብሔር አምላክ ጾሙን የበረከት ጾም ያድርግልን፡፡ አሜን፡፡
                               ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ዋቤ መጻሕፍት፡-
✍️ መጽሐፍ ቅዱስ
✍️ ፍትሐ ነገሥት
✍️ መጽሐፈ ድጓ
✍️ ሃይማኖት አበው
✍️ መጽሐፈ ስንክሳር
✍️ የቤተክርስቲያን ታሪክ በኢትዮጵያ
✍️ በዓላት
✍️ ጾምና ምጽዋት
✍️ Enclopedia of Aethiopica

በመ/ር ጌታቸው በቀለ

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ከ989 ሚሊዮን ብር በላይ የኮንትሮባንድ እቃዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

የጉምሩክ ኮሚሽን ከግንቦት 27 እስከ ሰኔ 3 ቀን 2018...

“እኔ እስካለሁ ድረስ ኢራን የኑክሌር መሣሪያ ባለቤት አትሆንም!”

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ትናንት ሰኔ 5 ቀን...

አገር እንዲህ ዓይንህን ለአፈር ይባላል?

በተጀመረው የአለም ዋንጫ ደቡብ አፍሪካ በሜክሲኮ መሸነፏን ተከትሎ አፍሪካ...

አሜሪካ እና ኢራን የመጀመሪያ ደረጃ ስምምነት በ24 ሰዓት ውስጥ እንደሚፈራረሙ ፓኪስታን አስታወቀች

ዩናይትድ ስቴትስ እና ኢራን በሰላም ድርድሩ ማዕቀፎች ላይ መስማማታቸውን...