
ከጥቂት ሳምንታት በፊት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የተሠማው ዜና አሳዛኝ እና አስደንጋጭ ነው፡፡ ኢትዮጵያን እንደ ሀገር ለማፍረስ ዘመናትን በተሻገረው ውጥን፣ ይቺ ቤተክርስቲያን መልከ ብዙ የጥፋት እና የጥቃት ዒላማ ኾና እንደኖረች አይካድም፡፡ ኾኖም የነበሩት ሒደቶች ኹሉ ሳይበግሯት እዚህ መደረሷ ጠላቶቿ ሌላ መላ እንዲመትሩ እንጂ ተስፋ ቆርጠው እንዲተኙ አላደረጋቸውም፡፡ ለዚህም ይመስላል፣ በርካታ የኢትዮጵያዊነት ካስማዎች ተንደው እና ተነቃቅለው ባለቁበት፣ ሀገራችንም እንደ “ሀገር” ለመቀጠል ጥቂት የሳሱ ክሮች የቀሯት በመሰሉት በዚህ አደገኛ ጊዜ፣ የኢትዮጵያን ተስካር ለማየት የጓጉ ሕልመኞች ያለ የሌለ ኃይላቸውን የቤተክርስቲያኗን ሕላዌ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ለማጥፋት ቆርጠው የተነሱት፡፡
ለዚህ ጉልህ ማሳያ የሚኾው ጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም በደቡብ ምእራብ ሸዋ ዞን ሶዶ ዳጬ ወረዳ በምትገኘው ሀሮ በዓለወልድ ቤተክርስቲያን የአንድ ዘውግ ፖለቲካ አቀንቃኞች ከቤተክርስቲያኒቱ ቀኖና ባፈነገጠ መንገድ በቋንቋ እና በብሔር ማንነታቸው ተለይተው ለተመረጡ 26 ቆሞሳት እና መነኮሳት ሰጡት የተባለው የ”ኤጲስ ቆጶስ”ነት ሹመት ነው። በዚህ በገጠራማ ሥፍራ በሚገኝ ቤተክርስቲያን የተፈጸመውን ቀኖናን የጣሰ አካሔድ ለማስቆም የተንቀሳቀሱ የአካባቢው ምእመናንም ሿሚና ተሿሚዎቹ ባሰለፏቸው መሣሪያን ያነገቱ ታጣቂዎች ምክንያት ሳይሳካላቸው መቅረቱ ጉዳዩ ምን ያህል ሥውር ዓላማን ያነገበ ለመኾኑ ብርቱ ማሳያ ነው፡፡ ይኽም የኋላ ኋላ ለገነፈለው የሕዝበ ክርስቲያኑ ቁጣ መንግሥትን ቀዳሚ ተወቃሽ እንዲኾን ከበቂ በላይ ምክንያት ኾኗል፡፡
መንግሥት ከዚህ ቀደም ለሁለት ተከፍሎ በሀገር ውስጥ እና በውጪ የነበረውን ቅዱስ ሲኖዶስ በእርቅ ወደ አንድነት በማምጣቱ መወድስ የሰጡት ወገኖችም፣ አሁን ላይ ቤተክርስቲያኒቱን ዘውግን ማዕከል ባደረገ ክፍፍል ለማፍረስ እየተሔደ ያለበትን ርቀት በዝምታ፣ አንዳንዴም ግልጽ በኾነ ድጋፍ ሲያጋግም መታየቱን በመጥቀስ ተቃውሟቸውን እየገለጹ ነው፡፡ በርግጥም ሀገራችን ካለፉት ዐራት ዓመታት ወዲህ እያለፈችበት ያለው የሕልውና ፈተና በቅጡ እንኳን ጋብ ሳይል፣ ለሺህ ዓመታት ሐዋሪያዊ እና ሀገራዊ ኾና የኖረችውን ቤተክርስቲያን እንዲህ ባለ መንገድ ለማፍረስ የተነሱ ቡድኖችን ስውር እና ግልጽ የኾኑ ድጋፎችን በመሥጠት ‹‹ግፉበት›› ማለቱ ምን ለመፍጠር ተፈልጎ ነው የሚለው ለብዙዎች ጥያቄ ከመኾን የተሻገረ ይመስላል፡፡
ዳሩ ግን አንድ መታወቅ ያለበት ንጥረ ሐቅ አለ፡፡ የኢትዮጵያዊ መልክ እና ሥሪት ኖሯቸው ለዘመናት የኖሩ፣ ከነገድ እና ከቋንቋ ማንነት ተሻግረው ዜጎችን አሰባሳቢ እና አስተባባሪ የሆኑ የሃይማኖት ተቋማትን እንዲህ ባለ መንገድ ለመሰንጠቅ፣ ለማኮሰስ እና ምእመኖቻቸውን ለማዋረድ መሔድ ዳፋው ለሀገር እንደሚተርፍ ለአፍታም ቢሆን መዘንጋት አይገባም፡፡
ሌላው ቢቀር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በፍትሓብሔር ሕጋዊ ሰውነት ያላት እና መብቷ ሊከበርላት የሚገባ ሉዓላዊት ተቋም ኾና ሳለ መንግሥት ሴኪዩላር በተባለው ሕግ ሳይቀር ሊያስኬደው የማይችል አቋምን ይዞ ለመታየት መንቀሳቀሱ እጅግ ያስተዛዝባል፡፡ ሀገሪቱ አሁን ላይ ከምትከተለው ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ውጪ ‹‹የሽግግር መንግሥት መሥርተናል” የሚሉ ቡድኖች ቢነሱ መንግሥት የሚወስደው እርምጃ ምን ሊኾን እንደሚችል ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ከዚህ ቀደምም በተለያየ መልኩ እንዲህ ዐይነት ቅርጽ ተላብሰዋል ብሎ ያመነባቸውን መሰባሰቦች አስመልክቶ ክቡር ጠ/ሚኒስትሩ ራሳቸው በግንባር ሚዲያ ላይ ወጥተው ያሰሟቸውን ዛቻዎች እና ኃይለቃሎች ማስታወስም አይከብድም፡፡
መንግሥትም ኾነ ክቡር ጠ/ሚኒስትሩ በተደጋጋሚ ‹‹ሀገር ናት›› ያሏትን የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን እንዲህ አማኞቿን እርስ በርስ ከመከፋፈል ጀምሮ ለግጭት እና ለብጥብጥ የሚዳርግ ሕገወጥ ድርጊት ሲፈጸም ሚናውን በተገቢው መልኩ ከመወጣት ዳተኛ መኾንን ምን አመጣው? የሚለው ጥያቄ መሠረታዊ የሚኾነውም ለዚህ ነው፡፡ አንድ መታወቅ ያለበት እውነታ ግን የሃይማኖት ተቋማት ሕልውና አማኝ ከኾነው አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ሕላዌ ጋር ያለው ጥብቅ ቁርኝት ነው፡፡ ይኽ በመኾኑ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየሰማናቸው ያሉ ለዘመናት የኖሩ ሃይማኖታዊ ተቋማትን በወቅት እና በፖለቲካ መሻት የመሰንጠቅ አካሔዶች አደጋቸው ዞሮ ዞሮ ሀገርን የማፍረስ ነውና ሁሉም ኢትዮጵያዊ ጉዳዩ ሊገድደው ይገባል ስንል መልዕክታችንን ለማስተላለፍ እንወዳለን፡፡