የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ2017 ዓ.ም የስራ ዘመኑ ከቀረቡለት 56 አዋጆች ውስጥ 49 አዋጆችን ማጽደቁ ተገለጸ።
ምክር ቤቱ የስራ ዘመኑን አፈጻጸም አስመልክቶ ባቀረበው የዕቅድ ክንውን ሪፖርት እንዳስታወቀው ካጸደቃቸው 49 አዋጆች ውስጥ 34 አዋጆች ለቋሚ ኮሚቴዎች ተመርቶ ይፋዊ የሕዝብ ውይይት ተደርጎ በሁለተኛ ንባብ ጸድቀዋል ብሏል።
15 አዋጆች ደግሞ የህዝብ ውይይት ሳይደረግባቸው ወደ ሁለተኛ ንባብ ተሸጋግረው መፅደቃቸውን አመላክቷል።
ለምክር ቤቱ ከቀረቡት 56 የሚሆኑ አዋጆች ውስጥ ሰባቱ አለመጽደቃቸውን የጠቆመው ምክር ቤቱ በተጨማሪም ከ2016 የተሸጋገሩ 2 አዋጆችም በተጠናቀቀው የምክር ቤቱ የስራ ዘመን በ2017 ዓ.ም አለመጽደቃቸውን አስታውቋል፤ አዋጆቹ ምን መሆናቸውን አልጠቀሰም።
በአጠቃላይ 9 አዋጆች ወደ 2018 በጀት ዓመት መሻገራቸውን የምክር ቤቱ ምክትል አፈ-ጉባኤ ወ/ሮ ሎሚ በዶ ባቀረቡት የምክር ቤቱን የ2017 በጀት ዓመት የተጠቃለለ የዕቅድ ክንውን ሪፖርት ተመላክቷል።
በተጨማሪም ምክር ቤቱ በስራ ዘመኑ የአስፈጻሚ ተቋማት ሚኒስትሮች በምክር ቤቱ በአካል በመገኘት የስድስት፣ የዘጠኝ እና 11 ወራት የዕቅድ ክንውን ሪፖርት እንዲያቀርቡና ከአባላትና ከሕዝቡ በተነሡ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ላይ ምላሽና ማብራሪያ እንዲሰጡ መደረጉንም አስታውቋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ2017 ዓ.ም የስራ ዘመኑ 43 መደበኛ ስብሰባዎችና 3 ልዩ ስብሰባዎች ማካሄዱን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
