የመድፉ ባለሟል ሻለቃ አለማየሁ ዘውዴ

Date:

እናት ሀገር በአራቱም ማዕዘን ጦርነት በተከፈተባት በዚያ  በውጥረት ዘመን ወጣቶች ሁሉ የሚንሾካሾኩት ከወታደራዊው መንግስት ስለቀረበው የሀገርክን አድን ጥሪ  ነበር። 1970 ጥቅምት ወር ወጣቱ  አለማየሁ  ዘውዴም የምስራቁን የሶማሊያ ወረራ ከመስማት አልፎ የዘማቹን  ምሊሽያ ተመልክተዋል። በወረራው የተፈናቀሉ የምስራቅ  ከተሞች ነዋሪዋች ህፃናትን ይዘው በየቀበሌው ተጠልለው  ተመልክተዋአል። ልባቸው ወደ ዘመቻ ከሸፈተ ሰነባብቷል።

ወረሀ ጥቅምት ላይ  የነበልባል መምሪያ አዲስ ወታደሮች ለመቅጠር  ሞጆ  ከተማ ላይ ምዝገባ እየካሄደ  የተመለከቱት ወጣቱ አለማየሁ ዘውዴ   አላወላወሉም  ከጓደኞቻቸው ጋር  ተመዝግበው ጨርቄን  ማቄን ሳይሉ በለበሱት ልብስ በወቅቱ ቆሞ በሚጠብቀው  የተወታደር  መኪና ተሳፍረው ጉዞ ወደ ደብረ ዘይት ያደርጋሉ።

ደብረዘይት የሚገኘው የብሔራዊ ጦር ማሰልጠኛ ግቢ  እንደደረሱ በግቢው ቀደም ብለው ከተለያየ ከተሞች  ከተሰበሰቡ  ወጣቶች ጋር  ተቀላቅለው ትንሽ  ጊዜ  እንዲጠብቁ  ይነገራቸዋል።ትንሽ  ቆይቶ አንድ የወታደር ዩኒፎርም አሟልቶ የለበሰ ሰው የተሰበሰቡትን  ወጣቶች  ከግቢው ወጥተው እስፋልቱን በማቋረጥ ከአዲስ አበባ  ድሬድዋ የተዘረጋው የባቡር መስመር(ሀዲድ) አጠገብ ባቡር  እንዲጠብቁ  ይነገራቸውና  ከግቢው ይወጣሉ ከጥቂት ቆይታ በኃላ የተባለው  ባቡር  መጥቶ ይቆማል ወጣቶቹ  ያለምንም ግርግር ተሳፍረው እንዳበቁ  ባቡሩ ጉዞውን  ይጀምራል የተሳፈሩበት ባቡር ናዝሬት ጣቢያ ሲደርስ  ይቆማል ወጣቶቹ  ለምን አይሄድም ይላሉ?! መልስ የሚሰጥ  የለም?! ከቆይታ  በኃላ  ውረዱ  የሚል  ትዕዛዝ  የሚያስተላልፍ ወታደራዊ  ልብስ የለበሰ ሰው ተከትለው  ወደ ናዝሬት  ከተማ  በመግባት  በኃይለማሪያም  ማሞ መታሰቢያ  ሆስፒታል ሜዲካል ምርመራ አጠናቀው  ወደባቡር ጣቢያው ሲመለሱ ባቡሩ ቆሞ ይጠብቃቸው ነበረ።በቀጣይ ተሳፍረው  በመጓዝ  አዋሽ  አርባ  የነበልባ ማሰልጠኛ  ይደርሳሉ። 

በማሰልጠኛው ከመላው ሀገሪቱ የተሰባሰቡ በብዙ ሽህ  የሚቆጠሩ ምልምሎች ጋር  ይደባለቃሉ። ይህ ማሰልጠኛ  በሰው ተጨናንቆ  መሰረታዊ  ነገሮች ለማሟላት እንከኖች ቢኖሩም ስለጠናውን ከመጀመር አላገዱትም። የሰልፍ  ትምህርት ወዘተ እየተካሄደባለበት  25ኛ ቀን በግቢው  ውስጥ  አንድ ነገር  ተፈጠረ  የሁሉም  ምልምል  የቀለብ  ሰነድ ማስፈረሚያ  እየተቀደደ  በጀርባው  ላይ በቃል  የሚነገሩ ጥያቄዋችን  በመፃፍ  መልሱን  አስፍረው  አንዲመልሱ ይታዘዛሉ በዚህ  አይነት ፈተና ላይ የተቀመጡት  ምልምል  ወታደር  አለማየሁ  ዘውዴ  ፈተናውን  በውጤት  በመደምደም በመኪና ተጭነው አዋሽ አረባ ወደ ሚገኘው  ካምፕ ተወሰዱ።

 ከተወሰዱት የመጀመሪያዋቹ አንዱ ቢሆኑም ለምን ጉዳይ እንደሆነ ያወቁት እዚያ ሲደርሱ  ነበር።በአዲሱ ካምኘ የኩባ  ወታደሮችና መኮንኖችም  ይገኙ ነበር በወቅቱ  ኩባዊያኑ  ያስደስታሉ ይዘምራሉ በከባድ  ሁኔታ በዚያ ንዳድ  ፀሀይ  ይሰራሉ ለኢትዮጰያዊያን በፍቅርና በፈገግታ ለማስተናገድና  ለመተዋወቅ  ይታትራሉ።ለኢትዮጰያዊያኑ ሌላ ነዳጅና አነሳሽ ለመሆን ችላል የኩባዊያኑ ቅንነት።ምልምል ወታደር  አለማየሁ ዘውዴ  አሁን የተፈለጉበት  ሙያ  በመድፈኛነት  ሀገራቸውን እንዲያገለግል ስለሆነ አዲስ በተቋቋመው  የ4ኛ  መድፈኛ  ብርጌድ   መምሪያ  ግንባር  ቀደም  አስተኳሽ  (ኦፒ) የመቶ  ውስጥ በመመደብ ትምህርታቸውን ተያያዙት።  ወደ ተመረጠ  ወረዳ  በእግር እየተጓዙ ትምህርታቸውን  ባልተሰላቸ ሁኔታ ቀጠሉ።    

ብርጌዱ በየካቲት ወር ላይ ወደ መቀሌ እንዲጓጓዝ  ትዕዛዝ  ደርሶት ተንቀሳቅሶ መቀሌ ደርሶም ተጨማሪ  ትምህርት  አልተቋረጠም አንዲህ እያለ እልህ አስጨራሹን ወታደራዊ ጥበብ በሚያከናውኑበት ወቅት ውጊያው ተጀምሮ  ለምን  ግንባር  አንገባም  እያለ ይጠይቃሉ።አዛዦችም  ትደርሳላችሁ  ሁሉም  ግንባር  አይገባም  እያሉ ያረጋጋሉ። በእንደዚህ  ያለ  ሁኔታ  ደጀን  ሆኖ ደቀመሀሪ  የደረሱት  ወታደር  አለማየሁ  ዘውዴ  ለሌላ  ትምህርት በመታጨት አስር  ከሚሆኑ የርሳቸው ቅጥርና  የክፍል  አጋሮቻቸው  ጋር  ወደ አስመራ  በመላክ ወ/ር  አለማየሁ  ዘውዴ  ትምህርቸውን በማጠናቀቅ የ20ኛው  ነበልባል ብርጌድ የሻለቃ ኮሚሳር ሆነው በመመደብ  ከመድፈኛነት  ወደ  እግረኛነት  ተዛውረው  በአስመራ  ዙሪያ  ውጊያዎች  መሳተፍ ጀመሩ።

 በ1971  ወርሀ  ሴኔ  ለልዩ  ግዳጅ  በኮሎኔል  ካሳ ገብረ  ማሪያም  አዛዥነት  ወደ  ሩራፀሊም  የዘመተው  ጦር  አካል  የሆነው  20ኛ ነበልባል ብርጌድ ውስጥ  የሻለቃ  ኮሚሳር የሆኑት ወ/ር  አለማየሁ ዘውዴ  ከምፅዋ  ተነስተው  በሸኢብ  በኩል አድርገው ሩራፀሊም  እስኪደርሱ  ድረስ  ድል በድል  ላይ  እየተሻገሩ ሩራፀሊም ይደርሳሉ።የሩራ ፀሊም ግዳጅ  በቀዳሚ መምሪያ ዘመቻ መኮንን ገ/ክርስቶስ  ቡሊ ትዕዛዝ  ሲበላሽና  ሶስቱ  ብርጌዶች  ከበባ ውስጥ  ሲወድቁ  የግብረኃይሉን  አዛዥ ኮሎኔል  ካሳ ገ/ማሪያምንና  መምሪያውን  ይዞ  ለመውጣት የ20ኛ ብርጌድ  አዛዥ  የነበሩት  ኮሎኔል  ከተማ  አይተንፍሱ  ወደእኔ  ይምጡና  ከበባውን  ሰብረን  እንውጣ  ሲሉ ያቀረቡላቸውን  ጥያቄ  ያልተቀበሉት ኮሎኔል  ካሳ  ገ/ማሪያም አንተ  የፈለከውን  እርምጃ እንድትወስድ  ፈቅጄልሀለሁ የሚል ምላሽን በማግኘታቸው 20ኛ ነ/ ብርጌድን  በማስተባበር  በአልጌና መስመር ይዞ  ለመውጣት በተደረገው  ትንቅንቅ ውስጥ የሻለቃ  ኮሚሳር  ወ/ር አለማየሁ ዘውዴ ሻለቃውን  በማስተባበር  ውጤታማ  ስራ ካከናወኑ  የክፍሉ አባላት ይጠቀሳሉ። 

በቀጣይ ለውጭ ሀገር  ትምህርት ከወራት በኃላ ከአልጌና  ወደ አስመራ  የመጡት ኮሚሳር  ወደ ታሰበለት ትምህርት  ሳየሄዱ አልጌና ግንባር  ሻዕቢያ እስትራተጂክ የሆነውን  የካተር ተራራን ለማስለቀቅ በከፈተው ከፍተኛ ማጥቃት ሳቢያ  ግንባሩን ለማስተባበር  ከተመደቡ የዕዙ  አባላት  ጋር  ተመልሰው  እንዲሄዱ በመደረጉ  ወደአልጌና በመመለስ የተከፈተውን መጠነ ሰፊ የሻዕቢያ ማጥቃት ለመመከት ከፍተኛ አስተዋፅኦን አድርገዋል። ከጥቂት ጊዜ  በኃላ በአልጌና ግንባር  እያሉ ለመላ ሰራዊቱ በተሰጠውን የ41ኛው ዙር  የእጩ መኮንንነት ፈተና ተሳትፈው በማለፋቸው ወደ ሆለታ ገነት ጦር ት/ ቤ ት ሊገቡ ችለዋል።

እጩ  መኮንን አለማየሁ ዘውዴ በኮርስ ቆይታቸው ቀድመው  ስልጠና ከጀመሩበት የመድፈኛነት  ሙያ ጋር  ድጋሚ  እንዲገናኙ  አስቻላቸው።ቀስመት የነበረውን የመድፈኛነት  ጥበብ በጦር  ትምህርት ቤቱ  አዳብረው የተመረቁት  ም/መ/ አለቃ አለማየሁ  ዘውዴ የ27ኛ  ሜካናይዝድ  ብርጌድ መድፈኛ ሻለቃ  የሆነው 275ኛ መድፈኛ ውስጥ ረዳት  ባትሪ  አዛዥ ሆነው ስራ በመጀመር  የመድፉ  ሊቀ መኳስነታቸውን በተግባር  አሰይይተዋል። ከ275ኛ መድፈኛ ጋር በመሆን ከማይሚዶ  ጀምሮ  እሰከ  አስመራ ዙሪያ  ግዳጃቸውን አመርቂ በሆነ ሁኔታ በመወጣት ላይ በሚገኙበት ወቅት ይህ አጋጣሚ ይፈጠራል።

ወቅቱ 1978 ዓ/ም ነው  ሻዕቢያ ባሬንቱን ወሮ  በመያዙ  የመልሶ ማጥቃት ይካሄዳል የመቶ  አለቃ  አለማየሁ  ዘውዴ  የሚመሩት ባትሪ  ለ21ኛ  ክፍለ ጦር ተደራቢ ሆኖ እግረኛ  ሰራዊቱ ማጐራቫይ በተባለው  ቦታ  እልህ  አስጨረሰሽ  ትንቅንቅ ተያይዞአል የሻዕቢያ ካሊበሮችና ዶሽቃዎች  እግረኛውን  አላንቀሳቅስ ብለዋል የሻለቃና የብርጌድ አዛዦች ክፍለ ጦሩን ይወተውታሉ የክፍለ  ጦሩ  አዛዥ  የተመደበላቸውን  መድፈኛች  ይህንን  ኢላማ  እንዲያጠፉ  ትዕዛዛቸውን ያስተላልፋሉ።

ጠንቃቃው  መድፈኛ ኢላማዎቻቸውን ነጥበው በመያዝ    ትዕዛዙ በደረሳቸው በደቂቃዎች ውስጥ ኢላማዋቹን አንድ ከአንድ ፀጥ በማሰኘት ላንቃቸውን እንዲዘጉ በማድረጋቸው እግረኛው ተሰፈንጥሮ ከጠላት ምሽግ በመግባት  ጠላትን ደምስሶ ቦታውን ይይዛል። ከተሰነይ አቅጣጫ  በጀ/ ደምሴ  ቡልቱ  የሚመራው የወገን  ጦር ግስጋሴውን  ቀጥሎ ባሬንቱን  መልሶ ይቆጣጠራል  ውጤታማው  የመድፈኛ  ባትሪ  አዛዥ  በተከታይ  ቀናት  የ27  ሜካናይዝድ  ብርጌድ  አዛዥ  ከነበሩት ኮሎኔል  በላይ  አስጨናቂ  ዘንድ  በመጠራት በተፋጠነ የማዕረግ እድገት የሻምበልነት ማዕረግ ተሰጥቷቸዋል። 

ሻምበል አለማየሁ ዘውዴ ከባሬንቱ  መልስ  ከ275 መድፈኛ ጋር  ፎሮ አና አዱሊስ በሚባሉት  አካባቢዎች  የመድፍ  ድጋፍ  ለሚፈልጉ  ክፍሎች  ግዳጃቸው ሲወጡ ቆይተው   አውጋሮ ላይ  ወደሚገኘው 2ኛ መድፈኛ  ሻለቃ በመዘዋወር በምክትል ሻለቃ አዛዥነት እና በዘመቻ መኮንንነት  አሰቸጋሪ  ግዳጆችን ተወጥተዋል።

በቀጣይ በሻለቃነት ማዕረግ የ16ኛ ሰንጥቅ መድፈኛ ሻለቃ አዛዥ በመሆን በነፋሲትና በደቀመሀሪ ግንባሮች ለእግረኛው ሰራዊት የተኩስ ኃይል  ድጋፍ በመስጠት ግዳጅ ላይ ቆይተው በመጨረሻው ሰአት ሰራዊቱ ወደ ሱዳን ሲወጣ አብረው በመውጣት በግል ስራ ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ።

ክብርና ምስጋና ለቀድሞው ሰራዊት አባላት!!!ምንጭ፡- Former Ethiopian Armed Force-የቀድሞዉ የኢትዮጵያ ሠራዊት

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የአንበሶቹ ትንሳኤ፦ የዳካር እንባ እና የቴራንጋ ድል

​በዳካር ሰማይ ስር ዛሬ ጨረቃ አልወጣችም፤ ይልቁንም በሚሊዮን የሚቆጠሩ...

የጥምቀት በዓል በመላ ሀገሪቱ በድምቀት እየተከበረ ነው

የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እና በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት...

“ሎዛ ዘፀአት”እና “የሎዛ ድርሳናት”ተከታታይ ረጅም ልቦለድ መጻሕፍት ተመረቁ

በጋዜጠኛና ደራሲ መርዕድ እስጢፋኖስ የተጻፉት ሎዛ ዘፀአት(2014 ዓ.ም) እና...

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለጥምቀት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

እንኳን ለኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓል አደረሳችሁ፣ አደረሰን!! በክርስቲያኖች ዘንድ ጥምቀት...