ከዩሮፓ ሊግ ፍጻሜ ሽንፈት በኋላ ከመገናኛ ብዙሃን ቆይታ ያደረጉት አሰልጣኙ “የክለቡ ባለቤቶች እና ደጋፊዎች ትክክለኛው አሰልጣኝ እንዳልሆንኩ ከተሰማቸው ካሳ ሳልጠይቅ እወጣለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።
አክለውም “ የደጋፊዎቻችን ሃዘን ይሰማኛል የተሻለ ውጤት ይገባን ነበር” በማለት በጨዋታው የነበራቸውን ብልጫ ጠቅሰዋል።
ስራቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ይለቁ እንደሆን ሲጠየቁ ፈቃደኛ አለመሆናቸውን በመግለጽ በክለቡ አሰልጣኝነት እንደሚቀጥሉ አስረግጠዋል።
ፖርቱጋላዊው አሰልጣኝ የቡድናቸውን ድክመት በተመለከተ ፊት ለፊት ቀጥተኛ ሆነው በመናገር ይታወቃሉ።
ማንችስተር ዩናይትድ በታሪኩ እጅግ ደካማውን የውድድር አመት ያሳለፈ ሲሆን ብቸኛ ተስፋውን ካደረገበት ዩሮፓ ሊግም አሳዛኝ ተሸናፊ ሆኗል።
ዩሮፓ ሊግን በማሸነፍ የቻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊነትን ለማሳካት ያለመ እቅዱም መክኖበታል።
ዩናይትድ በሚቀጥለው አመት ከየትኛውም የአውሮፓ ውድድር ውጭ መሆኑና ደካማ የውድድር አመት ማሳለፉ በክረምት የዝውውር መስኮት የሚፈልጓቸውን ተጫዋቾች ለማግኘት መሰናክል ሊሆንባቸው ይችላል ተብሏል።
በፕሪምየር ሊግ 39 ነጥብ በመያዝ 16ኛ ስፍራ ላይ የሚገኘው ዩናይትድ የፊታችን እሁድ አስቶን ቪላን በመግጠም የውድድር አመቱን ያጠናቅቃል።
