የማይዳሰሰው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት – የቁጥር ጨዋታ

Date:

በክቡር ገና

  • የማያባራው ጦርነት
  • የዋጋ ንረት እንቆቅልሽ
  • ብድር – ግዙፉ ዝሆን
  • የሀገር ውስጥ አመታዊ ጠቅላላ ምርት (GDP) – የተስፋ ዳቦ
  • መላው ምንድነው?

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ኢትዮጵያ ባለፈው አመት 7.1 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት አስመዝግባለች ይለናል፡፡ ቁጥሩ ወረቀት ላይ ያስደንቃል፡፡ መንግሥትም ሆነ አንዳንድ ዓለም አቀፍ ተቋማት ዜናውን ለማስተጋባት ይፈጥናሉ፡፡ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ እመርታ ላይ እንደሆነች ያውጃሉ፡፡

ነገር ግን ዘወትር እንደሚሆነው ሁሉ ዜናው ሌላ ታሪክ አለው፡፡ እንደሚታወቀው ቁጥሮች ይፈበረካሉ፡፡ በመሬት ላይ ያለው እውነታን አይቶ እንዳላየ በማለፍ ቁጥሮች ይፈበረካሉ፡፡ እናም እውነታው በጠራራ ፀሐይ እንዲደበቅ ይደረጋል፡፡

በጦርንት፣ በመፈናቀልና በዋጋ ንረት ፍዳዋን እያየች ያለችው ኢትዮጵያን በዓለም ላይ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገበች ያለች ሀገር ነች ይሏታል፡፡ ለአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ግን ይህ እድገት እንደ ሕልም ዓለም በርቀት የሚሰማና የሚታይ ቅዠት እንጂ በዜጋው የዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ የሚታይ አይደለም፡፡  እስቲ ጉዳዩን ዘለቅ ብለን እንየው፡-

የማያባራው ጦርነት

ኢትዮጵያ አሁንም እስከ ጉልበቷ ከተዘፈቀችበት ጦርነት አልጣችም፡፡ በፕሪቶሪያ የተፈረመው የሰላም ስምምነት በትግራይ የጠመንጃዎችን ላንቃ ቢዘጋም በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ግን የጦርነቱ የእሳት ላንቃ አሁንም እየተንቀለቀለ ነው፡፡ አሁንም ውድመት፣ መፈናቀል፣ የአውራ ጎዳናዎች መዘጋት፣ የተመረተውን እንኳ መሰብሰብ ያለመቻል፣ የቤተሰብ መበተንና እንደ ማህበረሰብ ተስፋ መቁረጥ የወቅቱ የሕይወት ገጽታ ሆኗል፡፡ ለዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ግን እነዚህ የሕይወት ሰቆቃዎች ከቁብ የሚቆጠሩ አይደሉም፡፡ ለዚህ ተቋም ጦርነት በዓመታዊ ጠቅላላ ምርት (GDP) እድገት ላይ ተጽዕኖ የለውም አሉ!

በዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ሪፖርት ውስጥ በሀገሪቱ እየካሄደ ስላለው ጦርነት የሚጠቀስ ነገር የለም፡፡ በተቋሙ የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ትረካ ውስጥ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ያለው መከራና ስቃይ የግርጌ ማስታወሻ ላይ የሚቀመጥ ነጥብ ያህል እንኳ ፋይዳ የለውም፡፡ ይህ ለሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ግን የሰበር ዜና ያህል ዋንኛ ርዕሰ አንቀጽ ነው፡፡ ኧረ ለመሆኑ የእርሻ ማሳዎች ጦማቸውን አድረው፣ ፋብሪካዎች ተዘግተው፣ ሚሊዮኖች ከቀያቸው ተፈናቅለውና ቤተሰቦች ተበትነው እንዴት ነው የኢኮኖሚ እድገት የሚመዘገበው?

የዋጋ ንረት እንቆቅልሽ

የዋጋ ንረቱ ከ32.5 በመቶ ወደ 20.7 በመቶ ዝቅ አለ ይሉናል፡፡ ይህም እንደ ስኬት ተቆጥሮ ብዙ ይባልለታል፡፡ ምስጥ ትልቁን ግንድ ቦርቡሮ እንደሚበላው ሁሉ ይህ ቀነሰ የተባለው 20 በመቶ የዋጋ ንረት እንኳ የአብዛኛውን ዜጋ የመግዛት አቅም እንደ ምስጥ በልቶ ያመነምነዋል፡፡ በመሆኑም የዳቦ፣ የነዳጅና የሌሎች መሠረታዊ ሸቀጦች ዋጋ ንሮ ሕይወትን እንደ መርግ ያከብደዋል፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ ደሞዝም ሆነ የዕለት ገቢ ባለበት እየረገጠ ነው፡፡ አድጓል የተባለው የደሞዝ ጭማሪም ውጤቱ ታይቷል፡፡

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ያወጣው ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ ተግባራዊ በመደረጉና ይህም ባንኮች የሚያንቀሳቅሱት የጥሬ ገንዘብ ዝውውር በመታነቁ የዋጋ ንረቱ የቀነሰ መስሏል፡፡ መንግሥትም የጥሬ ገንዘብ የሚፈስበትን ቧንቧ በመዝጋቱ የንግድ ሥራ የሚያከናውኑ የግል ድርጅቶች ብድር ማግኘት አልቻሉም፣ አምራቾች ለምርት ግብአት መግዣ የሚሆን ብድር ተነፍገዋል እንዲሁም በግብርናው ዘርፍ የተሰማሩ ዜጎች ለተለያዩ ግብአቶች የሚሆኑ ብድሮችን ማግኘት ባለመቻላቸው የኢኮኖሚው እድገት ታንቋል ማለት ይቻላል፡፡ ተቋሙ ግን መመሪያው ተግባራዊ ስለተደረገለት እድገት ተመዝግቧል ይለናል፡፡

ብድር – ግዙፉ ዝሆን

ኢትዮጵያ በቢሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር የውጭና የሀገር ውስጥ እዳ አናቷ ላይ የሚያናጥባት ሀገር ስትሆን የቅርብ ጊዜ መረጃዎች እንደሚያሳዩት የሀገሪቱ እዳ ከአጠቃለይ ዓመታዊ የሀገር ውስጥ ምርት 50 በመቶ ያህል ደርሷል፡፡ እናም የሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት በሚበሰርብት አጋጣሚ ሁሉ የሀገሪቱ ዕዳ ያልተጋበዘ እንግዳ ሆኖ በየመድረኩ እንደ ግዙፍ ዝሆን ይደነቀራል፡፡ እውነታውን የቱንም ያህል ለመሸፋፈንና ለመደባቅ ቢሞከርም በክፍል ውስጥ የተደነቀረውን ግዙፍ ዝሆን መደበቅ እንደማይቻል ሁሉ የሀገሪቱን ዕዳንም መደበቅ አልተቻለም፡፡ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ሆዬ ግን የሀገሪቱ የእዳ ሁኔታ ይህን ያህል የከፋ ሆኖም ሳለ መንግሥት ከዓለም አቀፍ አበዳሪዎች የእዳ ሽግሽግና የእፎይታ ጊዜ ለማግኘት የሚያደርገውን ጥረት ሲያደንቅ ይታያል፡፡ በዚያ ላይ ሀገሪቱ ያላት የውጭ ምንዛሪ ክምችት የአንድ ወር የገቢ ንግድ ለመሸፈን አንኳ ከማችል ደረጃ መድረሱንም ልብ ይሏል፡፡

የእዳ ሽግሽግና የእፎይታ ጊዜ መገኘቱ ለተቋሙ እንደ በጎ ዜና ቢወሰድም ለዜጎች ግን የእለት ጉርስ ወይም ወሳኝ መሠረተ ልማት ግንባታ ሊሆን አይችልም፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ብድር ተሸጋሸገም ሆነ የእፎይታ ጊዜ ተሰጠው ያው የሚከፈል እዳ መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ አበዳሪዎቹ መንግሥታትም ሆኑ ወይም ባንኮች አልያም የግል አበዳሪዎች ብድሩ ከነወለዱ እንዲከፈላቸው ይጠብቃሉ፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን የእዳው ጫና ሚወድቀው ወትሮውንም በኑሮ ወድነት ጀርባው በጎበጠው ዜጋ ላይ ነው፡፡  

የሀገር ውስጥ ዓመታዊ ጠቅላላ ምርት (GDP) – የተስፋ ዳቦ

በዘመናዊ ኢኮኖሚክስ የሀገር ውስጥ አመታዊ ጠቅላላ ምርት ከአስማት ጋር የሚመሳሰል ገጽታ አለው፡፡ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት ምጣኔ ጉዳይ ይበል የሚያሰኝ ነው ቢሉንም ውስጣዊ ይዘቱ ጥያቄ የሚያስነሳ ነው፡፡ ለምሳሌ አምና የፌዴራል መንግሥቱ ለካፒታል ፕሮጀክቶች የመደበው ከበጀቱ 35.5 በመቶ ዘንድሮ ወደ 38.6 በመቶ ቢያድግም በጀቱ በጦርነቱ የወደሙ መሠረተ ልማቶችን ጭምር መልሶ ለመገንባት የሚውል በመሆኑ ነገሩን ውሀ ቅዳ ውሀ መልስ ያደርገዋል፡፡

ጉዳዩን ትንሽ ጠለቅ ብለን ስናየው ደግሞ ከዘንድሮው የፌዴራል በጀት ውስጥ 19 በመቶ ለዕዳ ክፍያ የተመደበ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ እናም የዕዳ ክፍያ ሀገሪቱ ለሌሎች ወሳኝ ልማቶችና ለኢንቨስትመንት ልታውለው የሚገባትን ሀብት ለእዳ ክፍያ በማዋል የማይሞላ ጉድጓድ ለመሙላት ከሚደረግ ጥረት ጋር ያመሳስለዋል፡፡

ለዕዳ የሚከፈል ወጪ አዳዲስ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ እንዳይሆኑ እንቅፋት በመሆን እውነትኛ የኢኮኖሚ ሽግግር እንዳይኖር ሳንካ ይሆናል፡፡ እናም የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እያደነቀ ያለው እንዲህ ዐይነቱን የትናንቱን ቁስል በማከም የነገውን የልማትና የእድገት ትልም ተግባራዊ ለማድረግ የማያስችልን ለንቋሳ ኢኮኖሚ ነው፡፡

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም በሀገሪቱ ስላሉት 31 ሚሊዮን ሰብአዊ የእለት ደራሽ እርዳታ ስለሚፈልጉ ዜጎች፣ ስለ 32.1 በመቶ ሥራ አጥ ወጣቶች፣ በገጠር እንደ ጤናና ትምህርት የመሳሰሉት መሠረታዊ አገልግሎቶች ለማግኘት ብርቅ ሰለሆነባቸው ወገኖችና የዋጋ ንረት የእለት ጉርስ ማግኘት ቅንጦት ስለሆነባቸው ዜጎች ምንም የሚለው ነገር የለም፡፡

ስናጠቃልለው ዜጎቹን ከድህነት አረንቋ የማያወጣ የኢኮኖሚ ዕድገት ውስጡን ቢከፍቱት ተልባ እንደሚባለው ባዶ ነው፡፡ ያለ ተጨባጭ ድል ዘራፍ እያሉ ከመፎከርም ጋር ይመሳሰላል፡፡ ዜና ከሌለው ሰበር ዜና እንዲሁም የተስፋ ዳቦ ከማስመጥም ድርጊት ጋርም ይመሰላል፡፡

መላው ምንድነው?

ዘፋኙ እስቲ መላ ምቱ እንዳለው ከዚህ ዙሪያው ገደል ከሆነ ሁኔታ መውጫ መላ ልናበጅ ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት እውነተኛ እድገት የሚሻ ከሆነ የቁጥር ጨዋታውን ትቶ የጉዞ አቅጣጫ ለውጥ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ዕድገቱ የተወሰነውን አካል ብቻ ሳይሆን ሁሉን አካታች መሆን አለበት፡፡ መንግሥት በሰው ሀብቱ ላይ መሥራት ይጠበቅበታል፡፡ ይህንንም ዕውን ለማድረግ የተሻሉ ትምህርት ቤቶችንና ለሁሉም ተደራሻ የሆኑ ጤና ተቋማትን ማስፋፋትን እንዲሁም አቅም ለሌላቸው ዜጎች የማኅበራዊ አገልግሎት የሚያገኙበትን ስልት መንደፍ ይጠበቅበታል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን በቅድሚያ ጦርነት እንዲቆም ማድረግ አለበት፡፡ በትግራይ  ላንቃው የተዘጋው ጠመንጃ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎችም ሊዘጋ ይገባል፡፡

ሀገሪቱ በብድር ገንዘብ ፋይናንስ ከሚደረጉ ፕሮጀክቶች ጥገኝነት ተላቃ ትናንሽ የንግድ ሥራዎችና በየአካባቢው ያሉ ኢንዲስቱሪዎች እንዲያብቡ ኢኮኖሚውን ዘርፈ ብዙ ማድረግ ከመንግሥት ይጠበቃል፡፡

እናም ጉዳዩ ያለው የዓለም አቀፉ ገንዘብ ተቋም የኢትዮጵያ መንግሥት ኢኮኖሚያዊ እድገት አስመዘገበ ብሎ ከማወደሱ ላይ አይደለም፡፡ ቁም ነገሩ ያለው በያንዳንዱ የአዲስ አበቤ ሕዝብ ጓዳ መሙላት፣ በአማራና በኦሮሚያ ካለው ሕዘብ የኑሮ እድገትና በአጠቃላይ በሚሊዮን ከሚቆጠር የኢትዮጵያ ሕዝብ የሕይወት ለውጥና መሻሻል ላይ ነው፡፡ ከዚያ ወጪ ያለው የቁጥር ጨዋታ ውሃ አይቋጥርም፡፡

   [አቶ ክቡር ገና ታዋቂ የምጣኔ ሃብት ምሁር ናቸው፡፡ ሀገራችን ባለፉት ዓመታት እየተከተለችው ያለውን የኢኮኖሚ ፖሊሲም ኾነ ከስድስት ወራት በፊት ተግባራዊ መደረግ የጀመረውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ አስመልክቶም ጠለቅ ያሉ መጣጥፎችን በማስነበብ እና በተለያዩ መገናኛ ብዙኃንም አስተያየቶቻችን በመሥጠት ይታወቃሉ፡፡]

ግዮን መጽሔት ቅጽ 6 ቁጥር 222 የካቲት 8 2017 ዓ.ም

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የተፈናቀሉ ዜጎች በተጠለሉበት አካባቢ በቋሚነት መኖር የሚያስችላቸው 

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን የዳሰነች ወረዳ ከበኦሞ...

ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ 11ኛውን የኃይሌ ሆቴልና ሪዞርት በደብረ ብርሃን ከተማ አስመረቀ

ታዋቂው አትሌትና ባለሀብት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ በደብረ ብርሃን ከተማ...

በኢትዮጵያ ሪል ስቴት አልሚዎች ማህበር የተዘጋጀው የመጀመሪያው አህጉራዊ የሪል ስቴት ኤግዘቢሽን ተከፈተ

በኢትዮጵያ ሪል ስቴት አልሚዎች ማህበር አዘጋጅነት የመጀመሪያው አህጉራዊ የሪል...

በሊባኖስ እና በእሰራኤል የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ተራዘመ

ትራምፕ በሊባኖስ እና በእሰራኤል መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም በሦስት...