
በዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ ግብራቸው የቱንም ያህል የተቃራኒያቸው ያህል ቢኾንም፣ የምዕራቡ ዓለም መልክ እና ቅርጽ ያላቸው ተቋማት መሠረት ከተጣለ አንድ ክፍለ ዘመን አልፏል፡፡ ከዴሞክራሲ እና ከዜጎች መብት ጋር የተገናኙ ተቋማት ዕድሜ ግን አጭር ነው፡፡ የደርግን ውድቀት ተከትሎ ወደ ሥልጣን የመጣው ኢሕአዴግም ለዚህ መሰሉ ልምምድ ፈር ቀዳጅ ኾኖ ቢጠቀስም፣ በአንድ ወቅት ብርጋዴር ጀነራል አሳምነው ጽጌ ተናግረውት እንደነበረው ተቋማቱ ገቢራዊ ሚናቸው የሥርዓቱን ነውር እና የከፋ ሰብዓዊ መብት ጥሰት ከመሸፈን የተሻገረ አልነበረም፡፡ በዚህም ሳቢያ ዓለም በሥም የሚጋራቸው፣ በተግባር ግን ፈጽሞ የማይጠረጥራቸው ነውሮች በእነኚህ የዴሞክራሲ ተቋማት ሽፋን ሲፈጸሙ ኖረዋል፡፡
ድኅረ ኢሕአዴግ ባለው የብልጽግና አገዛዝ ደግሞ አዳዲስ እውነታዎች ክሱት ኾነዋል፡፡ ኢሕአዴግ በግላጭ በሃገረ መንግሥቱ ነባራዊ እና ታሪካዊ ተቃርኖዎች ዙርያ ሐቀኛ ንግግር እና ብሔራዊ እርቅ እንዲደረግ ለሁለት ዐሠርታት ያለመታከት ሲጠየቅ ‹‹የምን ዕርቅ ነው? የባል እና ሚስት ጠብ አስመሰላችሁት›› በማለት ሢሳለቅ የቆየበት ችግር ደድሮ ለብተና እና ለእርስ በርስ ፍጅት ሲዳርገው፣ በዓይኑ አማናዊ ምሥክር የኾነው ትውልድ ሳያልፍ ‹‹ዐዲሱ›› ብልጽግና፣ ይኽንን ብዙዎች የጮኹለት እና የሚጮኹለት አንገብጋቢ ጉዳይ የያዘበት አካሔድ ፍጹም የባሰ መኾኑ አሳሳቢ ነው፡፡
የጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት እርሳቸውን ጨምሮ ሹማምንቶቻቸውን ወደ ሥልጣን ያመጣው የሕዝብ ጥያቄ ንግግርን፣ ምክክርን እና ድርድርን ማዕከል በማድረግ እንዲፈታ ጎላ ብሎ ይነሳ የነበረውን ጥያቄ ለመቀልበስ የተከተሉት መንገድ፣ የአጭር እና የመካከለኛ ጊዜ ማምታታትን ስልታዊ ያደረገ ነው ለማለት የሚያስደፍር ነው፡፡ ለዚህ ወደ ሥልጣን ከመጡ ማግሥት ጀምሮ ያቋቋሟቸውን ኮሚሽኖች ታሪክ ማስታወስ ይበቃል፡፡ በሀገሪቱ የመጨረሻ የሥልጣን አካል በሚባለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተቋቋሙት የማንነት እና አስተዳደራዊ ወሰን ጉዳዮች ኮሚሽን እና የሀገራዊ እርቀ ሰላም ኮሚሽን ያለምንም እርባና ከዓመታት የታይታ ናሙናነት ወደ ፍርሰት እንዲያመሩ ተገድደዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ በዚሁ ግዮን መጽሔት ቁጥር 176 ዕትም ቆይታ አድርገው የነበሩት አርቲስት ደበበ እሸቱ ሲመሩት የነበረው ሀገራዊ እርቀ ሰላም ኮሚሽን ‹‹ሊቀጥል እንጅ ሊፈርስ አይገባም›› ከማለት ጀምሮ ‹‹የሦስት ዓመት ሪፖርት ለማቅረብ 15 ደቂቃ ብቻ ነው የተሰጠን›› ያሉበት ንግግራቸው በአባሪነት ሊጠቀስ ይችላል፡፡
የብልጽግና መንግሥትም ኾኑ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አሁንም በዚሁ አካሔዳቸው ቀጥለዋል፡፡ ለዚህ ሌላኛው ማሳያ የሚኾነው ደግሞ ‹‹የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን›› ተብሎ ከተቋቋመ ሦስተኛ ዓመቱ እየመጣ ያለው ተቋም ነው፡፡ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከተቋሙ ጥንስስ ጀምሮ ያላቸውን ጥያቄ ሲያነሱ ቢደመጥም፣ ዕለት ዕለት እየገዘፈ ከነበረው የሀገሪቱ ችግር አኳያ መንግሥት ነገሮች በኮሚሽኑ በኩል እልባት እንዲያገኙ የማርያም መንገድ ይተዋል ብለው ጠብቀው የነበሩ ቀላል አይደሉም፡፡ የኾነው ግን አሁንም በተቃራኒው ነው፡፡ ለዚህ ሁለት ዐበይት የሚባሉ ጉዳዮችን በአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ የመጀመሪያው በአዲስ አበባ እና በኦሮሚያ መካከል የነበረው አስተዳደራዊ የወሰን ችግር ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በደቡባዊ ኢትዮጵያ ባሉ የተለያዩ ዞኖች፣ ወረዳዎች እና ብሔረሰቦች የሚነሱ የአስተዳደር እና የፖለቲካ ጥያቄዎች ናቸው፡፡
መንግሥት እነኚህን ሁለት ሁሉን ያሳተፈ ንግግር እና ምክክርን የሚሹ ጉዳዮችን ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ተቋቁሞ ባለበት ሁኔታ ውስጥ፣ ኮሚሽኑን ገሸሽ አድርጎ በራሱ ለመወሰን ሁለቴ ማሰብ እንኳን ያስፈለገው አይመስልም፡፡ በዚህም ሳቢያ ሕዝብ ባልተነጋገረበት እና ባልተስማማበት በርካታ የአዲስ አበባ ከተማ አካል የኾኑ አካባቢዎችን ቆርሶ ‹‹ሸገር›› ያለውን ከተማ በማዋለድ ብዙ ሺህ ዜጎችን በ‹‹ሕገ ወጥነት›› ሥም ቤታቸውን አፍርሷል፡፡ የደቡብ ክልልንም እንዲሁ ተራ በተራ ወደ ዐራት ክልልነት ሲሸነሽን የምክክር ኮሚሽን ማቋቋሙን ማስታወስ የፈለገ አይመስልም፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ አስገራሚ የሚኾነው እንቆቅልሽ ግን፣ እንዲህ ያለውን ጉዳይ ‹‹ይፈታል›› ተብሎ ‹‹የሚጠበቀው›› ኮሚሽኑ መንግሥት በገዛ ፈቃዱ ሚናውን ሲቀማው ‹‹ለምን›› ብሎ የማይጠይቅ መኾኑ ነው፡፡ ለዚህ የመንግሥት የተለመደ የማምታታት አካሔድ ዳግም ሽፋን ከመኾን የተሻገረ ረብ ያለው ኃላፊነት መወጣት ባለመቻላቸውም በኮሚሽነርነት የተመረጡት ግለሰቦች ከታሪክ ተጠያቂነት ሊያመልጡ አይችሉም፡፡