የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ጋር በመቀናጀት፣ አዲስ ፈቃድ ላወጡ አስመጪዎች እና ላኪዎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሂሳብ ቁጥር በአጭር ጊዜ እና በዘመናዊ መንገድ የሚያገኙበትን የዲጂታል አገልግሎት መጀመሩን አስታውቋል።
ይህ አዲስ አገልግሎት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሂሳብ ቁጥሮች በጉምሩክ ኮሚሽን አንድ መስኮት አገልግሎት በኩል እንዲሰጡ የሚያስችል ሲሆን፣ ይህም የነበረውን ረጅም አስተዳደራዊ ሂደት በማቃለል ለንግድ ስራ ፈጣን እና ቀልጣፋ ድጋፍ የሚሰጥ መሆኑ ተገልጿል።
እንደ ባንኩ መረጃ፣ ይህ አገልግሎት ተጠቃሚ የሚሆኑት ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሂሳብ ቁጥር ለሚያወጡ እና አዲስ ፈቃድ ላገኙ አስመጪዎችና ላኪዎች ብቻ ነው።
ቀደም ሲል የሂሳብ ቁጥር ያላቸው የንግድ ተቋማት ግን ለገቢ እና ለወጪ ንግድ ግብይቶቻቸው ይጠቀሙበት የነበረውን ነባር ቁጥር እንደወትሮው መጠቀም እንደሚችሉ ተጠቁሟል።
