የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን በሚቀጥለው ሳምንት በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እና በኢትዮጵያ ጉብኝት ለማድረግ ማቀዳቸውን የቱርክ ኮሙኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ።
ቢሮው እንደገለጸው፣ ፕሬዝዳንት ኤርዶጋን በመጀመሪያ ሰኞ ዕለት ወደ አቡዳቢ የሚያቀኑ ሲሆን፣ በዚያም ከሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን ጋር ይገናኛሉ ተብሎ ይጠበቃል። ውይይታቸው በቱርክ እና በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ መካከል ያለውን ትብብር በማስፋፋት እንዲሁም በቀጠናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ክስተቶች ላይ እንደሚያተኩርም ታውቋል።
ፕሬዝዳንቱ ማክሰኞ ዕለት በጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ግብዣ አዲስ አበባ እንደሚገቡ የተገለፀ ሲሆን፣ በጉብኝታቸው ወቅት ድርድራቸው ተጠናቆ ዝግጁ የሆኑ በርካታ ስምምነቶች እና ሰነዶች ይፈርማሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የኮሙዩኒኬሽን ቢሮው መረጃ ያመለክታል።
ይህ የተገለፀው በጎረቤት ሱዳን ባለው ቀጣይነት ያለው ግጭት ምክንያት ቀጠናዊ ትኩረት በጨመረበት ወቅት ነው። በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ በዩናይትድ ስቴትስ የቱርክ አምባሳደር ሰዳት ኦናል፣ አንካራ ለሱዳን ሉዓላዊነት እና ግዛታዊ አንድነት የምታደርገውን ድጋፍ በድጋሚ አረጋግጠዋል።
አምባሳደሩ በዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው የዩናይትድ ስቴትስ የሰላም ኢንስቲትዩት የሱዳን ሰብአዊ ፈንድ ዝግጅት ላይ በተሳተፉበት ወቅት እንደተናገሩት፤ ቱርክ የሱዳን መረጋጋት ለሰፊው ቀጠና “በፅኑ አስፈላጊ” እንደሆነ ታምናለች።
ጦርነቱን ለማስቆም ውይይት እና ዲፕሎማሲ ተመራጭ መንገዶች መሆናቸውን አጽንኦት የሰጡት አምባሳደሩ፣ ግጭቱን ለመፍታት ለሚደረጉ ቀጠናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጥረቶች አንካራ የምታደርገውን ድጋፍ በድጋሚ ገልጸዋል።
በተጨማሪም ጉብኝቱ የሚደረገው፣ ኢትዮጵያ ከሱዳን ድንበር አቅራቢያ በሚገኘው በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ተዋጊዎች የሥልጠና ካምፕ እያዘጋጀች ነው የሚል የሮይተርስ የምርመራ ዘገባ ከወጣ ከጥቂት ቀናት በኋላ ነው።
ዲፕሎማሲያዊ፣ የደህንነት እና የመንግስት ምንጮችን እንዲሁም የሳተላይት ምስሎችን በመጥቀስ የወጣው ይህ ዘገባ፤ ካምፑ ለፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ አዳዲስ ምልምሎችን ሊያቀርብ እንደሚችል አመልክቷል። የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት እስካሁን ለቀረበባቸው ክስ ይፋዊ ምላሽ አልሰጡም።
