የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በአሜሪካ ለሚገኙ ሶማሊያውያን ስደተኞች ተሰጥቶ የነበረውን “ጊዜያዊ የጥበቃ ፈቃድ” ለማቋረጥ መወሰኑን የኋይት ሀውስ የፕሬስ ሴክሬታሪ አረጋግጧል።
የአሜሪካ የዜግነትና ስደተኞች አገልግሎት ባወጣው መግለጫ መሠረት፣ በዚህ የጥበቃ ፈቃድ አሜሪካ ውስጥ የሚገኙ የሶማሊያ ዜጎች እስከ መጋቢት 2018 ዓ.ም ድረስ ከአገር መውጣት ይኖርባቸዋል።
የሀገር ውስጥ ደኅንነት ሚኒስትሯ ክሪስቲ ኖም ውሳኔውን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፣ የጥበቃ ፈቃዱ ስያሜ እንደሚገልጸው “ጊዜያዊ ማለት ጊዜያዊ ነው” ካሉ በኋላ፣ በሶማሊያ ያለው ሁኔታ ተሻሽሏል የሚል እምነት እንዳላቸው ጠቁመዋል።
ይህ እርምጃ በትራምፕ አስተዳደር ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በሶማሊያውያን ስደተኞች ላይ ሲሰነዘር የቆየው የከረረ ትችት ውጤት እንደሆነ ተገልጿል። ፕሬዝዳንት ትራምፕ ሶማሊያውያን “ከዚህ መውጣት አለባቸው” በማለት በተደጋጋሚ ሲናገሩ የቆዩ ሲሆን፣ በተለይም በሚኒሶታ ግዛት ውስጥ የተከሰተውን የገንዘብ ማጭበርበር ቅሌት ከሶማሊያ ተወላጆች ጋር በማያያዝ ትኩረት ሰጥተውታል።
አሜሪካ ይህንን የጥበቃ ፈቃድ የምትሰጠው በተፈጥሮ አደጋ ወይም በሰው ሠራሽ ግጭቶች ምክንያት አገራቸው ለመኖር አስቸጋሪ ለሆነባቸው ስደተኞች ቢሆንም፣ የአሁኑ ውሳኔ ከአፍሪካ፣ ከላቲን አሜሪካ እና ከመካከለኛው ምስራቅ የሚመጡ ስደተኞችን ለመቀነስ የሚደረገው ጥረት አካል ተደርጎ ተወስዷል።
ውሳኔው በአሜሪካ በሚኖሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ሶማሊያውያን እና ቤተሰቦቻቸው ላይ ከፍተኛ ስጋት የፈጠረ ሲሆን፣ ከቀናት በፊት ሌሎች መሰል የጥበቃ ፈቃዶችም ሊሰረዙ እንደሚችሉ ፍንጮች ታይተዋል።
በመጋቢት ወር አጋማሽ ላይ ተግባራዊ የሚሆነው ይህ ትእዛዝ፣ በሶማሊያ ያለው ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታ ገና አስተማማኝ ባልሆነበት ወቅት መወሰኑ በሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ዘንድ ቅሬታን እያስነሳ ይገኛል።
