ደቡብ አፍሪካ አንጋፋውን የፀረ-አፓርታይድ ታጋይ እና የቀድሞ የመከላከያ ሚኒስትሯን ሞሲዋ ሌኮታን በሞት ተነጥቃለች።
ሌኮታ ከዚህ ዓለም የተለዩት በ77 ዓመታቸው ሲሆን፣ ለተወሰነ ጊዜ ሲከታተሉት በነበረው የጤና እክል ምክንያት ሕክምና ሲያገኙ ቆይተዋል።
ታዋቂው ታጋይ ከታላቁ የነፃነት መሪ ኔልሰን ማንዴላ ጋር በሮበን ደሴት ለዓመታት በእስር በማሳለፍ ለሀገራቸው እኩልነትና ነፃነት የከፈሉት መስዋዕትነት በታሪክ መዝገብ ደምቆ የሚጠቀስ ነው።
ሌኮታ ከፈረንጆቹ 1998 እስከ 2008 ድረስ በደቡብ አፍሪካ መከላከያ ሚኒስትርነት በማገልገል ለሀገራቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
በኋላም ከአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ በመገንጠል የራሳቸውን ተቀናቃኝ ፓርቲ በመመሥረት የፖለቲካ ተሳትፏቸውን ቀጥለው ነበር።
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ የሌኮታን ሕልፈት አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፣ “የነፃነት ታጋይ እና እውነተኛ የሕዝብ አገልጋይ” ሲሉ ታላቅ አክብሮታቸውን ገልጸዋል።
የሌኮታ ሕልፈት ለደቡብ አፍሪካውያን ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካ የነፃነት ታሪክ ትልቅ ኪሳራ ተደርጎ ተወስዷል።
