በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት በአዳማ መንበረ ጵጵስና የደብረ ገነት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ካቴድራል ቅዳሴ ቤቷ ክብረ በዓል ብፁዕ አባታችን አቡነ ጎርጎርዮስ የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳምና ሥራ አመራር መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ኃላፊ የቅዱስ ሲኖዶስ ቋሚ አባል እንዲሁም የኢትዮጵያ ሃይማኖቶች ተቋማት የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ሰብሳቢ : ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የምሥራቅ ጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና ብፁዕ አቡነ ኤልያስ የጋሞ ጎፋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ የኢሉባቡር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በተገኙበት በታላቅ መንፈሣዊ ሥነ ሥርዓት ተከብሮ ዋለ።
መርሓ-ግብሩን የመሩት ክቡር የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሲሆኑ በቅደም ተከተል በተቀመጠው ሰዓት እና ደቂቃ መሠረት በሊቃውንት እና በሰንበት ትምህርት ዘማርያን ያሬዳዊ ዜማ ቀርቧል።
በመቀጠል በብፁዕ አባታችን መልካም ፈቃድ የካቴድራሉ አስተዳዳሪ መልአከ ገነት ቆሞስ አባ ቶማስ ወልደ ጎርጎርዮስ አጭር ሪፖርት አቅረበዋል ። በተያያዘም የሕንፃ ቤተክርስቲያኑ ግንባታ ከተመሠረተ ጀምሮ በእውቀታቸው በገንዘባቸውና በጉልበታቸው ለረዱና ለተባበሩ ድርጅቶችና ለአባ ገዳዎች ለአደ ስንቄዎች ግለሰቦች እንዲሁም ለንዑሳን እና ዐቢይ ኮሚቴዎች በብፁዓን አባቶች የሽልማትና የእወቅና ሰርተፍኬት ተበርክቶአል።
በመቀጠል ብፁዕ አቡነ ጎርጎዮስ የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን ታሪክ ወኃላ በማንሳት መሠረት ከተጣለበት ጊዜ አንስቶ የነበሩ ለሕንፃ ግንባታው ሥር ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በመሥራት እራሳቸው በማደራጀት ይህንን የመሠለ ካቴድራል ተሥርቶ በቅዱስ ፓትርያርኩ ቡራኬ ተባርኮ በማየታቸው የተሠማቸው ደስታ እጥፍ መሆኑን በመግልጽ እንኳን ለዚህ ታሪካዊ ቀን በድጋሜ አደረሳችሁ ብለዋል። በተያያዘም በቀጣይ ያላለቁ እንደ የመሬት ወለል ምንጣፍ ሥራ የመሣሠሉ ሥራዎች በፍጥነት እንዲጠናቀቁ አባታዊ መመሪያ በመሥጠት የዕለቱን ትምሕርተ ወንጌል እንዲያስተምሩ ብፁዕነታቸው ጋብዘዋል ።
በግብዣውም መሠረት ብፁዕ አቡነ ኤልያስ የጋሞ ጎፋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ” ሰማዕኩ ጸሎተከ ወስእለተከ ዘሰአልከ ቅድሜየ ወገበርኩ ለከ በከመ ኵሉ ጸሎትከ ወቀደስክዎ ለዝንቱ ቤት ዘሐነጽከ (በፊቴ የጸለይኸውን ጸሎትህንና ልመናህን ሰምቻለሁ፤ ለዘላለምም ስሜ በዚያ ያድር ዘንድ ይህን የሠራኸውን ቤት ቀድሻለሁ፤ ( 1ኛ መጽሐፈ ነገሥት 9፥3) በሚል መነሻ ቃል የራቀውን አቅርበው የቀረበውን አጉልተው ሰፊ ትምህርተ ወንጌል ሰጥተዋል።
በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ (ዶ/ር) ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ሠጥተው የበዓሉ ፍጻሜ ሆናል።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ከሙሉው የሲኖዶስ ምላተ ጉባኤው ጋር ግንቦት 15 ቀን 2017 ዓ.ም ተገኝተው ባረከው የመረቁ ሲሆን በቅዱስ አባታችን ካቴድራል ተብሎ ተሰይሟል።
በቅዳሴ ቤቱ ክብረ በዓል ላይ ብፁዓን አባቶቻችንን ጨምሮ: የጠቅላይ ቤተ ክህነት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ክቡር መልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ገብረ መድህን ንጉሤ የምሥራቅ ሸዋ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣ ክቡር መልአከ ሣህል ነጋሽ ሀ/ወልድ የሀገረ ስብከቱ ም/ሥራ አስኪያጅ፣ ክቡራን የሀገረ ስብከቱ የየመምሪያው የሥራ ኃላፊዎች ክቡር መልአከ ገነት ቆሞስ አባ ቶማስ ወልደ ጎርጎርዮስ የካቴድራሉ አስተዳዳሪ ክቡር መልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ዜና ማርቆስ ፀጋዬ የና/ደ/ሰ/ቅ/ገብርኤል ካቴድራል አስተዳዳሪ የመወረዳ ቤተ ክህነት የሀገረ የየወረዳው ሊቃነ ካህናት የገዳማትና የአድባራት አስተዳዳሪዎች ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ት/ቤት ዘማርያን የወጣት ማሕበራት ጥምረት አባ ገዳዎች አደ ስንቄዎች በርካታ ምዕመናን ተገኝተዋል።
