የብራንድ አፍሪካ መሥራች እና ሰብሳቢ ቴቤ ኤካላፌንግ አፍሪካውያን በፈጠራ መስክ በዓለም አቀፍ ደረጃ ልቀው እየተገኙ ነው ይላሉ።
አዲስ አበባ ተካሂዶ በነበረው የብራንድ አፍሪካ የሽልማት ዝግጅት ላይ ሲናገሩ በፈጠራ ዘርፍ የሚወጡ ምርቶች እና አገልግሎቶች አህጉሪቱን የበለጠ ተጠቃሚ ያደርጋሉ ብለዋል።
“እንደ እኔ አመላካከት በዓለም አቀፍ ደረጃ አፍሪካዊነትን ለመግለፅ እንዲሁም ለኢኮኖሚ ነጻነት እድል ይሰጡናል።”
በሙዚቃ ዘርፍ ጉምቱ የሚባሉትን ከደቡብ አፍሪካ ሚሬም ማኬባና ሂው ማሴኬላ፣ ናይጄሪያዊው ፌላ ኩቲን፤ በፋሽን ዘርፍ የቀድሞዋ ዓለም አቀፍ ሞዴል ኢትዮጵያዊቷ አና ጌታነህ አፍሪካን በማስተዋወቅ ረገድ የተጫወቱትን ጉልህ ሚና አንስተዋል።
“ለምንድነው የእኛ የተሻለ እና የሚያምር ሆኖ ሳለ ኸርምስ፣ ሉዊ ቭታን፣ ዶልቼ እና ባሌንሲያጋን የምንለብሰው። አዚህ ኢትዮጵያ ስንመጣ ኢትዮጵያዊያን ራሳቸውን መስለው ሲታዩ ደስ ይላል። ስታይል፣ ፋሽን፣ ሐይማኖታቸው እና ፊደላቸው በጣም የተለየ ነው” ብለዋል።
