
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን እንዳስታወቀው ቁልፍ አለም አቀፍ አጋሮች የእርዳታ መጠንን በመቀነስና በአፍሪካ ምርቶች ላይ አዳዲስ ታሪፎችን በመጣል አህጉሪቱን እየፈተኑ ይገኛሉ ብሏል።
የህብረቱ ሊቀመንበር ሙሀመድ አሊ ዩሱፍ በአዲስ አበባ በተካሄደው በ24ኛው ልዩ የሥራ አስፈፃሚ ምክር ቤት መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ይህንኑ ሀሰብ አጉልተው አሳይተዋል ።
በተለይም ከአሜሪካ የሚገኘው የእርዳታ መጠን መቀነስ እንዲሁም የአፍሪካ ዕድገትና ዕድል ህግ (አጎዋ) እና እንደ ጋቪ ያሉ የክትባት ህብረት ድጋፎች መዳከም በጤና፣ በምግብ ዋስትናና በንግድ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑን ሊቀመንበሩ አመልክተዋል።
ሙሀመድ ዩስፍ አክለውም በአፍሪካ ምርቶች ላይ ሊጣል የታሰበው አዲስ የታሪፍ ጭማሪ የአባል ሀገራትን ኢኮኖሚ ሊያዳክም እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
አህጉሪቱ እነዚህን ተግዳሮቶች ለመቋቋም የራሷን የሀገር ውስጥ ሀብት ላይ በመተማመን የግል ዘርፉንና የውጭ ሀገር ነዋሪዎቿን በማሳተፍ የገንዘብ ፍላጎቷን ልታሟላ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በተጨማሪም የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠናን (AfCFTA) ማጠናከርና ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ማድረግ የአሁኑን ፈተና ወደ ዕድል ለመቀየር ወሳኝ መሆኑን ሙሀመድ አስረድተዋል።
የአባል ሀገራትን ገበያ በመክፈትና ያሉትን የንግድ እንቅፋቶች በማንሳት የንግድ ልውውጡን ማሳደግ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
CapitalNews