የኢትዮጵያን የዕውቀት ምንጭና መሠረት የዳሰሰው ሥራ!

Date:

የመፅሐፉ ርዕስ :- የኢትዮጵያ ረቂቅ ፍልስፍና

ደራሲ : – ወልደጊዮርጊስ ይሁኔ

አሳታሚ:- ፀጋ ማርያም ማተሚያ ቤት

የገፅ ብዛት :- 260

በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የፍልስፍና ፕሮፌሰር የነበረው ካናዳዊው ክላውድ ሰምነር ለመጀመሪያ ጊዜ ‹‹የኢትዮጵያ ፍልስፍና›› በሚል በሁለት ቅፅ ሰንዶ አቅርቦልናል። ነገር ግን ይህ ጉዳይ  አከራካሪ ሆኖ ሰነባብቷል። ክላውድ ሰምነር የሥነጽሑፍ ተመራማሪ ሲሆን የኢትዮጵያን የሥነጽሑፍ ዘመን በሁለት በመክፈል ያጠና ምሁር ነው። ከእነሱም ፍልስፍናዊ ይዘት አላቸው ካላቸው ድርሳናት የሀተታ ዘርዓያዕቆብ እና ሀተታ ወልደሕይወት ይጠቀሱበታል። ኾኖም ሁሉንም በዘርፉ ያሉ ምሁራን የሚያስማማ ጉዳይ አልሆነም። ገሚሱ ክላውድ የምዕራባዊ ዕሳቤ ላይ የተመሰረተ ኢትዮጵያዊ ፈላስፋ ማለትም እንደምዕራባውያኑ ለማሰብ የሚሞክር ኢትዮጵያዊ አለ ለማለት ታስቦ እንደተጠና አንስተው የኢትዮጵያን ፍልስፍና የምናጠናበት የራሳችን ሥነዘዴ ሊኖረን ይገባል ብለው የሚተቹ አሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ‹‹እውነትም ዘርዓያዕቆብ በ15ኛው ክፍለ ተከስቶ የነበረ ኢትዮጵያዊ ፈላስፋ ነው›› በማለት የሚከራከሩም አሉ። ኢትዮጵያ የራሷ ፍልስፍና የላትም የሚሉም አልጠፉም።

የመጽሐፉ ደራሲ ይህን መጽሐፍ ለማዘጋጀት ያነሳሳውን ገፊ ምክንያት ሲናገር፡-

አንደኛ የፕሮፌሰርነት እና የዶክተርነት ማዕረግ ከስማቸው ፊት አንጠልጥለው ለነገሮች የተሻለ ግንዛቤና አረዳድ አላቸው ተብለው በማኅበረሰቡ ትልቅ ግምት የተሰጣቸው አንዳንድ አካላቶች ለሀገራችን ችግር ምንጩ ኢትዮጵያ የራሷ የሆነ ፍልስፍና ስለሌላት ነው ብለው በድፍረት በየሚዲያው ሲናገሩ በመስማቴ ነው ይላል።

ሁለተኛው ረዥም ታሪክ ባስቆጠረው የሀገረ መንግሥት ምሥረታን መሠረቱን ለመናድ የተለያዩ የውሸት ትርክቶችን በመፍጠር የኮሎኒያሊስቶቹን ከፋፍለህ ግዛው እሳቤ ተግባራዊ ለማድረግ የሚጥሩ አካላትን በመቃወም እንደሆነ የመፅሐፉን አላማ በመቅድሙ ይነግረናል።

ሥልጣኔ የሌለው ህዝብ ከቶውኑ ሊኖር አይችልም!

መጽሐፉ በአራት ምዕራፎች እና በአስራ ሦስት ንዑስ ርዕስ የተከፋፈለ ሲሆን በመጀመሪያው ምዕራፍ የፍልስፍና ምንነት እና የተለያዩ ሀገራት የፍልስፍና መሠረቶችን ያጠናል። ለዚህም እንደ አብነት ከፍልስፍና ጋር አብሮ ስሟ የሚነሳው የጥንታዊት ግሪክ ፍልስፍና እና ጥንታዊ የሮማውያን  ፍልስፍና በማለት በሁለት ንዑስ ርዕስ ከፋፍሎ ይዳስሳቸዋል። እንደሚታወቀው አሁን ላለው የዘመናዊ ትምህርት፣ የመንግሥት አስተዳደር ሥርዓት መሠረት የሆነውን የጥንታዊት ግሪክ ፍልስፍና ላይ ትልቅ ተፅዕኖ ካሳረፉ ፈላስፎች ዋነኛው ሶቅራጠስ ነው። በሥነ ምግባር የአስተምህሮት ፍልስፍና ከፍተኛ ደረጃ የደረሱ ናቸው ይላቸዋል። በዋነኝነት ነፍስን መሠረት ያደረገው የሶቅራጠስ አስተምህሮ በጎ ሕይወት መኖር ደስታን እና እርካታን ለማግኘት አስፈላጊ እንደሆነ ያምን ነበር። ጥሩ ሕይወት ለመኖር እንደ ጥበብ፣ ፍትሕ እና ራስን መግዛትን የመሳሰሉ በጎነቶች አስፈላጊ እንደሆኑ እና እነዚህን በጎ ምግባራት ማሳደድ የእውነተኛ ደስታ መንገድ እንደሆነ ያምን ነበር፡፡ እነዚህ እውነተኛ እሴቶች ከውጫዊ ነገሮች የሚመነጩ ሳይሆኑ ከነፍስ ሀብቶች የሚመነጩ ናቸው። ስለሆነም የሰው ልጅ መልካም ምግባር፣ እሴት ከእውቀት እንደሚመጡ ይነግረናል።

በጥንታዊቷ ሮማ የነበረው የፍልስፍና መገለጫ የሆነው የሕግ እና የፍትሕ ሥርዓታቸው ነው። ይህ ጥንታዊ ሥርዓት በዋናነት በሁለት የሚከፈል ሲሆን የሕዝብ ሕግ እና የግል ሕግ በማለት ያብራራቸዋል።

የመጽሐፉ ሁለተኛ ክፍል የኢትዮጵያ ፍልስፍና በሰፊው የሚዳሰስበት ነው። ኢትዮጵያ የራሷ ፍልስፍና ነበራት? የሚለውን ጥርጣሬ አዘል ጥያቄ በመፋቅ የኢትዮጵያ የመንፈሳዊነት ፍልስፍና  በሥርዓቱ ተጠንቶ ስያሜ ተሰጥቶት በተደራጀ መልኩ ስላልቀረበ እንጂ ይህቺ ጥንታዊት ሀገር የራሷ ፍልስፍና የነበረው ሕዝብ እንዳላት ያስታውሳል። ለአብነትም የአኗኗር ይትባህላችንን  በመጥቀስ በሀዘን በደስታ ወቅት ማኅበረሰቡ የነበረው ጠንካራ መስተጋብር፣ የሰላምታ አለዋወጥ ሥርዓት፣ እርስ በእርስ የመከባበር እሴቱን በማብራራት የኢትዮጵያ ፍልስፍና መሠረቱ ቁሳዊ ሳይሆን መንፈሳዊ እንደሆነ ይነግረናል ።

በሦስተኛው የመጽሐፉ ክፍል የኢትዮጵያ ፍልስፍና ትሩፋቶች ምን ይመስላሉ የሚለውን ለመቃኘት የሞከረ ሲሆን ሥነ- መንግሥት እና የአስተዳደር ሥርዓቶች ከአክሱም አንስቶ የተለያዩ የታሪክ ዋቢ መጻሕፍትን በማጣቀስ ለማስቃኘት ይሞክራል። የጥንት የኢትዮጵያ ነገሥታት በንፁህ ሕሊናቸው እየተመሩ ሀገራችውን በሕግ እና በሥርዓት ለማስተዳደር ያደርጉት የነበረውን ጥረት እንዲሁም በዚሁ ክፍል አከራካሪውን የብሔረ ኢትዮጵያን ምሥረታ ከሥሩ ለመናድ እና ፍልስፍናውን ዋጋ ለማሳጣት የሚሞክሩትን አካላት ይወቅሳል። ለዚህም በዋነኝነት የሚጠቅሳቸው በዐፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ወደ ተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት የትምህርት እድል አጊኝተው በመሄድ በኢትዮጵያ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ጠንሳሽ የነበሩትን ያነሳል። ኾኖም ሀገሪቷ ከተመሠረተችበት መንፈሳዊ ፍልስፍና ጋር የሚጋጭ እና የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ እና በሊኒን እና በማርክሲዝም አስተምህሮ የሰከሩ የተማሪዎች ማኅበር አብዮታዊ እንቅስቃሴ የሀገሪቱ ሕግና የፍትሕ ሥርዓት ላይ ትልቅ ችግር እንደፈጠረ ብሎም የዓለም ሥርዓትን ወደ ኢትዮጵያ ማስገባቱ ለብሔርተኝነት ሕግ ማርቀቅ ጅማሬ ነው በማለት ያስረዳል። ፀሐፊው በኢትዮጵያ ከ1967 ዓ.ም ጀምሮ ኢትዮጵያ መሠረታዊ ሕግጋቶች የጠፋባት ሀገር ሆናለች ብሎ በገፅ (123) ላይ እምነቱን ይነግረናል።

በተለያየ ጊዜ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር በመድፈር አንድነቷን ጠብቃ እንዳትቆም እጃቸውን ሲያረዝሙ የነበሩ እና የተለያዩ ዓላማዎችን ይዘው በሃይማኖት ሽፋን አንድነቷን የጠበቀች ጠንካራ ሀገር እንዳትመሠረት ለማድረግ ሲሞክሩ የነበሩትን ሀገራቶችን በነፃነታቸው የማይደራደሩ ነገሥታቶች ነፃነቷን ጠብቀው ለማቆየት ያደረጉትን ጥረት ኋላ ላይም ዓለም የሚያውቀው  በአፍሪካ የነፃነት ምሣሌ እስከመሆን ያደረሳትን የዓድዋ ድል የጀግንነት ታሪክ የሕዝቦቿን ታላቅነት በማውሳት በዚህም ታላቅ ድል የሀገሬውን ሕዝብ በማስተባበር በታላቅ ሀገራዊ ፍቅር ቆራጥነት እና ጀግንነት ሲመሩ የነበሩትን የዐፄ ምኒልክ ታላቅነትም ይመሰክራል። በዐፄ ቴዎድሮስ ሁለተኛ ተወጥኖ ሳይሳካ የቀረውን አሁን ኢትዮጵያ ያላትን ይዞታና አሰፋፈር ሕዝቡን አንድ አድርጎ በመግዛት ለአሁኒቷ ኢትዮጵያ መሠረት ትተው አልፈዋል በማለት ያወሳቸዋል። ቢሆንም በተለያየ አጋጣሚ የውጪ ሀገራቶች ጣልቃ ገብነት ሀገሪቷን ሲያምሳት እና ይዛ የቆየችውን ባሕልና እሴት ሲያናጉት እንደነበር እንገነዘባለን።

የወደቀው የትምህርት ሥርዓት

ትምህርት ችግር መፍቻ መሳሪያ በመሆን ፈንታ በራሱ ችግር ሊሆን አይገባም በማለት የመፍትሔ ሐሳብ ያቀርባል። የሀገራችን የባሕላዊው ትምህርት የቤተ ክህነት ትምህርት አሰጣጥ ምን እንደሚመስል በደረጃ ያስቀምጣቸዋል። ይህም የንባብ ትምህርት፣ የዜማ ትምህርት፣ የቅኔ ትምህርት፣ የትርጓሜ ትምህርት ብሎ በደረጃ ከፍሎ ያሳያል። በተለይም በትምህርት አሰጣጡ ላይ አንድ ተማሪ የመጀመርያ ደረጃ የሆነውን የንባብ ትምህርት ከጨረሰ እና ወደ ሁለተኛው የተሸጋገረ ተማሪ ለመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ጀማሪው ያስተምረዋል። ይህም ሥርዓት በአሁኑ ጊዜ (students center) እንደሚባለው ነው። በማለት በገፅ 163 በባሕላዊው የትምህርት አሰጣጥ ዘዴ ኢትዮጵያውያን ሲጠቀሙበት የነበረ ሥርዓት እንደሆነ ገልጿል።

የኢትዮጵያ የዕውቀት ምንጭና መሠረት ‹‹ሥነ መለኮት ነው›› የሚለው ፀሐፊው፣ ይህ እውቀት የመንፈሳዊነትን እሳቤ የሚያሰርፅ ነው በማለት አያይዞ ይነግረናል።

ስለ ኢትዮጵያ ፍልስፍና ሲነሳ መቼም ስሙ ቀድሞ የሚነሳው የሬኔ ዲካርትን ዘመን የሚጋራው ፈላስፋው ዘርዓያዕቆብ ነው። ዘርዓያዕቆብ በ1599 የተወለደ ሲሆን በንጉሡ ገብረመስቀል ዘመነ መንግሥት እንደኖረ ይነገራል። ዘመንፈስ ቅዱስ አብርሃ ተብለው በታወቁት ሊቅ ከግዕዝ ወደአማርኛ ተተርጉመው የኢትዮጵያውያን ፊሎሶፊዎች፤ ‹‹ሐተታ ዘርዓያዕቆብ አክሱማዊ ወወልደ ሕይወት እንፍራዛዊ›› ብለው አሳተትመውልናል። ሊቁ ዘመንፈስ ቅዱስ አብርሃ ለመጀመሪያ ጊዜ ለኢትዮጵያውያን ስለመምህሩ ዘርዓያዕቆብና ስለ ደቀመዝሙሩ ስለ ወልደሕይወት ጽፈው የተዉልንን ሁለት የፍልስፍና መጻሕፍት በአንድ መጽሐፍ አካተው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲያውቅ ጥረት አድርገዋል።

በዚህም መጽሐፍ የዘርዓያዕቆብ እና የወልደ ሕይወት ታሪክን በጥቂቱ ካስቃኘ በኋላ ከ15 ዓመት በኋላ የተነሳው ጀርመናዊ ፈላስፋ ፍሬድሪክ ሄግል (Frederick Hegel) አፍሪካውያን የራሳቸው ባሕል፣ ታሪክ እና ሃይማኖት የሌላቸው የዕውቀት፣ የሥነ ምግባር እንዲሁም የሕግ ሥልጣኔ እንደሌላቸው ስሁት የሆነ አስተምህሮት በዓለም ላይ በማስተማር አሰራጭቷል። (ገፅ 173) በማለት ይህን የቀኝ ግዛት ዕሳቤ ሳይንሳዊ ለማድረግ ከመሰሎቹ ጋር የሄዱበት መንገድ ከሰው ልጆች ተፈጥሯዊ ጠባይ ጋር የሚጋጭ ነው ሲል ይተቻቸዋል።

በኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት ለፖለቲካ ለአስተዳደር በአጠቃላይ ለማኅበራዊና ለኢኮኖሚያዊ ችግሮች እንደ ዋና ምክንያት የሚሆነው በመንፈሳዊነት ፍልስፍና የተመሠረተ የትምህርት የዕውቀትና የምርምር ሥርዓትን ከዘመኑ ጋር ከማዋሐድ ይልቅ ሀገር በቀሉን ትምህርትም ሆነ ሥርዓት ወደ ጎን በመግፋት የምዕራብያንን የትምህርት ሥርዓት ተግባራዊ ለማድረግ የተሞከረው ሙከራ እንደሆነ ይገልፃል። ይህም ሥርዓት የቀድሞ ሶፊስቶችን አስተምህሮ የተከተለ በዘመነኛው ስያሜው ‹‹Pragmatism›› የተባለውን ፍልስፍና የተከተለ ነው ይላል። የዚህም አስከፊ ውጤት በተማሪው፣ በመምህሩ፣ በመሐንዲሱ እና በጤና ባለሞያው ላይ ያመጣውን አሉታዊ ተፅእኖ ያነሳል። በውጭ ሀገር ትምህርታቸውን ተከታትለው ለሀገራቸው የሥነ ጥበብና የኢኮኖሚ እድገት መሻሻል ከፍተኛ ሥራን ሰርተው አልፈዋል የሚላቸውን መንግሥቱ ለማን እና ገብረሕይወት ባይከዳኝን አስታውሷቸው መፍትሄ ነው ያለውን የሊቁ የእጓለ ገ/ዮሐንስን ‹‹በተዋሕዶ ከበረ›› ፍልስፍናዊ እሳቤ በማንሳት ዘመነኛውን እውቀት ከሀገር በቀል እውቀት እና ከሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር ማዛመድ እንዳለብን ጠቆም አድርጎን ያልፋል።

በመጨረሻው ምዕራፍ ጥንታዊ የቁሳዊ ሥልጣኔ ትሩፋቶችን የመገበያያ ገንዘቦች፣ ስለ አክሱም፣ ጎንደር፣ ላሊበላ የኪነ ሕንጻ ጥበብ የተለያዩ ማኅበረሰቦች የሥልጣኔ አሻራ ያረፈባቸው ናቸው በማለት እንደምሳሌ የአክሱም ሥልጣኔ ላይ የአገው ሕዝብ የነበረውን አስተዋፅኦ ያብራራል።

በሥነጽሑፉም ትልልቅ አሻራቸውን ያሳረፉትን የቅዱስ ያሬድ፣ የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ሕይወት እና ሥራዎችን በጥቂቱ የሚዳሰስ ሲሆን መጽሐፏ አነስ ያለች ብትሆንም ዳጎስ ያሉ ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸውን ሐሳቦች የያዘች ልትነበብ የሚገባ ቆንጆ መፅሐፍ ነች።

አንዳንድ ነገሮች

ታሪክ አሻሚ እና አወዛጋቢ እንደመሆኑ መጠን አንዳንድ መረጃዎች እንደዋቢነት ስንጠቀምም ሆነ ስናስተላልፍ በጣም ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለብን አስባለሁ፡፡ በተለይም እንደኛ ሀገር በአግባቡ  ሁሉንም የማኅበረሰብ ክፍል የሚያስማማ በሥርዓቱ የተጠና ወጥ ታሪክ ተሰንዶ ላልቀረበላት ሀገር ..

በመጽሐፉ ከደርግ በፊት የነበሩት የኢትዮጵያ ነገሥታት ፍጹማዊ ዐይነት ስብዕና ተላብሰዋል።  ይኸውም የተማሪዎች ጥያቄ እና የሥርዓት ለውጥ መሻትን ተመሥርቶ ብሎም በተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የአመፅ መነሻ የነበሩት ጥያቄ ፍጹማዊ ስህተት እንደነበሩ እና በንጉሡ ዘመን ሀገሪቱ ምንም ዐይነት ችግር ውስጥ እንዳልነበረች ያስመስላል። ይኽም የመጽሐፉን ሚዛናዊነት በማሳጣት አንባቢ ፀሐፊው ወደ አንድ ወገን እንዳዘነበለ እንዲሰማው የሚያደርግ ነው። ኋላ ላይ መልኩን የቀየረው ሥር-ነቀል ለውጥ አስተሳሰብ መጀመሪያ ሲጀምር ለዘብተኛ እና ሥርዓቱን ባለበት የማዘመን ሐሳብ እንደነበር የምናውቀው ነው፡፡ ሆኖም በባላባቱ ሥርዓት ግብዝነት፣ በተማሪው እና በወታደራዊ ደርጉ አርቆ አለማሰብና ከልምድ ማጣት፣ የሥልጣን ሽሚያ የተነሳ ሀገሪቱን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እንደመራት ልብ ይሏል። ይኽም አንዱን ጻድቅ ሌላውን አጥፊ ከማድረግ የፈራጅነት ሚና ወጥተን ታሪክን በአግባቡ እና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ የምንረዳበት እና የምንማርበት ሆኖ ቢቀርብልን የተሻለ ነበር እላለሁ።

አንዳንድ የቃላት ግድፈቶች እና የዓመተ ምሕረት በገፅ 78 ጥቅምት 25/1982 የተባለው በስህተት ይመስለኛል።

ሌላኛው በታሪክ አከራካሪ እና በቂ ማስረጃ ያልተገኘባቸው እንደ አፈ ታሪክ የሚነገሩ ከመላምት ያልዘለሉ ለምሣሌ የካህኑ ዮሐንስ ግዛት ጉዳይ በመጽሐፉ ውስጥ ተካቶ በማየቴ ጥያቄ ጭሮብኛል።

በተረፈ ይህን መፅሐፍ ሰንዶ ላቀረበልን ለደራሲ ወልደጊዮርጊስ እጅ ነስቼ እንድታነቡት ጋበዝኩኝ።

——–

ቅጽ 6 ግዮን ቁጥር 216 ጥቅምት 2 ቀን 2017 ዓ.ም

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ለኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ የሚውል የ40 ሚሊዮን ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ ተፈቀደ

የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ የልማት ክንፍ የሆነው ኢአይቢ ግሎባል (EIB...

ሃይንከን በአልኮል መጠኑ ጠንከር ያለ ቢራ ለኢትዮጵያ ገበያ አስተዋወቀ

ሃይንከን ኢትዮጵያ በእለም አቀፍ ደረጃ ዝነኛ የሆነውን ዴሰፔራዶስ (Desperados)...

ኢራን ድርድር ውስጥ ከገባች “እጇ ከቃታው ላይ” አይነሳም

ኢራን ከአሜሪካ ጋር ድርድር የምታደርግ ከሆነ ንግግር ውስጥ የምትገባው...