የኢትዮጵያ ቱሪዝም የሚገኝበት ደረጃ
የኢትዮጵያ ቱሪዝም የሚገኝበትን ደረጃ ለመፈተሽ በዘርፉ የሚከናወኑ ስራዎች የሚመሩባቸውን ስትራቴጂካዊ ሰነዶችና የሕግ ማዕቀፎች፣ የዘርፉን የቁጥርና አጠቃላይ መረጃዎች እንዲሁም የባለድርሻ አካላትን የአፈጻጸም አቅምና ብቃት በዋናነት ትኩረት ሰጥቶ መገምገም ያስፈልጋል፡፡ ለኢትዮጵያ የቱሪዝም ገበያ የቱሪስት ምንጭ የሆኑ አገራት ትንተናም ዘርፉ የሚገኝበትን ደረጃ ወይም አጠቃላይ ሁኔታ ሊያመለክተን የሚችል ተጨማሪ ጉዳይ ነው፡፡
ስትራቴጂካዊ ሰነዶችና የሕግ ማዕቀፎች
የኢትዮጵያ ቱሪዝም በተለያዩ ተግዳሮቶችና ማነቆዎች የተተበተበ ቢሆንም ከሁሉም በላይ የዘርፉ መገለጫ የሆነው ዋነኛው ችግር ግን የዘርፉን የዕድገት ዕድል እንዲሁም በዘርፉ የሚከናወኑ ስራዎችን አስተዳደር የሚያመለክቱ ስትራቴጂካዊ ሰነዶች አለመኖር ነው፡፡ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የተቋቋመው የመንግስት አስፈጻሚ አካላት መቋቋማቸውን በሚገልጸው አዋጅ (አዋጅ ቁጥር 4፣ 1995) መሰረት ነው፡፡
እ.ኤ.አ በ2009 የወጣው የቱሪዝም ፖሊሲም በኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ ውስጥ በጉልህ የሚጠቀስ ተጨማሪ ስትራቴጂካዊ ሰነድ ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፤ የዱር እንስሳት ጥበቃና አጠቃቀም አዋጅም ከአገሪቱ የቱሪዝም ዘርፍ ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ የሚጠቀስ ሌላኛው ጉልህ ሰነድ ነው፡፡
ያም ሆኖ ግን፣ ይህን መሰሉን ሰፊ እና የተለየ ዘርፍ ለማስተዳደር የሚያስችሉ ሰነዶች በበቂ መጠን ካለመኖራቸው በተጨማሪ መሰል ሰነዶች እርስ በእርስ የማይናበቡ መሆናቸውም የአገሪቱ የቱሪዝም ዘርፍ የሚገኝበትን ደረጃ የሚያመለክት ነው፡፡ ይህም በመሆኑ፣ በቱሪስት መዳረሻዎች የሚከናወኑ ስራዎች በዘፈቀደ የሚሰሩና አቅጣጫ ያልተበጀላቸው እንዲሁም የዘርፉን አላማዎችና ግቦች ያላማከሉ ሊሆኑ ችለዋል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፤ መሰል አካሄዶች ደረጃቸውን ያልጠበቁና አንዳንዴም ህገወጥ ድርጊቶች እንዲፈጸሙ በር ከፋች ሆነዋል፡፡
በሰነዶች ላይ የተደረገ ግምገማ እንደሚያሳየው ከቱሪዝሙ ዘርፍ ጋር የተያያዙ የፖሊሲና የስትራቴጂ ሰነዶች የሚከተሉት ናቸው፡-
- የኢትዮጵያ የቱሪዝም ፖሊሲ 2009
- የአዋጅ ቁጥር 839/2014 – ባህላዊ ቅርሶችን ብሔራዊና ክልላዊ ባህላዊ ቅርሶች በሚሉ መደቦች የከፋፈለው አዋጅ
- አዲሱ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግስት መቋቋሙን ተከትሎ የቱሪዝም ሚኒስቴር የተቋቋመበት አዲሱ አዋጅ 1263/2021፡፡
እ.ኤ.አ በ2018 ለአገሪቱ ኢኮኖሚ 7.4 ቢሊዮን ዶላር ገቢ (በ2017 ከነበረው የ2.2 ቢሊዮን ዶላር ጭማሪ አስመዝግቧል) ያስገኘው የቱሪዝሙ መስክ የሚተዳደርባቸውና የሚመራባቸው ሕጋዊ ሰነዶችና አዋጆች ከላይ የተጠቀሱት እንደሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የቱሪዝሙ ዘርፍ በአሁኑ ወቅት ከአገሪቱ አጠቃላይ ኢኮኖሚ የ9.4 በመቶ ድርሻ ይዞ ይገኛል፡፡
የቁጥርና አጠቃላይ መረጃ
አለማቀፉ የቱሪዝም ድርጅት በ185 የአለማችን አገራት በጉዞና በቱሪዝም ዘርፎች ላይ ባደረገው ጥናት ዘርፎቹ ከ2019 የኮሮና ቫይረስ ወረርሽን ክስተት በፊትና ከወረርሽኙ በኋላ ያስመዘገቧቸውን ውጤቶችና ያጋጠሟቸውን ተግዳሮቶች በዝርዝር ለይቶ አስቀምጧል፡፡ ይህ የጥናት ውጤት የኢትዮጵያን የቱሪዝም ዘርፍ በተመለከተ የሚከተለውን ይላል፡-
- ከአለማቀፉ የ3.9 በመቶ ዕድገትም ሆነ ከአፍሪካ የ5.6 በመቶ ዕድገት ከፍ ያለ ዕድገት አስመዝግቧል፤
- ለ2.2 ሚሊዮን የስራ ዕድሎችን ፈጥሯል ወይም ከአጠቃላዩ የስራ ዕድል የ8.3 በመቶ ድርሻ ይዟል፤
- በአብዛኛው ለመዝናናት በሚመጡ ተጓዦች የሚበዙበት ነው – ዘርፉ 79 በመቶ ገቢውን ያገኘው ከመዝናኛ ተጓዦች ሲሆን፣ 21 በመቶ ገቢውን ደግሞ ያገኘው ከንግድ ተጓዦች ነው፤
- አለማቀፍ ተጓዦች የሚበዙበት ነው – ዘርፉ 77 በመቶ ገቢውን ያገኘው ከአለማቀፍ ተጓዦች ሲሆን፣ 23 በመቶውን ገቢውን ደግሞ ያገኘው ከአገር ውስጥ ተጓዦች ነው፤
- እ.ኤ.አ ወደ አገሪቱ የገቡ ቱሪስቶች ቁጥር 849,000 መድረሱን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ከኢትዮጵያ ቱሪዝም የቁጥርና አጠቃላይ መረጃዎች ጋር በተያያዘ ከሚታዩ ችግሮች መካከል ተአማኒነት ያለው መረጃ አለመኖር፣ የተማለከ የመረጃ ማዕከል አለመኖር እና ከአገሪቱ የቱሪዝም እንቅስቃሴዎች ጋር በተያያዘ የተዛቡ መረጃዎች መኖራቸው ይጠቀሳሉ፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፤ መረጃዎች በየጊዜው በተገቢው መንገድ የሚሻሻሉ አለመሆናቸውም በዘርፉ የሚደረገው እንቅስቃሴ በበጎ አይን እንዳይታይ በር ሲከፍት እንደነበር ተስተውሏል፡፡
የስራ አፈጻጸም አቅምና ብቃቶች
የቱሪዝም ሚኒስቴር መቋቋሙ እንዲሁም ለዘርፉ የ10 አመት ዕቅድ መውጣቱና የስራ ፈጠራ ስትራቴጂካዊ ሰነድ መዘጋጀቱ፣ በአገሪቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለቱሪዝሙ ዘርፍ የተሰጠውን ትኩረት ያመላክታሉ፡፡ ያም ሆኖ ግን፤ አሁንም ቢሆን አጠቃላይ የፖሊሲ አቅጣጫ ማስመቀጥን እንዲሁም ተገቢነት ያላቸው የሕግ ማዕቀፎች ማውጣትና ተቋማዊ ስርዓት መዘርጋትን ግድ የሚሉ ክፍተቶች አሉ፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፤ በመላ አገሪቱ በቱሪዝሙ ዘርፍ የሚከናወኑ ስራዎች የሚመሩባቸውን የአሰራር ብቃት መመዘኛ ደረጃዎችንና ስርዓቶችን አውጥቶ ተግባራዊ በማድረግ የቱሪስቶችንም ሆነ በዘርፉ የተሰማሩ አካላትን እርካታ ማረጋገጥም ያስፈልጋል፡፡ በዘርፉ የሰው ሃይል ስልጠና፣ ልማትና አመራር ማስፋፋት የስራ አፈጻጸም አቅምና ብቃትን ከማሳደግ አንጻር ባለፉት ሁለት አስርት አመታት በአንጻራዊነት የተሻለ ትኩረት የተሰጣቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡
የቱሪስት ምንጭ አገራት
ወደ አገሪቱ ከሚገቡ ቱሪስቶች መካከል ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዙት ከአውሮፓ የሚመጡ እንደሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ያስከተለውን ቀውስ ማለፉን ተከትሎት፣ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ አለማቀፍ ቱሪስቶች ቁጥር ጭማሪ ማሳየቱንና በ2021 ሶስተኛው ሩብ አመት (ከሃምሌ እስከ መጋቢት) 331,000 አለማቀፍ ቱሪስቶች ወደ አገሪቱ መግባታቸውን ኒው ቢዝነስ ኢትዮጵያ ድረገጽ ያወጣው መረጃ ያመለክታል፡፡ ይሄው ድረገጽ እንደሚለው፡-
በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ወደ አገሪቱ ከገቡ ቱሪስቶች መካከል 56.4 በመቶው አፍሪካውያን ሲሆኑ፣ ከእነዚህም መካከል 18.2 በመቶው ከምስራቅ አፍሪካ አገራት 11 በመቶው ደግሞ ከምዕራብ አፍሪካ አገራት የመጡ መንገደኞች ናቸው፡፡ ከአሜሪካ የመጡት መንገደኞችም የ16.7 በመቶ ድርሻ ሲይዙ፣ የአውሮፓውያን መንገደኞች ድርሻም 12.6 በመቶ ነው፡፡ ቻይናውያን መንገደኞች በአንጻሩ የ3.8 በመቶ ድርሻ ይይዛሉ፡፡
ይህ መረጃ የኢትዮጵያ የቱሪስት ምንጭ የሆኑ አካባቢዎችና አገራት ሁኔታ በእጅጉ ለውጥ ማሳየቱን ይጠቁማል፡፡ ብሪታኒያ፣ ጀርመን፣ ጣሊያንና ፈረንሳይ በርካታ የመዝናኛ ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡባቸው ቀዳሚዎቹ አገራት ተብለው በተደጋጋሚ ሲጠቀሱ የኖሩ አገራት ሲሆኑ፣ ስዊድንና ሆላንድም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ቱሪስቶች ከሚመጡባቸው አገራት ተርታ የሚሰለፉ ነበሩ (ካርሜን 2018)፡፡
ተግዳሮቶች/ ማነቆዎች
እንደ አጠቃላይ በቱሪዝሙ ዘርፍ እንዲሁም በተለይ በአስጎብኝዎች ላይ ተጽዕኖ የሚፈጥሩ የተለያዩ ዋና ዋና ተግዳሮቶች እንዳሉ በጥናቱ የተሰበሰቡ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በዘርፉ ላይ ያስከተለው ጫና፣ ከቀረጥ ነጻ ከሚገቡ ተሽከርካሪዎች ጋር የተያያዙ ጉዳዮች፣ የግብር ህግና የኦዲት አሰራር እንዲሁም ዘርፉን እንደ ወጪ ንግድ ዘርፍ ተመልክቶ ትኩረት መስጠት፣ ከመሰረተ ልማት አውታሮች ጋር የተያያዙ ችግሮች፣ የቱሪስት መዳረሻዎች ከደረጃ በታች መሆን እንዲሁም በብሔራዊ እና በክልል ደረጃ በሚከናወኑ የቱሪዝም እንቅስቃሴዎች መካከል ያለው መናበብ አነስተኛ መሆን እንደተግዳሮት የተጠቀሱ ጉዳዮች ናቸው፡፡
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ
በኢትዮጵያ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ዘርፉን ለመደገፍ ከተወሰዱ እርምጃዎች መካከል ከቱሪዝሙ ዘርፍ የአገልግሎት ዘርፎች አንዱ የሆነው የሆቴሎችና መስተንግዶ ዘርፍ በአነስተኛ ወለድ ብድር እንዲያገኝ መደረጉ ይጠቀሳል፡፡ ከዚህ የብድር ድጋፍ መካከል ለአስጎብኝው ንዑስ ዘርፍ የደረሰው 11 በመቶ ያህሉ ብቻ ነበር፡፡ ለዚህም እንደ መከራከሪያ የቀረበው የሆቴል ዘርፍ ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል የፈጠረ እንደመሆኑ ጫናው ከፍ ያለ ነው፤ የአስጎብኝዎች ዘርፍ ግን ይህ ጫና የለበትም የሚል አመለካከት ነው፡፡ ሆቴሎች የሚያስተናግዷቸውን እንግዶች በዋናነት የሚያገኙት ከአስጎብኝዎች መሆኑን ግን መረዳት አያዳግትም፡፡
ስለሆነም እንግዶችን ለሚያመጣው ዘርፍ አነስተኛ ትኩረት በመስጠት የሚደረግ ድጋፍና እገዛ ውጤታማ ላይሆን ይችላል፡፡ በመሆኑም ለዘርፉ የሚደረገው ድጋፍ ለሁሉም የዘርፉ ባለድርሻዎች በፍትሃዊና በሚዛናዊነት መከፋፈል ይኖርበታል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፤ የ11 በመቶ የገንዘብ ብድር አቅርቦቱም ቢሆን ከአፈጻጸም ጋር በተያያዙ ቢሮክራሲያዊ አሰራሮች ምክንያት እስካሁንም ድረስ ተግባራዊ ሊደረጉ አልቻሉም፡፡
የተዛባ ግንዛቤ የተያዘበት የቀረጥ ነጻ ዕድል
አስጎብኝዎች ተሽከርካሪዎችን ከቀረጥ ነጻ ወደ አገር ውስጥ ማስገባት እንዲችሉ የተሰጣቸው ዕድል ምንም እንኳን ብዙ ሲወራለት የነበረ አጀንዳ ቢሆንም፣ ጉዳዩ ግን በራሳቸው በአስጎብኝዎች ዘንድ ሳይቀር የተለያዩ ስሜቶችን የፈጠረ ነው፡፡ የቀረጥ ነጻ ዕድሉ ስረ መሰረት፣ አላማ፣ ዕቅድ አወጣጥ እና አፈጻጸም እንዲሁም ክትትል ደካማ እንደነበር የኤፍ ጂ ዲ ተሳታፊዎች ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ተሳታፊዎች የቀረጥ ነጻ ዕድሉ ለአስጎብኝዎች ከበረከት እርግማን እንደሆነ አድርገው ነው የሚያስቡት፡፡
አንዳንድ አስጎብኝዎች የቀረጥ ነጻ ዕድሉን ባልተገባ መልኩ ሲጠቀሙበትና ሲያጭበረብሩበት መታየታቸው እንዳለ ሆኖ፣ በርካቶች ግን በዘርፉ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ተጠቅመውበታል፡፡ የኤፍ ጂ ዲ ተሳታፊዎች ከዚህ ባለፈም፤ የኢትዮጵያ መንግስት የቀረጥ ነጻ ዕድሉን ስረ መሰረት፣ አላማ፣ ዕቅድ አወጣጥ እና አፈጻጸም እንዲሁም ክትትል መልሶ መከለስና ዕድሉን ለአስር አመት ያህል ዘላቂ ማድረግ እንደሚገባውም ይስማማሉ፡፡
የግብር ህግና የኦዲት አሰራር
ከግብር ጋር በተያያዘ የአገሪቱን አስጎብኝዎች በሁለት ምድቦች ከፋፍሎ ማየት ይቻላል፤ ግብር ከአጠቃላይ ገቢያቸው ላይ የሚከፍሉ እና ከትርፋቸው ላይ የሚከፍሉ፡፡
ዋነኛው ችግር ግን፣ ኦዲተሮች ግብርን በሚያሰሉበት ወቅት የዘርፉን የንግድ ተፈጥሮና ባህርይ በሚገባ መገንዘብ አለመቻላቸው ነው፡፡ ለአብነትም የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ እንስሳት ኪራይን ጨምሮ መደበኛ ካልሆኑ አገልግሎት ሰጪዎች የሚሰበሰቡ ደረሰኞች አብዛኛውን ጊዜ በግብር ባለስልጣናት ህጋዊ ተደርገው አይታዩም፤ ተቀባይነት አያገኙም፡፡
ይህም በመሆኑ፣ የሚመለከታቸው አካላት በግብር ስርዓቱ ላይ የፖሊሲና ሌሎች ተገቢ ማሻሻያዎችን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለአስጎብኝዎች ተመሳሳይ የግብር ስሌት ስርዓትን በስራ ላይ ማዋልና ከተለያዩ አገልግሎት ሰጪዎች የሚሰበሰቡ ደረሰኞች ተቀባይነት እንዲያገኙ ማድረግ እንደሚገባ ይመከራል፡፡
ዘርፉን እንደ አንድ የወጪ ንግድ ዘርፍ እውቅና መስጠት
የቱሪዝሙ ዘርፍ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከሚያስገኙ ዋነኛ ዘርፎች አንዱ ነው፡፡ ዘርፉ ባለፉት አምስት አመታት በየአመቱ በአማካይ የ2 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማስገኘቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ያም ሆኖ ግን፣ ሁሉም የፖሊሲና የህግ ማዕቀፎች እንዲሁም የአሰራር መመሪያዎች ዘርፉ የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ አሳንሰው የሚያዩና ተገቢውን ትኩረት የማይሰጡ ናቸው፡፡ ይህን ችግር የመፍታት ጥረት የሚጀምረው፣ ዘርፉ አገልግሎትን ለወጪ ንግድ የሚያቀርብ እንደሆነ አምኖ በመቀበልና እውቅና መስጠት ነው፡፡ ከዚህ ባሻገርም ዘርፉ የግብር እፎይታ፣ የተለያዩ የጉዞና አስጎብኝ መሳሪያዎችንና ቁሳቁሶችን ከቀረጥ ነጻ ማስገባትን ጨምሮ ለወጪ ንግድ ዘርፎች ከተሰጡ ዕድሎች ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ ይገባል፡፡
የመሰረተ ልማትና የጥበቃ ችግሮች
በቱሪዝሙ ዘርፍ የሚታየው የመሰረተ ልማት ችግር እጅግ የከፋ ነው፡፡ የቱሪስት ስፍራዎች፣ ወደ ቱሪስት መዳረሻዎች የሚወስዱ መንገዶች፣ የቱሪስት አገልግሎት ሰጪዎችና ሌሎች ጉዳዮች እንደ አጠቃላይ በቂ ትኩረት አልተሰጣቸውም ማለት ይቻላል፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆኑ በርካታ አብነቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ እና ባሌ ብሔራዊ ፓርክ በዙሪያቸው የሚገኙ ነዋሪዎች በሚያደርጉባቸው ጣልቃ ገብነት ሳቢያ የሚገኙበት የከፋ ሁኔታ ቱሪስቶችን የሚያሸሽ ነው፡፡ ለዚህም ነው ፓርኮቹን የሚጎበኙ ቱሪስቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ በመቀነስ ላይ የሚገኘው፡፡ በ2005 ላይ 5300 የነበረው የጎብኝዎች ቁጥር በ2007 ወደ 20500 ቢያድግም፣ ከ2010 አንስቶ ግን የጎብኝዎች ቁጥር ቅናሽ ማሳየት የጀመረ ሲሆን በ2017 ላይ 7600 ደርሷል፡፡
የቱሪዝም መረጃ ክፍተት
በአገሪቱ ታሪክ ከፍተኛው የቱሪስቶች ቁጥር የተመዘገበው በ2017 ሲሆን፣ በአመቱ 933,000 ያህል ቱሪስቶች አገሪቱን እንደጎበኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በኤፍ ጂ ዲ ምላሻቸውን የሰጡ ተሳታፊዎች ግን የዚህን መረጃ ትክክለኛነት እንደማያምኑበት ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ አስገብኝዎች ማህበር ባሰራው ጥናት ላይ የተሳተፉ እንደሚሉት፣ ወደ አገሪቱ የመጡት ለንግድ ወይም ለሌላ ጉዳይ ሆኖ ሳለ የቱሪስት ቪዛ ይዘው የሚገቡ ወይም አዲስ አበባ ቦሌ አለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ ሲደርሱ የቱሪስት ቪዛ የሚጠይቁ ሰዎችን ማየት የተመለደ ክስተት ነው፡፡ ይህን መሰሉ የቱሪስት መረጃ አሰባሰብ ትክክለኛውን የቱሪዝም ገጽታ ለመገንዘብም ሆነ ለዘርፉ ውጤታማ ዕቅድ ለማውጣት ክፍተት እየፈጠረ ነው የሚገኘው፡፡
የአካባቢያዊና ክልላዊ የቱሪዝም ልማት ስራዎች ቅንጅት
ኢትዮጵያ የምትከተለው የፌዴራላዊ ስርዓት ዓላማ ህዝቦች ራሳቸውን የማስተዳደር ፖለቲካዊ መብቶቻቸው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻል ነበር፡፡ ይህም በአገሪቱ ዲሞክራሲንና ዲሞክራሲያዊ ባህልን ለማስፋፋት እንደ አንድ ወሳኝ ቅድመ ሁኔታ የሚታይ ነው፡፡ ያም ሆኖ ግን፤ ከብሔራዊ ዕቅድና ራዕዩ ጋር የማይጣጣሙ አካባቢያዊ አሰራሮች በመስፋፋታቸው ሳቢያ ቱሪዝምን በመሳሰሉ መስኮች በየክልሎች የሚከናወኑ የንግድ ስራዎች ችግር እየገጠማቸው ይገኛሉ፡፡ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚታዩት የተለያዩ የቱሪስት አገልግሎት ክፍያዎች፣ የቱሪስት አስጎብኝነት አገልግሎት መመሪያዎችና ሌሎች ከዘርፉ ጋር የሚያያዙ ጉዳዮች አስጎብኝዎች የራሳቸውን ዕቅድ እንዳያወጡና የቱሪስቱን ፍላጎት በሚገባ እንዳያሟሉ እንቅፋት እየፈጠረባቸው ነው፡፡
ልማቶች (ቁሳዊና ቴክኖሎጂያዊ መሰረተ ልማቶችን ጨምሮ)
የኢትዮጵያን የቱሪዝም ዘርፍ ልማት ዋነኛና መሰረታዊ ምዕራፎች እንደሚከተለው በሶስት አንጻር ማየት ይቻላል – የፖሊሲና የሕግ ማዕቀፍ፣ መዋቅራዊና ተቋማዊ፣ ማርኬቲንግና ፕሮሞሽን፡፡
ፖሊሲና የህግ ማዕቀፍ
በ2020 የወጣው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የ10 አመት የኢኮኖሚ ልማት ዕቅድ ቅድሚያ ትኩረት ከሰጣቸው ዘርፎች መካከል አንዱ ቱሪዝም ነው (ዘርፉ አሁንም ቢሆን በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ የሚገኝ ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ አጠቃላይ ኢኮኖሚ የ9.4 በመቶ ድርሻ አለው)፡፡
በ2018 የስራ ፈጠራ አጀንዳ ውስጥ ከፍተኛ የስራ ዕድል ይፈጥራሉ ተብለው ትኩረት ከሰጣቸው ዘርፎች አንዱ ነው (ዘርፉ 2.2 ሚሊዮን የስራ ዕድሎችን የመፍጠር ወይም ከአጠቃላዩ የስራ ዕድል 8.3 በመቶ ድርሻ የመያዝ አቅም እንዳለው ከግምት ውስጥ በመግባቱ፣ በአዲሱ የግልጽግና ዕቅድና የስራ ፈጠራ ስትራቴጂ ውስጥም ተካትቷል)፡፡
መዋቅራዊና ተቋማዊ
- አዲሱ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግስት በ2021 መመስረቱን ተከትሎ የቱሪዝም ሚኒስቴር የተቋቋመበት አዋጅ ቁጥር 123/2021፤
- የኢትዮጵያ ቱሪዝም ቦርድን የመሳሰሉ መዋቅሮች፤
- የኢትዮጵያ የሆቴልና ቱሪዝም ስልጠና ተቋም፤
- የኢትዮጵያ የቱሪዝም ድርጅት፡፡
ማርኬቲንግና ፕሮሞሽን
- “ምድረ ቀደምት” የተሰኘ አዲስ የማርኬቲንግና ፕሮሞሽን ስትራቴጂ፤
- በአለማቀፍ የቱሪዝም የንግድ ትርዒቶች ላይ የመሳተፍ ልምድ፤
- የኢትዮጵያ በዓላት አስተዋጽኦ (የኢትዮጵያ አየር መንገድ)፡፡
