የፈረንሳዩ ፒ ኤስ ጂ እና የእንግሊዙ ቼልሲ ምሽት 4 ሠአት ላይ በዓለም የክለቦች ዋንጫ ፍጻሜ ይገናኛሉ፡፡
በፍጻሜው የቻምፒየንስ ሊግ ዋንጫን ያነሳው ፒ ኤስ ጂ የተሻለ የአሸናፊነት ግምት አግኝቷል።
ከኋላ ጀምሮ በጠንካራ አደረጃጀት የተገነባው የሊዊስ ኤንሪኬው ፒ ኤስ ጅ ተጋጣሚዎቹን በቀላሉ በማሸነፍ ለፍጻሜው ደርሷል።
የኮንፈረንስ ሊጉ አሸናፊ ቼልሲ ተጫዋቾች በዛሬው ጨዋታ ፒ ኤስ ጅ ተገማች ቢሆንም ለሁሉም መፍትሄ አለን እያሉ ነው።
ተጫዋቾቹ ፒ ኤስ ጅን ማሸነፍ የምንችለው እኛ ብቻ ነን ብለዋል።
በምሽቱ ጨዋታ ጠንካራ ተጋጣሚዎችን ተራ የሚያስመስለው የኤንሪኬ የጨዋታ እሳቤና የማሬስካ ልጆች ምላሽ ይጠበቃል።
አሰልጣኝ ኤንሪኬ ሰነፍ እየተባለ የሚታማውን ባለ ተሰጥኦ ደምበሌን ወደ አስፈሪ እና ውጤታማ ተጫዋችነት የቀየሩበትና ቡድኑን ያዋቀሩበት መንገድ ከበርካቶች አድናቆት አስችሯቸዋል።
ለፍጹምነት የቀረበ የመሰለው የእርሳቸው ፒ ኤስ ጅም በዘንድሮው የውድድር ዓመት የተሳተፈባቸውን ዋንጫዎች ጠራርጎ ወስዷል።
በርካታ ተጫዋቾችን ያዘዋወረው ቼልሲም በማሬስካ ስር መሻሻሎችን ያሳየ ሲሆን በአይደክሜው ካይሴዶና ኤንዞ ፈርናንዴዝ የተገነባው አማካይ በርካታ ቦታዎችን የሚያካልል እና ጠንካራው ክፍል ነው።
በተጨማሪም እንደ ኮል ፓልመር ያሉ ልዩነት ፈጣሪ ተጫዋቾች በምሽቱ ጨዋታ የሚኖራቸው ሚናም ተጠባቂ ነው።
በፍጻሜ ጨዋታው የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እንደሚገኙ በትናንትናው ዕለት መገለጹ ይታወሳል፡፡
