‹‹የዛሬውን ሳይኾን የነገውን ትውልድ እንድፈራው ተገድጃለሁ›› ያሬድ ኃይለማርያም (የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

Date:

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል ዋና ዳይሬክተር የኾነው ያሬድ ኃይለማርያም በቅርቡ “የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ትውስታዎች” የሚል ርዕስ ያለው መጽሐፉን በርካታ የሙያ እና የሕይወት ዘመን ባልደረቦቹ በተገኙበት አስመርቋል፡፡ ፀሐፊው ያሬድ ኃይለማርያም ላለፉት ረዘም ላሉ ዓመታት በኢትዮጵያ ውስጥ ሰፍኖ የቆየውንና አሁን በተለያየ መልኩ የቀጠለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰትን ሲታገል እና በግሉም ሙያዊ ኃላፊነቱን ሲወጣ የቆየ ሰው ነው፡፡ ለመኾኑ ዐዲሱ መጽሐፉ ምን ምን ጉዳዮችን ይዟል? ከሚለው ጀምሮ በኢትዮጵያ ትውልዱ የደረሰበት አጠቃላይ ሞራላዊ እና ሥነ ምግባራዊ መለዮ፣ በቀጣይ መሠራት ስለሚገባቸው ወሳኝ ቁምነገሮች እና ሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች ከጋዜጠኛ ፍቃዱ ማኅተመወርቅ ጋር የሚከተለውን ቆይታ አድርጓል፡፡ መልካም ንባብ!  

ግዮን፡- በቅርቡ ያስመረቅከው መጽሐፍ ይዘቱ ምንድነው?

ያሬድ፡- የመጽሐፌ ርዕስ “የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ትውስታዎች” የሚል ነው፡፡ “ከማጂ እስከ ጄኔቫ” የሚል ንዑስ ርዕስም አለው፡፡ እኔ በሰብዓዊ መብት ላይ ስሠራ 25 ዓመት ይኾነኛል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሰብዓዊ መብት መግለጫዎች ሁልጊዜ ይወጣሉ፡፡ ነገር ግን ከሪፖርቶቹ ጀርባ የሰብዓዊ መብት ጉዳይ የሚመረምሩ ሰዎች እንዴት ሥራቸውን እንደሚሠሩ፣ ምን ተግባር እንደሚያከናውኑ ብዙ ሲወሳ አይታይም፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ሁኔታ ከዕለት ዕለት እየከፋ የመጣ ቢኾንም የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ቁጥር እያነሰ ሄዷል፡፡ በተለይ በእኛ ጊዜ የነበሩ ምሁራኖች፣ ጋዜጠኞች፣ በሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ላይ አተኩረው ይታገሉ የነበሩ ሰዎች በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሱ ነው፡፡ አሁን ያሉ የሲቨክ ማኅበራትም በዚያው ልክ እየተዳከሙ መጥተዋል፡፡ ስለዚህ “እንዴት ነበር ያንን አስቸጋሪ ዘመን ያሳለፍነው? ምን ነበር የነበሩብን ተግዳሮቶች? ለምን በዚያ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እስከመጨረሻ ለመሥራት ወሰንን?” የሚሉት ነገሮች ለአዲሱ ትውልድ መማሪያ ይኾነናል የሚለውን በማሰብና ታሪክን በአግባቡ መሰነድ በሚል መነሻ መጽሐፉን ላዘጋጀው ችያለሁ፡፡ መጽሐፉ ውስጥም ያሬድ ኃ/ማርያም ማነው? የሚለውን መልሻለሁ፡፡ እንዴት ነው ያደገው? የት ነው የኖረው? የሚለውንም መልሻለሁ፡፡ ኢሰመጉን እንዴት እንደተቀላከልኩና እንዴት ወደ ሰብዓዊ መብት ትግል ውስጥ እንደገባሁ አስቀምጫለሁ፡፡ በኢሰመጉ ሰብዓዊ መብት ትግል ውስጥ ያሳለፍነውን? ረጅም ጊዜ (8 ዓመት) እንዴት አስቸጋሪ እንደነበር አንስቻለሁ፡፡ እንዴትና በምን ምክንያት እንደተሰደድኩም? በስደት ሕይወት ውስጥም እንዴት እንዳሳለፍኩና እንደተመለስኩም ጭምር በዝርዝር አስቀምጫለሁ፡፡

ግዮን፡- የመጽሐፉ ምርቃት የት ነበር? እነማንስ በእንግድነት ተገኙ? የምርቃቱስ ሂደት ምን ይመስል ነበር?

ያሬድ፡- ምርቃቱ ላይ የተገኙት እንግዶች በርካታ ናቸው፡፡ በልዩ ሁኔታ ጥሪ ያደረግሁላቸው እንግዶች ነበሩ፡፡ እነዚያ ሰዎች ከሰብዓዊ መብት ትግል ጋር በአንድ ወይም በሌላ አጋጣሚ ከእኔ ጋር አብረን የቆየን የሥራ ባልደረቦች ናቸው፡፡ ከዚህ ውጪ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚከታተሉ አንባቢዎቼን ጋብዤ ነበር፡፡ እንዲሁም ቤተሰብና የሥራ ባልደረቦቼ በተጨማሪም እጅግ የማከብራቸው ለምሳሌ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ፣ ዶ/ር ዳንኤል በቀለ፣ ዶ/ር ዲዲሞስ ኃይሌ፣ ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ፣ የኢሰመጉ የአሁኑ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ የኔ መንግሥት፣ ኮሚሽነር መስከረም ገስጥ፣ ዶ/ር አረጋዊ በርሄ እና ሌሎችም ተገኝተዋል፡፡ ዶ/ር አረጋዊ በርሄ በተለይ በስደት እያለን እርሱ አምስተርዳም፣ እኔ ብራሰልስ ኾነን ብዙ ነገሮችን አብረን እንሠራ ነበር፡፡ በጋራ ያቋቋምነው “ድልድይ” የሚባል የውይይት መድረክም አለን፡፡ እኔና ዶ/ር አረጋዊ ከእነ ዶ/ር ነገደ ጎበዜ፣ አቶ አበራ የማነአብ እና ሌሎችም ጋር በመኾን ነው ድልድይ የተባለውን የውይይት መድረክ ያቋቋምነው፡፡ በአውሮፓ ፓርላማ ለመጀመሪያ ጊዜ 2005 ምስክርነት ስሰጥ ዶ/ር አረጋዊ አብሮኝ ነበር፡፡ በጥቅሉ እነዚህን ሰዎች ጨምሮ ብዙ ሰዎች በመጽሐፉ ምረቃው ላይ ተገኝተው ነበር፡፡

ግዮን፡- “ድልድይ” የሚባለው የውይይት መድረክ ለምን ነበር የተቋቋመው? አሁንስ አለ?

ያሬድ፡- ድልድይ የውይይት መድረክ ሲቋቋም መጀመሪያ መደበኛ የውይይት መድረክ አልነበረም፡፡ ለረጅም ዓመት በአካል በወር አንድ ጊዜ በብራስልስ የምንኖር ኢትዮጵያውያን እየተሰባበሰብን በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ እንመክር ነበር፡፡ እዚያው ውስጥ ዶ/ር ነገደ ጎበዜ፣ ጋዜጠኛ ገበያው ንጉሤ፣ አቶ አበራ የማነአብ፣ ዶ/ር ዳዲሞስን ጨምሮ ብዙ ታዋቂ ሰዎች ነበሩ፡፡ እየቆየን ስንመጣ ለምን የውይይት መድረኩን ወደ መደበኛ መድረክነት የማንቀይረው አልንና በሌላ የአውሮፓ ሀገራት ጀርመን፣ ስዊድን፣ ሲውዘርላንድ፣ አምስተርዳም፣ ያሉ ሰዎችን ጨምረን ወደ ማኅበር ቀየርነው፡፡ ድልድይ የሚለውን ስም አጭር ስሙ ነው፡፡ ዋናው ሥሙ “የኢትዮጵያውያን የውይይት መድረክ በአውሮፓ” የሚል ነው፡፡ ትልቁን ዓላማችን ወሳኝ በኾኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የውይይት መድረኮችን ማዘጋጀት ነው፡፡ በዚህም በጣም በርካታ የውይይት መድረኮችን አዘጋጅተናል፤ በአካል እነ ጋሽ የሱፍ፣ እነዶ/ር አረጋዊ በርሄ በርካታ ጽሑፎችን አቅርብበውበታል፡፡ የተለያዩ ሰዎችን እየጋበዝን ውይይት አድርገናል፡፡ የሴቶችን ቀን፣ ዓድዋን ድል አስመልክተን ብዙ የኦንላይን ውይይቶችን አድርገናል፡፡ አሁን በዚህ ወቅትም አንድ የውይይት መድረክ እየተዘጋጀ ነው፡፡ አሁን ሙሉ በሙሉ ብራስልስ ተመዝግቦ ሰርተፍኬት አግኝቶ የሚገኝ የመወያያ መድረክ ነው፡፡ የሚመራው በአቶ አበራ የማነአብ ሰብሳቢነት በእኔ እና በጓዶቻችን የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴነት ነው፡፡ ትልቁ ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ በፖለቲካ ችግር ሲኖር ለመንግሥትና ለባለ ድርሻ አካል ምክረ ሐሰብ ለመሥጠት ምሁራን ጠርቶ የሚያወያይ የውይይት መድረክ መኾኑ ነው፡፡

ግዮን፡- እስካሁን ሀገሪቱ በለውጡ መንግሥት እየገጠማት ካለው ችግር አንጻር ተወያይታችሁ ለመንግሥት ያቀረባችሁት ምክረ ሐሳብ አለ? ወደፊትስ ምን የታሰበ ነገር አለ?

ያሬድ፡- ድልድይ መቀመጫው ብራስልስ ስለኾነ ብዙ ጊዜ ብራስልስ ካለው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር እንሠራለን፡፡ ለምሳሌ ለውጡ የመጣ አካባቢ ያዘጋጀነው አንድ የውይይት መድረክ ላይ አምባሳደሮችን ሁሉ ጋብዘን ነበር፡፡ በብዙ ውይይቶች ለኢምባሲው ምክረ ሐሳቦችን ሰጥተናል፡፡ መግለጫዎቻችንን ለመንግሥት ይፋ አድርገናል፡፡ ከኢትዮጵያ የሚሄዱ የመንግሥት ባለሥልጣናት ሲኖሩ ደግሞ የድልድይ ተወካዮች ስብሰባ ላይ ተገኝተው የድርጅቱን አቋም እና ያለንን ምልከታ ለመንግሥት ሁልጊዜ ያደርሳሉ፡፡ በተለይ እነአቶ አበራ የማነአብ ይኽን ጉዳይ በደንብ ሠርተውታል፡፡

ግዮን፡- ከመጽሐፍህ ሰዎች ምን ይማራሉ? መጽሐፉን በውጪ ቋንቋዎች የማሳተም እቅድስ አለህ?

ያሬድ፡- መጽሐፉ በኢትዮጵያ ያለውን የሰብዓዊ መብት ሁኔታ አስቸጋሪነትና ከባድነት ይገልፃል፡፡ ዘርፉ ከሚወጡ መግለጫዎች ጀርባ ያልተተገበሩ ብዙ ታሪኮች ያሉበት፣ ፈተና የበዛበት አካባቢ መኾኑን ያሳያል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ በመጽሐፉ በእያንዳንዱ ታሪክ ውስጥ ኢትዮጵያን ማየት ይቻላል፡፡ ከጋምቤላ አንስቶ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ያለውን ምስቅልቅልና ሁለገብ ችግሮች ማየት ይቻልበታል፡፡ ለምሳሌ የመጽሐፉ የመጀመሪያ ክፍል አዲስ አበባ ውስጥ ሴተኛ አዳሪ የኾኑ ሕጻናት ሕይወት ምን እንደሚመስል ያሳያል፡፡ ይህን ታሪክ ብዙ ሰው አያውቅም፡፡ ስለዚህ በትክክል ኢትዮጵያን ከነገመናዋ እናውቃታለን ወይ የሚለውን የሚመልስ መጽሐፍ ነው፡፡ ጉዳዩ በምርምር በጥናት የታየ ሳይኾን እኔ በዕለት ዕለት ሕይወቴ የገጠመኝን ሰብስቤ ነው ለንባብ ያበቃሁት ነው፡፡

በሌላ በኩል መጽሐፉ በሰብዓዊ መብት ጉዳይ ላይ መሥራት ለሚፈልጉ ወጣቶች ጽናትን ያስተምራል፡፡ ለ25 ዓመት ከኢትዮጵያ እስከ ጄነቫ በዓለም ዐቀፍ መድረኮች ጭምር በሰብዓዊ መብት ጉዳይ ላይ ስንሠራ የነበርነው ጥቂት ሰዎች ነን፡፡ እነዶ/ር ዳንኤል በቀለም ነገ ታሪካቸውን ይጽፋሉ፡፡ እነብርቱካን ሚደቅሳም እንደዚያው፡፡ የነበርንበት ዘመን ታሪክም በአግባቡ ይሰነዳል፡፡ በውጪ ቋንቋ የመተርጎምን ጉዳይ በተመለከተ ሥራው ተጀምሯል፡፡ በትርጉም ሥራ ለሚታወቁ ባለሙያዎች ሥራው ተሰጥቷል፡፡ በቅርቡ የእንግሊዘኛው እትም ይወጣል፡፡ በደንብ ተሰንዶ በአማዞን ላይ እንዲሰፍርና በሌሎችም ዓለም አቀፍ የመጽሐፍ መሸጫ ተቋማት እንዲገኝ ለማድረግ እየተሠራ ነው፡፡

ግዮን፡- አሁን ካለው የሕትመት ዋጋ ውድነት አንጻር እንዴት ተቋቁመኽ መጽሐፉን ለማሳትም በቃህ?

ያሪድ፡- የሕትመት ዋጋው በጣም ከባድ ነው፡፡ የአንድ መጽሐፍ ዋጋ ማተሚያ ቤት የሚጠይቀው ገንዘብ በጣም ውድ ነው፡፡ እኔ እንደውም የተማርኩት ኢትዮጵያ ውስጥ የሕትመት ሚዲያው  የተዳከመው በሕትመት ዋጋ መናር መኾኑን ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ በሀገሪቱ የንባብ ባሕል የተዳከመው በዚሁ ምክንያት ነው ብዬ እንዳስብ አስገድዶኛል፡፡ ሀገራችን ድሮም አንባቢ አልነበረም፤ አሁን ደግሞ በኦንላይን የሚያገኛትን ቅንጫቢ ጽሑፍ ብቻ እውቀት ብሎ እንዲይዝ ተደርጓል፡፡ መንግሥት ከሌሎች ነገሮች ሁሉ የሕትመት ቁሳቁስን ውድ አድርጎታል፡፡ የኤሌክትሮኒክስ መኪና ከቀረጥ ነፃ የምታስገባ ሀገር የሕትመት ቁሳቁሶችን ላይ ከፍተኛ ቀረጥ ጥላለች፡፡ እንደሀገር የተሰጠው ትኩረት ደካማ ነው፡፡ ከትውልድ መቅረጫና ከዕውቀቱ ይልቅ ለኤሌክትሪክ መኪና ቅድሚያ ተሰጥቷል፡፡ የሕትመት ሥራውን መዳከም ጉዳቱ በሚቀጥለው ትውልድ ላይ ይታያል፡፡ ኢትዮጵያ ድሮ በሳምንት ውስጥ እስከ 10 መጽሔቶች የታተሙባት ሀገር ነበረች፡፡ አሁን አንድ መጽሔት በቀን ሳይኾን በሳምንትም ማግኘት እየከበደ ነው፡፡ ቢገኝ እንኳን ዋጋው ቀላል አደለም፡፡ ስለዚህ በሕትመቱ በኩል ትውልዱን ለመቅረፅና ማኅበረሰቡን ለማስተማር በመንግሥት በኩል የተሰጠው ትኩረት ከዜሮ በታች ነው፡፡ በዚህም የሕትመት ሥራው ውስጥ እኔም ተፈትኜበታለሁ፡፡

ግዮን፡- መንግሥት በዚህ ዙሪያ ምን ያድርግ ትላለህ?

ያሬድ፡- የሕትመት ውጤቱ በመድከሙ አንባቢ ትውልድ ጠፍቷል፡፡ ሁለት ድግሪ ይዘው ድርጅት እየመሩ አንድ መፅሐፍ ያላነበቡ በርካታ ግለሰቦች አሉ፡፡ ሕግ ተምረው ፖለቲካል ሳይንስ ተምረው መጽሐፍ እና ጋዜጣ የማያነቡ ሰዎች መጥተዋል፡፡ ከማንበብ ይልቅ ከማኅበራዊ ሚዲያና በቲክቶክ የሚሰጡ ቧልቶችን እውቀት አድርገው በሀገር ጉዳይ ላይ ትንታኔ የሚሰጡ ሰዎች ተበራክተዋል፡፡ አሁን ላይ ሰው ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ቁምነገር ከሚሰማ ይልቅ ቧልትና ስድብን ምርጫው አድርጓል፡፡ ተሳዳቢዎችን በሺ የሚቆጠሩ ሰዎች ቁጭ ብለው መከታተል ሙያ እየኾነ መጥቷል፡፡ በዚህ የተነሳ እኔ የዛሬውን ሳይኾን የነገውን ትውልድ እንድፈራው ተገድጃለሁ፡፡ ታሪኩን አያውቅም፡፡ የሚኖርባትን ሀገር እና ማኅበረሰብ ሥነ-ልቦና አያውቅም፡፡ ሲታይ ደግሞ ፍጹም ዘመናዊ የሚመስል ውድ ስልክ በእጁ የያዘ፣ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ንቁ ተሳታፊ፣ ነገር ግን ውስጡ ባዶ የኾነ ትውልድ እንዲፈጠር እየተደረገ ነው፡፡ ይኼ በሁለት መንገድ አደጋ አለው፡፡ የመጀመሪያው በማያውቀው ታሪክ መጣላቱ ነው፡፡ ዛሬ የምናያቸው ልጆች የነገ ባለሥልጣናት ናቸው፡፡ የዛሬዎቹ ባለሥልጣናት ትላንት በህወሓት ዘመን የደነቆሩ እና የካድሬ መጽሐፍ ብቻ ሲያነቡ የነበሩ ናቸው፡፡ አዲስ ዘመን ጋዜጣና በመለስ ጽሑፍ ውስጥ ብቻ ኢትዮጵያን ሲያዩ የኖሩ ናቸው፡፡

ይህ በመኾኑ አሁን አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንድንገባ ተገደናል፡፡ የዛሬዎቹ ፖለቲከኞች የፈጠሯት ኢትዮጵያ ወረቀት ጠል፣ ንባብ ጠል፣ በጣም ግልብ አስተሳሰብ ያነገቡ ሰዎች የሚኖሩባት ናት፡፡ ከዚህ አንፃር መጪው ትውልድ ኢትዮጵያን ምን ሊያደርጋት እንደሚችል ማሰብ በጣም ከባድ ነው፡፡ ስለዚህ በግሌ ለመንግሥት ከፓርክ ይልቅ እውቀት ይቅደም ማለት እፈልጋለሁ፡፡ ፓርክ ትውልድ እንዲቅምበት ነው’ንዴ የሚሠራው? አዕምሮ ላልተገነባ ማኅበረሰብ ፓርክ ቢሠራ፣ የሚያብረቀርቅ ነገር ቢሠራ፣ ኤሌክትሮኒክስ መኪና እንደልብ ቢገባ፤ በቁስ የበለጸገ ነገር ግን አዕምሮው የቀነጨረ ሰው ነው የሚፈጠረው፡፡ ያ ደግሞ የሀገርና የማኅበረሰብ ፍቅር ስለማይኖረው ሀገር ያጠፋል፡፡ የሞራልና የሥነ-ምግባር ተገዢ ስለማይኾን አደገኛ ትውልድ እየፈራ ነው፡፡

ግዮን፡- ከዚህ ቀጥሎ የሚወጣ መጽሐፍ አለህ?

ያሬድ፡- አዎ አወጣለሁ፡፡ የአሁኑ መጽሐፍ በሰብዓዊ መብት ጉዞዬ ላይ የሚያተኩር ነው፡፡ ያጠናሁት ሕግና ፍልስፍና ነው፡፡ ሁለቱን አቀላቅዬ በማኅበረሰባችን ውስጥ ችግር ናቸው የምንላቸው ወሳኝ ርዕሶች ላይ ምናልባትም በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ሁለተኛ መጽሐፍ ይዤ እመጣለሁ፡፡ ብዙ በጥልቀት ልናያቸው የሚገቡ የንባብ ባሕል መድከምን ጨምሮ በመጽሐፌ አባሪ ላይ የያዝኳቸው በርካታ አጫጭር ጉዳዮች አሉ፡፡ ለምሳሌ አንዱ “ፍርሐትን እያሰረፀ ያለው የኢትዮጵያ ፖለቲካ” የሚል ርዕስ አለው፡፡ በዚህ ርዕሰ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ማኅበረሰቡ ውስጥ ምን ያህል ፍርሐት እያሰፈነ እንደኾነ ትክክለኛ ጥናት አድርጌ ወደ ሦስት ተከታታይ ጽሑፍ ጽፌያለሁ፡፡ እነዚህን ጽሑፎች የበለጠ በጥናት አጠናክሬ ላቀርባቸው እፈልልጋለሁ፡፡

ግዮን፡- በኢትዮጵያ ውስጥ ያቋቋምከው የሰብዓዊ መብት ድርጅት ምን የሚባል ነው? ከተመሠረተ ምን ያህል ጊዜ ኾነው?

ያሬድ፡- ድርጅቱ “የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል” የሚል ሥያሜ አለው፡፡ ትልቁ ትኩረቱ በሰብዓዊ መብት ጉዳይ ላይ ነው፡፡ እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ውስጥ ጋዜጠኞች፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ሲዋከቡ፣ ሲታሰሩ፣ ቢሯቸው ሲታሸግ፣ በሐሰት ሲወነጀሉ ነው የኖሩት፡፡ እኛም በዚህ ውስጥ ነው ያለፍነው፡፡ በእኛ ጊዜ ለሰብዓዊ መብት ተሟጋች አልነበረም፡፡ ኢሰመጉ በጠቅላላ ሀገሪቱ ውስጥ ያለውን የሰብዓዊ መብት ሁኔታ ነው የሚያየው፡፡ ዋናው ሥራውም መግለጫ ማውጣት ነው፡፡ በሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች ለምሳሌ ኡጋንዳ በነበርኩበት ጊዜ እራሴ መሥራች የነበርኩበት የምሥራቅ አፍሪካ ቀንድ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ጥምረት ነበር፡፡ የተመሠረተው ለሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በአፍሪካ ቀንድና በምሥራቅ አፍሪካ ችግር ሲገጥም የፋይናንስ ድጋፍ ማድረግ፤ ሲታሠሩ ጠበቃ ማቆም፣ እንዲለቀቁ ድምጽ መኾን፣ ሥልጠና መሥጠት እንዲሁም አቅማቸውን ማጎልበት ላይ ነው የሚሠራው፡፡ ድርጅቱ በየሀገሩ ኬኒያ፣ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳ ሁሉም ሀገር ተመሥርቶ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ነበር ያልነበረው፡፡ በወቅቱ ሀገሪቱ ውስጥ የነበረው ሁኔታ እንኳን እንዲህ ዓይነት ተቋም መቋቋም ይቅርና ያሉትንም ድርጅቶች እያዳከመና እየዘጋ ነበር፡፡

ለውጡ ሲመጣ በመጀመሪያ ወደ ኢትዮጵያ ስመጣ እኔ ሰብዓዊ መብት ስሠራ የደረሰብኝ መጉላላት በሌሎች የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ላይ መድረስ የለበትም በሚል የዚህን ድርጅት ድጋፍ ይዤ ሌሎችን ሀገሪቱ ውስጥ የነበሩ ተቋማትን በመጨመር ወደ ስድሳ የሚኾኑ ተቋማትን ኢንተር ኮንቲኔንታል ሆቴል 2018 ላይ ለ5 ቀን በጋራ መከርን፡፡ 60 ሰው ፈርሞ የተቋቋመው ድርጅት ነው ፤ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ማዕከል፡፡ እስካሁን ከ500 በላይ ለሚኾኑ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች በመላው ሀገሪቱ ለጋዜጠኞች ጭምር ሥልጠና እየሠጠን ነው፡፡ ለታሠሩ ጋዜጠኞች ድምጽ እየኾንን ነው፡፡ ሲታሠሩ ካምፔን እናደርጋለን፡፡ ሰሞኑን ማኅበራዊ ሚዲያውን ዘግተወብናል፡፡ እንዲከፈትልን ጥያቄ እያቀረብን ነው፡፡ ለአንዳንድ ጋዜጠኞች ጠበቃም ቀጥረን ተከራክረናል፡፡ ጉዳት ለደረሰባቸው፣ እቃዎች ለወሰዱባቸውም ጋዜጠኞች የገንዘብ ድጋፍ አድርገናል፡፡

ግዮን፡- በሰብዓዊ መብት ተሟጋችነት ረዘም ያለ ጊዜ ከመቆየትህ አንፃር በመጽሐፍህ ከጠቀስካቸው ገጠመኞችህ አንዱን ብትነግረን?

ያሬድ፡- በመጽሐፉ ከጠቀስኩትና ከማይረሱ ገጠመኞቼ ውስጥ በተለይ ጋምቤላ ሄጄ ያጣራሁት ነገር አይረሳኝም፡፡ ሌሎች ገጠር ቦታዎች ላይም ሄጄ ያጣራሁት ነገር አንዳንዱ እንዳስፈላጊነቱ ትዝ ይለኛል፡፡ “ቱም” የምትባል ቤንች ማጂ ዞን ከተማ ውስጥ ለሥራ ሄደን ነበር፡፡ የብሐር ግጭት አለ ተብሎ 600ቤት ተቃጥሏል ተባለ፡፡ ቦታው ላይ ስንሄድ የዲዚና የሱርማ ብሔረሰቦች ተጋጭተዋል፡፡ ነገር ግን በሕዝቡ ውስጥ የከረረ ጥላቻ አልነበረም፡፡ መጥፎ አስተዳደር ያመጣው ግጭት እንደኾነ የሚታወቀው ተጋጭተዋል ተብሎ ጉዳያቸውን ልናጣራ የሄድንባቸውን ማኅበረሰቦች የሐሙስ ገበያ ላይ በፍቅርና በጋራ ሲገበያዩ ማግኘታችን ነው፡፡ በገበያው ላይ ፀብ የለ ምን የለ፡፡ እንዲሁም አንድ የሱርማና የዲዚ ወንድ አንድ የሱርማና የዲዚ ሴት አንድ ላይ አቅፌ ለማስታወሻ ፎቶ ተነስቻለሁ፡፡ የመጽሐፉ ሽፋን ላይ ያለውን ልጅ አቅፌ የተነሳሁበት ቦታ ይህ ቦታ ነው፡፡

እዚህ ቦታ ላይ የማልረሳው ትራንስፖርት አጥተን ለ3 ቀናት መቆየታችንን ነው፡፡ በዚህ የቆይታ ጊዜያችን ወደ ማረሚያ ቤት ሄድንና የማረሚያ ቤት አዛዡን ስለእሥር ቤቱ ሁኔታ ጠየቅነው፡፡ አዛዡ ሲነግረን እዚያ እሥር ቤት ለአንድ እሥረኛ በጊዜው የተመደበው 50 ሳንቲም ነበር፡፡ ይኼ መንግሥት የመደበው የእሥረኛው የቀን ቀለቡን ነው፡፡ ይህቺ 50 ሳንቲም ደግሞ ዳቦ እንኳን አትገዛም፡፡ ስለዚህ የእሥረኛውን 50 ሳንቲም በመሰብሰብ ቦርዴ የሚጠምቁ የአካባቢው ሰዎች ኮንትራት ይዘው እንዲያቀርቡ ተደረገ፡፡ ጠዋት በብዙ ባልዲ ቦርዴ ይቀርባል፡፡ ምሳና እራትም እንደጠዋቱ ሁሉ ቦርዴ ይቀርባል፡፡ ስለዚህ የእሥረኛው ቀለብ ከዓመት ዓመት ከቀን ቀን በጣሳ የተለካ ቦርዴ ብቻ ነው፡፡ ቦርዴው ስለሚያሰክር በቀን 3 ጊዜ ስለሚጠቀሙት ሁሌ ማታ ማታ እሥረኞቹ ይሰክራሉ፡፡ ይኽ መኾኑም ማረሚያ ቤቱ በየጊዜው ድብድብ እና ሁከት እንዲነሳበት አድርጓል፡፡ አንዳንዴ እሥረኞቹም ይገደላሉ፡፡ ምክንያቱም እሥረኛው ከከተማም በአካቢውም ካሉ ገጠሮች የተደባለቀ በመኾኑ ለረብሻ ቅርብ ነው፡፡ ይኼ ሰብዓዊ መብት በኢትዮጵያ ምን ያህል የከፋ እንደኾነ የሚያሳይ ነው፡፡

ግዮን፡- እስቲ ደግሞ ስለቤተሰብ ሕይወትህ አጫውተን?

ያሬድ፡- ሦስት ወንድ ልጆች አሉኝ፡፡ ባለቤቴ አይናዲስ ዳምጠው ትባላለች፡፡ የቀድሞው የኢሠመጉ ሠራተኛ ነች፡፡ ታሥራም ታውቃለች፡፡ ጠንካራ የመብት ተሟጋች ነበረች፡፡ አሁን ላይ የጤና ባለሙያ ኾና ቤልጂየም ሀገር በሥራ ላይ ትገኛለች፡፡ የመጀመሪያው ልጄ 19 ዓመቱ ነው፡፡ ልዑል ያሬድ ይባላል፡፡ ሁለተኛው ልጄ 13 ዓመቱ ሲኾን ምኒልክ ያሬድ ይባላል፡፡ ሦስተኛው ልጄ ደግሞ ረቂቅ ያሬድ ይባላል፡፡ ሰባት ዓመቱ ነው፡፡ መጽሐፉ አራተኛው ልጄ ነው፡፡ መጽሐፉ ከማጅ እስከ ጄነቭ የተባለበት ምክንያት ማጂ የተባለው ቦታ ከሄድኩባቸው ቦታዎች ሁሉ አስቸጋሪ በመኾኑ ነው፡፡ ቤንች ማጂ ዞን ማጂ ከተማ የሄድንበት መንገድ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የሰርግ ዘፍንም “መሄዴ ነው ማጂ፤ መሄዴ ነው ማጂ…” ተብሎ የተዘፈነለት አስቸጋሪ ቦታ ነው፡፡ ከዚያ ቦታ ወጥቼ በሰብዓዊ መብት ረገድ ከፍተኛ የሚባለውን ዓለም አቀፍ መድረክ ላይ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ካውንስል ውስጥ ሄጄ ድምጽ ማሰማት ችያለሁ፡፡ ስለዚህ የሁለቱን ቦታዎች ርቀትና በመሐላቸው ያለውን የ20 ዓመት እድሜ በአንድ ለመወከል ነው ከማጂ እስከ ጄኑቭ ያልኩት፡፡

በዚህ ውስጥ ጽናቴ ይታያል፡፡ እስከምን ድረስ ሄጄ የሕዝቡን ብሶትና አቤቱታ እንዳሰማሁ ያሳያል፡፡ ማጂ ኢትዮጵያ ውስጥ የሄድኩባቸው አስቸጋሪ ገጠራማ ቦታዎችን ይወክላል፤ ጄኔቫ ደግሞ በዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ውስጥ የሄድኩባቸውን ብዙ ቦታዎች ያሳያል፡፡ ጄኔቫ ብቻ ሳይኾን የአውሮፓ ፓርላማ ከአምስት ጊዜ በላይ ሄጃለሁ፡፡ ባለሥልጣናቱን አናግሬያለሁ፤ ለፓርላማውም በሀገራችን ያለውን ሰብዓዊ መብት ሁኔታ አስረዳ ነበር፡፡ የአፍሪካ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ለንደን ትላልቅ ዓለም አቀፍ ኮንፍረንሶች ውስጥ ተሳትፌያለሁ፡፡ ስለዚህ ጄኔቫ ዓለም አቀፍ መድረኮችን ይወክላል፡፡ ማጂ ደግሞ የኢትዮጵያ ገጠራማ እንግልቶችን ይወክላል፡፡ በዚህም ሁለቱን ጫፎች የመጽሐፌ ርዕስ አደረኳቸው፡፡

ግዮን፡- አሁን ባለው የሀገራችን ሁኔታ ምን ይሰማኻል? በለውጡ መንግሥት የነበረው ተስፋና የደረስንበትን ደረጃስ እንዴት ትረዳዋለህ?

ያሬድ፡- በተለያዩ ሚዲያዎች እንደተናገርኩት የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ሁኔታ ከድጥ ወደማጡ እየገባ ነው፡፡ በመጽሐፌ የከተብኩት የድጡን ዘመን ነው፡፡ አሁን ግን የማጡ ዘመን ፈተናችን ኾኖ መጥቷል፡፡ የማጡን ዘመን ማን እንደሚጽፈው አላውቅም፡፡ እኔ የድጡን ዘመን በምለው ጊዜ ውስጥ ሰብዓዊ መብትን የሚጥሰው መንግሥትና ታጣቂዎቹ ብቻ ነበሩ፡፡ ሰው በጥይት ይገደላል፣ ይታሰራል፣ ይፈናቀላል፣ ቢሮው ያታሸጋል…፡፡ አሁን ግን የእርጉዝ እናት ሆድ ተቀዶ “ይህ ልጅ ከተወለደ ለእኛ ሥጋት ነው” ተብሎ ከሆድ ወጥቶ የሚጣልበት ጊዜ ላይ ነን፡፡ የሰው አካል ቁጭ ተብሎ የሚበለትበት፣ የተገደለ ሰው በገመድ ታስሮ የሚጎተትበት፣ የመንግሥት ዩኒፎርም የለበሱ ሰዎች የጠረጠሩትን ሰው ቀጥቅጠው ገለው በእሳት እያቃጠሉ የሚሞቁበት ዘመን ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት አስፈሪ ጊዜ ይመጣል ብለን አስበን አናውቅም ነበር፡፡ ይኼ ለውጥ ሲመጣ ሁላችንም ተስፋ ነበረን፡፡ አዘቅዝቃ የነበረችው የኢትዮጵያ ጸሐይ እየወጣች ነው ብለን ተስፋ ነበረን፡፡ ለውጡ እንደመጣ ሕጎች ተቀይረው ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ “እኛ ነን አሸባሪዎች ይቅርታ አድርጉልን” ብለው ነበር፡፡ ሰው በግፍ አይታሰርም ተብሎ ነበር፡፡ አሁን ግን ኢትዮጵያ በሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ቁጥር ከዓለም አንደኛ ነች፡፡ ከአምስት ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ ግማሹ በማንነት ላይ ባተኮረ ጭፍጨፋ ነው የተፈናቅለው፡፡ ግማሹ በጦርነት የተፈናቀለ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ቤቱ እላዩ ላይ በግሬደር ስለፈረሰበት የተፈናቀለ ነው፡፡

እንዲህ ዓይነት ግፍ ኢትዮጵያ ውስጥ በእኛ እድሜ ተፈፅሞ አያውቅም፡፡ የውጪ ኃይል ሳይመጣብን የዘር ፖለቲካ በፈጠረብን ችግር ለዚህ ተዳርገናል፡፡  አሁን ያለው ሁኔታ ያስፈራል፡፡ ግን ደግሞ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ይሄ ነገር ቶሎ ተቀልብሶ በየክልሉ በዘፈቀደ ሀገር የሚያተራምሱ አካላት መንግሥት መስመር ያስይዛቸዋል ብዬ አስባለሁ፡፡ መንግሥት ውስጥ ኾነው ሕዝብን የሚበድሉ ለምሳሌ ሰሞኑን የዓድዋ በዓል ላይ የተሠራውን ነውር የጸጥታ አካላት ተጠያቂ የሚኾኑበት፣ መንግሥትም ወደ ቀልቡ ይመለሳል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ለእኔ የኢትዮጵያ ችግር የሕዝብ ችግር አይደለም፡፡ ከመንግሥት የሚመነጭ ችግር ነው፡፡ መንግሥት የሕግ የበላይነት ማስከበር ባለመቻሉ አዳዲስ ጉልበተኞች ተፈጥረዋል፡፡ እነዚህን ጉልበተኞች መንግሥት መስመር ማስያዝ አለበት፡፡ በመንግሥት ውስጥ ያለው ችግር መጥራት አለበት፡፡ የዘር ፖለቲካ ኢትዮጵያን ሳያጠፋት መስመር መያዝ አለበት፡፡ አዲስ የሕግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶ መንግሥት እርምጃ የማይወስድ ከኾነ የግጭቱ ባሕሪ የተወሳሰበ ነው፡፡ የሩዋንዳው ግጭት የዘር ግጭት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የዘርም የሃይማኖትም ግጭት አለ፡፡ የሩዋንዳው የዘር ግጭት በሁለት ብሔረሰቦች መካከል የተካሄደ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ማን ከማን እንደሚጋጭ ከባድ ነው፡፡ ከድንበር ጋር የተያያዘ የውስጥ ግጭት አለ፡፡ በውጪ ደግሞ ሀገሪቱ ከዓባይና መሰል ነገሮች ጋር ተያይዞ በእሳት ውስጥ የምትገኝ ሀገር ነች፡፡ ብዙ የውጪ ኃይሎች ያሴሩባትና ጥርስ ውስጥ የገባች ሀገር ነች፡፡

ግዮን፡- በሀገራችን ያለውን የሃይማኖት ጉዳይስ እንዴት ታየዋለህ?

ያሬድ፡- ኢትዮጵያ በሃይማኖት መቻቻል ምሳሌ የምትኾን የረጅም ጊዜ ልምድ ያላት ሀገር ነች፡፡ ችግሩ የብሔር ፖለቲካው መርዝ ሰውነት ውስጥ እንደሚሰራጭ የካንሰር በሽታ መኾኑ ነው፡፡ ፖለቲካውን ብቻ ይዞ የነበረውን የዘር መንፈስ አሁን የፖለቲካ ኃይሎችን አዳክሞ ወደ ሃይማኖት ተሸጋግሯል፡፡ በየጎጡ የተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ፈጥሮ ሲጨርስ ወደቀሩት እሴቶች እየተሸጋገረ ነው፡፡ ት/ቤት ውስጥ የዘር ፖለቲካ ገብቷል፡፡ ቤተክርስቲያን ውስጥም የኾነው ይኸው ነው፡፡ በመንግሥት የተዘራው የዘር ፖለቲካ መርዝ ሃይማኖቶችን ሰቅዞ ይዟል፡፡ ሕገመንግሥቱ “መንግሥት ሃይማኖት ውስጥ መግባት የለበትም” ይላል፡፡ የቀደሙት ሥርዓቶች ያደርጉት የነበረው የሃይማኖት የውስጥ ጉዳይ ላይ ሳይገቡ አናቱን መያዝ ነበር፡፡ ዓላማቸውም ግልፅ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የማኅበረሰብ አደረጃጀት በከፍተኛ ቁጥጥር የተያዘው በሃይማኖት ተቋማት ነው፡፡ “ሃይማኖቶች ካፈነገጡ ሀገር ማስተዳደር አንችልም” ብለው ስለሚያስቡ አናቱን ይዙ ነበር፡፡ በውስጥ ጉዳይ አይገቡም፡፡

የአሁኑ መንግሥት የሚለየው አናቱን መያዝ ሲያቅተው ሙሉ በመሉ በዘር ፖለቲካው ለመክፈል መጣሩ ነው፡፡ ሚሊዮን ሕዝብ ያስተሳሰሩ ተቋማትን በዘር ለመሰንጠቅ ነው የተጣረው፡፡ ኢትዮጵያ ወደለየለት ጄኖሳይድ ያልወሰዳትና ያልበታተናት የሃይማኖት ተቋማት መኖራቸው ነው፡፡ የቀረብን ብቸኛው መተሳሰሪያ ገመድ ሃይማኖት ነው፡፡ ጠዋት በብሔር ፖለቲካ ሲጣላ ያረፈደው ሁሉ ሲያመልክ ለአንድ አምላኩ በጋራ ነው፡፡ የየብሔሩ እግዚአብሔር ስለሌለ ሁሉም በየእምነታቸው ሄደው ለአንድ አምላክ ይሰባሰባሉ፡፡ ኢትዮጵያም ልትፈርስ ያልቻለችው በዚህ ምክንያት ነበር፡፡ አሁን ግን ይህን ያስተሳሰረ የሃይማኖት ክር ለመበጠስ እየታገሉ ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ ጽፌበታለሁ፤ ይህን ሴራ እኔ ኢትዮጵያን የማፍረሻ የመጨረሻው ገመድ መበጠስ ብዬ እወስደዋለሁ፡፡ የመንግሥት ሰዎች አደጋውን ካልተረዱት ተያይዘን ጠፊዎች ነን፡፡ ስለዚህ እጃቸውን ከሃይማቶች ላይ ያንሱ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የዘር ፖለቲካውን ያራከሰው በሃይማኖት ተቋማት ነው፡፡

ግዮን፡- በመጨረሻ ማመስገን የምትፈልገውና ለአንባቢዎችህ ማስተላለፍ የምትፈልገው መልዕክት ካለ?

ያሬድ፡- መጽሐፉ ላይ በምሥጋናው ገፅ ላይ ማመስገን ያለብኝን አመስግኛለሁ፡፡ አሁን ግን በአጭሩ ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያምን ነፍሳቸውን ይማረውና ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡ ፕ/ር መስፍን ሰብዓዊነት ምንድነው? ሰው መኾን ምንድነው? እስከምን ድረስ ለሰው ልጅ ትታገላለህ? የድፍረት ምንጭ ምን መኾን አለበት? የሚሉትን እውነቶችና የምርመራ ክህሎትን ያስተማሩኝ ናቸው፡፡ እርሳቸውን በሕይወት መስመሬ ባላገኛቸው ኖሮ አሁን ያለሁበት ቦታ ላይ አልገኝም ነበር፡፡ ከዚህ ውጪ ኢሰመጉ ውስጥ አብረውኝ ገጠር ለገጠር በርሃ ለበርሃ የተንከራተቱት ጓዶቼ ወንድማገኝ ጋሹን፤ ቸርነት ታደሠን ከልብ አመሰግናለሁ፡፡ በሦስተኛ ደረጃ የትግል አጋሬ የነበረችው ውዷ ባለቤቴን አመሰግናለሁ፡፡ ይህን መጽሐፍ ስጽፍ ልጆች በማሳደግ ቤተሰባዊ ግዴታዋን በመወጣቷ እጅግ አመሰግናታለሁ፡፡ በአራተኛ ደረጃ መጽሐፌን የገመገሙልኝና መቅድም የጻፉልኝ ዶ/ር መቅደስ መስፍን፣ ዶ/ር ዲዲሞስ ኃይሌ፣ ጋዜጠኛ መለስካቸው አመሐን ከልብ ላመሰግናቸው እወዳለሁ፡፡ እነዚህ ሰዎች ቃላት ጭምር ያረሙልኝና መጽሐፉን የገመገሙልኝ ናቸው፡፡ ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራም መጽሐፉን ገምግሞ የምርቃት ዕለት ስላቀረበልኝ ከልብ አመሰግናለሁ፡፡ ሽፋኑንም በመሥራት በኩል ለተባበሩኝ ጓደኞቼም በጠቅላላው የላቀ ምሥጋናዬን ማቅረብ እወዳለሁ፡፡

ግዮን፡- በአንባቢያን ሥም ከልብ እናመሠግናለን፡፡

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ደቡብ ሱዳን የነዳጅ ቅድመ-ክፍያ ውሎችን እንዳትፈጽም አገደ

የለንደን ፍርድ ቤት ደቡብ ሱዳን ከአሁን በኋላ አዳዲስ የነዳጅ...

” ከ140 በላይ ጠጠር አምራች ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ ቆመዋል ” – ማህበሩ

" ካላቸው ቅሬታ ማቅረብ ይችላሉ። ግን መሬቱ መቼ እንደተወሰደባቸው...

ትራምፕ “በኢራን ላይ ሊፈጸም ታቅዶ የነበረውን ጥቃት አንፈጽምም” አሉ

ትራምፕ በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ ቁልፍ የአሜሪካ አጋር ሀገራት መሪዎች...

በነዳጅ ጭማሪ በኬንያ በተቀሰቀሰ ተቃውሞ የአራት ሰዎች ሕይወት አለፈ

በኬንያ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪን ተከትሎ በዋና ከተማዋ ናይሮቢ በጸጥታ...