ከሃምሳ ለዘለሉ ዓመታት የኢትዮጵያን የፖለቲካ ዐውድ ቀይዶ የያዘው የሰሜን ፖለቲካ አሁንም ድረስ ዳፋው መሬት ሊነካ አልቻለም፡፡ በሃምሳ ዓመታት ውስጥ ሀገር በመግመስ፣ የሚሊዮኖችን ደም በማፍሰስ፣ ድፍን ኢትዮጵያውያንን በዘር ከፋፍሎ በማመስም ሊደመደም አልቻለም፡፡ በሻዕቢያ ተጀምሮ በህወሓት ቀጥሎ በአነግ ፍጻሜውን ለማግኘት የቋመጠው ኢትዮጵያን የመበታተን ትግል አሁንም ከዳር አልደረሰላቸውም፡፡ አሁን ላይ የህወሓት ፖለቲካዊ ጦሰኝነት የረገበ ቢመሲልም እሳቱን ወደ ደቡብ ሳይሻገር አልቀረም፡፡ ህወሓት ለሁለት ዓመታት በሰሜን ሲያደርግ ነበረውን ጦርነት በበቃኝ እረፍት ሲወስድ ዱላ ቅብብሉን ለአብሮ አደጎቹ የደቡብ ዘረኛ ኃይሎች ማቀበሉ በግልጽ እየተያየ መጥቷል፡፡ ለዚህም ይመስላል ቀድሞ ከዳር አገር የነበረው ጸረ ኢትዮጵያ ትግል አሁን ላይ መሐል ኢትዮጵያ የኾነው፡፡ የኾኖ ኾኖ ከሰሞኑ ህወሓትና የፌዴራሉ መንግሥት ያደረጉትን የሰላም ስምምነት በተመለከተ ከ50 በላይ ለሚኾኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ማብራሪያ ተሰጥቶ ነበር። ማብራሪያውን ከሰጡት መካከል የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሬድዋን ሁሴን ነበሩ።
መንግሥት ምንም እንኳን ቀደም ሲል ስለ ሰላም ስምምነቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ያላቸው ነገር ባይኖርም አሁን ላይ ሁሉንም ነገር ሲጨርስ ተቋዋሚዎች ሀሳብ እንዲሰጡበትና ጥያቄዎችን እንዲያነሱ እድል ሰጥቷቸዋል፡፡ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮችም ጠንከር ያሉ ጥያቄዎችን ያቀረቡ ሲኾን በዚህም ስለወልቃይት ባለቤትነት፣ ስለኤርትራ ወታደሮች፣ ስለሰላም ስምምነቱ ግልጽነትና የመረጃ አሰጣጥ፣ ስለሰላም ስምምነቱ ተደራዳሪዎች በዋናነት በጥያቄነት ተነስተዋል። ከዚህ አንጻር አነሰም በዛ እያንዳንዱ የፖለቲካ ፓርቲ ሕዝባዊ መሠረት አለውና የተነሱት ጥያቄዎች አብዛኞቹ የሕዝቡ አጀንዳዎች ናቸው፡፡ በተለይ የወልቃይት ጉዳይ የትግራይም ይሁን የአማራ ወይም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትኩሳት መገላበጫ ከኾነ ቆይቷል፡፡ የቀደመው የሰሜን ፖለቲካ ኢትዮጰያን የባሕር በር ሲያሳጣ የአሁኑ ደግሞ የሰሜን ኢትዮጵያን በር ሙሉ ለሙሉ እንዳይዘጋ ተሰግቷል፡፡ ለዚህም ሲባል የወልቃይት ጉዳይ ከአንድ ብሔር ወይም ክልል አልፎ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሕልውና እስትንፋስ ተደርጓል፡፡
ነገር ግን መንግሥት ምንም እንኳን የወልቃይት ጉዳይን በአጽንኦት እንዲያየው የጂኦፖለቲካዊ ሁነታ ቢያስገድደውም ውሳጠዊ ፖለቲካውን ለማሳለጥ ሲል ለህወሓት አሳልፎ እንዳይሰጠው ተሰግቷል፡፡ ይህን ስጋት የሚያጠናክረው ደግሞ መንግሥት ወልቃይትን አስመልክቶ ከፓርቲዎች ለተነሳለት ጥያቄ የሰጠው ማብራሪያ እና አንዳንድ እየተከተላቸው ያሉ እርምጃዎች ናቸው፡፡ ከፍ ሲል እንደተነሳው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ወልቃይትን አስመልክቶ ለፓርቲዎቹ በሰጡት ማብራሪያ የወልቃይት ጉዳይ በሕገ መንግሥቱ መሠረት እንደሚፈታ ጠቅሰዋል። እንደ አማካሪው ገለጻ ከጅምሩ የጦርነቱ ዓላማ ወልቃይትን ማስመለስ እና ህወሓትን ማጥፋት አልነበረም። የጦርነቱ ዋና ዓላማ የነበረው የአገሪቱን ሉዓላዊነት ማስከበርና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ማስፈን ነው፡፡ ህወሓትን እንደ ፖለቲካ ኃይል የማጥፋት ዓላማ ያለው ሰው ይኖራል፣ ነገር ግን የፌዴራል መንግሥቱ ዓላማ አይደለም ብለዋል።
ይህ የአማካሪው ገለጻ ግን ውሃ የሚያነሳ አይኾንም፡፡ ምክንያቱም በመጀመሪያ የወልቃይትን ጥያቄ በሕገ መንግሥቱ መሠረት መፍታት እንዳልተቻለ የተለያዩ ጊዜያት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ በተለያዩ አካላት የተገለጸ ጉዳይ ነው፡፡ ይህን ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቻ ሳይኾኑ የብልጽግና መንግሥትም ጠንቅቆ የሚያውቀውና ከጦርነቱ በፊት ለሁለት ዓመታት ሳይፈታው የቆየ ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም “ቦታው ከሕገ መንግሥቱ መጽደቅ በፊት በኃይል የሄደና ከጦርነት በኋላ በኃይል ወደባሌቤቶቹ የተመለሰ” የሚል ውዝግብ ሚነሳበት መኾኑ ይታወቃል፡፡ ስለዚህ ይህን ውስብስብ ቀውስ ለማስተናገድ ሕገ መንግሥቱ አቅም እንደሌለው በብዙኃኑ ዘንድ የታመነ ነው፡፡ በተጨማሪም ምንም እንኳ መንግሥት ለሕግ ማስከበር ዘመቻ ህወሓት ላይ መዝመቱን ቢገልጽም ጦር ሰብቀው ወልቃይትን ለማስመለስ ጊዜ የቀጠሩ ኃይሎች እንደነበሩ ግን አይካድም፡፡ አልፎ ላስተዋለ ደግሞ ለለውጥ አራማጁ የብልጸግና መንግሥት ሥልጣን መቆናጠጥ ፋና ወጊው የትግል አቀጣጣይ የወልቃይት ማንነት ማስመለስ ተጋድሎና የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጉዳይ መኾኑን አይዘነጋም፡፡
በሌላ በኩል በዚህ የአማካሪው ንግግር ላይ የሚታየው አደናጋሪ ነገር “ህወሓትን እንደ ፖለቲካ ኃይል የማጥፋት ዓላማ ያለው ሰው ይኖራል፣ ነገር ግን የፌዴራል መንግሥቱ ዓላማ አይደለም።” የሚለው ነው፡፡ መንግሥት ጦርነቱ በተፋፋመበት ወቅት ይህን ዓላማ አድርጎ ሲንቀሳቀስ እንደነበር የሚካድ አይደለም፡፡ ከዚያ ከፍ ሲልም ህወሓት አመድ ኾኖ እንደተበተነና ከምድረ ገጽ እንደጠፋ ሲደሰኮር መቆየቱም አይዘነጋም፡፡ ስለዚህ አልኾን ብሎ እንጂ ህወሓትን ለማጥፋት መንግሥት ተንቀሳቅሶ እንደነበር ማስተባበል አይቻልም፡፡ በተመሳሳይ “አንድ ሰው ትግራይን ሲወድ ካርታውን ብቻ ሳይሆን ሕዝቡን ነው፤ ነገር ግን ካርታውን ወዶ ሕዝቡን መጥላት አይቻልም።” የሚለው የአማካሪው ገለጻ ከዓመታት በፊት ኤርትራውያን “ኢትዮጵያ የምትሻው እኛን ሳይኾን ወደባችንን ነው” ይሉት የነበረውን ስላቅ የሚያስታውስ በመኾኑ የብሽሽቅ ፖለቲካውን ለማጓን የወረወሩት ቃል መኾኑ እሙን ነው፡፡ እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ያለ ኤርትራ ሠላሳ ዓመታትን ያለ ትግራይ ደግሞ ሁለት ዓመታትን እንደኖረች አስመስክራለች፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሀገር ሉዓላዊነት ሲዋደቅ ለሕዝቡ እንጂ ለመሬቱ ብቻ አለመኾኑ ልብ ሊባል ይገባል፡፡
አምባሳደር ሬድዋን የኤርትራ ሠራዊትን በተመለከተ “ህወሓት በጦርነቱ ጊዜ የጋራ ጠላታችን ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ህወሓት የጋራ ጠላት የሚሆነው ትጥቁን እስኪፈታ ነው። ትጥቁ ከሌለ አደጋ አይሆንም። ስለዚህ የኤርትራ ሠራዊት ይወጣል” ብለዋል፡፡ እንደቃላቸውም የኤርትራ ጦር ከወጣ ቀናት ተቆጥረዋል፡፡ አቶ ሬድዋን ግን እግረ መንገዳቸውን የኤርትራ ሠራዊት ከኢትዮጵያ ይውጣ የሚሉት አካላትን ከሰዋል፡፡ በክሳቸውም “የኤርትራ ጦር ይውጣ የሚሉ አካላት ሱዳን 50 ኪሎ ሜትር አልፎ ሲወር አፋቸውን ዘግተው ነበር” በማለት ይወርፏቸዋል፡፡ አክለውም “የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ካሳሰባችሁ ሱዳን ትውጣ ብላችሁ መግለጫ አውጡ፡፡” ሲሉ ተችተዋል፡፡ የኾኖ ኾኖ አሁንም በዚያ በኩል ያለው የፖለቲካ እሳት እየጋመ መኾኑ አያጠያይቅም፡፡ በተለይም የወልቃይትና የራያ ጉዳይ በቀላሉ ሊቋጭ እንደማይችል ግልጽ እየኾነ መጥቷል፡፡ ከዚህ አኳያ አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ሰሞኑን በሽሬ መስመር በአዲአርቃይ ግንባር የሚገኙ የአማራ ልዩ ኃይሎች፣ ፋኖ እና ሚሊሻ በአስቸኳይ እንዲወጣ ትዕዛዝ ተላልፎለታል። ይህ ደግሞ የፌደራል መንግሥት አካባቢዎቹን በተመለከተ እየሄደበት ያለው ስልት ምን እንደሚመስል የሚጠቁም ነው፡፡
የፌደራል መንግሥት የቱንም ያህል ለሰላም ስምምነቱ ዘብ ቢቆም እና የህወሓትን ጉዳይ ለመጨረስ ቢሞክር ቀጣይ የጦርነት ጦሶችን ከመጫር የተቆጠበ አይመስልም፡፡ ህወሓትም ቢኾን በቀላሉ ከትንኮሳ ሴራዎች እንደማይላቀቅ የታወቀ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር አሁን ላይ በትግራይ ክልል የሚሰራጩት የቴሌቪዝን ጣቢያዎችና የኤፍ ኤም ሬዲዮኖች የሚያስተላልፏቸው መልዕክቶች ሕዝቡን ውዥንብር ውስጥ የሚከቱ ናቸው። የትግራይ ቴሌቪዥንና የድምጸ ወያኔ ቴሌቪዥን የሰላም ስምምነቱን የሚያወድሱና የፌደራል መንግሥቱን ምላሽ የሚያጎሉ መልዕክቶችን ሲያስተላልፉ በመቀሌ የሚሰራጨው ኤፍ ኤም 104.4 ደግሞ አሁንም የትግል ቀስቃሽ መልዕክቶችንና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ጨምሮ የፌደራል መንግሥቱ ባለሥልጣናትን በስም በመጥቀስ ለፍርድ መቅረብ እንደሚገባቸው የሚገልጹ ዝግጅቶችንና ውይይቶችን በማስተላለፍ ላይ ይገኛል፡፡ ይህ የሚያመለክተው ደግሞ የህወሓትን ያልተቀየረ ልብጥ ማንነት ነው፡፡ የኤፍኤም ጣቢያው ይህን መሰል መልዕክቶች የሚያስተላልፈው ከህወሓት እውቅና ውጭ ኾኖ እንዳልኾነ ግልጽ ነው።
