ሕይወት ሁሉም የሚያነበው መጽሐፍ ነው፡፡ በዚህ መጽሐፍ ውስጥም ሁሉም ሰው የየራሱ እውነተኛ ገጸ-ባሕሪ አለው፡፡ ሁሉም ሰው በዚህች መጽሐፍ ሁሉም የየራሱን አዎንታዊና አሉታዊ ማንነት ከትቦ አሊያም አስከትቦ ያልፋል፡፡ ይህም ታሪክ ሆኖም ይዘከራል፡፡ የሰው ልጅ እንከን የለሽ ሆኖ አልተፈጠረም፡፡ ምሉዕነትም የፈጣሪው እንጂ የራሱ የሰው ልጅ መገለጫ አይደለም፡፡ ግለሰቦች በሕይወት ሳሉ የተናገሯቸው ንግግሮች መቼታቸው ምንጊዜም አይረሳም፡፡ ስማቸው በተነሳ ቁጥር ንግግራቸውም አብሮ ይወሳል፡፡ ከሕዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር ተያይዞ ሁሌም፤
“የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የላብ ፊርማ ያረፈበት ግድብ በመሆኑ የሕዳሴ ጉዟችን መሃንዲሶች እኛው፣ ግንበኞቹም እኛው፣ የፋይናንስ ምንጮችና አስተባባሪዎች እኛው፣ በአጠቃላይ የሕዳሴ ጉዟችን ባለቤት እኛው መሆናችንን የሚያሳይ የባለቤትነት ማረጋገጫ ካርታችን ነው፡፡” የሚለው ሟቹ የቀድሞ የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ንግግር ሲወሳ ይኖራል፡፡ ሟቹ የቀድሞ የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ይህን ንግግር የተናገሩት የሕዳሴ ግድቡ የመሰረት ድንጋይ በተቀመጠበት እለት ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመሰረት ድንጋዩን ካስቀመጡበት እለት ጀምሮ በዓባይ ወንዝ ላይ የፈላጭ ቆራጭነት መብት አለኝ የምትለው ግብጽም የሕዳሴው ግድብ ግንባታ እረፍት ነስቷታል፡፡ ባገኘችው አጋጣሚ የግድቡ ሥራ እንዲደናቀፍና እንዲንጓተት ያላደረገችው ጥረት፣ ያልፈነቀለችው ድንጋይ የለም፡፡ ይህ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሀገራቸውን የመንግሥት በትረ-ሥልጣን ለመቆጣጠር በሚሹ የግብጽ ባለሥልጣናት የግብጽን ሕዝብ ለመደለልና በሥልጣን ወንበር ላይ በዓመታት ተደላድለው ለመቀመጥ የሚፈልጉበት ሸቀጥ ከሆነ ሰንብቷል፡፡
ግብጽ በታሪክ የዓባይን ወንዝ ውሃ ከምንጩ ለመቆጣጠር ያላደረገቻቸው ጥረቶች የሉም፡፡ ከእነዚህ በርካታ የግብጽ ታሪካዊ ሙከራዎች አንዱም ቢሆን ለውጤት ደርሶ የግብጽን መንግሥት እና ሕዝብ አላስፈነደቀም፡፡ በግብጽና በኢትዮጵያ ተካሂደው የነበሩትን ጦርነቶች ጨምሮ ግብጽ በዓለም አቀፍ ዙሪያ ያደረገቻቸው እንቅስቃሴዎች ሁሉም ግብጽ የሽንፈት ካባ እንድትከናነብ ከማድረግ ውጭ ለግብጽ መንግሥትም ሆነ ለግብጽ ሕዝብ ያስገኙት ፋይዳ የለም፡፡ በዓባይ ወንዝ ላይ ግብጽ ከጥንት ጀምሮ ያላት ግልጽ ፍላጎት በዓባይ ወንዝ ላይ የሚደረጉ ማናቸውንም ልማቶችና እንቅስቃሴዎች በማደናቀፍ የዓባይን ውሃ በማን አለብኝ መንፈስ ለብቻዋ መቀራመት ነው፡፡ ይህ የግብጽ ፍላጎት እንደአውሮፓዊያን አቆጣጠር ሱዳን ከግብጽ-ብሪታኒያ ጥምር የቅኝ ግዛት ነጻ እስከወጣችበት እስከ 1956 ድረስ በቅኝ ገዢዋ ብሪታኒያ በከፊል የተሳካ ቢሆንም ከዚያ በኋላ ግን ስኬታማ ሊሆን አልቻለም፡፡ በዓባይ ወንዝ ላይ የበላይ አዛዥ ነኝ የሚለው የግብጽ ቀረርቶና ፉከራ ሙሉ ለሙሉ ባይሆንም በከፊል በሱዳናዊን ትግል ሊከስም ችሏል፡፡
በዓባይ ዙሪያ ኢትዮጵያ ለብዙ ዘመናት ከግብጽ በኩል ይደርሱባት የነበሩ ጥቃቶችንና ወረራዎችን ማሸነፍ ብትችልም፤ ዓባይ ከምድሯ እየፈለቀ ኢትዮጵያ በዓባይ ሳትጠቀም ሱዳንና ግብጽ በውሃው እንዲንበሻበሹ ስታደርግ ቆይታለች፡፡ በእነዚህ በርካታ ዘመናት ኢትዮጵያ ከዓባይ ወንዝ ያገኘችው ነገር ፉከራ፣ ቀረርቶና ዘፈን ብቻ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ኢትዮጵያ የዓባይን ውሃ በመጠቀም ወደብልጽግና የመሸጋገር አቅሙ እያላት በቀደምት መንግሥታት በኩል ለምን እንዳታልታሰበ በራሱ ጥያቄ የሚያሰነሳ ነጥብ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ አሁን እስካለንበት ዘመን ድረስ አንድ ወይም ሁለት ወይም ከዚያ በላይ ፕሮጀክቶች ኖረዋት ቢሆን ኖሮ ግብጽ ዛሬ ላይ በዓባይ ወንዝ ላይ በድፍረት የምታነሳው አቧራ አይኖርም ነበር፡፡ ትላንት ዳግመኛ ላይመለስ ራሱን በነበር ተክቶ ቢያልፍም ኢትዮጵያ ግን አለች፡፡ የኢትዮጵያ መኖር ከዘመን መለዋወጥ ጋር ተደምሮ ከዘመናት ማንቀላፋት በኋላ እነሆ ኢትዮጵያ ከዓባይ ወንዝ ማግኝት ያለባትን ጥቅም አውቃ በጥቅሟ ላይ እንድትንቀሳቀስ ረድቷታል፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያ የአባይን ወንዝ በተመለከተ ከነበረችበት የቁም እንቅልፍ ነቅታለች፡፡ የሕዳሴ ግድቡ መገንባት ለኢትዮጵያ ስኬት ለግብጽ ደግሞ ራስ ምታት ሆኗል፡፡
ከላይ እንደተለመከተው የሕዳሴ ግድብ ለግብጽ ባለስልጣናት የውስጥ ፖለቲካ አጀንዳ እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ ግብጽ በሕዳሴ ግድቡ እንዳይገነባ የሐሰት መረጃዎችን ለዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ በተለይም ለዐረቡ ዓለም ማሕበረብ እየሰጠች ቆይታለች፡፡ አሁን አሁን ግብጽ ለዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ በተለይም ለዐረቡ ዓለም ማሕበረሰብ እየሰጠች ያለችው መረጃ በእውነት ላይ ያልተመሰረተ እንዳልሆነ ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብና የዐረቡ ዓለም ማሕበረሰብ እያወቁትና እየተረዱት መጥተዋል፡፡ ግብጽ በሕዳሴ ግድብ ግንባታ ዙሪያ ስታድርጋቸው የነበሩና እያደረገቻቸው ያሉ እንቅስቃሴዎች ግብጽ በሕዳሴ ግድቡ መገንባት ምክንያት ሊደርሱ የሚችሉ ችግሮች ሳይሆን ግብጽ ለአፍሪካ አሕጉር ሐገራትና ለዐረቡ ዓለም ሐገራት ያላትን ኃያልነትና ስትራቴጂካዊ ሃይል ለማሳየት የምትጠቀምባቸው እንቅስቃሴዎች ናቸው የሚል አቋም አንዳንድ የዐረብ ምሁራን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡ በዚህ ሳምነት እ.ኢ.አ ረቡዕ ሐምሌ 8 ቀን 2012 የሕዳሴ ግድቡ የውሃ ሙሌት መጀመርን ከሰሙ በኋላ የግብጽና የዐረቡ የመገናኛ ብዙኃን ትኩረት ሰጥተውት አምሽተዋል፡፡ በተለይ ኳታር- ዶሓ የሚገኘው የአልጀዚራ የቴሌቪዥን ጣቢያ በዚሁ ላይ እንደሙሐመድ ኢብን ሙመድ አል-ዐሩሲ፣ ጀማል በሺርና ሓሊ ያሕያ ያሉ ኢትዮጵያዊያን እንዲሁም ግብጻዊያንና ሱዳናዊያን የፖለቲካ ተንታኞችን በመጋበዝ ሰፋ ያለ ዘገባና ፕሮግራም አሰተላልፏል፡፡
ከግብጻዊያኑ፣ ሱዳናዊኑና ኢትዮጵያዊኑ ውጭ በሕዳሴ ግድብና በኢትዮጵያ ዙሪያ ጥሩ ትንታኔ እየሰጡ የሚገኙትና በዶሐ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ሙሐመድ ሙኽታር አሸንቂጢ በጉዳዩ ዙሪያ ያላቸውን ሙያዊ መልከታ በዚሁ የአልጀዚራ ፕሮግራም ላይ አስተላልፈዋል፡፡ በአልጀዚራ ቴሌቪዥን በቀረበው ፕሮግራም ላይ በዋናነት ኢትዮጵያ የግድቡን የውሃ ሙሌት መጀመሯ በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ሲካሄድ በነበረው ሦስትዮሽ ድርድር ላይ ከፍተኛ ጫና አያደርስምን? የግድቡ ሙሌት መጀመር በድርድሩ ላይ ተስፋ መቁረጥን አያስከትልምን? ግብጽ የሕዳሴ ግድቡን የውሃ ሙሌት መጀመር ካወቀች በኋላ ድርድሩን በማቋረጥ ጉዳዩን እንደቀድሞው ወደተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ብትወስድ ከጸጥታው ምክር ቤት በኩል ግብጽ ልታገኘው የምትችለው ምላሽ ምን ይሆናል? የጸጥታው ምክር ቤት ለግብጽ አጥጋቢ ምላሽ ባይሰጥ ግብጽ ወታደራዊ ኃይልን እንደአማራጭ ልትወስድ ትችላለችን? የሚሉ ጥያቄዎች ተነስተው በኢትዮጵያዊኑና በኳታሩ ምሁራን አጥጋቢ መልስ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ የግብጻዊያኑ ምላሽና አስተያየት እርስ በእርሱ የሚጋጭ ከመሆኑ ባሻገር የድረሱልን ጥሪ ከመምሰል ውጭ በአሳማኝ መረጃዎች እና ማስረጃዎች ላይ የተደገፈ አልነበረም፡፡ የጉዳዩ ዙሪያ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ በአልጀዚራና በአልዐረቢያ ቴሌቪዥኖች የተጋበዙት የቀድሞው የሱዳን የመስኖ ሚኒስትር ዶ/ር ዑስማን አቶም የሕዳሴ ግድቡ ቴክንኒካዊ ጉዳይ ዙሪያ በሱዳን በሉል ምንም አይነት ስጋት እንደሌላ ከመናገራቸው ባሻገር በግድቡ ዙሪያ በሊነሳ የሚችል የጎላ ስጋት እንደሌለ ለዓለም አቀፍ ማሕበረሰብ አረጋግጠዋል፡፡
እንደዶክተር ዑስማን አቶም አስተያየት የግድቡ ውሃ ሙሌት በኢትዮጵያ በኩል ከመጀመሩ በፊት ከኢትዮጵያ በኩል ለሱዳን መነገር ነበረበት ይህ ባለመሆኑ የግድቡ ሙሌት ወደሩሴሪስ ግድብ በሚገባው የውሃ መጠን ላይ መቀነስ እንዲስትዋል አድርጓል በማለት የግድቡን የውሃ ሙሌት ኮንነው አልፈዋል፡፡ የውሃ ሙሌቱን አስመልክቶ ኢትዮጵያ ለሁለቱም ሐገራት አስቀድሞ የማሰወቅ ግዴት እንደሌለባት እንደማትገደድ የ2015 የሶስቱ ሐገራት ስምምነት ያስረዳል፡፡ ዶ/ር ሙሐመድ ሙኸታር አሸንቂጢ በዚሁ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ ግብጽ ጉዳዩን ወደጸጥታው ምክር ቤት መውሰዷ ምንም ፋይዳ እንደማያመጣላት የጸጥታው ምክር ቤት ከዚህ በፊት በአለም ላይ ለተፈጠሩና አሁን ተከስተው ላሉ ችግሮች በተሰጠው የመንግሥታት ሥልጣን መሠረት አንድም ፋይዳ እንዳላስገኘ በመጥቀስ አስረድተዋል፡፡ ይልቁንም ግብጽ ከጸጥታው ምክር ቤት ይልቅ የሚጠቅማት ከአፍሪካ ሐገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ማጠንከርና የግድቡን ጊዘያዊ የውሃ ሙሌት ችግርን ግብጽ የአስዋን ግድብን ጨምሮ በርካታ የውሃ አማራጮችን መጠቀም እንደምትችል ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡ የግብጽን አካሄድ ግብጻዊያን ሱዳናዉያን የተቃወሙት ሲሆን በተለይ ሱዳናዊያን ግብጽ የሕዳሴ ግድቡ ላይ በጦር ኃይል እርምጃ የመውሰድ ፍላጎት ካላት ግድቡ ላይ በሚደርስ ማንኛውም አደጋ በዋነነት ተጎጂ የምትሆነው ሐገር ሱዳን በመሆኗ ይህን ለመከላከል ሱዳያናዊያን ከኢትዮጵያ ጎን በመሰለፍ ጥቃቱን እንደመሚክቱ በቲውተር ገጾቻቸው ላይ ጽፈዋል፡፡ ወሰላም!! ግ
