
‹‹ቅርስ የሌለው ሕዝብ ከወደቀበት ተደግፎ የሚነሳበት ምርኩዝ የለውም››
‹‹ብዙ ሐሳብ የሚያፈልቁ አዕምሮዎች ተቆልፎባቸዋል››
ክብራን የመጽሔታችን አንባቢያን ባሳለፍነው ዕትም ከቅርስ ባለውለታው አለባቸው ደሳለኝ ሐበሻ ጋር ስለሕይወቱ እና ስለሙያው ብሎም ከጓዶቹ ጋር ለሀገሩ ስለከፈለው መሥዋዕትነት ሰፋ ያለ ቃለ ምልልስ ማድረጋችን ይታወሳል፡፡ በሁለተኛው እና በመጨረሻው ክፍል ደግሞ የዳያስፖራውን መልከ ብዙ ኢትዮጵያ ተኮር ተሳትፎዎች፣ ቅርስ ማሰባሰብን ስለተመለከቱ ጉዳዮች፣ ኢትዮጵያ አሁን ስላለችበት እውነታ እና ተያያዥ አጀንዳዎች የሚከተለውን ቆይታ አድርገናል፡፡ መልካም ንባብ!
ግዮን፡- አቶ አለባቸው ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ስለተወለድክ ብቻ ኢትዮጵያዊ መሆን አይቻልም›› የሚል ለኢትዮጵያዊነት ልዩ ሥፍራ እንዳለህ የሚገልጽ ኃይለቃል በተደጋጋሚ ትናገራለህ፡፡ እስቲ ኢትዮጵያዊነት አንተ ዘንድ ያለውን ትርጉም አጋራን?
አለባቸው፡- አየህ ኢትዮጵያዊነት ለኔ የተለየ ትርጉም አለው፡፡ ኢትዮጵያዊነት የድል አድራጊነት ፍልስፍና ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ብዙ ብሔረሰቦች የተገመዱበት፣ በአንድነትና በውበት የደመቀ ሕብረ ብሔራዊ ቀለም ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት የጋራ ነፃነት ያለው የመንፈስ ኩራት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት የአፍሪካውያንን ነፃነት ያወጀ የፍትሕ ተምሳሌት ነው፡፡ ይህንን ማወቅና በጥልቀት መረዳት ከፈለግን በፖለቲከኞች ትርክት ከምንደናበር ሊቃውንት አባቶቻችን ከትበው ያስቀመጡልንን የታሪክ ድርሳናት ብንፈትሽ እኛነታችንን ፈልገን ማግኘት እንችላለን፡፡ ‹‹ኢትዮጵያዊነት›› የሚለውን መጠሪያ ከኛ በተሻለ ክንዳችንን የቀመሱት ነጮች ቀጥተኛ ትርጉሙን ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡ ጥቂት የማይባሉት አፍሪካውያን ወንድሞቻችን ከነፃነት በኋላ የሀገራቸውን ምልክት ሰንደቅ ዓላማ አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለም እንዲሆን ሲመርጡ ቀለሙ ደስ ብሏቸው እንዳይመስልህ፡፡ አፍሪካዊነት ኢትዮጵያዊነት መሆኑን ያረጋገጡበት ውሳኔ ስለኾነ ነው፡፡
እኛ በጅላንፎ ፖለቲከኞች ትርክት ተጠልፈን ሐውልታችንን እያፈረስን ስንደናበር ጥቁር የጃማይካ ወንድሞቻችን ሰንደቅ ዓላማችንን ለብሰው በዓለም አደባባይ ይደምቁበታል፡፡ ለጊዜው ኢትዮጵያዊነት ክብራችንን በማይመጥን በዘረኝነት እድፍ ሊያቆሽሹት ቢሞክሩም ነገ ትውልዱ እጅ ለእጅ ተያይዞ ከወደቀበት ያነሳዋል፡፡ ትውልድ አልፎ ትውልድ በተተካ ቁጥር ኢትዮጵያዊነት ክቡሩ ደምቆ እያበራ ከፍ ብሎ ለዓለም የሚታይ አልፋና ኦሜጋ ይሆናል፡፡ ሁልጊዜ የማዝነው ግን ‹‹ኢትዮጵያዊነት›› የሚለውን ምሥጢር ፖለቲከኞቻችን በቅጡ አለማወቃቸው ነው፡፡ ለዚህ ነው በመሃከላችን የሚፈጠሩትን ልዩነቶቻችን በመከባበር መፍታት እንዳንችል እርስ በእርስ እንድንጨራረስ እሳት የሚያነዱብን፡፡ ትክክለኛ ታሪክን ለትውልድ ከማስተማር ይልቅ የውሸት ትርክት እየጋቱ ሕዝቡን የሚያደናብሩት፡፡ የተደናበሩ የጎሳ ፖለቲከኞችን በዚህ ምክንያት ነፍሴ ትፀየፋቸዋለች፡፡ ስለዚህ ጥያቄህን የማጠቃልለለው በአንድ ዓረፍተ ነገር ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት መቼም ማንም የማይሽራርፈው የብሔራዊ ክብራችን ጽናት ነው፡፡
ግዮን፡- የሸበተው ጎፈሬህን (ፀጉርህን) ‹‹ለኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ክብር ማስታወሻ›› ያደረግከው እንደኾነ አንድ መድረክ ላይ ተናግረሃል፡፡ ከአያትህ ጀምሮ አባትህ፣ አክስቶችህ አርበኞች እንደነበሩ፣ አንተም ለኢትዮጵያ ክብር በቀድሞው ጦር ኃይሎች ውስጥ በጦር መኮንነት እና በተለያዩ ወታደራዊ ግዳጆች ላይ እንዳሳለፍክ አጫውተኸናል፡፡ አርበኝነት ለአንተ የተለየ ትርጉም አለው?
አለባቸው፡- በቅድሚያ አርበኝነት የተወለደው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡ በተለያዩ ዓለሞች አርበኝነት አልነበረም እያልኩህ አይደለም፡፡ እውነተኛ አርበኝነት ግን የጥቁር አፍሪካውያን መለያ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ አፍሪካውያን በቅኝ ግዛት ሥር ሲወድቁ ‹‹የነጭ የበላይነትን አንቀበልም›› በማለት ታስረውበት ከነበሩበት የባርነት ሰንሰለት በጥሰው እንዲወጡ ምክንያት የኾነው ኢትዮጵያ ውስጥ የተወለደው የአልደፈር ባይነት አርበኝነት ነው፡፡ የእኛ አባቶች አያሌ የሕይወት ዋጋ ከፍለው ነፃነታቸውን ያወጁበት ወታደራዊ ዝግጅት ማለቴ ነው፡፡ ከአውሮፓ እስከ እስያ፤ ከአፍሪካም ጭምር በየጊዜው የተነሱ ታላላቅ ጦረኛ መንግሥታትን የኢትዮጵያ አርበኞች አሳፍረው መልሰዋቸዋል፡፡ አንድም ቀን ሉዓላዊነቷ ተደፍሮ በቅኝ ግዛት ተግዛታ አታውቅም፡፡ ከ2 ሺህ ጊዜ በላይ የወረራ ሙከራ አገራችን ላይ ተደርጎባት እንደነበረ የታሪክ ድርሳናት ይናገራሉ፡፡ ኾኖም ግን ኢትዮጵያ በጀግኖች አርበኞቿ ቆራጥነት ክብሯን አስጠብቃ ሉዓላዊነቷንም አስከብራ ቀጥላለች።
ፀጉሬን በተመለከተ ለጠየከኝ ጥያቄ … ራሱን የቻለ ታሪክ አለው፡፡ የኢትዮጵያ አርበኞች አብዛኛዎቹ የአየሩን ፀባይ ለመመከት ሲሉ ፀጉራቸውን ስለሚያሳድጉት ጎፈሬዎች ናቸው፡፡ በዚህ ምክንያት ፀጉርን ማሳደግ የአሸናፊነት እና የነፃነት ማወጃ ምልክት ተደርጎም ይታይ ስለነበረ ይህንን ታሳቢ በማድረግ ለአንድ ዝግጅት አርበኞችን ወክዬ ለመቅረብ ፀጉሬን አሳደኩት፡፡ ዝግጅቱ የጥንታዊ ኢትዮጵያ ጀግና አርበኞች 80ኛ ዓመት የሚከበርበርት ቀን ነበረ፡፡ በወቅቱ በውጭ ጉዳይ ዘርፍ ሓላፊነት እኔ የምመራው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ምክር ቤት ለጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግና አርበኞች የምሥጋና ቀን አዘጋጅቶም ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ትያትር አዳራሽ ልዩ ልዩ ኪነጥበባዊ ዝግጅት፣ ምሳ ግብዣ ደግሞ በኢትዮጵያ ሆቴል አድርገን በሳምንቱም ሌላ የምሳ ግብዣ በኩሪፍቱ ሆቴል፣ እንዲሁም እንጦጦ ላይ የመዝናኛ ፕርግራም ጨምረን ለሀገራቸው ክብር ደማቸውን እና አጥንታችውን የከሰከሱትን አባት አርበኞች ለማክበርና ለማመስገን አንድ ዝግጅት አድርገን ነበረ፡፡ ዝግጅቱን ያስተባብረነው ውጭ ሀገር ሆነን በስልክና በዙም ስብሰባ ነው፡፡
ከአርበኞች ጋር በአካል አልተገናኘንም፡፡ ነገር ግን በዙም ስብስባችን የጥንታዊ አርበኞች ፕሬዝዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን አብረውን ይሰበሰቡ ነበር፡፡ በፀጉሬ ተደምመው ‹‹አንተ ግን ልክ እንደ ጥንት አባቶቻችን አርበኞችን ትመስላለህ›› አሉኝ፡፡ እኔም ‹‹እንግዲያውስ ፀጉሬ ለነሱ መታሰቢያ ይሁንልኝ›› አልኳቸው፡፡ ዝግጅቱም በጥሩ ሁኔታ ተጠናቆ እነሱም እኛም ደስ አለን፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ፀጉሬን ተቆርጨው አላውቅም፡፡ ጥያቄህን በትክክል መልሼ እንደሆን አላውቅም፡፡ በተፈጥሮ ነጭ የሆነው ፀጉሬ ምሥጢሩ ይኸው ነው፡፡
ግዮን፡- ከአንድ ዓመት በፊት በለንደን ሊሸጥ የነበረን የኢትዮጵያ ቅርስ ማሳገድ ችላችሁ ነበር፡፡ የዚህ እንቅስቃሴ መሪ ደግሞ አንተ ነበርክ፡፡ በርካታ የኢትዮጵያ ቅርሶችንም ትሰበስባለህ፡፡ በዚህ ምክኒያትም በአንዳንድ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ‹‹ዐቃቤ ቅርስ›› እያሉ ይጠሩኻል፡፡ ሌሎቹም ደግሞ ‹‹የቅርስ ባለውለታ›› ይሉኻል፡፡ እስቲ ስለዚህ ሥራህና የቅርስ ማስባሰብ ፍላጎት እንዴት እንዳደረብህ በዝርዝር ሒደቱን አጫውተን?
አለባቸው፡- በቅርስ ጉዳይ ጨጓራዬ ተልጧል፡፡ ላለፉት 28 ዓመት ተሰማሁም አልተሰማሁም አላውቅም፡፡ ነገር ግን ለኢትዮጵያ ቅርሶች ሕልውና ተሟግቻለሁ፡፡ የተወሰኑትን በገንዘቤ እየገዛሁ የማልችለውን ተፅዕኖ በመፍጠር ከሽያጭ እንዲታገዱ ከመሰል ጓደኞቼ ጋር ትግል አድርገን ውጤት አግኝተንባቸዋል፡፡ በኔ በኩል አቅሜ የሚፈቅድልኝን ሁሉ ከማድረግ ተቆጥቤ አላውቅም፡፡ ቢያንስ ከሕሊና ወቀሳ ራሴን ነፃ ማድረግ ችያለሁ፡፡ መጀመሪያ ስለ ኢትዮጵያዊነት ጠይቀኸኝ መልሼልሃለሁ፡፡ ዝም ብሎ ከመሬት ተነስቶ ኢትዮጵያዊ መሆን አይቻልም፡፡ በአስተዳደግህ መከተብ አለብህ፡፡ ኢትዮጵያዊነት የነፃ ሐገር ምልክት በመሆኑ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ አባቶቻችን ለዓለም ሥልጣኔ ያበረከቷቸውን ቅርሶች ጠብቆና አስከብሮ ለማስቀመጥ ከጦር ሜዳ ያላነሰ ወኔን የሚጠይቅ ጀግንነት ነው፡፡ ምዕራባውያን ቅርስና ታሪክን የሚዘርፉት አንገት ለማስደፋት ነው፡፡
ይኽም አንዱ የዘመናችን ጦርነት ሆኗል፡፡ የራሳችን ጉዶች ሳይቀሩ ለግል ጥቅማቸው ቅርሶቻችንን ከአገር እያስወጡ አብልጦ ለሚከፍላቸው ባዕድን አሳልፈው ይሸጧቸዋል፡፡ ብዙዎቹም የራሳቸውን የፖለቲካ አጀንዳ ይዘው የሚንቀሳቀሱ ናቸው እንጂ ብሔራዊ ስሜትን የሚያነቃቁ ታሪካዊ ቅርሶቻችንን ቢሸጡ ቢለወጡ አይጎረብጣቸውም፡፡ ዳያስፖራውንም የዳቦ ሥም እያወጡ ለነሱ ሥልጣን መወጣቻ መሰላል አርገው በዘርና በጎሳ ሲያናክሱት ነው የኖሩት፡፡ ስለዚህ ታሪክ አልባ ቢሆን ደንታ የላቸውም፡፡ እንደኔ አረዳድ ግን ቅርስ የሌለው ሕዝብ ከወደቀበት ተደግፎ የሚነሳበት ምርኩዝ የለውም፡፡
ወደ ጥያቄህ ስመለስ በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች የቅርስ ሽያጭ ማስታወቂያዎች ሲለጠፉ አንዳንድ ወዳጆቼ ጥቆማ ይልኩልኛል፡፡ ሁሉንም ማሳገድ ባንችልም ጠቃሚና መልሰን ልንገኛቸው የማንችል መስሎ ከታየኝ ከኤጀንቱና ሽያጩን ያቀረበውን ግለሰብ በማግባባት የዋጋ ድርድር በምሥጢር አድርገን ለኛ እንዲሸጡልን እናግባባለን፡፡ እምቢ ካሉን ግን ተቃውሞ አስነስተን ቅርሱን ከዌብሳዩቱ ላይ እንዲነሳ ሕዝቡን እናስተባብርባቸዋለን፡፡ የአክሱም ሀውልትን፣ የዐፄ ቴዎድሮስ ሹሩባ እንዲመለሱም ጥረት አድርገናል፡፡ ነፍሱን ይማረውና ከፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረሰት ጋር የመቅደላ ቅርስ አስመላሽ ኮሜቴ ውስጥ አብሬው ሰርቻለሁ፡፡ ፓንክረስት ጎበዝ ሰው ነበር፡፡ መኖሪያ ቤቴም ከባለቤቱ ከሪታ ፓንክረስት ጋር ተመላልሰው የምሰብስባቸውን ቅርሶች ጎብኝተዋቸዋል፡፡ በመጨረሻም የጻፋችውን መጻሕፍቶች ሰብስቦ ፊርማውን አሰቀምጦ አንድ ቀን ጧት በታክሲ ወደኔ ቤት ልኮ አመስግኖ በሥጦታ አበርክቶልኛል፡፡ በምኖርበት እንግሊዝ አገርም ማኅበረሰቡ የኢትዮጵያን ታሪክ እንዲያውቅ የባሕል ልውውጥ እንድናደርግ በየኮለጁና ዮኒቨርሲቲዎች እየዞርኩ ታሪካችንን እንዲያውቁ ጊዜያዊ ኤግዚቢሽን እያዘጋጀሁ አሳይቻለሁ፡፡ የኢትዮጵያ ቅርስ ማበልፀጊያ ማኅበርን ከዛሬ 26 ዓመት በፊት አቋቁሚያለሁ፡፡
እንግሊዞችም የ2000 ሚሌኒየም ክብረ በዓላቸውን ሲያከብሩ ለማኅበረሰቡ መልካም ሥራ የሰሩትን ከተለያዩ ኮምኒቲዎች እውቅና ሲሰጡ፣ እኔንም ለዚህ ክብር አብቀተውኛል፡፡ እውቅና መሥጠት ብቻ ሳይሆን የሕይወት ታሪኬን ቀርፀው ከፎቶግራፌ ጋር ለንደን ሙዚየም ውስጥ በክብር አስቀምጠውታል፡፡
ግዮን፡- ሰሞኑን የእንግሊዝ መንግሥት የልዑል አለማየሁ ቴዎድሮስን አጽ ወደ ትውልድ ሀገሩ ኢትዮጵያ እንደማይመልስ አስታውቋል፡፡ በዚህ ዙሪያ ከዚህ ቀደም ያደረጋችሁት ጥረት ምን ያህል እንደነበር ማወቅ ይቻላል?
አለባቸው፡- የልዑል አለማየሁ ቴዎድሮስ አጽም ወደ ትውልድ ሐገሩ ወደ ኢትዮጵያ ለማስመለስ የተደረገው ሙከራ ዛሬ የተጀመረ ሳይሆን የዛሬ ዐሥራ ሰባት ዓመት ገደማ ነው፡፡ ነፍሱን ይማረውና እውቁ ጋዜጠኛ መጽሐፈ ሲራክ ከዋሽንግተን ዲሲ በመምጣት የዐፄ ቴዎድሮስን 4ኛ ትውልድ ናቸው የተባሉትን ቤተሰቦች ለንደን አስተዋውቆኝ ነበር፡፡ እንዴት ተደርጎ አፅሙ ወደ ትውልድ ሐገሩ መግባት እንዳለበት ተመካክረን ነበር፡፡ እኔም ይህንን ጉዳይ ለፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ነገርኳቸው፡፡ እሳቸውም አንድ ‹‹church of england heritage expert›› ኾኖ የሚሰራ ዶክተር እንዳለ ነግረው ሥሙን ላኩልኝ፡፡ ሔጄ ፈልጌ ቀጠሮ ይዤ አነጋግሬዋለሁ፡፡ የነገረኝ የአለማየሁ ቴዎድሮስን አፅም ካረፈበት ቦታ ማንሳት እንደማይቻል ነው፡፡ ምክንያቱም ‹‹አጽሙ ከተነሳ ከሱ አጠገብ የተቀበሩትን አፅሞች መቃብር ሊናጋ ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ ቅርስን ማጥፋትና ማበላሸት ስለሆነ ከፍተኛ ጥንቃቄን የሚጠይቅ ሥራ ነው፤ በኔ እምነት የሚሞከር አይመስለኝም፡፡ የእንግሊዝ የቅርስ ባለሥልጣንም አይፈቅድም፡፡ እሱ የተቀበረበት ቤተክርስቲያንም የራሱ ደንብና ሕግ አለው›› ነበር ያለኝ፡፡ በመቀጠል ለኢትዮጵያ ሚሌኒየም ይኼው ጥያቄ ተነስቶ እንደማይቻል በአለማየሁ ቴዎድሮስ የሕይወት ታሪክ ላይ ጥናት ያደረጉትና ያልታተመ መጽሐፍ የጻፉት ወ/ሮ አንጀሊና የተባሉ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያላቸው ሴት ገልፀውልኛል፡፡ ከእርጅና በስተቀር ሴትዮዋ አሁንም ለንደን በሕይወት ይገኛሉ፡፡
ግዮን፡- ባለፉት ዓመታት የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ተከስቶ በነበረ ወቅት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለመደገፍ ‹‹የዳያስፖራ ቱሪዝም›› የሚል ሥራ ስትሠራም ነበር፡፡ ምን ያህል ውጤታማ ነበር?
አለባቸው፡- እውነት ነው፡፡ እኔ ያለሁበት የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ምክር ቤት ነው ፕሮጀክቱን የነደፈው፡፡ በወቅቱ የተግባር ኮሜቴው ሥራ አስፈፃሚ. የእቅድና ፕሮጀክት ሓላፊ ስለነበርኩ ‹‹እንቁጣጣሽ ኢትዮጵያ የፍቅር ጉዞ›› የሚል 500 ዳያስፖራን ወደ ሐገር ቤት የሚያስገባ ፕሮጀክት ቀርፀን ተንቀሳቅሰን ነበር፡፡ የጉዞውም ዋና ዓላማ የዳያስፖራ ቱሪዝምን ወደ ሐገር ውስጥ ለማስገባት ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡ እንደሚታወቀው ወቅቱ የኮቪድ ወረርሽኝ ዓለምን ያስጨነቀበት ጊዜ ነው፡፡ ሰዎች ከአንዱ አገር ተነስተው ወደ ሌላ አገር ለመሔድ እንቅስቃሴ ገደብ ቢጣልም ለሐገራችንን ያለንን አለኝታ ለማሳየት ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ተሰባስበን ኢትዮጵያ ገብተናል፡፡ እንዳልኩህ ሀገራችን ሰው በሚያስፈልጋት ሰዓት መገኘት አለብን በማለት እያንዳንዳችን የሆቴልና የአየር ትኬታችንን ከፍለን በተጨማሪም ለልዩ ልዩ እርዳታዎች የሚውል 2000 ዶላር በነፍስ ወከፍ አዋጥተን የኢትዮጵያ መንግሥት በውጭ ምንዛሪ እጥረት እንዳይቸገርም ለማገዝ ስንመጣ አንዳንድ የመንግሥት ባለስልጣናት ጉዟችንን ሊያስቆሙ ቢሞክሩም አልቻሉም፡፡
ግዮን፡- 500 ዳያስፖራ ወደ ሀገር ቤት ለማምጣት ያዘጋጃችሁት ፕሮጀክት ዋና ዓላማን መግለጽ ይቻላል?
አለባቸው፡- የቡድኑ መሪም እኔ ስለነበርኩ ልንሰራቸው አስበን የነበርነው አምስት ዓላማዎች ነበሩን፡፡ 1ኛ ሐገራችን ኢትዮጵያ የቃልኪዳኑን የሕዳሴ ግድብ የመሠረተችበትን 10ኛ ዓመትና ሁለተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት የተከናወነበትን ክብረ በዓል ምክንያት በማድረግ ለ65 ሚሊዮን ሕዝብ ተስፋ የተጣለበት የዓባይ ወንዝ ተፈጥሯዊ መብታችን እንዲጠበቅና የልማት መሠረታችን እንዲሆን ተደርጎ በመገንባቱ፣ በቦታው በአካል በመገኘት የሕዳሴውን ግድብ መጎበኝትና ሌት ከቀን የደከሙትን የልማት ጀግኖችን ለማመስገንና ለማበረታታት፡፡ 2ኛ በገጽታ ግንባታ ላይ የተጀመሩትን የሸገርና የእንጦጦ እንዲሁም የወዳጅነት ፓርክ በመጎብኘት እንዲሁም በተለያዩ ቦታዎች የተጀመሩትን ገበታ ለሐገር ፕሮጀክቶች ለማስቀጠል አስፈላጊውን እገዛ ለማድረግ፡፡ ዳያስፖራው የራሱን አረንጓዴ አሻራ እንዲያስቀምጥ የአንድ ቀን የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ለመፈፀም፡፡ 3ኛ በሀገራችን ያለውን ዴሞክራሲ ለማዘመን በተደረገው ሀገራዊ ምርጫ አሸናፊውን ፓርቲና ተፎካካሪ ፖርቲዎችን፣ የክልል ፕሬዝዳንቶችና ሚኒስትሮች፣ የመከላከያ ሰራዊት ተወካዮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ጋዜጠኞች፣ የምርጫ ቦርድ አባላት፣ ምሁራኖች እና ታዋቂ ኢትዮጵያውያን በተገኙበት ‹‹ኢትዮጵያ ማሸነፏን የምናበስርበትና ለቀጣዩ አምስት ዓመት ኢትዮጵያን እንዲመራ ለተመረጠው መንግሥት ኢትዮጵያን በአደራ የምናስረክብበት የቃልኪዳን እራት ማዘጋጅት፡፡ 4ኛ ‹‹ኢትዮጵያን ለማዳን እዘምታለሁ! የትም፣ መቼም›› በሚል መርኅ ሥር በሀገር ውስጥ የተከፈተብንን የሕልውና ጦርነት በመቃወም ከመከላከያ ሰራዊት እና ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን መቆማችንን የሚያረጋግጥ የደም ልገሳ በማድረግ ደማችንን ከሰራዊቱ ደም ጋር በማዋሐድ ኢትዮጵያዊነትን ማንገስ፡፡ 5ኛ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ሙዚየምን መሠረት መጣልና ቅርሶቻችንን ወደ ሐገር እንዲመለሱ ለማበርታት የሚሉ ነበሩ፡፡
እቅዳችሁን አሳክታችሁ ተመለሳችሁ ወይ ላልከው 80 በመቶ እቅዶችችንን አስካክተናል፡፡ ነገር ግን በአንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣኖች በኩል ትብብር ልናገኝ ባለመቻላችን በቁጥር 3-5 የተጠቀሱትን ዋና ዋና ፕሮግራሞች ማስፈፀም አልቻልንም፡፡
ግዮን፡- ከወራት በፊት ከም/ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን እጅ ለነበረህ ሀገራዊ የዳያስፖራ አበርክቶ የዕውቅና ሽልማት ተበርክቶልሃል፡፡ ኢትዮጵያ የሚለፉላትን ማመስገን ጀምራለች ብለህ ታስባለህ?
አለባቸው፡- ሽልማቱ በግል ለኔ የተሰጠኝ አይደለም፡፡ ሽልማቱ ለኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ምክር ቤት በሕልውና ዘመቻ ወቅት ለተጎዱ ክልሎችና ለመከላከያ ሰራዊቱ ላደረግነው ድጋፍ ‹‹ኢትዮጵያ ታመሰግናለች›› በሚል መርኅ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ምክር ቤት በተደረገለት ጥሪ መሠረት ድርጅቱን ወክዬ ነበር የተገኘሁት፡፡ በመሠረቱ በመንግሥት ደረጃ የዳያስፖራ ኮሚኒቲውን ከየአገሩ ስብስቦ መሸለም የተለመደ ስላልነበረ መንግሥት ከዳያስፖራው ጋር ጤናማ ግንኙነት ለመፍጠር የተጠቀመበት መልካም ጅምር በመኾኑ በደስታ ተቀብለነው ነበር፡፡ ከዝግጅቱ መንፈስ እንደተረዳሁትም በመንግሥት የተሰጠው እውቅናና ምሥጋና ብቻ ሳይሆን አደራም ጭምር ነበር፡፡ ማንም የዳያስፖራ አባል ሀገሩ በተቸገረችበት ወቅት በቁርጠኝነት ተነሳስቶ ለመርዳት መዘጋጀቱ እንደዜጋ ሓላፊነቱን ለመወጣት ነበር እንጂ እውቅናና ሽልማት እቀበላለሁ ብሎ አልነበረም፡፡ ነገር ግን መንግሥት ምሥጋና በመጀመሩ በዳያስፖራው ውስጥ ከፍተኛ የሞራል መነቃቃት ፈጥሮ ነበር፡፡ በተለይም በተከፈተብን የሕልውና ጦርነት የዘመቻው አጋር በመኾን ከሕዝብና ከሰራዊቱ ጎን ተሰልፈን አጋርነታችንን በማረጋገጣችን ፍፁም ደስተኞች ነበርን፡፡ ከማንም በፊት ቀድመን በጦርነቱ የፈራረሱ ቤቶችን በመጠገን የተጎዱ የሰራዊት አባሎችን በመደገፍ የዜግነት ግዴታችንን ተወጥተናል፡፡ በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ምክር ቤት በሦስት ዋና ዋና ጉዳዮች ፕሮጀክት ቀርፆ በመሥራት ላይ ይገኛል፡-
1ኛ በገፅታ ግንባታና በቱሪዝም ላይ ይሰራል፡፡ የሐገሪቱን ቱሪዝም ለማዘመን በሚደረገው ማናቸውም እንቅስቃሴ ተሳታፊ ቢሆንም በተለይ የዳያስፖራ ቱሪዝም ወደ ሐገር ውስጥ በማስገባት አገራችንን የቱሪዝም ተጠቃሚ ለማድረግ በእቅድ ላይ ነው፡፡ 2ኛ በትውልድ ቀረፃ ላይ! በታሪክና በቅርስ ላይ ትኩረት በመሥጠት ጠንክረን እየሰራን ነው፡፡ በቅርቡ እንኳን የዓድዋን 127ኛ ክብረ በዓል በድምቀት እንዲከበር በዋና ዋና ሀገሮች ያስተባበረው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ምክር ቤት ነው፡፡ ዓድዋን እንደ አንድ ትልቅ በዓል አድርገን ስለምናከብረው ዓለም አቀፍ የዓድዋ ዘካሪያን ማኅበር አቋቁመናል፡፡ ይህ ትልቅ መነቃቃት የሚፈጥር ከአፍሪካ ወንድሞቻችን ጋር በጋራ የምናከብረው የድል ቀን ነው፡፡ 3ኛ በልማት ላይ ነው፡፡ ዳያስፖራው ሀገሩ ላይ ጥሪት እንዲኖረው እና በልማት እንዲሳተፍ የኢትዮጵያ ወዳጆችንም ጭምር አብረን እናበረታታለን፡፡
ግዮን፡- ዳያስፖራው ሁለት ዓመት በዘለቀው የሰሜኑ ጦርነት ከመንግሥት ጋር ያራመደው አቋም በውጤት ሲለካ ኢትዮጵያን አሸናፊ ያደረገ ነበር ብለህ በሙሉ ልብህ ታምናለህ?
አለባቸው፡- ከላይ በዝርዝር እንደገለፅኩልህ በሕልውናው ጦርነት ወቅትም ሆነ በመልሶ ግንባታው ዳያስፖራው ሁለገብ ሆኖ ተሳትፏል፡፡ ውጤቱ በሰላማዊ ሽምግልና ሲጠናቀቅ የኢትዮጵያ ሕዝብ ትልቅ እፎይታ ነበር የተሰማው፡፡ ዳያስፖራውም ከሕዝቡ ጋር ደስታውን ቢገልፅም በድርድሩ የቀረቡት ስምምነቶች ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ይሆናሉ ብሎ አይገምትም፡፡ ትሕነግ ፕሪቶሪያ ላይ ከፈረመው ባለ 15 አንቀፅ ሰነድ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ትጥቅ እንደሚፈታና ተዋጊዎቹ በሙሉ ወደ ተሐድሶ (ማሰልጠኛ) ካምፕ እንደሚገቡ ነበር፡፡ ይህንን ስምምነት የማስፈፀም ሙሉ ኃላፊነት ከተጠያቂነት ጋር የተሰጠው ለፌደራል መንግሥቱ እና በአፍሪቃ ሕብረት በኩል ለአሸማጋዮቹ ነበር፡፡ ይህ ስምምነት በትክክል ባለመተግበሩ በዳያስፖራው ውስጥ ትልቅ ሥጋትና ጥርጣሬን እንደፈጠረ ነው፡፡
ግዮን፡- ከሁለት ወር በፊት የዓድዋን ድል መታሰቢያ አስመልክቶ መንግሥት በበዓሉ አከባበርም ኾነ በዜጎች ላይ ያደረሰውን ጉዳት ተከትሎ የተለያዩ የዳያስፖራ ማኅበራት ለጠ/ሚኒስትሩ ደብዳቤ ጽፋችሁ ነበር፡፡ ምን መልስ አገኛችሁ?
አለባቸው፡- ምንም መልስ አላገኝንም፡፡ የመንግሥትን አሠራር ስለምናውቀው መልስ ሰጡን አልሰጡንም ብዙም አያስጨንቀንም፡፡ ብሔራዊ ክብራችን በሚነካበት ወቅት መንግሥትን ደግፈን እንቆማለን፡፡ ትክክል ያልመሰልንን ድርጊቶች ደግሞ መንግሥት እንዲያሻሽል እናበረታታለን፡፡ በ127ኛ የዓድዋ ክብረ በዓል ዝግጅት ወቅት መሆን ያልነበረበት አሳፋሪ ድርጊት ተፈፅሟል፡፡ ለዚህ ምንም ትዕግስት አልነበረንም፡፡ ወዲያውኑ ለመንግሥት ቅሬታችንን በመግለጫ ገልፀናል፡፡ በመሠረቱ የዓድዋ በዓል የሕዝብ ነው፡፡ ሕዝቡም በአዋጅ እንዲያከበር በፀደቀበት ቦታ ማክበር ፍላጎት ካለው መንግሥት መከልከል የለበትም፡፡ የበዓላት አከባበር አዋጁ ይደግፈዋል፡፡ ለ127 ዓመታት ሕዝቡ ሲያከብርበት ከነበረበት ከምንይልክ አደባባይ አስለቃሽ ጭስ እየተኮስክ በወታደር አስፈራርተህ አስገድደህ ትዝታውን መቀማት አትችልም፡፡ ዓድዋ ማለት ለትውልድ መዳን፣ ለትውልድ አንገት መቃናት የፈሰሰ ደም፣… የወደቀ የጀግና አፅም፣ …በባሩድ የነደደ ሥጋ ነው!! አባቶቻችን ለኛ የከፈሉት የእድሜ ልክ መታሰቢያችን ነው፡፡ ስለዚህ መንግሥት በሕዝቡ በዓል ውስጥ ጣልቃ እየገባ የራሱ የገፅታ ግንባታ ሊያደርገበት ሲሞክር አልቀበልም የማለት መብት ሕዝቡ አለው፡፡ ወደፊትም ቢሆን መንግሥት የሕዝቡን ደህንነት መጠበቅና ለበዓሉ ድምቀት የሚሆኑ እርዳታዎችን ከማድረግ በዘለለ በኃይልና በጉልበት የሕዝቡን በዓል ቀምቶ የፖለቲካ ንግድ ለማድረግ መሞከር ከሞራል አኳያም ተገቢ አይደለም፡፡ ከአንድ ጤነኛ መንግሥትም የሚጠበቅ ሥነ ምግባር አይደለም፡፡ በአውሮፓና በአሜሪካ ነጩን ሰረገላ በፈረስ እያስጎተትን ሰንደቅ ዓላማችንን ለብሰን እያቅራራን እና እየፎከርን፣ ኪንግስ ክሮስን የምንይልክ አደባባይ ስናስመስለው ደስ ብሎን እንድናከብር ትብብር ከማድረግ ውጭ ምንም ትንኮሳ አልተደረገብንም፡፡ የፀጥታ አባሎቻቸው ከኛው ጋር ደስታችንን እየተጋሩ ደህንነታችንን ከመጠበቅና ከመተባበር በስተቀር በዝግጅታችን ውስጥ ጣልቃ አልገቡም፡፡ ሥልጣኔ ማለት እንደዚህ ነው፡፡
ግዮን፡- ኢትዮጵያ አሁን ላይ እየሔደችበት ያለው አጠቃላይ አካሔድ፣ ዳያስፖራው ለዘመናት ሲታገልለት የኖረውን ኢትዮጵያዊነትን ማዕከል ካደረገ ፖለቲካ እያፈነገጠ ነው የሚለውን አስተያየት እንዴት ትመዝነዋለህ? ፖለቲካውንስ እንዴት እየተከታተልከው ነው? በተለያዩ ሐገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ጠንካራ ሐሳቦችን በጽሑፍ ትሰነዝር ነበር፣ ትንሽ ቀዝቀዝ ብለኻል ለምንድ ነው? ፖለቲካው አልተመቸህም?
አለባቸው፡- እንደውም ከመጨረሻው ጥይቄህ ልነሳ፡፡ መጻፌን አላቆምኩም፡፡ ምናልባት በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ የምፅፋቸውን ዐይነት ሐሳቦች ማለትህ ከሆነ ትክክል ነህ ለግዜው ለዓምዱ የማይስማሙ ከኾኑ አልካቸውም፡፡ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ነው የምፅፈው፡፡ ማወቅ የሚኖርብህ የምትፅፈው ጽሑፍ የሕዝቡን ፍላጎት የማይገልፅና የማይወክለው ከሆነ ማን ያነብልኻል፡፡ የተደራጀ ሐሳብ ማዘጋጀት እና የፖሊሲ ፍተሻ አድርገህ ትንተና የማታቀርብ ካልሆነ ያንተን ጽሑፍ ማን ያነብልኻል፡፡ የማኅበረሰቡን ጥያቄ እና የልብ ትርታውን አዳምጠህ ካልፃፍክ ማን ይቀበለኛል ብለህ ትፅፋለህ፡፡ ችግሩ የዓለምን ወቅታዊ ተጨባጭ ሁኔታ የተረዳን አልመሰለኝም ወይንንም ፖለቲካውን በደንብ አላወቅንበትም፡፡ ታሪካችንን ጠንቅቀን ባለማወቃችንም እጅና እግር በሌለው የብሽሽቅ ፖለቲካ ላይ ነው ጊዚያችንን የምናባክነው፡፡ ስለዚህ ከነባራዊው የሀገሪቱ ሁኔታ አንጻር እኛ የምናነሳቸውን አማራጭ ግዙፍ ሐሳቦች መንግሥትም ሕዝብም የማይቀበላቸው ከኾነ መጻፋችን ምን ትርጉም አለው፡፡ የለውጥ ኃይሉ ውስጥ የተቀላቀሉ ምንም ፍላጎት የሌላቸው አመራሮች ጣታቸውን እየቀሰሩ የሚዲያ ነፃነትን አግተው ብዙ ጋዜጠኞችን በወንጀል ተጠያቂ ሲያደርጓቸው እያየህ ምን ለውጥ አመጣለሁ ብለህ ትፅፋለህ፡፡ ስለዚህ የአገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር እጅግ በጣም በመዘጋጋቱና መላወሻ በመጥፋቱ ወቅቱ ለጋዜጠኞች እጅግ አስቸጋሪ የፈተና ወቅት ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ብዙ ሐሳብ የሚያፈልቁ አዕምሮዎች ተቆልፎባቸዋል፡፡ በዚህም በጣም አዝናለሁ፡፡ መንግሥት በአስቸኳይ መላ እንዲፈልግ በዚህ አጋጣሚ መልዕክቴን አስተላልፋለሁ፡፡
ግዮን፡- በመጨረሻ እድሉን ልስጥህና ምኞትህን ልትነግርኝ ትችላለህ?
አለባቸው፡- ደስ እያለኝ፡፡ በእርግጥ ምኞት አይከለከልም፡፡ ነገር ግን አብረውኝ ለኢትዮጵያ ክብር ሲፋለሙ በየበረሃው ወድቀው የቀሩትን የቀድሞው የኢትዮጵያ ስፔሻል ፎርሶች ልፋታቸውና ድካማቸውን ረሀብና መጎሳቆላቸውን፣ ለክብር መሞታቸውን ደጋግሜ ባስብኩ ቁጥር ለዓላማዬ ጽናት ለመንፈሴ ኩራት ቢሰጠኝም ሀገሬ አንድም ቀን ከጦርነት ነፃ ሳትሆን ሕዝቡም ነፃነቱን ሲያጣጥም እስከ አሁን ድረስ ባለማየቴ እጅግ አድርጎ ይከፋኛል፡፡ በሌላ በኩል ግን በኢትዮጵያዊ ማንነት ኮትኩቶ አሳድጎ የሰው ሰው ላደረገኝ ለኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ፍቅሬንና አክብሮቴን የምገልፀው በአንድ ነገር ብቻ ይመስለኛል፡፡ ‹‹ስሞት ወታደራዊ ልብሴን ከነ ማዕረጌ እንደለበስኩ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ለብሼ ብቀበር ደስ ይለኛል›› ይህንንም ጽኑ ምኞቴን ሐገሬ እንደማትነፍገኝ እርግጠኛ ነኝ፡፡ በመጨረሻም የግዮን መጽሔት አዘጋጆች ይህንን ዕድል ስለሰጣችሁኝ ምስጋናዬ ይድረስችሁ፡፡ ከልብ አመሰግናለሁ፡፡
ግዮን፡- ለነበረን ቆይታ በአንባቢያን ሥም ከልብ እናመሠግናለን፡፡
አለባቸው፡- እኔም ክብረት ይሥጥልኝ እላለሁ፡፡