ፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ በኢትዮጵያ የንግድ ሥርዓት ውስጥ ያለውን ቅጥ ያጣ የአምራችና የተጠቃሚ ግንኙነት ለማሳለጥ በዘርፉ ኢንቨስት ለማድረግ የመጣ ድርጅት ነው፡፡ ድርጅቱ ከተቋቋመ ገና ጥቂት ዓመት ቢኾንም በሀገሪቱ ላይ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ተቀባይነትን እያገኘ መጥቷል፡፡ በዚህም ድርጅቱ ወደ ሥራ ከገባ በኋላ በተለይ ቀደም ሲል በአምራቹና በሸማቹ መካከል ያለውን የደላላ ሥርዓት በመበጣጠስ የተለያዩ የግብርና ውጤቶችን ከበሬው በቀጥታ ወደ ሸማቹ በማቅረብ እጅግ ውጤታማ ሥራን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ አሁን ላይ ተቋሙ በአዲስ አበባ ብቻ ከሁለት ሺህ በላይ ሠራተኞች ያሉት ሲኾን ከጊዜ ወደጊዜ እየሰፋ በመሄድም የዲጂታል ገበያ ሥርዓቱን በከፍተኛ ሁኔታ በማሳለጥ ላይ ይገኛል፡፡ ድርጅቱ በዚህ ብቻ ሳይወሰን ሰሞኑን ደግሞ ሁለተኛውን የሪልስቴት ፕሮጀክቱን ይፋ አድርጓል፡፡
አልፎም ከሪልስቴቱ በተጨማሪ “ሙቭመንት አጌነስት ሀንገር” የተሰኘ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በጸረ ድህነት ላይ የሚያሳትፍ ኢንቨስትመንትም ይፋ አድርጓል፡፡ ይህ እንቅስቃሴ በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ውስጥ ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ አሳታፊ እንደሚያደርግ የድርጅቱ መሥራች ዶ/ር ፍሰሐ እሸቱ ተናግረዋል፡፡ በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ ወደ 500ሺ የሚጠጉ የዲያስፖራ አባላትም የእንቅስቃሴው አካል እንደሚኾኑ ገልጸዋል፡፡ እንቅስቃሴው የተቸገሩ መርዳትን ሳይኾን ብድር በመስጠት እርዳታን ወደ ቢዝነስ መቀየር ዓላማም እንዳለው ተናግረዋል፡፡ በሀገራችን እየተናጋ የመጣውን ኢኮኖሚ ለመቋቋም ኢትዮጵያውያን ገንዘባቸውን በባንክ ከማስቀመጥ ይልቅ እንደሠለጠነው ዓለም ሁሉ ወደ አክሲዮኖች በመሄድ ኢንቨስት ሊያደርጉበት እንደሚገባ የተናገሩት ዶ/ር ፍሰሐ፤ ፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ ለዚህ እንቅስቃሴ ገንዘብ የሚያዋጡ አካላትን ባለአክስዮን በማድረግም ከዓለም የኢንቨስትመንት ሲስተም ሥርዓት እንደሚለይ ገልጸዋል፡፡ ሰዎች ይህን ነገር ኢንቨስት ሲያደርጉ እንደጋራንቲ (ማስያዣ) ሊወስዱት የሚገባው ነገር ማስቀመጥ ስለሚገባም ተቋሙ ወደ ሪል ስቴት ግንባታ እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡
ይህ የሚገነባው ሪል ስቴት በዓይነቱ ልዩ የኾነና ከዓለም በስምንተኛ ደረጃ በአፍሪካ ደግሞ አንደኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ የሚችል ነው የሚሉት የብላክ ፐርፐዝ ኢትዮጵያ መሥራቹ ዶ/ር ፍሰሐ ሪል ስቴቱ “ገበሬው ታወር” የተሰኘ ስም ሲኖረው ለመገንባት ከ61 ቢሊዮን ብር በላይ ይጠይቃል ብለዋል፡፡ ሕንጻው የኢትዮጵያን ክብር የሚገልጽና ኢትዮጵያ ወደፊት የምትደርስበትን ደረጃም የሚያመላክት ነው ብለዋል፡፡ ሕንጻው በውስጡ የተለያዩ አገልግሎቶችን ያቀፈ ሲኾን በኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ ሆቴል፣ ትልቅ ሱፐርማርኬት፣ ትልቅ የኮንቬንሽን እና የማኅበረሰብ ማዕከል፣ ትልቅ የቢሮ ግቢ ውስጥ ትልቅ የመኪና ማቆሚያ ቦታ፣ ትልቅ የሲኒማ እና የመዝናኛ ኮምፕሌክስ እና ምርጥ የቅንጦት አፓርታማዎችን እንደሚያካትትም ተመላክቷል፡፡ በዚህም መሠረት ዋናው “ገበሬው ታወር” የተሰኘው ሕንጻ 115 ወለሎች ሲኖሩት ከሌሎች ሕንጻዎች ግንባታ ጋር በአጠቃላይ 500,000 ካሬ ሜ ቦታ እንደሚሸፍን ወይም 20ሺ ስኩዌር ሜትር ላይ የሚያርፍ እንደሚያርፍና በጥቅሉ 6 ህንፃዎችንም እንዳካተተ ተመላክቷል፡፡
በመኾኑም ባለ50 ፎቅ ሕንጻ ባለ6 ኮከብ ሆቴል በጠቅላላ 100,000 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው፣ ባለ50 ፎቅ ኮንቬንሽን እና የማኅበረሰብ ማእከል 100,000 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው፣ ባለ 50 ፎቅ ለዋና መሥሪያ ቤት እና የቢሮ ማማ በጠቅላላው 100,000 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው፣ አምስት ፎቅ የገበያ ማዕከል በጠቅላላው 65,000 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው እና በጠቅላላው 30,000 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው A-15 ደረጃ የመኪና ማቆሚያ ሕንፃ እንደሚገነባ ተመላክቷል፡፡ የአክሲዮን ግዢውን በተመለከተም ዝቅተኛው ኢንቨስትመንት 1000 ብር ሲኾን ከፍተኛው ኢንቨስትመንት 1 ቢሊዮን ብር እንደኾነ ተጠቁሟል፡፡ በዚህ አክሲዮን ላይ በግልም ይሁን በማኅበር ወይም በቡድን ኾኖ መሳተፍ እንደሚቻልም ተጠቁሟል፡፡ ዓለም አቀፍ የገበሬው የምስጋና ታወር በተለይም ገበሬውን እናመሰግናለን የምንልበት ራሳችንን በኢኮኖሚ እያበለፀግን ለሰዎች የምንደርስበት ነው ተብሏል። መርሐ ግብሩን በሕሊና ፀሎት ያስጀመሩት የፐርፐዝብላክ ኢቲኤች ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ፍስሃ እሸቱ የገበሬው ምስጋና ታወር በተላይም በኢትዮጵያ የገንዘብ አያያዝ ሁኔታን እንዲሁም እርዳታን ወደ ኢንቨስትመንት በመለወጥ ርሃብን መዋጋት የሚሉትን መሰረታዊ ሀሳቦች መነሻ እንደኾኑት በመግለፅ ኢንቨስት በማድረግ ለብዙዎች መድረስ የምንችልበት ልዩ የኾነ ፕሮጀክት በመኾኑ ሁሉም ሰው ተሳታፊ ይሁን ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ህንፃው እ.አ.አ በ2026 ጥር ላይ ለማጠናቀቅ በእቅድ ተይዞ እየተሠራ ነውም የተባለ ሲኾን ከፍ ሲል እንደተገለጸው የፕሮጀክቱ አባል መኾን የሚፈልጉ ግለሰቦች፣ ማህበራት፣ ኩባንያዎች፣ የሀገር ውስጥና የውጪ ኢንቨስተሮች መሳተፍ የሚችሉ መኾኑ ተመላክቶ በቅድሚያ ግን ለኢትዮጵያዊያን እንደሚሰጥ ተጠቁሟል። የዚህ ታሪክ ባለቤት ለመኾን የሚፈልጉና በሁለት ወር ውስጥ ኢንቨስት በማድረግ ሀገር ለመለወጥ ቆርጠው ለተነሱ የራዕይው ተጋሪዎች ቅናሽ እንዳለው ዶ/ር ፍስሐ ገልፀዋል። በመኾኑም ከ30 ሚሊዮንና ከዛ በላይ ኢንቨስት በማድረግ የከገበሬው ህንፃ/ታወር ባለአክሲዮን ለሚኾኑ ሁሉ ባለ 4 መኝታ ቤት የመኖሪያ ቤት አፓርታማ፣ እንዲሁም ከ55 ሚሊዮን በላይ ኢንቨስት ለሚያደርጎ ደግሞ 450 ካሬ ላይ ያረፈ ቅንጡ አፓርታማ በነፃ የሚያገኙ መኾኑም በመርሐግብሩ ተጠቅሷል። የከገበሬው ታወር ኢንቨስተሮች ፐርፐዝ ብላክ ኢቲኤች በተሠማራባቸው ዘርፎች በሙሉ የባለቤትነት ድርሻ እንደሚኖራቸውም ተገልጿል። በመርሐ ግብሩ በርካቶች ባለቤት ለመኾን ፍላጎት ሲያሳዩ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ሰዎች ደግሞ ተመዝግበዋል።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከፐርፐዝ ብላክ ኢቲኤች ጋር አብሮ የመሥራት ፍላጎት እንዳለው ገለፀ፡፡ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ይህንን ያለው የፐርፐዝ ብላክ ኢቲኤች የኮሙኒኬሽን ዲፓርትመንት አጠቃላይ የኮሙኒኬሽን ሥራዉን በሚመለከት የልምድ ልውውጥ ባደረገበት ወቅት ነው፡፡ ኩባንያው ፐርፐዝ ብላክ ኢቲኤች በዋናነት የተቋቋመበት ዓላማ ሀገርን የሚያቀና ሕዝብን የሚደግፍ መኾኑን በመጠቆም በአጭር ጊዜ ውስጥ አያሌ ሥራዎችን ማከናወኑ የሚደነቅ መኾኑን አንስቷል፡፡ በልምድ ልውውጡ ላይ አጠቃላይ የተቋሙን አሠራርና የኮሙዮኒኬሽን ሥራዉን በሚመለከት ለፐርፐዝ ብላክ ኢቲኤች የኮሙዮኒኬሽን ዲፓርትመንት ገለፃ የተደረገ ሲኾን በተላይም ከፐርፐዝ ብላክ ኢቲኤች ጋር የንግድ ሥርዓቱን ማሳለጥ የሚቻልበት ሁኔታ ላይና የኢትዮጵያ ምርት ገበያ እየሠራበት ባለው “Forward trade” ላይ አብረን መሥራት እንችላለን ብለዋል፡፡ የፐርፐዝ ብላክ ኢቲኤች የኮሙዮኒኬሽን ዲፓርትመንት ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ጋር በጋራ መሥራት የሚያስችለውን ሁኔታዎች በመርመር አብሮ ለመሥራት የሚያቻልበት ዙሪያ ላይ ሁኔታዎች እንደሚያመቻች በመግለፅ የልምድ ልውውጡ ተጠናቋል፡፡
