
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አዋጅ ቁጥር 1238/2013 የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የዕለት ተዕለት ሥራውን እንዳያከናዉን ለተቋሙ ቦርድ የተሰጠው ሥልጣን “የሕግ ክፍተት ያለበት በመሆኑ” እና ያንን ለተቋሙ ሥራ አስፈፃሚ መመለስ አስፈላጊ በመሆኑ ማሻሻል እንዳስፈለገ ገልጿል።
የፖለቲካ ፓርቲ አባል መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የቦርድ አባል መሆኑን የሚፈቅድ አዋጅ ፀደቀ
የብዙኃን መገናኛ ዘርፍ ምህዳርን እንዳያጠብ ያሰጋል በሚል ማሻሻያው ውድቅ እንዲደረግ ውትወታ ሲደረግበት የቆየው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ረቂቅ ማሻሻያ አዋጅ ዛሬ ሐሙስ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀደቀ።ዛሬ በዋለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ከተገኙ 248 አባላት በአንድ ተቃውሞ እና በአንድ ድምፀ ተዐቅቦ በአብላጫ ድምፅ የፀደቀው ማሻሻያ አዋጁ፣ በአዋጁ እና በተቋሙ አደረጃጀት ምክንያት “ተዳክሟል” የተባለውን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የሚያጠናክር ነው ተብሏል።
ምክር ቤቱ የማሻሻያው ዓላማ “ጠንካራ ተቋም የመመሥረት ጥረት ነው” ቢልም ጥያቄ ያነሱ ምክር ቤት አባላት በሀገሪቱ “ሚዛናዊ የሚዲያ አሠራር” እንደሌለ በመጥቀስ ዘርፉ በተጨባጭ አተገባበር ካልተመራ የሕግ ማሻሻያው ብቻውን ውጤት ሊያመጣ አይችልም ብለው ተከራክረዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አዋጅ ቁጥር 1238/2013 የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የዕለት ተዕለት ሥራውን እንዳያከናዉን ለተቋሙ ቦርድ የተሰጠው ሥልጣን “የሕግ ክፍተት ያለበት በመሆኑ” እና ያንን ለተቋሙ ሥራ አስፈፃሚ መመለስ አስፈላጊ በመሆኑ ማሻሻል እንዳስፈለገ ገልጿል።
“የባለሥልጣኑ የቦርድ አባላት ስብጥር ከሁሉም አካላት መሆን አለበት” በሚል የፖለቲካ ፓርቲ አባል የሆኑ ሰዎች የዚህ ተቋም የቦርድ አባል መሆን አይችሉም በሚል ተደንግጎ የነበረውን አንቀጽ በመሻር የፖለቲካ ፓርቲ አባል የሆኑ ሰዎች የተቋሙ ቦርድ አባል እንዲሆኑ የሚያስችላቸውን ማሻሻያ የተወካዮች ምክር ቤት አጽድቋል።
የአዋጁን ማሻሻያ 14 የሙያ ማህበራት ከዚህ በፊት በጋራ ባወጡት መግለጫ ተቃውመውት ነበር። በዛሬው የምክር ቤቱ ውሎም አዋጁ የተቋሙን የበላይ ኃላፊ አካል ማለትም “የቦርዱን ገለልተኝነት ጥያቄ ውስጥ በሚያስገባ ኹኔታ” ነው የተሻሻለው በሚል ተቃውሞ ተነስቶበታል።
ሌሎች የምክር ቤት አባላትም “የአዋጁ የማሻሻያ አስፈላጊነት አሳማኝ አይደለም” ሲሉ ተከራክረዋል። በተመሳሳይ “ሚዛናዊ የሚዲያ አሠራር መገንባት” እና የወጡ ሕጎችን በትክክል የመተግበር ጉዳይ እንጂ ሕጎችን በየ ጊዜው ማውጣቱና ማሻሻሉ በተጨባጭ በሀገሪቱ ያለውን የመገናኛ ብዙኃን መልክ አይለውጥም ብለዋል።
አሁን ማሻሻያ የተደረገበትና የፀደቀው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን አዋጅ ከዐመታት በፊት ሲፀድቅ ብርቱ ድጋፍ እና ይሁንታ ያገኘ ነበር። በሂደት በዘርፉ እና በጋዜጠኞች ላይ የሚታይ ፈተና ተጋርጧል ያሉ ሌላ የምክር ቤት አባል በበጎ ታይቶ የነበረውን የሕግ ድንጋጌ ማሻሻሉ ያንን ዐውድ ክፉኛ እንዳይቀለብስ ሥጋታቸውን ጠቅሰዋል።
በጉዳዩ ላይ ከዚህ በፊት ተደርጎ በነበረ ሕዝባዊ ዉይይት “ሕጉን የማሻሻሉ ሀሳብ፣ ሂደት እና ፍላጎት ሙሉ በሙሉ ፖለቲካዊ ጉዳይ ብቻ እንደሆነ ያሳያል” የሚሉ ብርቱ ትችቶችም ቀርበው ነበር። “የሀገሪቱ ሚዲያ የሀገሪቱ መልክ” መሆኑን የገለፁ ሌላ የምክር ቤት አባል የሕዝብ (የመንግሥት) በሚባሉትም፣ በግል ከሚተዳደሩትም “ማኅበረሰብ የማያዳምጣቸው” በመኖራቸው የተሻለ ሥራ ማከናወኑ እንደሚበጅ አመልክተዋል።
በዛሬው የምክር ቤቱ ውሎም አዋጁ የተቋሙን የበላይ ኃላፊ አካል ማለትም “የቦርዱን ገለልተኝነት ጥያቄ ውስጥ በሚያስገባ ኹኔታ” ነው የተሻሻለው በሚል ተቃውሞ ተነስቶበታል።
ተሻሽሎ የፀደቀው አዋጅ ለኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ቦርድ ተሰጥተው የነበሩት የፈቃድ ወይም የምዝገባ ምስክር ወረቀት የማደስ፣ የማገድ፣ የመሰረዝ፣ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ መስጠትን የመሳሰሉት ኃላፊነቶች አሁን ለባለሥልጣኑ ሥራ አስፈፃሚ ተሰጥቷል።
ብዙኃን መገናኛዎች በሚያደርጉት የቀጥታ ሥርጭት ላይ ለሚፈጠር ችግር ተጠያቂነት እንዲኖርባቸውም ያደርጋል። በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ እውነቱ አለነ የዚህን ምክንያት አስረድተዋል።”ቀጥታ ሥርጭት በሕግ መሠረት መሆን አለበት። ቀጥታ ሥርጭት ስለሆነ ዜጎችን ከዜጎች የሚያጋጭ፣ አንዱን ሃይማኖት ከአንዱ ሃይማኖት ጋር የሚያጋጭ አድርጎ እንዲያቀርብ መደረግ የለበትም”
በማሻሻያ ረቂቁ ላይ ሕዝባው ውይይት በተደረገበት ወቅት ብሔራዊው የመብቶች ተቋም ኢሰመኮ ማሻሻያው የሚዲያ ምህዳሩን የማጥበብ፣ የዲሞክረሲ እና የሰብዓዊ መብት ነፃነቶችን ችግር ላይ የመጣል እና የቦርዱን ገለልተኛነት እና ነፃነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነው በሚል ተችቶ ነበር። መሰል ሥጋቶች በዛሬው ጉባኤም ተነስተዋል።
በፓርላማው የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ ግን የሚያሠጋ ነገር የለም ሲሉ የመንግሥታቸውን አቋም አንፀባርቀዋል።”የቀረቡ ነገሮች ተቋሙ [የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን] የበለጠ ነፃ፣ ገለልተኛ እና ብቁ ሆኖ እንዲገነባ” የሚያደርግ ነው።